Home News and Views “የባላንጣዎች ቡድን?”

“የባላንጣዎች ቡድን?” [በይልማ አዳሙ]

 

እርስ በርስ የሚጋጭ ሃሳብ ያዘለ ስለሚመስል “የባላንጣዎች ቡድን” ብሎ ነገር ግር ሊል ይችላል። ስመ ጥሩዋ የታሪክ ተመራማሪ ዶሪስ ጉድዊን “Team of Rivals” በሚል ርዕስ ስለ አብርሃም ሊንከን ያቀለመችው ድንቅ መጽሐፍ ነው ። “ስለ ሊንከን አሥር ሺህ የሚደርሱ መጻህፍትና መጽሔቶች ታትመው ሳለ ዶሪስ ምን ይሁን ብላ ነው ሌላ መጽሐፍ የምትጨምረው?” ያሉ ሁሉ አፋቸውን በጨው አጥበዋል። ዶሪስ ታሪክን የምታበጥረው ለርሷ ብቻ በተቸረ ዓይነት የተመራማሪነት ስልት ነውና መጽሐፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አንብብያን አገኘ።

ይህን መድብል ያጣጣምሁት ቀርቶኛል ብየ በማልጠረጥረው ትጋትና የመረዳት ስሜት ነበር። ጥሩ ደራሲ፤ ፈታኝ ሀገራዊ ሁነቶችና ኮከብ ገጸ-ባህርያት እንዲህ ያለ ወግ ያላብሳሉ። የማገናዘብንና አሻግሮ የማየትን ፍላጎትን ያነሳሳሉ። ታዲያ ባሜሪካው ሰቆቃዊ የታሪክ ዘመን ውስጥ እየተጓዝሁና መሪዎቹና ሕዝቡ እንዴትስ ብለው ፈተናውን እንደተወጡት እየተገርምሁ እዝነ-ልቦናዬ ጭልጥ እያለ ወደ ሀገራችን ሁኔታ መንጎዱን አላቆም አለ።

“በሥልጣን ላይ ያሉትና ለሥልጣን የሚዘጋጁ መሪዎቻችን ይህን መጽሐፍ በጥሞና ቢያነቡ ምን ያህል ትምህርት ባገኙበት?” አልሁ። “ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና በበጎም በጥርጣሬም ዙሪያቸውን ለተሰለፉ ሁሉ ቀበቶዬን አስሬም ቢሆን መጽሐፉን ገዝቼ ልላክላቸው?” የሚል ነገርም ዳዳኝ።

መጽሐፉ በመረጃ የራሰ፤ ልብ የሚያንጠለጥሉ የታሪክ ሁነቶች የበዙበት፤ አንጀት የሚበሉና ቅስም የሚሰብሩ ትራዥዲዎች የሚፈራረቁበት፤ የመሪነት፤ የጀግንነት፤ የጭካኔና የምሕረት ስብዓዊ ባህርዮች የሚጠላለፉበት፤ እንደ ልብወለድ የሚነበብ መጽሐፍ ነው። የ750 ገጽ ትረካን በሦስት ገጽ መጣጥፍ ላጠቃል ብል ከ’ብደት ይቆጠርብኛልና የዛሬው አነሳሴ መጽሐፍ ትችት ላይ አላሰላም። በርሱ ፈንታ አገራችን ለምትገኝበት የፖለቲካ ቁልፍልፍ ተመክሮ አለው ብዬ ባመንሁበት አንድ ቁምነገር ላይ ጥቂት ላምባዲና ላበራበት ፈለግሁ። “ባላንጣ” ማለት “ጠላት” አለመሆኑንና ባላንጣዎች ባንድ ቡድን ተሰባስበው ሀገርና ወገንን ሊታደጉ እንደሚችሉ የታሪክ ጭብጥ ልሰጥ አሰብሁ።

