Home News and Views ሰው ሊኖርባትና ለማስተናገድ የምትችል ኢትዮጵያን እንገንባ !

ሰው ሊኖርባትና ለማስተናገድ የምትችል ኢትዮጵያን እንገንባ ! [ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)]

 መግቢያ

በተለይም ካለፉት አርባ ዐመታት ጀምሮ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያኖች ከአገራቸው በመውጣት በተለያዩ የአውሮፓ፣ የአፍሪካ፣ የአረብ አገሮች፣ በአሜሪካ፣ በአውስትራሊያና በኒው ዘላንድ ተሰደው ይኖራሉ። ለዚህ ዐይነቱ ከአገር ወጥቶ በስደት ዓለም ውስጥ መኖር የተለያዩ ምክንያቶች ይሰጣሉ። እ.አ በ1960ዎቹና በ1970ዎች መጀመሪያ ላይ አብዛኛዎቹ ወደ ውጭ አገር ሲወጡ የተሻለ የትምህርት ዕድል እናገኛለን ብለው በማሰብ ነው። በዚህ ዘመን ይወጡ የነበሩት ወጣት ኢትዮጵያውያን ቢያንስ የአውሮፕላን ቲኬት ለመግዛት የሚችሉና፣ ለጊዜውም ቢሆን በሚኖሩበት አገር ውስጥ የስራ ወይም የትምህርት ዕድል እስኪያገኙ ድረስ ለስድስት ወር ወይም ለአንድ ዐመት ለቀለብና ለቤት ኪራይ የሚሆናቸውን ገንዘብ ይዘው ለመውጣት የሚችሉ ነበሩ። ይህም ማለት በመጀመሪያው ወቅት በተለይም ወደ አሜሪካና ወደ ምዕራብ አውሮፓ ለትምህርት እንዲወጡ የተገደዱ ኢትዮጵያውያን በኢኮኖሚና በማህበራዊ ሁኔታ ሻል ብሎ ከሚገኝ ቤተሰብ የተወለዱ ነበሩ ማለት ይቻላል። አንዳንዶችም ስኮላርሽፕ አግኝተው የወጡና አብዮቱ ከፈነዳ በኋላ ጥቂቶቹ አውሮፓና አሜሪካ ሲቀሩ፣ ሌሎች የግራ አመለካከት ዝንባሌ ያላቸው ደግሞ ወደ አገር ቤት ተመልሰው በመግባት አብዮቱን የተቀላቀሉ እንዳሉ የማይካድ ጉዳይ ነው። በጊዜው በነበረው ምስቅልቅል ሁኔታ የተነሳ ከፍተኛ አለመግባባት በመፈጠሩ አብዛኛዎቹ ህይወታቸውን ሲያጡ፣ የተቀሩት ደግሞ ክሞት ሲተርፉና የቀውጢው ዘመን ምስክሮች ሲሆኑ፣ ከነዚህ ውስጥ አንዳንዶች ውጭ አገር ተሰደው በመኖር በኑሮ ባይሰቃዩ እንኳ የትግል ጓደኞቻቸውን በማጣታቸው የህሊና ሀዘን እንደሚሰማቸው መገመቱ ከባድ አይሆንም።

በብዛት ኢትዮጵያውያን ወደ ውጭ መውጣት የጀመሩት የቀይና የነጭ ሽብር የሚሉት የወንድማማቾች የእርስ በርስ መተላለቅ መፋፋም ከጀመረ በኋላ ነው። አብዛኛዎቹ እ.አ በ1970ዎቹ መጨረሻና ከ1980ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በሱዳንና በሱማሊያ በኩል አድርገው በተለይም ወደ አሜሪካ የገቡ ናቸው። በጊዜው ገደብ ያጣውን ግድያ ለማምለጥ ብለው የወጡ ኢትዮጵያውያን፣ አንዳንዶቹ በረሃን ሲያቋርጡ በእባብ የተነደፉና በውሃ ጥማት የተነሳና በሌሎች የበረሃ በሽታዎች በመለከፍ ያለሙት አገር ሳይደርሱ በየበረሃው ተበታትነው የቀሩና የሞቱ ቁጥራቸው በቀላሉ የሚገመት አይደለም። ከዚህም ባሻገር ወያኔ ስልጣን ከያዘ ጀምሮና በተለይም ከምርጫ 1997 ዓ.ም ጀምሮ ጭቆናውን ሲያፋፍም በብዙ መቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ለቀው እንዲወጡ በመገደድ፣ የተወሰኑት እንደዚሁ በየበረሃው ለሞት ሲዳረጉ፣ አንዳንዶቹ ደግሞ አሜሪካንና አውሮፓ የመግባት ዕድል አግኝተዋል። በተጨማሪም ቀደም ብሎ በ1980 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ ፈላሻዎቹ የሚባሉ የይሁዲ ሃይማኖት ተከታዮች በይፋ እንዲወጡ እንደተገደዱና እስራኤል እንደሚኖሩ የታወቀ ጉዳይ ነው። እነዚህኞቹ በይፋ መንገድ የሄዱ ሲሆን፣ ከዘረኝነትና ካባህል ሾክ በስተቀር ይህንን ያህልም በኑሮአቸው የተጎሳቆሉ አይደሉም። ባጭሩ የብዙዎቻችንን በየአገሩ ተበታትኖ መኖር የተለያየ ምክንያት ቢሰጠውም ወይም መስጠት ቢቻልም፣ ዞሮ ዞሮ የኛ ሁሉ መሰደድና በውጭው ዓለም ተበታትኖ መቅረት በቀጥታ ከአገራችን ኋላ-ቀርነት ጋር የሚያያዝ ነው።  ይህ ዐይነቱ ኋላ -ቀርነት በተለያየ ዐይነት የሚገለጽ ሲሆን፣ እ.አ ከ1942 ጀምሮ ስልጣንን የያዙት ሶስት ተከታታይ መንግስታት ለጠቅላላው ህዝባችን የሚሆን አገር በስነ-ስርዓት ለመገንባት አለመቻላቸው ሁሉም የተሻለ ዕድል አገኛለሁ በማለት ውጭ አገር እንዲሰደድ ተገደደ። በሌላ ወገን ግን የሰው ልጅ ተንቀሳቃሽ እንደመሆኑ መጠን አገሩ በደንብ የተገነባች ብትሆንም፣ ወደ ሌላ አገር ሄዶ መኖርን የሚመርጥ እንዳለ መታወቅ አለበት። ላይ ለማስቀመጥ እንደሞከርኩት አንድ አካባቢና አገር ስርዓት ባለው መንገድ ከተገነቡ የሰው ልጅ ተዝናንቶ ሊኖርባቸው ይችላል፤ ማንነቱን የበለጠ ይገልጽበታል፤ በዚያው መጠንም የመፍጠር ኃይሉ ይዳብራል።

