Home News and Views በኢትዮጵያዊነት ካባ! የርዕዮት ስውር ደባ…” (አዳነ ኃይሉ)

በኢትዮጵያዊነት ካባ! የርዕዮት ስውር ደባ…” (አዳነ ኃይሉ)

አዳነ ኃይሉ

በሳምንት አንዴ በፌስ ቡክና በዩቱዩብ የቀጥታ ስርጭት የሚቀርበው በዋናነት የጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬ እንደሆነ የሚነገርለት ርዕዮት ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ማድመቅ ዋና መርሃችን ነው ሲል በተደጋጋሚ አድምጠነዋል።

በኔ እይታ ግን ይህ ርዕዮት የተሰኘው ሳምንታዊ ፕሮግራም “ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን” በዋና መርህነት ደጋግሞ ይጥቀስ እንጂ የሚቀርቡበት ትንታኔዎችና የሚያራምዱት አቋም መርሃችን ከሚሉት ጽንሰ ሃሳብ በእጅጉ የራቀ ምናልባትም በተቃራኒ የቆመ ነው።

ኢትዮጵያዊነት ሲደምቅ ማድመጥ፤ ኢትዮጵያ እንደሃገር ስትወደስ መስማት የኢትዮጵያዊው ዜጋ የዘመናት ረሃብና ናፍቆት እንደሆነ ይታወቃል። ለዚህም ይመስላል የፕሮግራሙ መሪዎች ይህንኑ አቋም ከመዝሙር ባላለፈ ቅላጼ(በተግባር የልተደገፈ) በተደጋጋሚ ያንቆለጳጵሱታል፤  ያወድሱታል….. ።

ይሁንና በተደጋጋሚ ያስተዋልኩት ኢትዮጵያዊነትን ማድመቅ ዋና መርሃችን ነው እያሉ “ኢትዮጵያ”ን የሚለውን ወገን ሲያጠለሹ ነው። ቴዎድሮስ ጸጋዬ ከዚህ ቀደም የቴዲ አፍሮ “ኢትዮጵያ” የሚለው ሙዚቃ ለአድማጭ ጆሮ ከበቃ 24 ሰአታት እንኳ ሳይሞላው የመዘዘበት የማጥላላት ጎራዴና፤ ጅራፍ ምን እንዳስከተለበት ከማናችንም በላይ እሱ ራሱ ያስታውሰው ይመለኛል። ሌላውን ለመግረፍ በገመድነው ጅራፍ እራሰችን ስንገረፍበት ሊፈጠር የሚችለው ስሜት ቶሎ የሚረሳ አይመስለኝምና ነው። ቀጥዬ ለማነሳው ጉዳይ መንደርደሪያ ቢሆን ብዬ እንጂ በግዜው በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙዎች አስተያየታቸውን ሰጠተውበታልና አሁን አልመለበትም።

ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ግሩም የሆነ የቋንቋ ችሎታና የሰላ አንደበት አለው። በንባብ የዳበረ ሁለ ገብ የሆነ እውቀቱም የሚደንቅ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እያለም በሬድዮ በሚያቀርባቸው ዝግጅቶቹ ተወዳጅ እንደነበረም አውቂያለሁ። ውጭ ከወጣ በኋላም የጀመረው ርዕዮት የተሰኘው ዝግጅቱም የአድማጭን ቀልብ ለመግዛት ብዙ ግዜ አልፈጀበትም። እኔም ከአድናቂዎቹ አንዱ እንደነበርኩ አልደብቅም። በያንስ ቴዲ አፍሮ ላይ የጭቃ ጅራፉን እስኪመዝ ድርስ ።

ከዚያ በኋላ ግን ዝግጅቱን የምክታተለው በአድናቆት ሳይሆን በጥርጣሬ ነበር፡፤ ኢትዮጵያዊነትን ማድመቅ ዋና መርሁ ያደረገ ዝግጅት በኢትዮጵያዊው ብሄርተኛ ላይ ያነጣጠረ ተደጋጋሚ ትችትና ተቃውሞ የማቅረቡ እንቆቅልሽ በፈጠረብኝ ጥርጣሬ። (ቀዳማይ እንቆቅልሽ በሉልኝ)

