Home News and Views የሀብታሙ አለባቸው «ታላቁ ተቃርኖ»

የሀብታሙ አለባቸው «ታላቁ ተቃርኖ» [አቻምየለህ ታምሩ]

የሀብታሙ አለባቸው «ታላቁ ተቃርኖ»

ሀብታሙ አለባቸው «ታላቁ ተቃርኖ» በሚል ርዕስ የጻፈውን አዲስ «መጽሐፍ» አንዳንድ ሰዎች ሳይሳሱ የአድናቆት ቃላትን ሲደረድሩ ተመልክቻለሁ። መጽሐፉ ከርዕስ ጀምሮ [The Greatest Contradition ከሚለው] በእንግሊዝኛ እየታሰበ በአማርኛ እየተተረጎመ የተጻፈ ይመስላል። ወያኔዎች በተለያየ ጊዜያት የሚያቀርቧቸው ማደናገሪያዎች ፈረንጆች በእንግሊዝኛ አስበው ወደ አማርኛ የሚመለሱ ሀሳቦች መሆናቸውን መቼም ነጋሪ የሚያሻ አይመስለኝም። የሀብታሙን «ታላቁ ተቃርኖ» አንዳንድ ሰዎች እስከማጣቀስ ደርሰዋል። ወዳጄ Girma Gutema የሀብታሙን «መጽሐፍ» በመጥቀስ ከሚከራከሩት መካከል ቀዳሚው ነው።

ኦቦ ግርማ በትናትናው እለት ከTedla G Woldeyohannes ጋር ባደረገው አንድ ሙግት ላይ «ዳግማዊ ምኒልክ የአማራና የትግሬ ጠባቂ የኦሮሞ ገዢ ነኝ» ብለዋል ሲል ሲናገር ሰምቼው ምንጭ እንዲያቀርብ በጠየቅሁት መሰረት እንደመከራከሪያ ያቀረበውን «ሀሳብ» ከሀብታሙ አለባቸው መጽሐፍ እንዳገኘው ነግሮኛል። ሆኖም ግን ግርማ ለጠቀሰው ጭብጥ ሀብታሙ ካቀረበው የፈጠራ ታሪክ በስተቀር አንድም ቦታ ተጨባጭ ማስረጃ ማግኘት አይቻልም።

ከሁሉ በላይ የገረመኝ የሀብታሙን መጽሐፍ እንደ ምሁራዊ ስራ በማጣቀሻለት ለመጠቀም የሚሞክሩ ምሁራንን ማየቴ ነው። የሀብታሙ አለባቸውን መጽሐፍ ወዳጄ BefeQadu Z. Hailu ልኮልኝ አንብቤ ከጨረስሁ ቆይቻለሁ። ሀብታሙ አለባቸውን በሚገባ አውቀዋለሁ። መቀሌ ዩኒቨርሲቲ አስተምር በነበረበት ወቅት እኔ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል፤ እሱ ደግሞ ፖለቲካል ሳይስን ትምህርት ክፍል ውስጥ ያስተምር ነበር። እኔና ሀብታሙ ከመተዋወቅም አልፈን ከሁለት አመታት በላይ ያህል ማታ ማታ አንድ ሁለት እያልን ዱላ ቀረሽ ሙግት እናደርግ ነበር።

ሀብታሙ መስተፋቅር ከተሰራበት ሰው በላይ ወያኔን የሚያፈቅር የመለስ ዜናዊ አምላኪ ነው። ሁል ጊዜ ስንከራከር «ኢትዮጵያ ሌላ ኢየሱስ አያስፈልጋትም፤ መለስ ዜናዊ የሚባል ኢየሱስ ሞቶላታል» ይለኝ ነበር። እኔ ደግሞ ኢትዮጵያን እግዚያብሔር እንደማይጥላት ሊያጠፏት የተነሱትን የአድዋዎቹን መለስ ዜናዊንና አባ ገብረ መድህንን ሳይጥሏት መቅደሙን አነሳለት ነበር። ለሙግት አጀንዳ ስንገልጥም ሆነ በመንገድ ስንተላለፍ አልያም ቡን ስንጠጣ ከመጣገባችን የተነሳ እኔ «ኮምኒስቱ»፤ «ድጋዩ» ፤ «የወያኔ ሎሌው» ፤ «አገልጋዩ» ወዘተ እያልሁ ስጠራው እሱ ደግሞ በበኩሉ እኔን በወያኔ ቋንቋ «ጸረ ሕዝቡ» እያለ ይጠራኝ ነበር።