የአለፈውን ሰባ ዐመታት የአገራችንን የህብረተሰብ ዕድገት ሁኔታ ስንመለከት በተለያየ ወቅት አገራችንን ሲያስተዳድሩ የነበሩት አገዛዞች እኛም ሆነ እዚያው የቀረው ህዝባችን ተረጋግቶና ተደስቶ ሊኖርባት የምንችልባትን ኢትዮጵያ መገንባት አልቻሉም። ከተማዎችንና መንደሮችን በስነ-ስርዓት አልገነቡም። በየክፍለ-ሀገሩና ዋና ዋና ከተማዎችም ሆነ ወረዳዎችና ምክትል ወረዳዎች እንዲሁም ትናንሽ መንደሮች እኛም ሆነ ህዛብችን ልንኖርባቸውና ማንነታችንን ልንገልጽባቸው የሚያስችሉንን በልዩ ልዩ መልክ ሊገለጹና እኛን በመሳብ የፈጠራ ችሎታችንን በማዳበር እዚያው እንድንቀርና የዕድገትም አራማጆች እንድንሆን የሚያስችሉ የሙያ መስኮችንና የባህል መድረኮችንን አልዘረጉልንም። ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋትና እንዲዳብሩ በማድረግ ርስ በራሳቻን እንድንተሳሰር ለማድረግ አልቻሉም። የሃሳብ አድማሳቸውም ጠባብ በመሆኑ አንድ አገር እንደማህበረሰብና ህብረተሰብ ሆኖ እንዲገነባና የባህል አገር እንዲሆን በሳይንስና በፍልስፍና ላይ የተመሰረተ የአገር ግንባታ ስራ ማካሄድ ባለመቻላቸው አብኛዎቻችን ውጭ ውጭውን እንድንመለከት ተገደድን። የዚህ ሁሉ ውጤት የኋላ ኋላ እንዳየነው ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ ቀውስን ያስከተለና በየቦታው ተበታትነን እንድንቀር ያደረገ ነው። ከዚህ በመነሳት እስቲ ያደግንባቸውንና እስከተወሰነ ደረጃም ድረስ ህይወታችንን ያሳለፍንባቸውን መንደሮቻችንና ከተማዎቻችን ወደ ኋላ ዞር ብለን እንቃኝ።

 

ወደ ኋላ ተመልሶ መቃኘት !

ወደ ኋላ ዞር ብለን ከዛሬው አንፃር የተወለድንበትንና የአደግንበትን፣ እንዲሁም ትምህርት ቤት የሄድንበትን ሁኔታ ስንቃኝ በመሰረቱ በማዕከለኛው ዘመን ሁኔታ ውስጥ ነው ተወልደን ያደግን ነው የሚመስለኝ። ድሮም ሆነ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከአንዳንድ ከተማዎች በስተቀር ከ90% በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ግዛት የሰው ልጅ ለመኖር የሚያስፈልጉት ነገሮች ሁሉ የጎደሉት ነበር፤ ነውም ማለት ይቻላል።  የተወለድንበትን፣ የዳኸይንበትን፣ የተጫወትንበትንና ያደግንበትን፣ እንዲሁም የተማርንባቸውን ትምህርትቤቶች ወደ ኋላ ዞር ብለን ለመቃኘት ስንሞክር በምድር ላይ ይታዩ የነበሩና ዛሬም ያሉ ተጨባጭ ሁኔታዎች በአስተሳሰባችን ላይ በአማዛኝ ጎናቸው አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደራቸው አልቀረም። እንደየቤተሰባችን የማህበረሰብ ሁኔታና(Social Status) እንደ ንቃተ-ህሊናቸውም የኛም የማሰብም ሆነ የኋላ ኋላ ለአንድ ቁም ነገር መድረስም ሆነ አለመድረስ ሊወሰን የሚችለው ከአስተዳደጋችን ጋር በተያያዙ ነግሮችና በጊዜው በምድር ላይ በሚታየው ተጨባጭ ሁኔታ ነው ማለት ይቻላል። በሌላ ወገን ግን ከኢትዮጵያ አጠቃላዩ የህብረተሰብ አወቃቀርና የባህልና የስነ-ልቦና ወይም ህሊና ሁኔታ ስንነሳ በመሰረቱ የኛን የማሰብና ያለማሰብ ሁኔታ ሊወስን የሚችለው በተናጠል የሚታየው ተጨባጩ ሁኔታና ሊታይ የማይችለው በባህልና በስነ-ልቦና የሚገለጽ ጉዳይ ሳይሆነ በአጠቃላዩ የህብረተሰብ አወቃቀርና ባህላዊ ሁኔታ ነው። ይህም ማለት በአጠቃላይ በአገራችን በጊዜው ሰፍኖ የነበረው የህብረተሰብ አወቃቀር ወይም በማህበረሰብ ሳይንስ (Social Science) አጠራር ፊዩዳላዊ ስርዓት የምንለውና ከዚህ ዐይነቱ ስርዓት ጋር የተያያዘው ባህል የማሰብ ኃይላችንና ድርጊታችንን በአማዛኝ ጎኑ ለመወሰን መቻሉ የሚክድ ያለ አይመስለኝም።  በሌላ ወገን ግን ግሎባል ካፒታሊዝም ከተስፋፋና የብዙ አገሮችን ዕድል መወሰን ከጀመረ ቢያንስ ከሰባ ዓመት ጀምሮ የሁላችንም አስተሳሰበ በሁለት መሀከል(In Beteewn) የሚዋልል ለመሆን በቅቷል። ይህ ዐይነቱ ዘመናዊ የሚባለው የባህልና የዕድገት ተጽዕኖ አገራችን ውስጥ ሰተት ብሎ ሲገባ ከባህላዊ የመንፈስ ተሃድሶ ጋር የተያያዘ ባለመሆኑ ራሱም በአስተሳሰባችንና በድርጊታችን ላይ የበኩሉን አሉታዊ አስተዋፅዖ ለማድረግ ችሏል ማለት ይቻላል።  ይህ አገር ቤት ውስጥ ያለውን ሁኔታ ሲመለከት፣ ከሃያና ከሰላሳ ዐመት በላይ አደጉ በሚባሉት የምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም አውስትራሊያና በሌሎች ከኛ ሻል ብለው የሚገኙ አገሮች ተበታትነን የምንኖር ኢትዮጵያውያን በብዙ ሚሊዮኖች የምንቆጠር ስንሆን አስተሳሰባችንም በሁለት ባህሎች መሀከል ብቻ የሚገለጽ አይደለም። ካፒታሊዝም የራሱ የውስጠ-ኃይል ስላለውና ወደድንም ጠላንም እሱ ስለሚያሽከረክረን የኛ አስተሳሰብና አካሄድ እንዲሁም ድርጊት በመጠኑም ቢሆን በሱ የሚወሰን ሊሆን በቅቷል። ይሁንና ግን የቱን ያህል በብዙ መልኮች በሚገለጸው የካፒታሊዝም የኢኮኖሚና የባህል ክንዋኔዎች ውስጥ ሰምጠን በመግባት እንደምንኖርና እንደምንዋኝ ብዙም የሚታወቅ ጉዳይ አይደለም።