ሰሞኑን ደግሞ ጥርጣሬዬን የፈጠረውን ቀዳማይ እንቆቅልሽ ገለጥለጥ ያደረጉ ዳግማዊ እንቆቅልሾችን ያረገዙ ሁነቶችን አስተዋልኩ።

አንደኛው ሁነት፦

ቴዎድሮስ ጸጋዬ የወያኔ አገዛዝን የሚቃወመውን፤ የአብዛኛውን ዲያስፖራ ቀልብና ጆሮ ማግኘት የቻለው በችሎታው በመታገዝ፤ በወያኔ መራሹ አገዛዝ ላይ በሚያቀርበው የሰላ ትችት ነው። ሥርዓቱን ይህ ቀረሽ በማይባል መልክ ይተቻል፡፤ ይህ ደግሞ የነጻነት ናፋቂውን ልብ ከፍቶ ለመግባት ብቸኛው ቁልፍ ነው። ይህ በእንዲህ እያለ ይህ ሰው በቅርቡ በአገር ውስጥ ከሚተላለፍ ኢትዮ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጋር ተፈራርሞ የራሱን ዝግጅት ሊጀምር እንደሆነ ከሰይፉ ፋንታሁን ጋር ያደረገውን ቃለ መጠይቅ ሰማሁ https://youtu.be/TUBiZl6yWrY (እስካሁን ጀምሮ ይሆናል) ።

ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ወያኔ መራሹን አገዛዝ ሲያብጠለጥል የሚታወቅ ሰው አገር ቤት ሬዲዮ ላይ ዝግጅት እንዲያቀርብ እንዴት ሊፈቀድለት ቻለ? ከአገዛዙ ባህሪ የምናውቀው፦ ራሱን የቻለ ፕሮግራም ከፍቶ የሚያብጠለጥለውን ጋዜጠኛ ቀርቶ በተቃውሞ ሰልፍ ላይ ታይታችኋል ያላቸውን ዲያስፖራዎች እንዴት እንደሚያሳድድ ነው። ይሁንና ባልተለመደ መልክ ቴዎድሮስ ጸጋዬ በኤፍ.ኤም ሬድዮ ዝግጅት እንዲያቀርብ መፈቀዱ ዳግማዊ እንቆቅልሽ አይደለም ትላላችሁ? ነው እንጂ። ቢሆንም ግን የዚህ እንቆቅልሽ መልስ ከላይ የጠቀስኩትን ቀዳማይ እንቆቅልሽ ጨምሮ ግልጽ የሚያደርግ ይመስለኛል፡፡

ከዚህ በመነሳት ቴዎድሮስ ጸጋዬ ወደ አሜሪካ የመጣው አገዛዙን የሚቃወመው ዲያስፖራ ሊሰማው የሚፈልገውን ሁሉ እየተናገረ አድማጩን ካሰባሰበ በኋላ ባገኘው ቀዳዳና አጋጣሚ እውነተኛውን ተቃዋሚ ወገን የመምታት ተልዕኮ ይዞ ነው ወደሚል ድምዳሜ ደርሻለሁ(በግሌ) ። የናንተን  ….

ነጻነት ናፋቂው ወገን ለመስማት የሚፈልገውና ጆሮ የሚሰጠው ደግሞ

 1. የአገዛዙን እጸጾች የሚያጋልጡ ዝግጅቶችን ሲሆን
 2. በተጓዳኝም የዘር ፖለቲካን ትርከት እያወገዘ፤ ህልውናዋ አደጋ ውስጥ ያለውን ሃገራችን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነት የሚያደምቅ ዝግጅት ነው።

ቴዎድሮስ ጸጋዬም ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት አውደ ሃሳቦች መሰረት አድርጎ በሚያቀርበው ዝግጅት እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ የአድማጩን ጆሮ ማግኘት ችሏል።(ካሁን በኋላ ግን አይመስለኝም)።

በውጭው ዓለም ሆኖ አገዛዙን እየተቃወመ በሃገርቤት ሬዲዮ ፕሮግራም እንዲያዘጋጅ ፍቃድ ያገኘ የመጀመሪያው ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ብቻ ይመስለኛል። ለምንና እንዴት …? አስተያይቴ ከወያኔ ባህሪ የመነጨ እንጂ ጭፍን ፍረጃ አይደለም! ተከተሉኝ…

