Home Poems ምነው ሳትነግሩን?

ምነው ሳትነግሩን? [ ክሱታፌ ምግባር]

ምነው ሳትነግሩን?

ምነው ሳትነግሩን ምስክር ሳትሆኑ
ታምር ተፈጽሞ ድብቅብቅ መሆኑ
ወንጌል ሲተገበር እምነት ሲራቀቅ
ተራሮች ሲሄዱ እያሉ ፈቀቅ
ዳሸን ስፍራ ለቆ ሲገባ ትግራይ
ላሊበላ ነቅሎ አዲግራት ሲታይ
ምነው ሳትነግሩን ምስክር ሆናችሁ
የስናፍጭ ቅንጣት እምነትን ይዛችሁ
ተራራውን ከንበል እልፍ ያረጋችሁ
እንላቸው ነበር እንኳን ደስ አላችሁ
ምነው ሳትነግሩን ምስክር ሆናችሁ?
ግሙዝ ነኝ እያለ ሐጎስ ወንድማችሁ
ስፈልግ ኦሮሞ አኝዋክ መዠንገር 
ወልቃይቴ ደቡብ እንዲሁም አፋር
ደግሞም ጎጃሜ ነኝ ስፈልግ ዓባይን
ጎንደሬ እሆናለሁ ስፈልግ ደጀንን
ጥምር ዜጋ ነኝ ከልካይ የሌለኝ
ወርቁን ከፈለኩም ደቡብ ሕዝብ ነኝ
እያለ ሲራቀቅ ጎይቶም ወዳጃችሁ
ሰባኪያን ገጣሚዎች ምነው ዝምታችሁ
ታምርን መመስከር ተሳነው ብዕራችሁ
አንደበተ ርቱዐን ሰባኪ ትንታጎች
መናፍቅ ተሃድሶ ነገረ ስርአቶች
ወገን ለማሳደድ ሴራ ጠንሳሺዎች
መርፌ የምታጠሩ ግመል የምትውጡ
ውነቱን በሃሰት የምትሽቃቅጡ
ተራሮች ሲሄዱ በእግር ሲራመዱ
ምስክርነቱ የት አለ መንገዱ?
ይሄ ነው ወንጌሉ የጌታ ትምህርቱ?
እንዲህ ነው ዮሐንስ ምስክርነቱ?
በሄሮድስ የተስዋው ሰማዕትነቱ?
አረ ተመልከቱ ዓይናችሁን ክፈቱ
ዓይናችሁ ካላየ ይህን በግዝፈቱ
ተራራ ሲራመድ አናይም ማለቱ
መልስ አይሆናችሁም በዳግም ምፅዓቱ
ግዙፉን ተራራ ሲሄድ ካላያችሁ
ዝምታ ይሻላል አንደበት የላችሁ
እርስዎስ ፓትርያርኩ ምነው ዝምታዎ
የሱባዔ ውጤት የጸሎት ፍሬዎ
ተራሮች ሲጓዙ እያዩ ባይንዎ
ተመስገን ይበሉ ይህን ላሳየዎ
ዝም አይበሉ አቡነ እግዜር ካሳየዎ
 
   ክሱታፌ ምግባር

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here