Home News and Views ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ የጻፈው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ ምረቃ

ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ የጻፈው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ ምረቃ [ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ]

ክቡራትና ክቡራን፤
የዛሬው ሥነ ሥርዓት ኒው ዮርክ ከተማ በመሆኑ፥ ደራሲው ክቡር ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ በምረቃው ከሚያገኘው ደስታ ጋራ የሚወዳደር ደስታ ይሰማኛል። ዋሽንግተን ዲ. ሲ. በተደረደው ሥነ ሥርዓት ላይ ባለመገኜቴ የተሰማኝን ቁጭት አኮስምኖልኛል። ለዚህ አጋጣሚ ከአምላክ ሌላ የማመሰግነው ይኖር ይሆን?
ዶክተር አክሊሉ የዚህን መጽሐፍ ረቂቅ እንድመለከተው ሲልክልኝ፥ ሌላ የጀመርኩት ሥራ ስለነበረኝ ያንን ስጨርስ እመለከተዋለሁ ብየ ገፋ ከማድረጌ በፊት፥ ገጾቹን ማገላበጥ ጀመርኩ። ሥራየን ትቼ አንብቤ እስክጨርሰው ድረስ በዚያው ምርኮኛው ሆኜ ቀረሁ። ጣመኝ፥ ጣፈጠኝ። በራሴ ድርሰት ላይ እንደማደርገው፥ ዓይኑ ዐ፥ ሐመሩ ሐ፥ ፀሓዩ ፀ፥ እያልኩ የፊደል ለውጥ ማድረግ ጀመርኩ። ዕውቀትን በማያደናቅፍ አማርኛ የማቅረብ ሀብት የተሰጣቸው ደራሲዎች ጥቂቶች ናቸው። አንዱ ዶክተር አክሊሉ ነው።
ስለ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ብዙ አንብቤለሁ፥ ሲታሙም ሰምቻለሁ፤ ትምህርት ለኢትዮጵያ በሽታ መድኃኒት መሆኑን ያንን ያህል ጽኑ እምነት እንደነበራቸው ያወቅሁት ግን፥ “ማን ይናገር? የነበር”፥ እንዲሉ፥ ከነበረው፥ ሲያድግ ካየውና ካሳደገውም ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ  ደራሲ ከዶክተር አክሊሉ ሀብቴ ነው። ብዙ ነገር ተምሬበታለሁ።ይህ መጽሐፍ አክሊሉን አለቃየ ከመሆን አልፎ አስተማሪየም አድርጎታል።
ስለ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ብዙ ተጽፏል። ሐውልቶች ተቀርጸውላቸዋል፤ ድርጅቶች በስማቸው ተጠርተዋል። ዘላቂውን ታሪካቸውን የያዘው ግን፥ ይህ  ዛሬ የምንመርቀው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ ነው። የንጉሠ ነገሥቱና የዶክተር አክሊሉ ዋና ፍልስፍና መማር ዳግማዊ ልደት፥ መማር አዲስ የሚያደርግ ጥምቀት፥ መማር ለሁለተኛ ጊዜ መፈጠር፥ መማር ከድኽነትና ከበሽታ ነፃ የሚያደርግ  መሆኑን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ ቋሚ ምስክር ነው።  ለዘመኑ ትምህርት ባዳ የነበረን ሕዝብ በፖሊስ እያሳደዱ ከከፍተኛ ደረጃ ያደረሱት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፤ የዚያ ጥረት ውጤቶች፥ (እኛ እዚህ የተሰበሰብነውና ያልተሰበሰብነው ማለቴ ነው) አንዱ ሐውልታቸው ሲሆን፥ ሁለተኛው ሐውልታቸው ዛሬ የምንመርቀው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ ነው። ሌሎቹ ሐውልቶች ሊፈርሱ ይችላሉ፤ ሲፈርሱም አይተናል። ትምህርት ያፈራውና የተጻፈው ታሪክ ግን፥  የማይፋቅ የማይሰረዝ ሐውልት ሆኖ ይኖራል።  የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ  አክሊሉ ያቆመላቸው ነፋስ፥ ቢነፍስ፥ ዝናም ቢዘንም፥ መሬት ቢንቀጠቀጥ የማይነቃነቅ ሐውልት ነው። የንጉሠ ነገሥቱን ስም ከዩኒቨርሲቲው የፋቁት ኀይሎች የዚህን መጽሐፍ ረቂቅ አግኝተውት ቢሆን ኖሮ፥ “የቀበርነውን አነሣብን” ብለው ያቃጥሉት ነበር። ዶክተር አክሊሉ ይኸንን የብዙ ዓመታት ጥናቱን መታሰቢያ ያደረገው ለንጉሠ ነገሥቱ ነው። እንዲህ ያከበራቸው ሊያዋርዳቸው በሚሞክረው ትውልድ ማህል ያላንዳች ይሉኝታ ቀጥ ብሎ ቆሞ ነው። ስማቸው ወደ ቀድሞው ክብሩ በፍጹም ከተመለሰ፥ ከተጠያቂዎቹ አንዱ ዶክተር አክሊሉ ሀብቴ ይሆናል።