ያም ሆነ ይህ እዚህ ምዕራብ አውሮፓ ወይም አሜሪካ ተቀምጠን በሃሳብ ማዕበል በመዋጥ ወደ ኋላ ዞር ብለን ስንመለከትና የዛሬውንም የአገራችንን ሁኔታ ስንመረምር አጠቃላዩ ሁኔታ በብዙ ቅራኔዎች የተዋጠ ነው። ይህ እዚያው በዚያው የሚድበሰበስ ቅራኔ፣ የፍሪድሪሽ ሄገልን ዲያሌክቲካዊ አባባል ልጠቀምና፣ አንድን ነገር በማጥፋት ወይም በመያዝና በዚያው ውስጥ ደግሞ አንድ ፍሬን በማፍራት የሚገለጽ አይደለም። በሌላ አነጋገር ሄገል እንደሚለን አንድ ዘር ሲዘራ ዘርነቱ እንዳለ ይጠፋል። ይህ ዘር ግን ወደ ስር፣ ግንድና ቅጠል በመለወጥ  የመጨረሻ መጨረሻ ወደ ፍሬ ይለወጣል። ሄገል ይህንን ዐይነቱን ተፈጥሮአዊ ሂደት ቴሲስ፣ አንቲ-ቴሲስና ሲንቴሲስ(Thesis, Anti-thesis and synthesis) ብሎ ይጠራዋል። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ ተፈጥሮአዊ ሂደት የበለጠ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው የሰው ልጅ በማሰብ ኃይሉ እንክብካቤ ካደረገለት ብቻ ነው። ይህም ማለት ማንኛውም ፍጡር ነገር፣ ራሳቸው አትክልቶችም ሆነ ዘሮች ውስጣዊ የሆነ የማደግ ኃይል ቢኖራቸውም፣ ከሌሎች አመቺ ነገሮች ባሻገር፣ ማለትም የመሬቱ ዐይነት፣ በቂ ፀሀይና ዝናብ የተመቻቹ ቢሆንም የሰው ልጅ ጣልቃ-ገብነት በአትክልቶች ማደግና ፍሬ መስጠት ላይ የራሱን የሆነ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊኖረው ይችላል። በሌላ አነጋገር የሰው ልጅ በማሰብ ኃይሉ የፍሬዎችን ፍሬያማነትና ታፋጭነት ሊወስን ቢችልም፣ በሌላ ወገን ግን የማሰብ ኃይሉ ውስን ከሆነ የተጠበቀው ፍሬና  ታፋጭነት ዕውን ሊሆኑ አይችልም። ይህም ማለት አንድ ሰውም ሆነ ህብረተሰብ በተፈጥሮ ላይ አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደር ይችላሉ ማለት  ነው።

