Home Poems መንታ ፍቅር

መንታ ፍቅር [ፍሬዘውድ ተስፋዬ]

          መንታ ፍቅር

          (. . . . እስከ ቀብር)

የሰው ቁንጮ ምሳሌውን ፣ የልቡን ላይ ውበት ቃኝተን
ቅያሜውን ይቅር ብሎ ፣ በይቅርታው ሙቀት ሟሙተን
ከድፍን ጥላቻ ይልቅ ፣ የፍቅር ጉልበቱን አየን
በዛብህን እስከትሎን ፣ ቀብር አፋፍ አደረስን     

የስስት እቅፉን ወዶ ፣ በሃሳቡ ተበራይቶ
ከልቦናው በመነጨ ፣ በእርሱ መቁነን ተለክቶ
በጫማው ልክ የተጫማ ፣ በመንፈሱ የፈጠነ
ከትውልዱ መኻከል ሰቦ ፣ “ጎጃም ማሬን. . .” አዘፈነ

የጽናት ገጹ ብሩህ ነው ፣ ዘመን ሻግሮ ድንቅ ያሳያል
ወዲያ ላለው ክፋይ ገላ ፣ ለማሰሪያ ይማልዳል
የሰውን ግብሩን እየለየ ፣ ድፍን አገር ያስመዝናል

ከመቃብር ጥቁር አፈር ፣ በጎ ስራን ያስመዝዛል                                                      

ይኖራል በፍስሃ አለም ፣ ቅንነት ልቡ ላይ ጽፎ
ረሃብ ቸነፈር ስደት ፣ መጣለት ከአገር ተገፎ
ይባዝናል ህልሙን ሊያየው ፣ አባቶቹን ተደግፎ
የተጣደው የዘመን ድስት ፣ ቢሆንበት ንፍሮ ገንፎ

ስንቱ ልሂቅ ስንት አጣኝ ፣ “ አዲዮስ ” ብሎ የተወውን
ለዕለት ቂጣ አየሸጠ ፣ ቅድስና ብኩሩናውን
ዕጣ አውጥቶ እየሰጠ ፣ መከበሪያ ብርቅ ጌጡን
እርሱ ግን  . . . ሚስጢሩን ሊያየው ፣ ይዳስሳል ብራናውን

እንደደራሽ ውሃ ፈሶ ፣ የጨለመ ብርሃን ሊገፍ
እጁን ከእጇ  አቆላልፎ በመቻቻል ክንፍ ሊያከንፍ
ልቦናውን እያስዋበ ፣ ሽምግልና ሃሳብ ማግዶ
በመንፈስ እየከነፈ ፣ ልብራ ይላል እርሱ ነዶ  

በስሜቱ ከልብ ደራሽ ፣ መላሽ ነው ውለታ መላሽ
በታሪክ መስመር ተጓዥ ነው ፣ እንደ መልካም ውሃ ፈሳሽ
ኮከብ ሆኖ ላለፈው ሰው ፣  ለላቡ ለደሙ ዋጋ ለድካሙ ስንኝ አውራሽ          

የስቃይ ምጥ አማጭ አናት ፣ መከታነት ያጣን  አባት
ሰብሳቢ አልባ ህፃት ፣ ለልመና የውጡ አያት
ለጉልበቱ ማዋያ መስክ ፣ የተስፋ ስንቅ ያጣ ወጣት

የጭካኔን ጥጋት አይቶ ፣ በእንባ ዥረት መታጠብን
በይስሙላ ሸንጎን በደል ፣ በአንጋች ዱላ መዋከብን
ገደል አፋፍ የቆመ ህዝብ ፣ በተስፋ ዕጦት የደካየ
“. . . አይነጋም ወይ . . “ ብሎ ይላል ፣ የጨለመ አገር እያየ

በምጣድ ላይ የተጣለ ጥርኝ ፍሬን ተመስሎ ፣ በግለቱ በፍግ ያራል
የተራበ  እራስ ቢያጣም  ፣ ለፍቅር ራብ ማስታገሻ  አጋፔውን  ይጋግራል
ለወገኑ ለአገሩ አንጋጦ ከላይ እያየ ፣ ምህረት ዝናብ ከአርያም ይለምናል
እንደ እናትም እንደ አባት እንደ አያትም እየሆነ ፣ ኤሎሄ ብሎ ይጮኻል

ጥላቻን ያሉ እንደሆነ ፤ ይሄ ዘመን ጉድ  አሳየን
በቃኤል ገፅ የተሳለ ፣ ወንድማችን በረታብን
እንደ ዮሴፍ ለመከራ ፣ ማሳደዱን አበዛብን
ባልተገራ ፈረስ ስግሮ ፣ የፍቅር እርከኑን ስብሮ
ከዜግነት ክብር ዙፋን ፣ እኛን ጣለን አሽቀጥሮ

ከአብራኩ እንዳልወጣ ፣ ርህራሄ አንጀት ነስቶት
በጲላጦስ አምሳል በቅሎ ፣ ያለ ሃጥያቱ ሃጥያት ሰጥቶት                                                  

በፈጠረው ደረቅ ወሬ ፣ ስንቱን በነፍስ ፈረደበት
ያረገዘ ቂም አጓጉሎ የአጓጎለ አመርቅዞ ፣ አይጨክኑ ጨከነበት

አስከፍሎት ህይወት ዋጋ ፣ መግደሉ አልበቃ ብሎ
ጥርኝ አፈር ተበድሮን ጥርኝ አፈር ከሆነበት ፣ ካረፈበት ተከትሎ
ቀብር ከፍቶ አስከፍቶ ፣ በአፅሙ ላይ እያፈጠ
በማይሰማው  ቅሪት አካል ፣ በድቤው ላይ አላገጠ

እንዲህ ነው ፣ እንዲህ ሆነናል
በሁለት ጎን የተሳለን ፣ ቢላዋን ተመስለናል
በአንድኛው ስናክምበት ፣ በሌላው ገለንበታል
ገሚሱ አገር ሲያቀና ፣ ለማፍረስ ቀሪው ይተጋል

ጉስቁል ገላ ፣ የከሳ አገር ፣ በድን ሃሳብ ፣ የደም አፈር ፣ ጩኸት ዋይታ እያየ ነው
ከትውልዱ መኻከል ወጥቶ ፣ “ . . . ጎጃማ ማሬ . . .” ን የተቀኘው
ያለፈን የፍቅር ታሪክ ያለፈን የፍቅር ጊዜ ፣ ኋሊት ሄዶ የተመኘው ።    

ፍሬዘውድ ተስፋዬ

ነሃሴ 2009/Augest 2017

antachew@hotmail.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here