ሀብታሙ ለቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ያለውን የመረረ ጥላቻና አዜብ መስፍን ልታፈቅረው ከምችለው በላይ ለመለስ ዜናዊ ያለውን ፍቅር ሳስብ ብአዴን የሚባሉት ነውረኛ ቅጥረኞች ድቅን ይሉብኛል። በመለስ ዜናዊ ተገርፎ ዘብጥያ የወረደው የቤንሻንጉሉ ያረጋል አይሸሹም የመለስን ሞት እስር ቤት ሆኖ ሲሰማ ልክ ኃይለ ማርያም ደሳልብኝ እንዳደረገው አፉን እስከ መጨረሻው ወደላይ ከፍቶ ነግቶ እስኪመሽ ሲያነፈርቅ እንደዋለ አብሮ ታስሮ የነበረው ወዳጄ ተመስገን ደሳለኝ አጫውቶኛል። አንዳንድ ጌዜ ሳስበው ሀብታሙ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ላይ ያለው ጥላቻ የሚያመልከው መለስ ዜናዊ ጸበል አፍልቆ ቢያጠምቀውም እንኳ የሚወጣለት አይመስልም 🙂

ሀብታሙን ስለማወቄ ይህንን ያህል ካልሁ ወደጻፈው ድርሳን ቁም ነገር ልመለስ። ሀብታሙ በመጽሐፉ ውስጥ ስለሚያነሳቸው የታሪክ ጽሁፎች አንድም ቦታ ባግባብ ያቀረበው ምንጭና ዋቢ ሰነድ የለም። ልብ በሉ የመጽሐፍና ልዩ ልዩ መጣጥፎች ርዕሶችን አልዘረዘረም አለልሁም፤አልጠቀሰም እንጂ። ማንም ሰው የፈለገውን ጽፎ የማይገናኝ መጽሐፍ ርዕስ ሲዘረዝር ይችላል፤ ይህ ማለት ግን ምንጭ ቀርብሏ አያሰኝም። ሀብታሙ ገጽና ምዕራፍ ሳይጠቅስ ሾላ በድፍን የዋቢ ሰነድ ርዕስ ብቻ በመጽሐፉ መጨረሻ ገጾች ያጠራቀመው ደግሞ ሆን ብሎ ያደረገው ነው። ሀብታሙ ምንጭ ሳይጠቅስ ሊገናዘብ የማይችል የማይገናኝ ዋቢ የሚዘረዝረው የደረተው ትርክት የፈጠራ ነው ተብሎ እንዳይቆጠርበት ክፍተቱ ለመደበቅ ሲል የተጠቀመበት ስልቱ ነው።

ለምሳሌ በመጽሐፉ ገጽ 27 የመጀመሪያ አንቀጽ አምስተኛ መስመር ላይ እንዲህ ጽፏል፤

« አንዳንድ የታሪክ ጸሐፊዎች ይህንን ከቅኝ ግዛት የማይተናነስ ዲፕሎማሲያዊ ጫና “የአጼ ኃይለ ሥላሴን ጥንቃቄ የተሞላበት አያያዝ ያሳየ” ነው ሲሉ ይከራከራሉ (መርስኤ ኀዘን ቂርቆስ 2008)።»

«የአማርኛ ዋቢ ሰነዶች መዘርዝር» በሚል ርዕስ በመጽሐፉ ገጽ 392 ላይ ከታች ወደ ላይ ስንቆጥር በሁለተኛነት በዘረዘረው ረድፍ ላይ ከፍ ሲል ያቀረብሁት የሀብታሙ አረፍተ ነገር መጨረሻ ላይ የተቀመጠውን «ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ( 2008) የሚለውም ምንጩን በዝርዝር ሲጽፍ « ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ (1998) የሐያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ፣ የዘመን ታሪክ ትዝታዬ ካየሁትና ከሰማሁት 1896-1922። አዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ ፕሬስ።» ይላል።

ሀብታሙ ሲያጣቅስ «2008» የሚል አመተ ምህረት ተጠቅሞ ምንጩን ሲዘረዝር ግን «1998» ያለው የራሱ ሀብታሙ ግድፈት እንጂ እኔ የፈጠርሁት የአሀዝ ስህተት አይደለም።