1855-1865 አሜሪካ

ለግንዛቤ ይረዳ ዘንድ በአጭር ትረካ ልጀምር። ዘመኑ ባሜሪካው ሰሜናዊና ደቡባዊ ስቴቶች መሀከል የጥቅም፤ የተደማጭነትና ያስተሳስብ ፉክክር የጎላበት ነበር። ሁለቱን ወገኖች ያንድ ታሪክ ሕዝብና ያንድ ትልቅ ራዕይ ማሕበርተኛ አድርገው የሚያስተሳስሩ ድርና ማጎች የመብዛታቸውን ያህል ክልል-ተኮር ስሜቶችና የኤሊቶችን እኔ-እበልጥ እኔ-እበልጥ ለማስመስከር ሲባል የተፈለሰሙ የፖለቲካ እንዝርቶች የጦዙበትም ዘመን ነበር።

የሰሜኑ ኤሊት በሁለት ዓቢይ ምክንያቶች ባርነት እንዲያከትም ፈለገ። አንደኛው ምክንያት የባሪያዎች ነጻ መውጣት በታሪካዊው ያሜሪካ ሕገ መንግሥት ውስጥ በጉልህ የተቀረጸውን የሰው ልጆች እኩልነት ዕውን የሚያደርግ ሲሆን ሁለተኛዋና ስውሯ ምክንያት ደግሞ የባርነት መወገድ ሰሜኑ ክፍል ለፋብሪካዎች መስፋፋት የሚያስፈልገውን የሰው ኃይል ስለሚያፈልስለት ነበር።

ባንጻሩ የደቡብ ስቴቶች ያለባሪያ ጉልበት እርሻውም ሌላውም የኑሮ ጣጣ አይሳካላቸውምና “ሞተን እንገኛለን!” አሉ። ድሮም ቢሆን ሰሜኖቹን “ተመጻዳቂ” አርገው ስለሚያዩዋቸው ነገራቸውን አይወዱላቸውም። የደቡብ ኤሊቶችም ስውር ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሕዝቡን ያነሳሱት “ሰሜነኞች ነጻነትህን ሊገፉህ ነው! በባሪያ ለመገልገል እግዜር የሰጠህን ፀጋ ሊያነሱብህ ነው! ለም መሬትህን ሊነጥቁህ ነው!” በሚል የስጋት ፕሮፓጋንዳ ነበር ። ስሜታዊነትና የስጋት ድባብ መጨረሻው ክረት ላይ ሲደርሱ በመገንጠሉ ገፍተውበት የኮንፌደሬት መንግሥት አወጁ፤ የጦርነትንም በር ከፈቱ።

 

ብሔራዊ አንድነትን የሚፈታተን፤ የሕይወትና የንብረት ጥፋትን የሚያስከትል ጥቁር ዳመና ባንዣበበበት በዚያ ቀውጢ ዘመን አብርሃም ሊንከን በፕሬዚደንትነት ተመርጦ ካቢኔ ለማቋቋም ይንደፋደፍ ነበር። ዕውቀቱም ልምዱም ሁሉም አላቸው የሚባሉት ምሁሮች እርስ በርስ ሲናቆሩ ነበርና ሊንከን ሹልክ ብሎ ፕሬዚዳንት የሆነው ባገሪቱ ውስጥ የጥርጣሬ አየር ሰፈነ። በዚያው ልክም የሊንከን ጣጣ በረከተ…. የሕዝቡንና አብረውት የሚሠሩትን ሰዎች አመኔታ ባጭር ጊዜ ውስጥ ማሸነፍ ነበረበት፤ የበርካታ ተጻራሪ ሃይሎችን የጥቅም ግጭት ማስታረቅ ነበረበት፤ የርስ በርስ ጦርነቱ የሚጠይቀውን የሰውና የማቴሪያል ኃይል ስለማግኘቱ እርግጠኛ መሆን ነበረበት፤ ባሪያዎች ነፃ መውጣት አለባቸው በሚለው ጥያቄ ላይ በራሱ ፓርቲ ውስጥ እንኳ ወጥ አመለካከት አልነበረምና እንዲጣጣም ማድረግ ነበረበት፤ በዲፕሎማሲው መስክ ደግሞ አውሮፓውያን “ሕዝባዊ መንግሥት” የሚሉት ነገር እያፈረጠመ መሄዱ ያባንናቸው ነበርና ኮንፌደርሬቱን ቢደግፉ የኃይል ሚዛን ወደደቡብ ያጋድላል የሚል ስጋትም ያስጨንቀው ነበር።
አሜሪካ እንዲህ ያለ ፈተና ገጥሟት አያውቅም። ጥርጣሬ የነገሰበትና ልጆቿ ፊትና ጀርባ የሆኑበት ጊዜ አልነበረም። በብዙ መስዋዕትነት የተገነባው ብሔራዊ አንድነቷ እንዲህ የተፈተነበት ወቅት አልነበረም። የጠቀስኳቸውንና ሌሎችንም ብዙ ፈተናዎች አልፎ ነው የአብርሃም ሊንከን ቡድን ዛሬ የምናውቃትን የዴሞክራሲ ቀንዲል፤ የሁሉ መጠጊያና መጠለያ የሆነችውን አሜሪካን ያቆየን።
የባላንጣዎች ቡድን