የዶክተር አክሊሉን የሕይወት ታሪክ ረጋ ብለን ብናጠናው፥ የአፄ ኃይለ ሥላሴን የትምህርት ራእይ እውን ለማድረግ አምላክ “ዘኀረይኩከ እምከርሠ እምከ” (ከእናትህ ማሕፀን የመረጥኩህ ነህ)  የሚላቸውን የነቢያት ታሪክ ያስታውሰዋል። በስማቸው በተሰየመው ትምህርት ቤት ተማረ፤ አስተማሪዎቹ ዐይናቸውን ጣሉበት፥ በዘመኑ የሚመረጠው የከፍተኛ ትምህርት ሕግ፥ ሕክምና መሀንዲስነት ሲሆን፥ አክሊሉ ትምህርትን መረጠ።  አስተማሪዎቹ ሲሄዱ፥ አሁንም የዘመነ ነቢያትን አነጋገር ልጠቀምና፥ አጽፋቸውን አውርሰውት ሄዱ። አጽፉን ተጐናጸፈው፥ አጌጠበት፥ አሸበረቀበት፤ እኛንም ተማሪዎቹንና አስተማሪዎቹን አስጌጠበት።
የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የዘመኑ ትምህርት በረጅም ጉዞ የደረሰበት የመጨረሻው ምዕራፍ ነው። የዶክተር አክሊሉ ታሪክ ያንን ጉዞ ለመተረክ እንደተጠራ ያመለክታል። አክሊሉ በትምህርት ሥራ ላይ በነበረበት ጊዜ፥ ጊዜ ወስዶ  በየቦታው የተቋቋሙትን ትምህርት ቤቶች ስለጎበኛቸው ዩኒቨርሲቲው ከምን ላይ እንደቆመ ያውቃል። አሁን ደግሞ ይህን መጽሐፍ ሲያዘጋጅ ኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ውጪ የሚገኙ ሰነዶችን አስሳዷል፤ አንዱም አላመለጠውም ለማለት ይቃጣኛል።
ዩኒቨርሲቲያችን የሀገራችን የትምህርት ጉዞ ውጤት አለመሆኑ አክሊሉ ጥርሱን ነክሶ መናደዱን ድርሰቱ ጮክ ብሎ ያጋልጠዋል። ትምህርቱን በልጅነቱ ቀምሶታል፤ የትምህርት አሰጣጡን ገዳማቱን እየዞረ ተመልክቷል፤ ሥርዓተ ትምህርቱን መርምሮታል፥ በየምዕራፉ መጨረሻ የተዘረዘሩት ምንጮች እንደሚያሳዩት ስለ ሥርዓቱ የተጻፉ መጻሕፍትን አጥንቷቸዋል። ቁጭቱን ለመወጣት ታሪኩን ከሥርና ከጥንት ጀምሮ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ተርኮታል። የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ  የሁለት ሥርዓተ ትምህርቶች ታሪክ ነው። “እኛ ምን ትምህርት  አለን?” የሚል ሰው ሲያጋጥማችሁ፥ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲን ታሪክ አንብብ በሉት። ከውጪስ  ምን አመጣን? ማን አመጣልን”  የሚል ሰው ሲያጋጥማችሁ፥ ደግሞ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲን ታሪክ አንብብ በሉት። ታሪክ ማንበብ የሚፈልግ ሰው ሲመጣባችሁ፥ ደራሲው እንደሚለው “የትምህርት ታሪክ የሕዝብ ታሪክ” ስለሆነ፥ ከምትሰጡት የመጽሐፍ ዝርዝር ውስጥ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክን ማስገባት እንዳትረሱ።
ልጅ ካሳ ወልደ ማርያም የዩኒቨርሲቲውን አመራር የለቀቀው ዩኒቨርሲቲው እንደ ሀገሪቱ በፖለቲካ ውጥረት ላይ በነበረበት ጊዜ ነበር። ተማሪዎቹ “ሁሉንም ውሰዱት፥ መላሳችንን ተውልን” እያሉ በነፃ የመናገር መብት እንዲሰጣቸው ጠየቁ፤ አስተማሪዎቹ የዩኒቨርሲቲውን መሪ የመምረጥ መብት ይሰጠን አሉ። ግቢውም ሀገሪቱም “ሕዝብ የፖለቲካ መብት አለው” በየሚል ለሀገሪቱ ባዳ በሆነ ሐሳብ ተወጠሩ። ሁኔታውን ስገምተው መሪያችሁን ምረጡ ብንባል ዶክተር አክሊሉ ሀብቴን ነበር የምንመርጠው። ንጉሡ ቀደሙን። ደስታና ብስጭት አሳደሩብን።
