Home News and Views የዘመን መለወጫ በዓላችን አከባበር ለማደናቀፍ ወይም ለማዳከም ሲደረጉ የነበሩና እየተደረጉ ያሉትን አሻጥሮች...

የዘመን መለወጫ በዓላችን አከባበር ለማደናቀፍ ወይም ለማዳከም ሲደረጉ የነበሩና እየተደረጉ ያሉትን አሻጥሮች [ታጠቅ መንጂ ]

 

ወያኔዎች ሃገራዊና ሕዝባዊ ሉዓላዊነታችንን ከተቆጣጠሩበት 1983 ዓ.ም ጀምሮ በእኛነታችን ላይ ያደረሱትን ግዙፍና ሁለገብ ጥቃቶች  መዘርዘሩ ለቀባሪ መርዶ መንገር ዓይነት ስለሚሆንብኝ – ያንን ወደ ጎን ትቼ ከአርእስቴ ጋር ወደ ሚዛመደው ነጥብ አመራለሁ ። ከዚያ አሳዛኝ (ትራጂክ) ሁኔታና የታሪክ አጋጣሚ ወቅት ጀምሮ  በሚከተሉት ምክንያቶች  ሰፊውና ጭቁኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፥ ባህላዊ ፣ ልማዳዊ ፣ታሪካዊና ሃማኖታዊ ወዘተርፈ በዓሉን ወይም አውደ ዓመቱን በሥነ-ሥርዓት እንዳያከብር አድርገውታል። ይኽውም፤

  • ከእነሱ ጋር የጎሣ ሰንሰለት የሌለው ፣ ከእነሱ ጋር በጥቅማ ጥቅም ያልተቆራኘው ፣ በወያኔነት ፖለቲካ መሃደራቸው ውስጥ የሌለውን ወዘተ..ጭቁኑና ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ፥ ከቅጥር ሥራውን በማባረር፣ ንግዱን በመንጠቅ፣ አርሶ ከሚኖርበት መሬቱን በማባረር፣ አከራይቶ የሚኖርበትን ቤቱን በመቀማት፣ ከውትድርና ሞያው በማስወገድ  ወዘተ.. ፍጹም (አብሱልት) ድሃ አድርገውታል። ስለሆነም ዶሮ ቀርቶ እንቁላል እንኳን ገዝቶ  አውደ ዓመቱን ማክበር እንዳልቻለ  በተደጋጋሚ በተለያዩ ድረገጾች የተገለጸ ሃቅ ነው ።
  • ተሰባስበው በአንድነት ሃይማኖታዊ/እምነታዊ በዓል ማክበር በሽብርተኛነት ስለሚያስፈርጅ
  • በሃይማኖት ላይ ሃይማኖት ፣ በሰነዶስ ላይ ሰነዶስ፣ በመስጊድ ላይ መስጊድ፣ በሼካ ላይ ሼካ ወዘተርፈ በማደራጀትና ሁከት በመፍጠር- ሃማኖተኞች መንፈሳቸው ተረጋግቶ ሃይማኖታዊ በዓላቸውን እንድያከብሩና እንዳይፀልዩ እንቅፋት በመፍጠር
  • የጋራ የሆነና በጋራ የምታከብሩት ብሄራዊ (ታሪካዊ ቀን፣አውዳዓመት፣ክብረ-በዓል) ወዘተርፈ የላችሁም በማለት፤ዛሬ የነዚህ ብሄር/ስብ ቀን ነው ፣ነገ የነዚያ ብሄር/ስብ ቀን ነው ፣ከነገወዲያ  የእነኚያ ብሄረስብ ቀን ነው  እያለ የወል እሴታቸውን በጋራ እንዳያከብሩ በማደናቀፍና በመከፋፈል
  • ዛሬ የዚህ ጎሳ ባንድራ ቀን ነው ፣ ነገ የዚያ ዘውግ ባንድራ ቀን ነው፣ከነገወዲያ የእነኚያ ብሄር/ስብ  ባንድራ ቀን ነው  ወዘተ..በማለት በአንድ ሰንደቅ ዓላማ ሥር ተሰባስበው አያቶቻቸውን፣ቅድመ አያቶቻቸውና ፣ቅም አያቶቻቸውን የጀግንነት ታሪክ የሰሩበትን መታሰቤያ ቀን እንዳያከብሩ በማደናቀፍ ወዘተርፈ።

እነዚህን መሰሪ ተንኮሎችና ስልቶች እንዳሉ በባእዳን አገሮች ባሉት ኢትዮጵያውያን  ላይ ለማዋል ካድሬዎቻቸውን በቁጥር በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን  ወደ ሚገኙበት ባዕዳን አገሮች እየላኩ ፤                       1.በኢትዮጵያውያን መካከል አንድነት እንዳይኖር ፣ የጋራ ኮሚኒቲ ፣ የጋራ ቤተክርስቲያን ፣ የጋራ መስጊድ  የጋራ ዕድር እንዳይኖራቸው                                                                                                2.የወል ባህላዊ ፣ ታሪካዊ ፣ሃይማኖታዊ፣ወጋዊ(የሠርግ)፣አውደ ዓመታዊ ወዘተርፈ ቀኖችና በዓሎች    በጋራ እንዳያከብሩ