ሁሉም ፈላስፋዎች የሚስማምቡት አንድ ነገር አለ። ይኸውም ዓለምን ቅርጽ ሊሰጣት የሚችለው አዕምሮ ወይም የማሰብ ኃይላችን ነው በሚለው ላይ ነው። ተፈጥሮን ማሳመር የምንችለው በማሰብ ኃይላችን ወይም በአርቆ አሳቢነታችን ብቻ ነው። በዚያው መጠንም ተፈጥሮን የምናበላሸው፣ በተፈጥሮ ላይ አደጋ በማድረስ እኛ መኖር እንዳንችልባት የምናደርገው የማሰብ ኃይላችን የቀጨጨ ወይም ያልዳበረ ከሆነ ብቻ ነው። በጠቅላላው የሰውን ልጅ ዕድገት ታሪክ፣ ዛፍ ላይ ተንጠልጥሎ ከመኖር አንስቶ፣ እያደነና ፍራፍሬዎችን እየለቀመ በመመገብ ረጋ ብሎ በመኖር መንደርን በመመስረትና የእርሻን ተግባር ማካሄድ ከጀመረ ጀምሮ ያለውን የሰውን ልጅ ታሪክ ስንመለከት የማሰብ ኃይሉም እየዳበረ እንደመጣ እንመለከታለን። በሌላ ወገን ግን ይህ ዐይነቱ ዕድገት በአንዳንድ አካባቢዎች በዚህ ልክ ወደፊት ለመግፋት እንዳልቻለና፣ ራሱ የሰው ልጅ አውቆም ሆነ ሳያውቅ በፈጠረው ባህልና የአኗኗር ስልት ሰለባ በመሆን የሳይንስ ባለቤት ሊሆን እንድላቻለ እንመለከታለን፤ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በማዳበር ወደ ከፍተኛው የህብረተሰብ ዕድገት ወይም የኑሮ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደማይችልም እንገነዘባለን። በተለይም የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል የፖለቲካ ስልጣንን በመቀዳጀትና የተፈጥሮ ሀብትን በመቆጣጠር ዕድገትን ባለህበት እንዲቀር ለማድረግ ይችላል። በዚህም ምክንያት የተነሳ የሰውም የማሰብ ኃይል ቀጭጮ እንዲቀር በማድረግ በአጠቃላይ ሲታይ አብዛኛው ህዝብ በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖር ይገደዳል። ያለውን የጥሬ ሀብት በስነ-ስርዓተ በማውጣጥና ወደ ተጠቃሚነት በመለወጥ የኑሮውን ሁኔታ ሊለውጥ አይችልም። የዚህ ዐይነት የሃሳብ መቀጨጭና ፖለቲካዊ ግልጽነት(Political Enightenment)  አለመኖር የግዴታ እንደተስቦ በመሳሰሉት በሽታዎች፣ በአውሮፓ ምድር የጥቁር-ሞት(Black Death) እያሉ በሚጠሩት በአንዳንድ ቦታዎች እስከ ሁለት ሶስተኛው ህዝብ እንዲሞት ተደርጓል። ይህ ዐይነቱ የሰውን ህይወት ቀጣፊ የወረርሽኝ በሽታ በጊዜው ሊከሰት የቻለው ከተማዎችና መንደሮች በዕቅድና ስርዓት ባለው መልክ ባለመገንባታቸው ነው። አብዛኛው ህዝብ ተበታትኖ የሚኖርና፣ በአንዳድ መንደሮች ደግሞ ተጨናንቆ ይኖር ስለነበር ሳይወድ በግድ የዚህ ዐይነቱ የወረርሽኝ በሽታና የሌሎችም ህይወት ቀጣፊ በሽታዎች ሰለባ ለመሆን በቅቷል። ይህንን ዐይነቱን ቅስፈት የእግዚአብሄር ቁጣ አድረገው ያልወሰዱ በጊዜው የተገለጸላቸው ምሁራንና ሳይንቲስቶች ጣልቃ በመግባትና ህብረተሰብአዊ ኃይል በመሆን የግዴታ የሰውን ልጅ የማሰብ ኃይል በማዳበር በመጀመሪያ በደንብ የተጠኑ ከተማዎችንና የገበያ ቦታዎችን በመገንባትና በማስፋፋት ግልጽ የሆነ የስራ ክፍፍል በማዳበር ለፈጠራ ስራ የሚያመች ቦታዎችንና አካባቢዎችን ማስፋፋት ችለዋል። ይህ ዐይነቱ ግልጽነት ያለው የከተማ አገነባብና የስራ-ክፍፍል መዳበር ለሳይንቲስቶችና ለገጣሚዎች፣ ለአርክቴክቸር ሙያ አዋቂዎች መፍለቅ አመቺ ሁኔታ ፈጥሯል ማለት ይቻላል። እነ ጋሊሌዮ፣ ኮፐርኒከስና ኬፕለር፣ እንዲሁም ሌሎች አያሌ ሳይንቲስቶችና ሰዓሊዎች የዚህ ዐይነቱ ዕድገት ክስተቶች ናቸው ማለት ይቻላል። ይህ ሁኔታ የኋላ ኋላ እንደተመለከትነው ለሶስት ተከታታይ የመንፈስ ተሃድሶ ምሁራዊ እንቅስቃሴዎች አመቺ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። ሬናሳንስ፣ የፕሮቴስታንት ሃይማኖት ብቅ ማለትና የካቶሊክን ዶግማ መዋጋት፣ ወይም ማክስ ቬበር(Max Weber) እንደሚያስተምረን የፕሮቲሰታንት ስነ-ምግባርና የካፒታሊዝም ዕድገት መታየት፣ ከዚህም ጋር ተያይዞ በ17ኛው ክፍለ-ዘመን የኢንላይተንሜንት እንቅስቃሴ መፈጠር፣ እነዚህ ሁሉ የሚያመለክቱት ሌላ ነገር ሳይሆን የአዕምሮ መታደስ አጋዦች ናቸው ማለት ይቻላል። ስለሆነም ነው ሳይንስና ቴክኖሎጂዎች በአውሮፓ ምድር ውስጥ ማደግ የቻሉት። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ክላሲካል፣ ጎቲክና ባሮክ የሚባሉት የህንጻ አሰራሮችና እንዲሁም ውብ ውብ ከተማዎች ሊገነቡ የቻሉት ከመንፈስ ተሃድሶ ጋር በመያያዛቸው ብቻ ነው። ከፍሎሬንስ እስከፓሪስ ድረስ፣ ሎንደንና፣ ቪን እንዲሁም ሳልዝበርግና ሌሎች የአውሮፓ ከተማዎች የምናያቸው የህንጻ አሰራሮችና የከተማ አወቃቀሮች፣ እንዲሁም በከተማ ውስጥ ብዙ ጋርደኖች መስፋፋታቸው፣ ይህ ሁሉ የሚያመለክተው የሰው ልጅ የማሰብ ኃይል በልዩ ዕውቀት የሚታገዝና የሚታደስ ከሆነ የሚኖርበትን መኖሪያ ቤትና አካባቢ ጥበባዊ በሆነ መልክ መገንባትና ማዘጋጀት እንደሚችል ነው።

ወደኛ አገር ስንመጣ ኢትዮጵያ አገራችን የሶስት ሺህ ዐመት ታሪክ አላት ቢባልም ይህንን ዐይነቱን የመንፈስ አዳሽ ዕውቀት ህዝባችንና አገዛዞች ለመቀዳጀት ወይም ከሱ ጋር ለመተዋወቅ ባለመቻላቸው የህዝቡም ሆነ የአገዛዞች ኑሮ እዚያው በዚያው  ሊሆን በቅቷል። ይህ ዐይነቱ ሁኔታ ለስምንት መቶ ዐመታት ያህል በመቆየት አገዛዞችም ሆነ ህዝቡ ኑሮውን ለማሻሻል አለመቻሉ ብቻ ሳይሆን፣ በተፈጥሮ ላይ በመዝመት ተፈጥሮን ሊያወድማት ቻለ። በጊዜው ዛፍ ለመሳሪያና ቤት ለመስራት የሚያገለግል ብቸኛው የጥሬ-ሀብት በመሆኑ፣ ለቤት ስራ፣ ለማገዶና ለሌሎች ነገሮች እየተቆረጠ በመዋሉ ይህ በራሱ በመሬቱ ምርታማነት ላይ አሉታዊ አስተዋፅዖ በማድረግ ህዝባችን ለተከታታይ ረሃብ ሊጋለጥ ቻለ። በታሪካችን ወይም በባህላችን ውስጥ ተከታታይነት(Sustainability)የሚለው ጽንሰ-ሃሳብ የሚታወቅ ባለመሆኑ አንድ ዛፍ ሲቆረጥ እሱን የመተካት ባህል ማዳበር አልተቻለም። የመንደሮችና የከተማዎችንንም አገነባብ ሁኔታ ስንመለከት በሰፈነው የማሰብ ኃይል ጥበት የተነሳ ጥበባዊ ከተማዎችን መገንባት አልተቻለም። ይህም በራሱ ለዕደ-ጥበብ ስራዎችና ለንግድ እንቅስቅሴ አመቺ ሁኔታዎች ሊፈጥር አልቻለም።