ሊንከን አሜሪካ የገጠማትን ታላቅ ፈተና በድል መወጣት የምትችለው በዕውቀትም በልምድም የነጠሩ ሰዎችን ማሰባሰብ ከቻልሁ ብቻ ነው ብሎ በጹኑ ያምን ነበር። አስተዳደሩ ሁሉንም ስቴቶች እንደመስታወት የሚያሳይና ሁሉንም በሀቅ የሚወክል፤ ስጋቶችንና ምኞቶችን ያገናዘበ እንዲሆን ይፈልግ ነበር። ከዚህ ዕምነቱ ተነስቶ ነው በምርጫ ላይ ያሸነፋቸውን ባላንጣዎቹን ጭምር በካቢኔው ውስጥ እንዲያገለግሉ ቅድሚያ ጥሪ ያደረገላቸው።

“ገና የሺንፈቱ ምሬት ሳይጠፋላቸው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ እንደሚንቁት እያወቀ ባላንጣዎቹን አብረውት እንዲሠሩ መጋበዙ የለየለት የዋህነት ነው!” አሉ ያደባባይ ተችዎችና ጋዜጠኞች።
ሊንከን ለዚህ ጥሩ መልስ ነበረው። “አገሬ በብልህ ልጆቿ እንዳትገለገል የማድረግ መብቱም ፍላጎቱም የለኝም…የምርጫው ውድድር በኔና በተፎካካሪዎቸ መሀል የነበረውን ግንኙነት አላልቶት እንደሁ እንጅ የዜግነት እስስራችንንና አንደኛችን ለሌላችን ያለንን ከበሬታ ከቶውንም ሊያጠፋው አይችልም!” አላቸው።
ሊንከን በራሱም በዜጎቹም ላይ ያለው ዕምነት ጠንካራ ነበርና ተፎካካሪዎቹን እቤታቸው ድረስ እየሄደ ከማግባባት ወደኋላ አላለም። አሜሪካ የገጠማት ፈተና የያንዳንዳቸውን እውቀትና መስዋዕትነት እንደሚጠይቅ አሳሰባቸው። ጥሪውን ከተቀበሉ ደግሞ በሙሉ ነጻነትና ከሙሉ ድጋፍ ጋር እንደሚሠሩ ቃል ገባላቸው። አገሪቱ ያለችበትን ችግር በፖለቲካው ውስጥ ከሰነበቱት ባላንጣዎች ይበልጥ የሚረዳ አልነበረምና፤ እንዲሁም ደግሞ በሊንከን ያልተፈተነ ያመራር ችሎታ ሀሳብ ገብቷቸው ነበርና ባላንጣዎቹ ጥሪውን ተቀብለው ካቢኔውን ተቀላቀሉ። ዊሊያም ሲዋርድን፤ ኤድዋርድ ስታንተንን፤ ሳልመን ቸስን፤ ኤድዋርድ ቤትስን፤ እነዚህን ከባድ ባላንጣዎች አጠገቡ ሳያደርግ መረጋጋትና ድል አጠራጣሪ ይሆኑበት ነበርና ሊንከን በጣሙን ነበር የዘየደው። በሳል ታዋቂና ዘርፈ-ብዙ ግንኙነት ያላቸውን ፖለቲከኞች ባንድ ካቢኔ ውስጥ ማሰባሰቡ በጣሙን ጠቀመው።