ብዙ ጊዜ ተማርዎቹን “ኮሙኒስም የሚባል የውጪ አገር ርእዮተ ዓለም አመጡብን” እያልን እንወቅሳቸዋለን። እንደትክክሉ ከሆነስ አዲሱ ርእዮተ ዓለም “ሕዝብ አገዛዙን የመጠየቅ መብት አለው” የሚለው ነው። “የሕዝብ መብት” የሚሉት ነገር፥ “ንጉሥ አይከሰስ፥ ሰማይ አይታረስ” የሚለውን ሥር የሰደደውን ባህላችንን አስረሳን።  የተቀባው ንጉሥ የፈላጭ ቈራጭ ሥልጣን የተሰጠው መሆኑን ረስተን አስተዳደሩን የጭቆና አስተዳደር አድርገን ተዳፈርነው። አንበሳና ነምር ሲጣሉ ግልገሏን ንስር እንደወሰዳት ሁላችንም መናችንን ቀረን። የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች የተባለው ደረሰብን።
ዶክተር አክሊሉን ያወቅሁት አለቃየ በነበረበት ዘመን ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት በ1955 ዓመተ ምሕረት  እንዲቀጥረኝ ማመልከቻ ያቀረብኩለት ጊዜ ነው። ያን ጊዜ የአርት ፋከልቲ ዲን ነበረ። በቅርብ ያወኩት ግን የቀዳማዊ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ሆኖ ቢሮውን ስድስት ኪሎ ያደረገ ጊዜ ነው። በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የጠየኩትን ከልክሎኝ አያውቅም። ግን አክሊሉንና እኔን የሚያስተሳስረን ግዕዝ ከሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና አንዱ ሆኖ መግባት ነው። ሐሳቡን ሳቀርብለት በደስታ ተቀበለው።  የሌሎቹን መምህራን ጥያቄዎችንም እንደዚሁ በአዎንታ እንዳስተናገዳቸው እገምታለሁ።
ሆኖም ሳያስቸግረን፥ አስቸጋሪያችን ሌላ ሆኖ ሳለ፥ እናስቸግረው ነበር። ዋናው ጥያቄያችን ፖሊስ ከዩኒቨርሲቲው ግቢ አይግባ ነው። “ፖሊሶቹን ለመቆጣት፥ የፖሊስ አዛዥ አይዶለሁም፥ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አይዶለሁም፥ የሸዋ አውራጃ ገዢ አይደለሁም፥ የአገሪቱ ንጉሥ አይደለሁም፥ ምን አርግ ነው የሚትሉኝ” ማለት ሲችል፥ አላለም። “በኔ የአመራር ዘመን ግቢው ባይደፈር፥ ከማናችሁም የበለጠ ደስተኛው እኔ እሆን ነበር” አላለም። ሁሉንም በጽሞና አሳለፈው።
ንግግሬን ከመጨረሴ በፊት፥ በአጋጣሚው ልጠቀምና ስለ ዶክተር አክሊሉ ያለኝን የግል ስሜት ልናገር። ዶክተር አክሊሉ ሕይወቱን በቅንነት የሚመራ ደግ ሰው ነው። “አክሊሉ በሥልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ የበደላችሁ እንዳላችሁ ይቅርታ እንዲጠይቃችሁ እጃችሁን አንሡ” ብንባል፥ ሁላችንም ያለ እጅ የተፈጠርን ነው የምንመስለው። ከስድስት መቶ በላይ ያለውን የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ታሪክ ስታነቡ ማንንም ሰው አንድ ቦታ ሲያሳጣው አታዩም። ደራሲዎች የባለቤታቸውን እርዳታ ይጽፋሉ። ዶክተር አክሊሉ ግን ወይዘሮ ሰላማዊትን “መካሪዬ” ነው ያላት። ዶክተር አክሊሉንና አፄ ምኒልክን አርአያ አድርጎ የሚስቱን እውነተኛ ሞያ ሳይፈራ ሳያፍር  እውነቱን  የሚናገር ባል አንድ ቀን እንደሚወለድ ተስፋ አለኝ።
ዶክተር  አክሊሉ፤ የተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤትን፥ ተማሪዎቹን፥ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲንና አባሎቹን አስከብረሃቸዋል። አምላካችን እንዳከበረ ያኑርህ። ለእሳቸውም የማይፈርስ ሐውልት ስላቆምክላቸው ነፍሳቸው ትባርክሃለች። እኔም ለዚህ የታሪክ ሰነድ አክብረህ ቀዳሚ ቃል እንድጽፍ ዕድሉን ስለሰጠኸኝ ከልብ አመሰግናለሁ። መጽሐፍክን ፖስተኛው ሲያመጣው መጽሐፎቼ “ሐዊሳ በምጽአትከ”  (እንኳን ደኅና መጣህ) እያሉ በሆታና በዝማሬ ነው የተቀበሉት።
ስለጋበዛችሁኝ፥ ስላዳመጣችሁኝ አመሰግናለሁ።
ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here