3.የጋራ የስፖርትና የባኅል ቀን እንዳይኖራቸው – እንቅፋት ሲፈጥሩና ሲከፋፍሉ መኖራቸውን በያለንበት የምናየው ሃቅ ነው ። እነዚህ ዓይነት ችግሮች ካሉባቸው ባዕዳን አገሮች ወይም እስቴቶች አንዱ ሜልበርን (አውስትራሊያ) ነው ።ከእነዚህም አንዱ የወያኔ ቅጥረኞች በየዓመቱ ‘የዘመን መለወጫ በዓላችን አከባበር ለማሰናከል/ለማደናቀፍ’  የተለያዩ ሥልቶች የሚጠቀሙ መሆናቸውን ነው ። እንዴት (ሃው )? ምንና ምን  ተብዬ ብጠየቅ መልሴ የሚከተሉት ይሆናሉ

ሀ/  በየዓመቱ የኢትዮጵያውያን ኮምኒቲ የዘመን መለወጫ በዓላችን የሚያከብርበትን ዕለት ጠብቀው፤ ካልተሣካላቸውም ከሣምንት በፊት ወይም  ከሳምንት በኋላ እውቅ ዘፋኝ/ኞች በማስመጣት ወደ በዓላችን የሚመጣውን ማህበረሰብ በተለይም ወጣቱን ወደዚያ በመሣብ ፤ በዓላችን ደመቅ ብሎ እንዳይከበርና ከአውደዓመቱ የምናገኝውን ገቢ እንዲዳከም ማድረግ

ለ/ ከሁለት ወይም ከሦስት ወይም ከአራት ሣምንታት በፊት የተሰማውን መርዶ አቆይቶ የዘመን መለወጫ በዓል በሚከበርበት ቀን/ዕለት በማርዳት ሰው ወደ በዓሉ እንዳይሄድ ጠልፎ ማስቀረት

ሐ/ የአንድ ክፍለ ሃገር ፣ አውራጃ ፣ ወረዳ ፣ ሠፈር ወዘተ..ተወላጅ በመሆን ምክንያት ከሚቀራረቡት ወስጥ አንዱ/አንዷ – የነቃሁ ነኝ ወይም አሰባሳቢያችሁ ነኝ ባይ ወያኔ ፤ነገር ግን ወያኔነቱ/ቷ በዚያ ቡድን አባሎች የማይታውቅ/የማትታወቅ ሥውር ወያኔ ፤ እቤቱ/ቷ ቅልጥ ያለ ደግስ አዘጋጅቶ/ታ የዚያ ጎጥ አባሎች በዓላችንን ወደ ምናከብርበት ቦታ እንዳይሄዱ ማድረግ/ማስተጓጎል

መ/ የአንድን ጎስ ቋንቋ ተናጋሪ በመሆን የሚተዋወቁና በዚያ ዙሪያ የተሰባሰቡትን ጎሰኞች- የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ የዘመን መለወጫ በዓል የሚደግሥበትን ቀን ጠብቀው ሰለሚደግሱ

ሠ/ በየዓመቱ የኢትዮጵያውያን ኮሚኒቲ የዘመን መለወጫ በዓል የሚያከብርበትን ዕለት ተጠብቆ- አገር ቤት በሚመላለሱ በወያኔ ቤተክርስቲያን አባላት የሚዘጋጅ – ቀንና ለሊት የሚያስጨፍር መጠነ ሰፊ ግብዣ/ፓርቲ ስለሚደረግና ጥሪውም ወደ በዓላችን በሚመጡትን ኢትዮጵያውያን ላይ ያተኩር መሆኑን

ረ/ይህንን ዕለት ጠብቆ ሠርግ መሠረግ

ከዚህ በላይ የዘረዘርኳቸውን ፀረ-እንቁጣጣሽ በዓላቸችን አሻጥሮች አንዳቸውም-በቅድመ ወያኔ በትረ  ሥልጣን ያልነበሩ ናቸው ፤ በስሌት ተንኮል ሳይሆን በአጋጣሚ በዚያ ዕለት ሌላ ድግስ ለመደገስ ወይም መርዶ ለመቀመጥ ያሰበ/ች ቢኖር/ብትኖር እንኳን ፤ኮሚኒቲያችን የዘመን መለወጫ በዓል የሚያከብርበት ቀን መሆኑን ካወቁ ፤ድግሱም መርዶውም ለሌላ ቀን ይሸጋሸጉ ነበር ።