 

የካቢኔው ተቀዳሚ ተግባር ጦርነት እንዲቆምና እርቅ እንዲወርድ የሚያደርጉ ሀሳቦችን በጥልቀትና በድፍረት ማማንጨት ነበር። ከሀገር መገንጠል በመለስ ሊደርጉ የሚችሉ ሰጥቶ-መቀበሎችን መመዘን ነበር። የሠላም አማራጮች ፋይዳ ባይሰጡ ደግሞ ጦርነቱ በሰው ኃይል፤ በፋይናንስ በዲፕሎማሲና በሌላው ዘርፍ የሚጠይቀውን አቅም ማጥናትና እንዴትስ እንደሚሰባሰብ ስትራቴጅ ማውጣት ነበር። የሠላም አማራጭች ገዥ ቦታ ይኖራቸው ዘንድ የሊንከን ዓይነ-ልቦና ምንጊዜም ክፍት ነው። የተለያዩና አንዳንዴም የማይዋጡ የሚመስሉ የክልል ፍላጎቶችን ለማስተናገድ ወኔ አንሶት አያውቅም።

 

ከሁሉ በፊት ግን እርሱና ባላንጣዎቹ ልብ ለልብ ይገናኙ ዘንድ ምቹ የሥራ ዓየር መፍጠር የሊንከን ፋንታ ነበር። ለዚህ ደግሞ መልካም ሰብዕናውና ጥልቅ አሳቢነቱ ጥሩ መነሻዎች ሆኑት። ለሰዎችና ለሀሳባቸው የሚሰጠው ከበሬታ የወዳጅ አዝመራ አበዛለት። የተወሳሰቡና ውጥረት የሚያስከትሉ አጀንዳዎች ነርቭ ሲነኩ ወዛም ቀልዶቹንና አገራዊ ተምሳሌቶቹን ማርገቢያና ማረጋጊያ መሣሪያ አደረጋቸው። ሳይውል ሳያድር ካቢኔውም፤ ሚዲያውም፤ የሩቁም፤ የቅርቡም በዚህ ሰው ቀና ተፈጥሮና ያመራር ችሎታ ከመማረክ ሌላ አማራጭ አጡ።

 

ትናንት በፉክክርና በጥርጣሬ መጋረጃዎች ተለያይተው የነበሩ ባላንጣዎች በአንድ ሰው ጥረት፤ አስተዋይነትና የማስተባበር ችሎታ አንድ-አካል አንድ-አምሳል ሆነው አገርና ወገንን በመታደግ ክቡር ሥራ ላይ ተሰማሩ። ባላንጣነት በልብ ወዳጅነትና በወንድማማችነት ስሜት ተተካ።
ቀጥሎ ደግሞ ሊንከንን ታላቅ መሪ፤ የባላንጣዎችን ቡድን ደግሞ የቻምፒዎን ቡድን እንዲሆኑ የረዱትን ባህርዮች በጭር ባጭሩ ላነጥብላችሁ እሞክራለሁ!