የሆነው ሆኖ፦ ተቃዋሚ መስሎ ተቃዋሚን የማጥፋት ይህን መሰሉ የአገዛዙ ተልዕኮ የመጀመሪያ ፕሮጀክት በጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ (አውራምባ) ተሞክሮ አለመሳካቱን ልብ ይሏል። ቴዎድሮስ ጸጋዬም ዳዊት አውራምባ ያከሸፈውን ፕሮጀክት የማሳካት ተልዕኮውን አንግቦ ወደ ዲያስፖራው ተቀላቅሏል እንድል ያስገደደኝን ሌላ ማስረጃ ልጥቀስ።

ሁለተኛው ሁነት፦

ቴዎድሮስ ጸጋዬ ከባልደረቦቹ ከታምራት ነገራ እና ሄኖክ ጋር  በ14/04/2018 ባቀረበው ዝግጅት ላይ ለአንድ አመት ተኩልና ከዚያ በላይ ተደክሞበት በቅርቡ በአሜሪካ ምክር ቤት የጸደቀውን HR 128 ሰነድ አፈር ሲያስገብት ተደምጠዋል።አብጠልጥለውታል።  በተለይ ታምራት ነገራ የተባለው ሰው የሰነዱን መጽደቅ ከመቃወም አልፎ  እንዲጸድቅ የደከሙትን ወገኖች በሃገር መክዳት ሲወነጅል መስማት ለኔ አስደንጋጭ ነበር።https://www.youtube.com/watch?v=qk2p_pfX1g8  (ከ14 ደቂቃ ጀምሮ ያድምጡት) በዚህ ጉዳይ ላይ ሄኖክ የተባለው ተሳታፊ በመጠኑም ቢሆን ሚዛናዊ የሚመስል አስተያየት የሰጠ ቢሆንም በአጠቃላይ ግን የርዕዮት ዝግጅት ክፍል  በHR 128 መጽደቅ ከተደሰተው ኢትዮጵያዊ በተቃራኒ መቆሙን ያየሁበት አንዱ አሳዛኝም አስገራሚም አጋጣሚ ነበር።

በዚሁ እለት ዝግጅት ሌላው ለትችን የቀረበው አጀንዳ አቶ ነአምን ከቢቢሲ ሃርድ ቶክ ጋር ያደረጉት ቃለ መጠይቅ ነው። በዚህ የትንተና ክፍል ደግሞ ሶስቱም ተሳታፊዎች አቶ ነአምን ባድሜ የኤርትራ ነች እንዳሉ በመውሰድ ፤ በሃገር ላይ ክህደት ፈጽመዋል የሚል ውንጀላ የተቀላቀለበት አመለካከት አንሸራሽረዋል። (ከላይ የተቀመጠውን ሊንክ ከ16 ኛው ደቂቃ ጀምረው ያድምጡ)

በኔ እይታና አረዳድ  አቶ ነአምን ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት መልስ በሃገር ክህደት ሊያስወነጅላቸው የሚችል ሆኖ አላገኘሁትም። ባድሜ የኤርትራ ነው ሲሉም አላደመጥኩም።

ለአቶ ነዓምን የቀረበው ጥያቄ ይዘት፡ አዲሱ የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ለኤርትራ ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ ኤርትራ የምትቀበለው ከሆነ እናንተ ቤት የለሽ መሆናችሁ አይደለም ወይ ? የሚል ነው።

አቶ ነዓምን የሰጡት መልስ ደግሞ ።

ይህ የሚሆን አይመስለኝም፡፤ ይህ እንዲሆን ከሁሉ በፊት በአናሳ ብሄር ተወላጆች የተመሰረተው መንግስት (minority regime) ወታደሮች ድንበር አካላዩ ኮሚሽን ለኤርትራ ከፈረደው መሬት መውጣት ይኖርባቸዋል፡፤ ይህ ደግሞ የሚሆን አይመለኝም ።ምክንያቱም አብዛኞቹ ትግራዋያን ባድሜ የትግራይ ነች ብለው ስለሚያምኑ አገዛዙ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ይቸግረዋል። ሁሉንም ሲሆን ብናየው ይሻላል ። የሚል ይዘት ያለው ነው