ኢትዮጵያ ነፃ ወጣች የተባለበትንና  ንጉሳዊ አገዛዝ እንደገና ተመልሶ አገዛዙን ቀስ በቀስ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረበትን ሁኔታ ስንመለከት፣ ኢትዮጵያ የዘመናዊ ስልጣኔ ቀማሽ በመሆኗ ይህ ተቆንጽሎ የገባው ዕድገት የሚባለው ነገር በህዝባችን ላይ የአስተሳሰብ  ለውጥ በፍጹም ሊያመጣ አልቻለም። የፈጠራ ችሎታውን ሊያዳብር በፍጹም አልቻለም። መንደሮችንና ከተማዎችን ዕቅድ ባላቸው መልክ ሊገነባ በፍጹም አልቻለም። በሌላ ወገን ግን ጣሊያን ለስድሳ ዐመትም ሆነ በኋላ በተቀረው የኢትዮጵያ ግዛት ሲቆይና ስንዋጋ የገነባውን እንደጅማ የመሳሰሉ ከተማዎችን፣ የአድሚንስትሬስን ቦታዎችና ሆስፒታሎችንና የገበያ አዳራሾችን የበለጠ ውበት በመስጠት ማሻሻል አልተቻለም። ጣሊያን ጅማን የገነባት በአምስት ዐመት ብቻ ነው። ለአንድ ከተማ አስፈላጊ የተባሉትን ነገሮች ሁሉ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ነው መገንባትና ማስፋፋት የቻለው። እነዚህን የመሳሰሉ ከተማዎችና አዲስ አበባም ጭምር የባህል ከተማዎች ከመሆን ይልቅ በአማዛኝ ጎናቸው የአስረሽ ምችው ቦታዎች በመሆን የፈጠራ ችሎታን ማቀጨጭ ቻሉ። በጊዜው የነበረው ንጉሳዊ አገዛዝ ከጊዜው የህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር የሚመጣጠኑ ከተማዎች ለመገንባት ባለመቻሉና፣ በዚያውም መጠንም መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟሉ የሚያስችሉ ኢንስቲቱሽኖች እንዲዋቀሩ ስላላደረገ በሃምሳኛው፣ በስድሳኛው ዐመትና እስከዛሬም ድረስ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ግዛት በአውሮፓ ምድር ውስጥ ሰፍኖ የነበረው የካቶሊክ ሃይማኖት የማዕከለኛው ዘመን የአኗኗር ስልት ተስፋፍቶ ይገኛል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ህዝባችን ተፈጥሮን የመቆጣጠርና የመቅረጽ ወይም የማሳመር ኃይሉ በጣም ደካማ በመሆኑ፣ የተማረውም ተፈጥሮን ለማሳመር የሚችል ዕውቀት ለመቅሰም ባለመቻሉ ህዝባችን ብቻውን ካለ አለኝታ እየባከነ እንዲቀር ተገዷል ማለት ይቻላል።

ይህ ጉዳይ በአብዮቱ ዘመንና አሁንም ቢሆን የተለወጠ አይደለም። በተለይም የዛሬው አገዛዝ 27 ዐመታት ያህል በሚያካሂደው ያልሰለጠነ አገዛዝ ተፈጥሮና ህዝባችን ከፍተኛ ዘመቻ እንዲካሄድባቸው ተደርገዋል። በአገዛዙ ካድሪዎችና በኤርትራ ማፍያዎች በተለይም የአምስትመቶና ከዚያም በላይ ዕድሜ ያላቸው ዛፎች እየተቆረጡ በመወሰዳቸውና፣ የተቀሩትን ደግሞ ከውጭ በተራድዖ ስም የመጡ አንዳንድ ድርጅቶችና ግለሰቦች ከአገሮቻቸው የሀብት ዘራፊዎች ጋር በመተባበር የአገራችን ውብና ተተኪ የማይገኝላቸው ዛፎች እየተቆረጡ እንዲወሰዱ ተደርገዋል። በየወረዳውና በየምክትል ወረዳው የተፈጥሮን ሀብት ለመከላከል የሚያስችሉ ኢንስቲቱሽኖች ባለመኖራቸው የገጠሩ ክፍል የውጭ አገር ሰላዮችና ሀብት ዘራፊዎች መፈንጫ ለመሆን በቅቷል ማለት ይቻላል። አብዛኛውም ህዝብ ጥሩ መጠለያ በማጣቱ የሚመካው በዛፍ ላይ ብቻ ነው። ዛፎችን እየቆረጠ ነው ለቤት ስራና ለማገዶ የሚያደርገው። ለኃይል ማመንጫና ለቤት ስራ፣ ለአካባቢ የሚያመቹ ዛፎች በጥናት እየተለያዩ በማይተከልበት አገር ዛፎች ካለምንም ርህራሄ እንዲወድሙ ተደረገዋል፤ እየተደረጉም ነው። ከዚህም ባሻገር በገጠር ውስጥ የሚኖረው ህዝብ ራሱ ከዱር አራዊት ለመከላከል የሚያስችለው ከጡብና ከዲንጋይ የተሰሩ ቤቶች ስለሌሉትና ግቢውም በደንብ የታጠረ ስላልሆነ በቀላሉ ለጅብ፣ ለነብርና ለአንበሳ እንዲዳረግ ተደርጓል። ሰሞኑን በሰሜን ሸዋ አንድ ገበሬ በነብር ተነክሶ ሲጮህ ሊያድኑት ከመጡት ሰዎች ውስጥ አንድ ዲያቆን በነብር ተነክሶና ተበልቶ ህይወቱን እንዲያጣ ተደርጓል። ይህ ሁሉ የሚያሳየን ያቺ አገራችን ብለን የምንጠራትና የምናለቅስላት ኢትዮጵያ የህዝቦቿ መኖሪያ ለመሆን እንዳልቻለች ነው። ባልሰለጠነ አገዛዝ ምክንያት የተነሳ አካባቢ እየወደመና፣ ክቡር የሆነው የሰው ህይወት ኑሮን ሳይኖራት ህይወቱን እንዲያጣ እየተደረገ ነው።