  • የራዕይ ጥራት ~ “የሰሜን-ደቡብ” ቅራኔ ለብዙዎች ባርነትን የማጥፋትና ያለማጥፋት ጥያቄ ይሁን እንጅ ለሊንከን ከዚያ የበለጠ ትርጉም ነበረው። “ያሜሪካ መፈራረስ የሕዝቦች-በሕዝቦች-ለሕዝቦች የተሰኘው አዲስ የዴሞክራሲ ሥርዓት ራሱን ችሎ መቆም የማይችል ቅዠት ነው ለሚሉ ወገኖች የፖለቲካ መሣሪያ ይሆናልና ያንድነት ኃይሎችን መሸነፍ እንደ አማራጭ አንቀበለውም” አለ። የዚያ ትውልድ ኃፊነት ዓለማቀፋዊ እንድምታ እንዳለውም አሳየ። ከዚህም ሌላ “ባሜሪካ መገነጣጠል የሚጠቀሙት ዜጎች ሳይሆኑ እዚህና እዚያ በሚፈጠሩ ትናንሺ ግዛቶች መንበር የሚፈልጉ የሥልጣን ጥመኞች” መሆናችውን አበክሮ ተከራከረ።
  • የሀሳብ ልዩነትማ ማለፊያ ነው ~ ሊንከን በካቢኔው ውስጥ የጦፈ ክርክር እንዲካሄድ ያበረታታ ነበር። የተለያዩ ሃሳቦችን ተቀብሎ የማነፃፀርና የማስተናገድ ችሎታው የመጠቀ ብቻ ሳይሆን ሰዎች በተለየ ሀሳባቸው ቅጣትም መገለልም እንዳይደርስባቸው ተግቶ ስላስተማረ በብልሆችና በታታሪዎች ተከበበ። ግራ የሚጋባው በርሱ ሀሳብ ተሺቀዳድመው በሚስማሙ ሰዎች ነበር። “ሁሌም በኔ ሀሳብ የሚስማሙ ከሆነ ሚኒስትሮችስ አማካሪዎችስ ለምን ያስፈልጉኛል?” ይላል። የሰዎች ምጥቀትና ታዋቂነት ለርሱና ላገሩ ብርቱ መገልገያዎች እንጅ የስጋትና የቅናት መነሾ መሆን እንደሌለባቸው ይናገራል።
  • ድልን ማጋራት ስህተትን መካፈል ~ አስተዳደሩ ድል የሚቀዳጅበትን አጋጣሚ ጭፍሮቹ የሚሞገሱበትና የሚሸለሙበት አጋጣሚ ለማድረግ ይጣደፋል – ሊንከን። ባንጻሩ ደግሞ የካቢኔው አባላት ጥፋት ሠርተው ከተገኙ ቁንጮው እርሱ ራሱ ነውና “ተጠያቂው እኔ ነኝ” ለማለት ወኔና ሀቀኝነት ጎድለውት አያውቅም። ለዚህም ነበር የሊንከን ቡድን በልበ-ሙሉነትና ወደር በሌለው ታታሪነት ይሠራ የነበረው። ስህተት ከተሠራ ሕዝብ በጉልህ የሚያየው የርምት ርምጃ ይወስድ ነበርና ባስተዳደሩ ላይ አመኔታ በረከተ።
  • ስሜታዊነት ጠላት ነው ~ አገርን የማስተዳደር ያህል ውቅያኖስ ውስጥ የተነከረ ሀላፊ የሚያበሳጨውና አንዳንዴም የሚያሳብደው ነገር ያጣል ማለት ዘበት ነው። ሊንከን ለዚህ ጥሩ ዘዴ ነበረው። ደብዳቤ ይጽፍና በይደር ያቆየዋል። ታዲያ በማግስቱ ብስጭቱም ስሜታዊነቱም ሲረግብ የሚልከው ደብዳቤ የሚቆጭበት አይሆንም። በስሜታዊነት ድባብ ውስጥ እንዳለ ያመለጡ ዳብዳቤዎች ቢኖሩ እንኳ ሰውየውን የሚያረጋጋና ቂም ያልያዘበት መሆኑን የሚያረጋግጥ ተከታይ ደብዳቤ ይልክለታል። ፀያፍ ቃል ካፉ ወጥቶ አያውቅም።

 

