Home News and Views ፓትርያርኩ: የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስን “ቀንደኛ...

ፓትርያርኩ: የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ የማነ ዘመንፈስ ቅዱስን “ቀንደኛ ሌባ” አሉት

  • በሕመምተኛ ልጁ ሕክምና ስም በርካታ አጥቢያዎች በ፻ሺሕዎች እያወጡ በሰጡበት ኹኔታ፥ “እኔ ሳላውቅ ስሜን ለማስጠፋት የተሠራ ነው” በሚል ምዝበራውን ለማስተባበል እየጣረ ነው
  • ግማሽ ሚሊዮን ብር እንዲሰጠው የተወሰነበት የእንጦጦ ኪዳነ ምሕረት አስተዳደር ኮሚቴ ውሳኔ ቃለ ጉባኤ፣ በአስተዳደራዊ ውሳኔ ተሽሮ ውሳኔውን በሚያስተባብል ሌላ ቃለ ጉባኤው እንዲቀየር ሓላፊዎቹን አስገድዶ ነበር
  • “ድጋፉን የሰጠነው ተዋቅሮ በተላከ ኮሚቴ በተጠየቅነው መሠረት ነው፤” ያሉት ዐሥር የገዳሙ አስተዳደር ኮሚቴ አባላት ትእዛዙን ባለመቀበላቸው በየማነ ከሥራና ከደመወዝ ታግደው ነበር
  • የእገዳ ርምጃውንና አጠቃላይ ኹኔታውን ከገዳሙ ሓላፊዎች ያዳመጡት ፓትርያርኩ፥ “እርሱ ቀንደኛ ሌባ ነው፤ እናንተም ሌቦች ናችኹ” ሲሉ ገሥጸው ጉዳዩ በአስቸኳይ እንዲጣራ አዘዋል
  • በሥራ አስኪያጅነት ሥልጣኑ አጥቢያዎችን በማስፈራራት ከብር 3 ሚሊዮን በላይ የሰበሰቡለት አማሳኝ አጋሮቹ፥“እርሱ አያውቅም፤ ከግል ገንዘባችን ነው የረዳነው” በሚል ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማዳንና ምዝበራውን ለማስተባበል ልዩ ጽ/ቤታቸውን ደጅ እየጠኑለት ነው
  • “እገሌንና የእገሌን ልጅ አሳክመናል፤ ከኪሳችን እንጂ ከሙዳየ ምጽዋት አልነካንም፤” የሚሉት አማሳኞቹ፥ “የቅዱስነታቸውን አእምሮ እንቀይራለን” በሚል ጉዳዩን ለማዳፈን ይንቀሳቀሳሉ

አዲስ አድማስ፤ ቅጽ ፲፮ ቁጥር ፰፻፵፭፤ ቅዳሜ መጋቢት ፲፯ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም.)(ቃለ ጉባኤውን ከዜናው በታች ይመልከቱ)የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ለልጃቸው ሕክምና የገንዘብ ርዳታ የወሰኑላቸውን የእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ዐሥር የአስተዳደር ኮሚቴ አባላትን ከሥራና ከደሞዝ ያገዱ ቢኾንም ፓትርያርኩ እግዱን ሽረውታል፡፡

ሥራ አስኪያጁ፣ “ለታማሚ ልጃቸው ማሳከሚያ” በሚል ገንዘብ በማሰባሰብ ላይ እንደነበሩ መዘገቡ የሚታወስ ሲኾን፤ ከእንጦጦ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ገዳም ብቻ ግማሽ ሚሊዮን ብር በገዳሙ አስተዳደር ኮሚቴ እንዲሰጣቸው ቢወሰንም፤ የገዳሙ ሒሳብ ሹም ክፍያውን አልፈጽምም በማለታቸው ውዝግብ ተፈጥሮ እንደነበር ይታወቃል፡፡