ክዚህ ስንነሳ አገራችን መሰረታዊ ለውጥ ያስፈልጋታል ብለን ውትወታ ስናደርግ ማየትና ማሰላሰል የማንቻለቸው አያሌ ነገሮች እንዳሉ መገመት እንችላለን። አብዛኛዎቻቸን ስለመሰረታዊ ለውጥ ያለን አስተሳሰብ ወይም ግምት ተፈጥሮን፣ የሰውን ልጅ አኗኗር፣ የከተማዎችንና የመንደሮችን አቀራረጽና አገነባብ ሁኔታ ያላከተተ ነው ማለት ይቻላል። ፖለቲካ የሚባለውንም ትልቅ ጽንሰ-ሃሳብ ከነዚህ መሰረተ-ሃሳቦች ነጥለን በማየት ነው የምናስተጋበው ወይም ገለጻ ለመስጠት የምንሞክረው። ይህንን ዐይነቱን አመለካከት ታላላቅ ፈላስፎች ክስተታዊ ዕውቀት ብለው የጠሩታል። ማለትም አንድ ነገር ከሌላው ተነጥሎ የሚታይ ከሆነ አንድ አገር ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮም ትናጋላች። የህብረተሰብንና የተፈጥሮ ህግን በመጣስ የሰው ልጅ ኑሮ የመረረ እንዲሆን ሳናውቀው የበኩላችንን አስተዋፅዖ እናደርጋለን። ታላላቅ ፈላስፋዎች እንደሚስያስተምሩን ፖለቲካ ከአጠቃላዩ የሰው ልጅ የአኗኗር ሁኔታ ተነጥሎ የሚታይ ነገር አይደለም። የሚበላው፣ የሚጠጣው፣ የሚኖርበትና የሚንቀሳቀስበት፣ የመንደሮችና የከተማዎች አገነባብ፣ የፈጠራ ስራዎችና ሌሎች እንደባህል ማዕከሎች፣ ስፖርትና የወጣቶች መዝናኛዎች ወይም የሃሳብ ማጎልመሻ ቦታዎች በሙሉ… ወዘተ.  እነዚህ ሁሉ ከፖለቲካ ጋር የሚያያዙ ናቸው። ይህም ማለት ፖለቲካን በሁለንታዊ መልኩ እስካልተረዳን ድረስ ፖለቲካ እያልን የምንወተውተው ነገር ዘለዓለማዊ ትርምስ ውስጥ ነው የሚከተን። ህብረተሰብአዊ መረጋጋትን ከማምጣት ይልቅ አለመረጋጋትን ነው የሚያስከትለው። ይህንን በመረዳት ነው ለአዲስ ህብረተሰብና ማህበረሰብ መታገል የሚያስፈልገው። ትግሉ መቀናበበር ያለበት ሲሆን፣ መተባበርን፣ መተጋገዝንና የሃሳብ ለሃሳብ መለዋወጥን የሚጠይቅ ነው። አንድ ሰው አንድ ነገር ሊሰራ ወይም ሃሳብ ሊያፈልቅ ቢችልም ወደ ተግባርነት ሊለወጥ የሚችለው ግን ብዙ ሰዎች ሲሳተፉበት ብቻ ነው።

 

መጭውና ዋናው ተግባራችን !

ሌሎችን ነገሮች ትተን አጠቃላዩን የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ ማለትም የመንደሮችንና የከተማ „አገነባብ“ ሁኔታ ስንመለከት ያቺ አገራችን እያልን የምንጠራት አገር በአብዛኛው መልኳ ስልጣኔ እየተባለ በሚጠራው ሁኔታ ውስጥ እንዳልደረሰችና ለመድረስም የሺህ ዐመታት ጉዞ መጓዝ እንዳለባት ነው የሚሰማኝ። ከዚህ ስንነሳ አንዳንድ ጊዜ ብልጭ ሲልብኝ የምጠይቀው ጥያቄ ለመሆኑ አገር ማለት ምን ማለት ነው ? አንድ አገርስ በምን መልኩ ነው ሊገለጽ የሚችለው ? በአንድ አገርና በዚያ ውስጥ በሚኖረው ህዝብ መሀክልስ ምን ዐይነት ግኑኝነት መኖር ነው የሚገባው ? በህዝቡና በተፈጥሮ መሀከልስ ያለው ግኑኝነት በምን መልክ ነው ሊገለጽ የሚችለው ? ህብረተሰብስ ማለት ምን ማለት ነው ? አንድን ሰው ሰው የሚያሰኘው ምንድነው ? አንድስ አገር የጥቂቶች መኖሪያና መፈንጫ  ወይስ የጠቅላላው ህዝብ አገር ? እነዚህና አያሌ ጥያቄዎች በጭንቅላቴ ውስጥ በመመላለስ ማስጨነቅ ከጀመሩ ዘመናት አልፈዋል። በተለይም ለዕረፍትም ሆነ ለሌሎች ጉዳዮች ወደ ተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ከተማዎች ስሄድ የምመለከተውን ሁኔታ ከአገራችን ተጨባጩ ሁኔታ ጋር ሳነፃፅር የሚሰማኝ አንድ ነገር የሚጎለን ነው የሚመስለኝ። ከስርዓት ባሻገር( Indpendent of Social systems) ማለትም ከካፒታሊዝም ወይም ከሶሻሊዝም ባሻገር በአጠቃላይ ሲታይ የሰው ልጅ የሚኖርበትን አካባቢ የመለወጥ ኃይል አለው። ይህም ማለት ማንኛውም የሰው ልጅ ሃሳብን የማፍለቅ፣ የራሱን ሃሳብ ከሌላው ጋር የማቀነባበር፣ ይህንን ሃሳቡን በስነ-ስርዓት የመንደፍ፣ ወይም ዕቅድ የማውጣት፣ የማደራጀትና ይህንን ሁሉ ጥበባዊ በሆነ መልክ ተግባራዊ የማድረግ ኃይል አለው። ስለሆነም የሰው ልጅ የሙዚቃ ደራሺና ዘማሪም ወይም ዘፋኝ ነው። አካባቢውንና ራሱን እንዲሁም የሌላ ሰውን የኑሮ ሁኔታ በስዕል መልክ የመግለጽ ችሎታና ኃይል አለው። ቤቶችንና ከተማዎችን በመስራት ከተፍጥሮ አደጋና ከአራዊት ራሱን የመከላክል ችሎታና ኃይል አለው። ዛሬ የምናያቸው በተለያየ መልክ የሚገለጹ ዕቃዎችም ሆነ መሳሪያዎች በሰው ልጅ የማሰብ ኃይልና ችሎታ የተፈጠሩ ናቸው። ራሱ ገንዘብም የስራ-ክፍፍል ውጤት ሲሆን በሰው ልጅ እንደየአስፈላጊነቱ የተፈጠረና የመገበያያ መሳሪያ ነው።  ባጭሩ ማንኛውም ሰው ወይም ህዝብ ታሪክን የመስራት ኃይል አለው። አካባቢዎቻቸውን መለወጥና ታሪክ ለመስራት የማይችሉ እንስሳዎች ብቻ ናቸው። ታዲያ የሰው ልጅ ሁሉ በዚህ ዐይነቱ የመንፈስ ወይም ሃሳብን የማፍለቅ ኃይል ጋር ከተወለደ ለምንድነው የአገራችን ሁኔታ አሁንም የሚዝረከረከው? ለምድንነው አሁንም ህዝባችን በድህነት ዓለም ውስጥ የሚኖረው ? የሚሉት ጥያቄዎች እኔን ብቻ ሳይሆን አብዛኛዎቻችንን፣ በተለይም ወጣቱን ትውልድ የሚያስጨንቁት ጉዳዮች ናቸው።