  • ርሕራሄና ታላቅነት ~ ሊንከን ፍጹም ሩህሩህ፤ ከቅጣት ይልቅ ምሕረት ሰዎችን ወደበጎ የመመለስ ኃይል አለው ብሎ የሚያምን ሰው ነበረ። በጦር ሜዳ ያሸነፋቸው ጀኔራሎች ላይ ውርደት እንዳይደርስ፤ የተፈታው ጦር ሠራዊት ደግሞ ከነፈረሱና ከነመሣሪያው ቤተሰቡ ጋር ተቀላቅሎ ኑሮውን እንዲቀጥል መፍቀዱ የወዳጆቹንም የባላንጣዎቹንም ከበሬታ አስገኘለት። ሀገሪቱን ወደ እርቅና ስምምነት ጎዳና አፋጥኖ ወሰዳት። ለዚህ ነው ሊንከን “አባታችን” የሚለውን የፍቅርና የአቅርቦት ቅጽል ሥም ከወገኖቹ የተቸረው።

. እርቅና ስምምነት ~ ጦርነቱ አብቅቶ ሊንከን ለሁለተኛ ጊዜ ተመረጠ። ባስመዘገባቸው ድሎች ከመኩራራት ይልቅ ታሪካዊ ንግግሩን ብሔራዊ እርቅ አንዲሰፍንና የአንድነት ስሜት እንደገና እንዲነግስ መንገድ መክፈቻ አደረገው። ብሔራዊው የትኩረት አቅጣጫ ምን ሊሆን እንደሚገባ ማመላከቻ አጋጣሚ አደረገው። ያ አቅጣጫ በብሩህ ተስፋ የተቃኘ፤ በዕርቅና በሠላም መዓዛ የታጀበ ነበርና አገሪቱን ከዳር-እዳር አወዳት።

 

በማንም ላይ የጥላቻና የበቀል ስሜት ሳይኖረን፤ በጽኑ ፍቅር ተሳስረን የጀመርነውን ያገር ግንባታ እንቀጥላለን። ከፍጹም ይቅር መባባል ተነስተን ያገራችንን ቁስል እናክማለን፤ ሕብረታችንን እናድሳለን አለ።

  • በምሳሌነት መምራት ~ ሊንከን ከሕዝብ መሀል የወጣ ስለሆነ ከሕዝብ ጋር የማያቋርጥ ግንኙነት ማድረግን ይወድ ነበር። ስለሆነም ቤተመንግሥቱን ለጎብኝዎች ክፍት አደረገ። ዜጎችን ወደ ጦር ሜዳ ከማሰማራት የከበደ ውሳኔ የለምና ሊንከን ራሱን ከጦር ሜዳ ለይቶ አያውቅም። ከወታደሩ ጋር ይወያያል፤ ብሶታቸውን ያዳምጣል፤ ያበረታታቸዋል፤ ያስተምራቸዋልም። ይህን በማድረጉ ከታሸና ከተኳኳለ የሹሞች ሪፖርት ራሱን መከለል ቻለ። የሊንከን የጦር ሜዳ ጉብኝት የወታደሩን ሞራል ለማነቃቃት ጠቃሚ ቢሆንም አደጋ ይደርስበታል ብለው ለሚሰጉ ጀኔራሎቹ ግን ራስ ምታት ነበር።
  • ዘና ማለትማ ተፈጥሯዊ ነው ~ በሥራ ብዛት የተወጠረች ነፍስ ዕረፍት እንደሚያስፈልጋትና የተሟጠጠ ጉልበት በሳቅና በጨዋታ መታደስ እንዳለበት ሊንከን ከልቡ ያምን ነበር። እርሱ ራሱ የተዋጣለት ቀልድ አውሪ ብቻ ሳይሆን አስተዳደሩ በውጥረት ቅንፍ ውስጥ ተወጥሮ እንዳይሠራ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። የቱን ያህል ጫና ቢበዛበት ለቲያትር ቤት ጊዜ አያጣም ነበር። ሊንከን ማስመስልና መኮፈስ የማይወድ ውነተኛ ሰው ነበር።

 