በሥራ አስኪያጁ እግድ ተላልፎባቸው የነበሩት የአስተዳደር ኮሚቴ አባላት፣ ሥራ አስኪያጁ ከትላንት በስቲያ፣ መጋቢት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በጽ/ቤታቸው ጠርተዋቸው፣ “ስሜን ለማስጠፋት እኔ ሳላዛችኹ ኾን ብላችሁ የሠራችኹት ነው፤” በሚል ግማሽ ሚሊዮን ብር ለመስጠት የወሰኑበትን ቃለ ጉባኤ ውሳኔውን በሚያስተባብል አስተዳደራዊ ውሳኔ ሽረው ቃለ ጉባኤን እንዲቀየሩ እንዳዘዟቸው ይናገራሉ፡፡

በሥራ አስኪያጁ ዕውቅና ተዋቅረው ከተላኩት የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴዎቹ ሦስቱ መጥተው በጠየቁት መሠረት መኾኑን በመጥቀስ በተለይ የገዳሙ አለቃ በስተርጅና እንደማይዋሹና ኹለት ቃል እንደማይናገሩ በማስረዳት፣ የሥራ አስኪያጁን፥“ውሳኔያችኹን በውሳኔ አስተባብሉ’’ ትእዛዝ ባለመቀበላቸው፤ “በስሜ አጨብርብራችኋዋል፤ እኔ ይሰጠኝ ብዬ አላዘዝኩም፤ ሒሳብ ሹሟ ክፍያውን አልፈጽምም ማለታቸው ትክክል ናቸው፤ ልታግዷቸው አይገባም ነበር፤” በማለት ኹሉንንም ከሥራና ከደመወዝ ማገዳቸውን እንዳሳወቋቸው ገልጸዋል፡፡

“ሥራ አስኪያጁ እገዳውን ካስተላለፉብን በኋላ የታገድንበትን ደብዳቤና የገንዘብ ድጋፉን የወሰንበትን ቃለ ጉባኤ ይዘን ቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር በመግባት አስረዳናቸው፤” ያሉት የአስተዳደር ኮሚቴው አባላት፣ የገንዘብ ድጋፉን ስለሰጡበት ኹኔታና ስለ እግዱ የሚከተለውን ብለዋል፡-

“የሲ.ኤም.ሲ ቅዱስ ሚካኤል አለቃ፣ የሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም እና የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ጸሐፊዎች መጥተው አዋጡ አሉን፤ ባናዋጣ እንደምንባረር ዛቱብን፤ ትባረራላችሁ፣ ርምጃ እንወስድባችኋለን ሲሉን እኛ ምን እናድርግ? ወደን አይደለም፤ ከሥራችን እንባረራለን፤ ከደረጃችን እንወርዳለን፤ ማን የሚሰማን አለ? ሰበብ ፈጥሮ ነው የሚያግደን፤ ፍትሕ የሚሰጠን አጥተን ነው ይህን ያደረግነው፤ ሒሳብ ሹሟን፥ እነርሱን አግጄ ወደ ሥራ እመልስሻለሁ ብሎ በማለሳሰለስ እኛን ኹላችንን አገደን፡፡”

ፓትርያርኩ፣ “ገንዘቡ በትክክል ወጥቷል ወይ?” ብለው የጠየቋቸው ሲኾን እነርሱም፥ “አዎ፣ አሰባሳቢ ኮሚቴዎች መጡ፤ አግዙን ብለው ጠየቁን፤ እንዲሰጥ ተፈራርመን ወሰንን፤ እኛ ማወራረድ ስላለብን ቸግሮን በቃለ ጉባኤ ተፈራርመን ሰጠነው እንጂ ሌሎቹ አጥቢያዎች በእጁ አይደለም ወይ ያለሰነድ የሰጡት፤” በማለት ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡

አቤቱታውን ያዳመጡት ፓትርያርኩ፤ የሀገረ ስብከቱን ሥራ አስኪያጅና የገንዘብ ርዳታ የወሰኑትን አቤቱታ አቅራቢዎች፣“እርሱ ቀንደኛ ሌባ ነው፤ እናንተም ሌቦች ናችሁ፤ እኔ ታምሜአለሁ ብላችሁ 500 ሺሕ አውጥታችሁ ልትሰጡኝ ነው ወይ? ገመናችሁ ባይወጣ ስትሞካከሹ ትኖሩ ነበር፤” በማለት መገሠጻቸው ተነግሯል፡፡

እገዳውን በተመለከተም፣ “ማን ላይ ነው ጨዋታ የሚጫወተው፤ እርሱ ንጹሕ መስሎ እናንተን ሕግ ተላላፊ ለማድረግ አይችልም፤” በማለት በአስቸኳይ እገዳው ተነሥቶላቸው ወደ ሥራቸው እንዲመለሱና ጉዳዩም እንዲጣራ በልዩ ጽ/ቤታቸው በኩል ለሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ ትእዛዝ መስጠታቸው ታውቋል፡፡

ጉዳዩ የብዙዎች መነጋገርያ ከመኾን አልፎ በፓትርያርኩ ተግሣጽና ውሳኔ ክፉኛ መረበሹ የተነገረለት የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ፣ ባለፈው ቅዳሜ ረፋድ አማሳኝ አጋሮቹን በሀገረ ስብከቱ አዳራሽ በመጥራት፣ እርሱ ሳያውቅ ከየግላቸው እንደተሰበሰበና የአጥቢያዎቹ ገንዘብ እንዳልተነካ በማስመሰል የሚያስረዱ አምስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ወደ ፓትርያርኩ መላኩ ተገልጿል፡፡

“እኛ የኃይሌን[ኃይሌ ኣብርሃ] ልጅ ሌላም አሳክመናል፤ ግን ከራሳችን ከግል ገንዘብ ነው፤ ለእርሱም ያደረግነው ይኼን ነው፤ እርሱ ግን አያውቅም፤” በማለት፣ ሕጋዊነት ሳይኖራቸው ቁጥጥር የማይደረግበትን ገንዘብ በሕክምና ድጋፍ ስም በማሰባሰባቸው ከሚከተላቸው ተጠያቂነት ራሳቸውን ለማዳንና ሥራ አስኪያጁም በሚሊዮኖች የመዘበረበትን አካሔድ ለማስተባበል የፓትርያርኩን ልዩ ጽ/ቤት ደጅ በመጥናት ላይ መኾናቸው ተመልክቷል፡፡ “ከኪሳችን የመርዳት ልምድ ስላለን ቅዱስነታቸውን አግኝተን አእምሯቸውንና አመለካከታቸውን ማስተካከል አለብን፤” በሚል ተግሣጻቸውን ለመመለስና ለመቀየር ማቀዳቸው ታውቋል፡፡

ከአሰባሳቢ ኮሚቴው አባላት፡- የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የሲ.ኤም.ሲ ቅዱስ ሚካኤል፣ የመካኒሳ ቅዱስ ሚካኤል፣ የሳሪስ ጻድቁ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ፣ የጀሞ ቅድስት ሥላሴ፣ የገርጂ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ የጻድቁ አቡነ አረጋዊና ገብረ ክርስቶስ፣ የደብረ ይባቤ ቅዱስ ያሬድ አለቆች፤ የሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም አለቃና ጸሐፊ፤ የብሔረ ጽጌ ቅድስት ማርያምአለቃና ሒሳብ ሹም፤ የደብረ ጽጌ ቅዱስ ዑራኤል አለቃና ተቆጣጣሪ፤ የብሥራተ ገብርኤል ጸሐፊና ሒሳብ ሹም፤ የመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም፣ የጽርሐ አርያም ቅዱስ ሩፋኤልና የደብረ አሚን ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖትጸሐፊዎች ይገኙበታል፡፡

*          

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here