የአገራችንን አጠቃላዩን ሁኔታ ስንመለከት አገራችን በተፈጥሮ አቀማመጥ ውብ ነች። ተራራዎችና ሜዳዎች እንደልብ የሚገኙባት ነች። ወንዞችና ባህሮች እንደልብ አሏት። የተለያዩ እንስሳዎችም እንደልብ ይገኛሉ። በሌሎች አገሮች በተለይም በምዕራብ አውሮፓና አሜሪካ የማይበቅሉ የእህል ዐይነቶች የሚበቅሉባትና የሚገኙባት አገር ነች። ጤፍ በተለያየ መልክ፣ ከሰላሳ በላይ የሚጠጉ የስንዴና የገብስ ዐይነቶች ወይም ዘሮች፣ ማሽላና ዘንጋዳ፣ ዳጉሳ፣ በቆሎ፣ አተር፣ ባቄላና ሽምብራ ሌሎችም የጥሬ እህሎች በብዛት ሊበቅሉባት የሚችሉ አገር ናት። ለዘይት ጭማቂ ከሚያገለግሉ የሰብል ዐይነቶች ሰሊጥ፣ ኑግ፣ ተልባ፣ ሱፍና ለኦሊብ ዘይት የሚያገለግል አትክልት ሊበቅልባት የሚችል አገር ነች። ቡናና ሻይ፣ ማንጎና ፓፓዬ፣ ትርንጎና ብርቱካን እንዲሁም ኮክ በአገራችን ምድር እንደልብ ይበቅላሉ። ከአትክልት ዐይነቶችም ሽንኩርት፣ ጎመንና ቆስታ እንዲሁም ሌሎች ወደ ታች የሚበቅሉ የአትክልት ዐይነቶች፣ እንደ ድንች፣ ወይጭኖና እንዲሁም ጎደሬ የምታፈራ አገር ነች። ይህ ሁሉ እያለ ህዝባችን ከዐመት ዐመት ይራባል። አስፈላጊውን የምግብ ዐይነቶች፣ ማለትም ቪታሚንና ፕሮቲና እንዲሁም ልዩ ልዩ ሚኒራሎችን ያዘሉ ምግቦችን በማጣቱና ለመመገብ ባለመቻሉ በቀላሉ ለበሽታ ይጋለጣል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ለአማራጭ ህክምና የሚያገለግሉ የተለያዩ አትክልቶች አሉ። እነዚህ ሁሉ የተፈጥሮ ስጦታዎች እያሉን በማሰብ ኃይል ዕጥረት የተነሳ በብዛትም ሆነ በጥራት እያመረትን ራሳችንን መመገብ የምንችል አይደለንም። በተበላሽ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የተነሳ ወደ አንድ አቅጣጭ የሚያዘነብል የአሰራር ስልት በማዳበራችን ለዕድገታችንና ለብልጽግናችን የሚያገልግሉ ሰብሎችና ፍራፍሬዎች እንዳይስፋፉ እንቅፋት ፈጥረናል። የኑሮንና የተፈጥሮን እንዲሁም የአገርን ትርጉም ለመረዳት ባለመቻላችን ወይም ባለመፈለጋችን በራሳችን ላይ ብቻ ሳይሆን በተከታታዩ ትውልድናና በተፈጥሮ ላይ ከፍተኛ ዘመቻ እያካሄድን ነው።

ወደ ሌሎች ነገሮች ስንመጣ በቀላሉ ቤት መስራት ስንችል አሁንም በ21ኛው ክፍለ-ዘመን አብዛኛው ህዝባችን በጎጆና በወዳደቁ የቆርቆሮ ቤቶች ውስጥ እንዲኖር ተገዷል። ጡብ ለመቅረጽ ወይንም ለመጥበስ የሚያገለግል የአፈር ዐይነት በብዛት አለን። የተለያዩ የዲንጋይና የዕብነ-በረድ ዐይነቶች እንደልብ ይገኛሉ። ቤት ለመስራት ከደለል የሚገኝና ከጊፕስ ጋር በመቀላቀል ዲንጋዮችን ወይም ጡቦችን የሚያጣብቅ የተፈጨ የሚመስል አሸዋ እያለን ይህንን በስነ-ስርዓት በማውጣትና በመጠቀም የሚያማምሩ ቤቶችና መስሪያ ቤቶች እንዲሁም የንግድ አዳራሾችን፣ ቤተክርስቲያኖችንና መስጊዶችን መስራት አልቻልንም። እነዚህን ሁሉ መጠቀም አቅቶን ህዝባችን ከእንስሳ ጋር እየተጋፋ እንዲኖር ተደርጓል። ለዱር አራዊትና ለተፈጥሮ አደጋ የተጋለጠ ህዝብ ነው።