እዚህ ላይ ባጠቃልለው ደግ መስለኝ። ያሜሪካው የርስ በርስ ጦርነት 620 ሺህ ያህል ሕይወት የጠፋበት እጅግ አስከፊ ጦርነት ነበር። ከሚሊዮን በላይ ዜጎች አካለ ስንኩል ሆነውበታል፤ ሠላማዊ ኑሮ ተናግቶ ዕድገት የኋልዮሺ ተመልሳለች። ይህ ጦርነት ሊወገድ ይችል ነበር ወይ የሚለው ጥያቄ “ሙት” ጥያቄ ነውና ፋይዳው አስተማሪነቱ ላይ ብቻ ነው።
ራሳችንን በማታለል አባዜ ውስጥ ተተብትበን ካልሆነ በቀር በኢትዮጵያ ውስጥ ማሕበራዊ ቀውስ የመከሰቱ አደጋ የማይታሰብ ነው የሚባል አይደለም። ያንዱ አስተዋጽኦ ከሌላው ይለይ እንደሁ እንጅ ባገሪቷ ፖለቲካ ውስጥ ሚና ያላቸው ድርጅቶች ይህ ቀውስ እንዳይከሰት ኃላፊነት የተሞላው ርምጃ ሲወስዱ አለመታየታቸው ያሳስበናል። የፖለቲካ ቅራኔዎች እየተንገዋለሉ እንዲቆዩ ማድረግ ባልታወቀ ሠዓት የሚፈነዳ ቦምብ አቅፎ የመተኛት ያህል ነውና ስንባንን መኖር የለብንም። ልዩነቶቻችንን ማቀራረብ አለመቻላችን፤ የጠባብ ብሔር ስሜት እንዲስፋፋ ማድረጋችን፤ ሕዝቦች እየተራራቁ እየተፈራሩና መግባቢያ ቋንቋ እያጡ እንዲሄዱ ማድረጋችን የራሳችንን እግር ደግመንና ደጋግመን በጥይት የማቁሰል ያህል ቂልነት አለው። ያዲሳባው የወለጋው የሱማሌው የኮንታው ወዘተ ወጣቶች የሚግባቡበት ቋንቋ ተደልዟላ!

ለዚህ ነው ምንጊዜም በባላንጣነት የሚተያዩት ያገራችን ፖለቲከኞች ይህን ጊዜው ያለፈበት የፖለቲካ ቄንጥ አውልቀው መጣል ያለባቸው። በዚህ በምንኖርበት ዘመን አለመደማመጥንና አለመከባበርን የሚያክል ፋራነት የለም። አማረ ማሞ በተርጎሙት “ዴዚደራታ” ላይ እንደተጻፈው እንኳንስ ከተማረና “ከዳተኞችም ሆነ ከደደቦች ቁምነገር አይታጣም” ብሎ ማመን ብልህነት ነው። የናንተን አላውቅም እንጅ ባገሬ ጉዳይ ያገባኛልና ተቆርቁዋሪ ንኝ የሚሉ ድርጅቶች ሁሉ ሲጨባበጡ ማየት እፈልጋለሁ። ባንድ ስብሰባ አዳራሺ ግምባር ለግምባር ገጥመው ሲመክሩ ማየት እመኛለሁ። ምን ማድረግ ይቻላል? የተመሰከረልኝ በጎ አሳቢ ነኛ!

አሜሪካ አንድ ታላቅ መሪ ባስፈለጋት ሰዓት ሊንከንን አግኝታለች። የሊንከንን የባላንጣዎች ቡድን አዋቅራ ከመዓት ድናለች። እኛ ደግሞ ሳይውልና ሳያድር የራሳችንን ሊንከን መፍጠራችን ወሳኝ ነው። ማለቂያ በሌለው ጉስቁልና የሚማቅቀውን ሕዝባችንን የሚታደግ የባላንጣዎች ቡድን ለማደራጀት ከዚህ የተሻለ የታሪክ አጋጣሚ የለም። አስፈላጊነቱም እንዲህ አንገብጋቢ ሆኖ አያውቅም።

kuchiye@gmail.com

“Team of Rivals”

May 10, 2018

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here