ለኔ እስከገባኝ ድረስ በዚህ መልስ አቶ ነአምን ያስረዱት፤

 • 1ኛ) ድንበር አካላይ ኮሚሽኑ ባድሜን ለኤርትራ መወሰኑን ነው።(ይህ ደግሞ እውነት ነው)
 • 2ኛ) በመሆኑም የኤርትራ መንግስት በድንበር አካላዩ ኮሚሽን ከተፈረደለት መሬት ላይ የወያኔ ጦር እስካልወጣ ድረስ የሰላም ጥሪውን የሚቀበል አይመስለኝም ነው ያሉት።(ይህም የኤርትራ መንግስት አቋም ነው)
 • 3ኛ) አብዛኛው ትግራዋያን ባድሜ የትግራይ ነች ብለው ስለሚያምኑ ወያኔ መራሹ መንግስት (minority regime) ጦሩን ከባድሜ  ያስወጣል የሚል እምነት እንድሌላቸው ነው።
 • ይህ ዕምነታቸው ደግሞ የኤርትራ መንግስት ለዶክተር አብይ የሰላም ጥሪ ከሰጠው ምላሽ የሚነሳ ስለመሆኑ የሰሞኑን ፖለቲካዊ ሁነቶች ለሚከታተል ሰው የሚጠፋ አይደለም።

የሚገርመው ግን በርዕዮት ዝግጅት ላይ አቶ ነዓምን ባድሜ የኤርትራ ነች አሉ! በሚል በሃገር ክህደት ለመወንጀል መረባረባቸው ነው።

አቶ ነዓምን ከሃርድ ቶክ ጋር ያደረጉትን ቆይታ በተመለከተ ከበርካታ ወገኖች ጋር ሃሳብ ተለዋውጫለሁ። የእርካታ መጠናቸው ይለያይ እንጂ ሁሉም (ራሴን ጨምሮ) በጣም ረክተዋል። ሲጀመር ፈንጂ በተቀበረበት ሜዳ ላይ እንደመጨፈር ያህል አደገኛ በሆነው የሃርድ ቶክ ፕሮግራም መቅረብ በራሱ ከፍተኛ የሆነ በራስ መተማመን ይጠይቃል። ሲቀጥል በዚህ የፈንጂ ወረዳ ውስጥ ቆይቶ ፈንጂ ሳይረግጡ መውጣት ደግሞ እድለኝነት ሳይሆን ብቃትን የሚጠይቅ ነው።  ይሀው ሰው መለስ ዜናዊን እንዴት አድርጎ ፈንጂ እንዳስረገጠውና ያ ሁሉ ምራቁ ደርቆ ውሃ ውሃ እንዳሰኘው ሳስታውስ የአቶ ነዓምን በሰላም መውጣት እንዳደቅ እገደዳለሁ ። ይሁንና አቶ ነዓምን ከፈንጂ ወረዳው በሰላም መውጣታቸው አልዋጥ ያላቸው

ርዕዮቶች የራሳቸውን ፈንጂ በመወርወር ለማቁሰል መሞከራቸው ከትዝብት ውጭ ምንም አላተረፈላቸውም ባይ ነኝ።

እዚህ ላይ በተለይ ታምራት ነገራ የሚባል ስሜታዊ ሰው ለአግ7 ያለውን ስር የሰደደ ጥላቻ ሳይደብቅ በመናገሩ አመለካከቱም የዚሁ ጥላቻው ውልድ እንደሚሆን ግልጽ አድርጓልና በጥላቻ ስለተለበጠ አስተያየት መነጋገር ደግሞ ግዜ ማጥፋት ስለሚሆን አልፈዋለሁ።

ለቴዎድሮስ ጸጋዬ ግን ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ቀዳዳ ያገኘ በመሰለው ጊዜ የአገዛዙ ቀንደኛ ጠላቶች ናቸው የሚባሉ ወገኖችን የሚመታበት የዋናው ተልዕኮው ትግበራ መገለጫ ነው እለላሁ።አልያማ እውን ስለ ሃገር መክዳት የሚወነጀለው አግ7 ወይስ ወያኔ መራሹ አገዛዝ?