አሁን ያለንበት ሉል ማኅበረሰብ (ግሎባል ኮምኒቲ) ከሌሎች አገር ዜጎች የሚለየን፤

  • በባድራችን ፣በቋንቋችን ፣ጎላባሉ በባህላቻችን (manifested/obvious culture) ፣ታሪክ የሚያውቁ -ከባዕዳን ቅኝ አገዛዝ ነጻ ሆነን የኖርን ሕዝብ መሆናችንን ወዘተርፈ ሲሆን
  • በየምንኖርባቸው ባዕዳን አገሮች ማኅበረሰብ- እውነተኛ እኛነታችን ማወቅ የሚችለው -በብሄራዊ ክብረበዓሎቻችን፣በአውደዓመቶቻችን፣ በስፖርትና በባህላዊ ፋንጣዚያዎቻችን እና በሠርጎቻችን ወዘተርፈ ዕለቶች/ወቅቶች በምናድርጋቸው -እንግዳ አቀባበላችን፣ ሰላምታችን፣በባህላዊ (ልብሶቻችንና አለባበሳችን፣ ምግቦቻችንና የአበላል ዘቤያችን፣ ውዝዋዜዎቻችና ጭፈራዎቻችን፣ የጫወታ መሳርያዎቻችን ፣ሥነ-ሥርዓቶቻችን ወዘተርፈ ነው ።

ለእነዚህን የእኛነታችን እሴቶች በየደረስንበትና በያለንበት -መጨነቅ፣ መኮትኮት፣ መንከባከብ ፣ ማበልጸግ ፣ ማሳደግ  ወዘተ.. ትውልዳዊና ዜጋዊ ግዴታችን ነው ። ‘ትውልዳዊ’ ያልኩበት ምክንያት በባዕዳን አገሮች ዜግነት የምንኖር ስላለን ነው (citizen by naturalization not by birth) ።

 ሁሉም ብሄሮች/አገሮች ለዘመን መለወጫ በዓላቸው ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡት ሁሉ- እንቁጣጣሽ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ቁንጮ ወይም እምብርት አውደ በዓላችን ነው ። ከእናት አገራችን  እጅግ በጣም እርቀን በምንገኝባቸው ባዕዳን አገሮች ተሰባስበን በጋራ የዘመን መለወጫ አውደ ዓመታችን እንዳናከብር  የሚደረጉትን የተለያዩ የወያኔ ካድሬዎች አሻጥሮችን ተባባሪ መሆን በእኔነት ላይ መዝመት፣የእኔነት ድንቁርና፣ የእኔነት ቀውስ (identity crisis) ወዘተ… አይሆንምን ? የወያኔ ካድሬዎች በደገሱበት ሁሉ መብላት፣ መጠጣት ፣መጨፈር ወዘተ..ስለምችል የኢትዮጵያውያን ኮምኒቲ ወደ አዘጋጀው የዘመን መልወጫ በዓል ምን አስኬድኝ ከሆነ? ማናቸውም ብሄራዊ አውደ ዓመቶቻችን፣ታርካዊ ቀኖቻችንና        ክብረ -በዓሎቻችን የምናከብረው ፣ ለበመብላት ፣ለመጠጣት፣ለመጨፈር ወዘተ.. ብቻ አይደለም ። ይህ ቀን እኔነቴን ከሚመሰከሩባቸው ቀኖች አንዱ ነው፤ ይህ በዓል የጋራ እኛነት(collective identity) ከሚንፀባረቁባቸው ቀኖች አንዱ ስለሆነ በቦታው መገኘት አለብኝ በሚል ሥነልቦና፣ በባህላዊ ልብሶችና ጌጣጌጦች አጊጦ በቦታው መገኘት፣በዓሉን ማድመቅና ለሌሎች ምሳሌ መሆን ነው።

“ማን ነኝ ? ምንድ ነኝ ? የት ነኝ ? የመኖሬስ ጥቅም ምድነው ? ተብሎ  ባልተመረመረ ሕይወት ውስጥ መኖር – የመኖር ትርጉም የለውም” ( ሶቅራጠስ – ጥንታዊው የግሪክ ፈላስፋ) ። ምርጥ ሸቀጦች ሽማች መሆን ፣ሃብት ማካበትን ፣ በቅንጦት ቁሳቁሶች(conspicuous/luxry goods) መታጅብ ፣ በግለኝነት  ሕይወት መደሰትን ወዘተ  የጥሩ  ሕይወት ምሳሌዎች አይደሉም ፤ ጥሩ ሕይወት ማለት ፦ ለጋራ እሴቶች ፣ ለጋራ እኛነት ፣ ለጋራ ብልጽግና (for the common or the collective good) ወዘተ.. ስንቆም፣ስንታገል፣ስንተባበር፣ስንመካከር ወዘተርፈ ነው ።

  

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here