ልብ በሉ! ከፍ ሲል ያቀረብሁትን ሀብታሙ በመጽሐፉ ያካተተውን የመርስኤ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ሀሳብ ከመጽሐፉ ከየትኛው ገጽና ምዕራፍ እንዳገኘው አይናገርም። ሀብታሙ የጠቀሰው የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ መጽሐፍ ባለ 455 ገጽ ነው። ይህ ማለት የሀብታሙን ባለ 400 ገጽ መጽሐፍ የሚያነብ አንድ ሰው ሀብታሙ የጠቀሰውን የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ለማረጋገጥ የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስን ባለ 455 ገጽ መጽሐፍ ማንበብ አለበት ማለት ነው።

የሀብታሙ መጽሀፉ ጉድለት ይሄ ብቻ አይደለም። መጽሐፉ በፈጠራ ታሪክ የታጨቀም ሀብታሙ ወለድ ትርክት ነው። ለምሳሌ ከፍ ሲል ያቀረብሁት ሀብታሙ «የጠቀሰው»ን የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ሀሳብ ብንወስድ ሀብታሙ ከብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ መጽሐፍ ያጣቀሰው ከጥሊያን ወረራ በኋላ ማለትም ከ1933 ዓ.ም. በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የወሰዷቸውን እርምጃዎች ለማነወር ነው። ሆኖም ግን ሀብታሙ የጠቀሰው የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ የትዝታ ዘመን የሚያቆመው በ1922 ዓ.ም. ነው። ብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ ሀብታሙ በጠቀሰው መጽሐፍ ውስጥ አንድም ቦታ ከ1922 ዓ.ም. ስለሆነው ታሪክ አያወሩም። ይህ ማለት ሀብታሙ የጠቀሰው የብላታ መርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ የሀብታሙ ፈጠራ ነው ማለት ነው። ሀብታሙ መጽሐፉን ሙሉ በሙሉ የሞላው በዚህ መልክ አንድም ቦታ ምንጭ ሳይጠቅስ ነው።

እንግዲህ! ሀብታሙ መጽሐፉን የጻፈው አንድም ቦታ ምንጭ ሳይጠቅስ ሙሉ በሙሉ ሾላ በድፍን ነው። እኔ ግን የገረመኝ የሀብታሙ መጻፍ አይደለም። እኔን የገረመኝ አንድም ምንጭ ሳይጠቀስ የተጻፈን ድርሰው እንደ ቁም ነገር ቆጥረው የሚያጣቅሱ የተማሩ ሰዎችን ማየቴ ነው። ሀብታሙ ከዚህ በፊት «አውሮራ» የሚል መጽሀፍ አሳትሟል። አውሮራን ያነበበ አንድ ወዳጄ «የአስመራን መንደሮች ከኦሮማይ በኋላ ያስጎበኘንን አዲስ መጽሐፍ አንብበሀል ወይ?» ሲል ጠየቀኝ። ገርሞኝ ሳቅሁ። ሀብታሙ አስመራን አያውቀውም። ከመረብ ማዶም ተሻግሮ አያውቅም። ብዙ ሰው ግን አውሮራን አንብቦ ሀብታሙ አስመራን ከበዓሉ ግርማም በላይ እንደጁ መዳፍ የሚያውቃት አድርጎ ሲናገር ሰምቼ እገረም ነበት።

እንግዲህ! መቼም አንድ ትምህርት ቤት የገባና ተምሬያለሁ የሚል ሰው ሀብታሙ ገጽና ምዕራፍ ሳይጠቀስ ከፍሲል በቀረበው መልኩ ሾላ በድፍን የደረተውን ነጭ ትርክት እድነ እውነተኛ ምንጭ እያጣቀሰ የምር ሙግት የሚከፍት አይመስለኝም።

የአንድ ጽሁፍ ጥራት የሚለካው ጽሁፉ በአግባብ በሚያቀርበው የማስረጃ ጥራት ነው። አንድም ቦታ ምንጭ ያልጠቀሰን የልብ ወለድ ደራሲ እንደ ሀቅ ጸሐፊ መቁጠር የሚችል ቢኖር ጭንቅላቱን አሸዋ ውስጥ ቀብሮ፤ አንጎሉን መርጎ፤ ማሰቢያውን ደፍኖ የሚያነብ ሰው ብቻ ነው።

የሀብታሙን መጽሐፍ ያነበቡና የተደነቁ ሰዎችን አንድ ነገር challenge ላደርጋቸው እወዳለሁ። እስቲ «ተደጋግሞ ይነበብ» ስትሉ የመሰከራችሁለት የሀብታሙ አለባቸው መጽሀፍ አንድ ቦታ ገጽና ምዕራፍ ቆጥሮ ያጣቀሰው  ምንጭ ካለ አሳዩኝ?

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here