ስለ ሃገር ክህደት እናውራ እንዴ? እናውራ..? እረ እናወራለን…

 • አገር መክዳት ማለት፦ 1000 ሺህ ኪሎሜትር የሚዘልቀውን የሁመራ ለም መሬት ለሱዳን መንግስት አሳልፎ መስጠት ነው ።
 • በሃገር መክዳት የሚያስወነጅለው፦ የምጽዋ ወደብ የኤርትራ እንጂ የኛ አይደለም ብሎ መግፋት ነው።
 • ሃገር መክዳት ማለት፦ ዜጎቻችን በየሃገሩ መብታቸው ሲገፈፍና ንብረታቸው ሲቀማ፤ እህቶታችን ባደባባይ ሲደፈሩ፤ ለባዕዳን ቀማኞችና ወንጀለኞች ወግኖ በዜጎቻችን ላይ የተፈጸመው በደል ተገቢ ነው! ህገ ወጦች ናቸው! ብሎ ጭራሹኑ። በወገኖቻችን ላይ የተፈጸመው በመቃወም ሰልፍ የወጣውን ዜጋ መደብደብ ነው። ….ከጭብጡ ላለመራቅ ስል እንጂ ስለ ሃገር ክህደት  ሌላም ሌላም ማለት ይቻላል።

ደግሞስ አግ7 ኤርትራን እንደ መከለያ መቁጠሩ አገር መክዳት ከሆነ፤ የዛሬው አገዛዞች በበርሃ እያሉ የግንጠላ አላማቸውን ለማሳካት ሃገራቸውን ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታቸውን ክደው ከጋዳፊ ጋር ሶላት ሳይቀር መስገዳቸውን በምን ልንመድበው ይሆን። ከዚያድ ባሬ ጦር ጋር ወግነው ወንድማቸው መዋጋታቸውን ምን እንበለው… ? ለዚያውም ግንጠላን መሰረት ላደረገ እርኩስ አላማ …አረ አያምርባችሁም…

ወደ ኋላ መለስ ለበልና፡ ቴዎድሮስ ጸጋዬ በቴዲ አፍሮ አልበም ላይ ባቀረበው ተገቢ ያልሆነና የቸኮለ ትችት ሳቢያ ከበርካታ ወገኖች ይደርስበት ከነበረው ትችት በጣም የሚያናድዱኝ የትግራይ ተወላጅ መሆኑን በመጥቀስ የስነዘሩበት የነበሩት ስድቦች ነበሩ። ተግባርን እንጂ ዘርን መሰረት ያደረገ ትችት በፍጹም አይመቹኝም። ትግራዋይ በሙሉ ወያኔ ናቸው ማለት ፍጹም ስህተት ነው። በነገራችን ላይ የቴዎድሮስን የትግራይ ተወላጅነት የተረዳሁት በራሱ ፕሮግራም ላይ ታምራት ነገራ ዘመዶችህ እያለ በቀልድ መልክ ሲገልጽ ነው። በግዜው ታምራት የርዕዮት አድማጮች የቴዎድሮስን ትግራዋይነት እንዲያውቁ የፈለገበት ምክንያት ባይገባኝም አልወደድኩለትም። ይሁንና ቴዎድሮስ የታምራትን የስላቅ ጥቆማ በመቃወም ወዲያውኑ “ኢትዮጵያዊው ሁሉ የኔ ዘመድ ነው” የሚል ይዘት ያለው መልስ መስጠቱ አስደስቶኛል።

በኋላም በታምራት የስላቅ ጥቆማ የቴዎድሮስን ትግራዋይነት የተረዱ አንዳንድ ጭፍኖች በብሄር ማንነቱ ላይ ያነጣጠረ ስድብ ሲያወርዱበት በእጅጉ አዝኛለሁ። ቴዎድሮስ ጸጋዬ ይህንኑ ዘለፋ ምክንያት አድርጎም በገጹ ላይ “ለኔ ትግራዋይነት ማለት ኢትዮጵያን እንደ ሰፌድ ብንወስዳት፤ ሰፌዱ ሊሰበዝ በሚጀምርበት ቦታ ላይ መወለድ ማለት ነው” በሚል የሰጠውንም መልስ በጣም ወድጄለታለሁ። የዘር ፖለቲካ ደምን እንጂ ምክንያትን አይመረምርምና ለቴዎድሮስ የትግራዋይነት ትርጉም “ሰፌድም እኮ የሚተረተረው ከማሃል ነው” በሚል የተሰጠ አስተያየት አንብቤ አዝኛለሁ ። ለዚህም ይመስለኛል ወያኔ ለ27 ዓመታት የዘራው ዘርን ያማከለ ጥላቻና ያለመተማመን ከማንም በላይ የሚጎዳው የትግራይ ህዝብን መሆኑ ብዝዎችን እያሳሰበ የሚገኘው።

ወደ ቀደመ ነገሬ ስመለስ፦ ከላይ ያለውን አጋጣሚ የጠቀስኩት በቴዎድሮስ ጸጋዬ ላይ እያቀረብኩት ያለው ትችት ድርጊቱን እንጂ ዘሩን ማዕከል ያደረገ እንዳልሆነ አድምቄ ለማሳየት ነው። ለኔ ታምራት ነገራም ቴዎድሮስ ጸጋዬም የአገዛዙ መሳሪያ ለመሆን የፈቀዱ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።

የትችት ጭብጦቼም የተጸነሱት ከሚከተሉት ጥያቄዎች ነው፦

1ኛ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ማድመቅ ዋና መርሁ አድርጎ እንደሚሰራ ጠዋት ማታ የሚሰብክ አካል በምን ምክንያትና ለምን አብዛኛው ነጻነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊ የተደሰተበት የኤች አር 128 መጽደቅ ሊጎረብጠው ቻለ?

2ኛ)፡አገዛዙን በጽናት ከሚቃወመው ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ በተለየ ቴዎድሮስ ጸጋዬ በሃገር ቤት ሬድዮ ጣቢያ ላይ እንዲሰራ የተፈቀደለት ለምንድነው?

3ኛ)  በአግ7ና መሰል ኢትዮጵያዊ ብሄርተኛ ድርጅት ላይ ይህን ያህል የመረረ ጥላቻ ለምን ያራምዳሉ? በሌላ አገላለጽ “መርሃችን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ማድመቅ ነው” የሚል አካል በምን ምክንያት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት የሚሰራ አገዛዝን የሚቃወመውን ወገን ያጥላላል?

በመጨረሻም ያልወለድኩት ልጅ አባባ ቢለኝ አፌን ዳባ ዳባ አለኝ እንዲሉ HR 128 ሰነድ መጽደቅ ያንገበገባቸው ቴዎድሮስ ጸጋዬና ባልደረቦቹ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ሲሉ ማድመጥ “ዳባ ዳባ …” እያለኝ መሆኑን በማስረገጥ አስተያይቴን እቋጫለሁ።

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር

አዳነ ኃይሉ

adanehailu2002@gmail.com

1 COMMENT

 1. የርዕዮት “*ውር ደባ”በሚል ስም ተገኘለት፦ዕውነት ነው።ብዙ ጊዜ ለተለያዩ ኢትዮጵያዊነትን የማጠልሸት ጥፋቶች የሚጋገሩት፣በቴዎድሮስ ፀጋዬ ምጣድ ላይ በሚሰነዘሩ ሀሳቦች በኩል ነው፤ምክንያት እና ሰበብ ይኖራቸው ይሆን ብዬ ብዙ ማጥናት ሞክሬአለሁ፣ባይሳክልኝም።አንድ የመፅሐፍ ቅዱስ ትምህርተ-ሚሥጥር ውል አለብኝ፤”የሠይጣን ልዩ መሳሪያው ምንድነው?”ተብሎ ቢጠየቅ፣የሚያውቅ ይወቅበት ትክክለኛ መልሱን ግን ቴዎድሮስ ፀጋዬ እና ተንኮለኞቹ በሙሉ ያውቁታል ብዬ አምናለሁ፤”ማስመሰል”ነው።
  እስኪ የዘመናችንን ተንኮለኞችን በጥንቃቄ እዩዋቸው፤መሰሪዎች ናቸው፣ሲያዙ “ተሳስቼ፣ሳላውቅ፣መስሎኝ…” ብለው ሊያመልጡ ይሞክራሉ፤የሚያሳዝነው ደግሞ ደጋግመው መያዛቸው ነው፤ልክ እንደቴዎድሮስ ፀጋዬ።እናም ይህንን ያነበበ ሁሉ አንድ ብሎ ልብ ይበል። አዳነ ኃይሉ ፣ጨማምሮ ተንኮለኞችን የሚፈውስ ኃይል ይስጥህ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here