ወደ ከተማዎችና መንደሮች አሰራር ስንመጣ አሰራራቸው በሙሉ የተፈጥሮንና የኮስሞስን ህግ የሚጻረሩ ናቸው። ከተማዎች ወደ ቆሻሻ መኖሪያነት ተለውጠውል። ከአንድ ዐመጥ በፊት ቆሼ በሚባለው ቦታ የተከማቸው ቆሻሻ ተደርምሶ ቁጥራቸው በቅጡ የማይታወቁ ሰዎች መሞታቸው የሚያመለክተው የቱን ያህል የማሰብ ኃይላችን የተወሰነ መሆኑን ነው የሚያመለክተው። የሰለጠነ አገዛዝ እንደሌለን ነው ይህና አንዳንድ የቆሻሻ መኖሪያ ቦታዎች የሚያረጋግጡት። ከተማዎችና መንደሮች ለሰው ልጅ መኖሪያ ታስበው የተሰሩና የሚሰሩ አይደሉም። አባዛኛዎቹ ከተማዎች የወዳደቁ ከመሆናቸው የተነሳ የሰውን የማሰብ ኃይል የሚያቀጭጩ ናቸው። የዳበረና የጎለመሰ ህብረተሰብ እንዳይፈልቅ የሚያግዱና የሰውን ጭንቅላት የሚረብሹ ከተማዎች ናቸው በየቦታው የተስፋፉት። ከተማዎች በዕቅድ ካለመሰራታቸው የተነሳ በተለይም ደካማው የህብረተሰብ ክፍል፣ አሮጊቶችና ሽማግሌዎች ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው። በከተማ ውስጥ መናፈሻና መጠለያ ቦታዎች የሉም። ሰው ከገበያ ሲመጣ አረፍ የሚልበት መጠለያና መቀመጫ ቦታ የለውም። በተለይም የአገራችን የከተማዎችና የመንደሮች አገነባቦች ፀረ-ህፃናት ናቸው። ህፃናትና ጎረምሳ ልጆች በደንብ ተዛናንተው የሚጫወቱባቸው ቦታዎች የሏቸውም። በየከተማዎች ውስጥ ወጣቱ እንደልብ ባስኬትና የእግር ኳስ የሚጫወትባቸው ቦታዎች የሉትም። እዚህ የምኖርበት በርሊን ከተማ ውስጥ ብቻ ቢያንስ ወደ መቶ የሚጠጉ የኳስ መጫዎቻ ቦታዎች አሉ። ወደ መቶ አርባ የሚጠጉ መናፈሻዎች አሉ። ከተማው በጫቃ ጥቅጥቅ ያለ ነው የሚመስለው። በየመንገዱ ዳር በ20 ሜትር እርቀት ዛፎች ተተክለው ለከተማው ውብት ይሰጣሉ። ዝናብም ለመዝነብ የበኩላቸውን አስተዋፅዖ ያደርጋሉ። የመጸዳጃ ቦታዎች እንደልብ ይገኛሉ። የመንገዶች አሰራር ለመኪና፣ ለእግረኛና ለቢስኪሌት በደንብ ተሰምረው የተሰሩ ናቸው። ሰውና መኪናዎች እየተጋፉ አይሄዱም። የእግር መንገዶች በደንብ የተከለሉ ናቸው። እነዚህ ሁሉ የተሰሩት እንደኛው ባሉ የማሰበ ኃይል ባላቸው ሰዎች ነው። እኛስ ለምን ቆንጆ ቆንጆ ከተማዎችን አንገነባም ? ምንስ ይሳነናል ? ወይስ በዚህ ዐይነት መልክ የመኖር መብት የለንም ወይ ? እግዚአብሄር ረግሞናል ወይ ? እነዚህና ሌሎችን ጥያቄዎች መመለስ አለብን።

ከዚህ ስንነሳ አንድን አገር እንደ አገርና ህብረተሰብ የሚያሰኙት ከላይ የዘረዘርኳቸው ነገሮች ሲሟሉ ብቻ ነው። የሰው ልጅ በጊዜና በቦታ የሚኖር ነው። ጊዜ መለኪያ ሲሆን፣ ቦታ(Space) ደግሞ የሰው ልጅ በማሰብ ኃይሉ የሚያቀናጀው፣ የሚነድፈውና መኖሪያው የሚያደርገው ነው። የአንድ ህዝብ ምንነት የሚገለጸው ስንትና ስንት ሺህ ዘመን ወደ ኋላ ተጉዞ አባቶቹና እናቶቹ በሰሩት ስራ በመዝናናት ሳይሆን፣ ዛሬና ነገ በሚሰራቸው ነገሮች ብቻ ናቸው። ሄገልና ላይብኒዝ እንዲሁም ካንት በምትህት(Myth) አያምኑም። ስለዛሬውና ስለነገው ብቻ ነው የሚያስቡት። ይህም ማለት፣ የሰው ልጅ ወደ ኋላ በመጓዝ የሚዝናና የሚጽናና ወይም ጉራ መንዛት ያለበት ሳይሆን ባለበት ወቅት ታሪክን በመስራት ለመጭው ትውልድ አንድ ነገር ጥሎ ማለፍ እንዳለበት ነው የሚያሳስቡት። ይህ ማለት ግን አንዳንድ ጥሩ ባህላዊ ነገሮችን እንርሳ ወይም ክብደት አንስጣቸው ማለታቸው አይደለም። እንክብካቤ ማድረግ የሚገባንን ባህሎች በመጠበቅ አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር አለብን ማለታቸው ነው። አንድ ህዝብ በዘለዓለማዊ ጦርነትና ድህነት ውስጥ ሲኖር ምክንያቱን በመመርመር መፍትሄ መፈለግና ማቅረብ ያስፈልጋል ማለታቸው ነው። እኛ ኢትዮጵያኖች እኛ ብቻ ታሪክ ያለን ይመስል በተለይም ወጣቱ ትውልድ ታሪክን እንዳይሰራ የማይሆን ነገር እየተረክንለት ነው። ይህንንም ሆነ ያንን ዘፈን እየዘፈን ከቁም ነገር እያዘናጋነው ነው። በተለይም በአሁኑ ወቅት የሚናፈሰው ወሬና ሀተታ ወይም አንዳንድ የዘፈን ዐይነቶች ያለንበትን ሁኔታ በቅጡ እንዳንረዳ እያደረጉን ነው። ዘመኑ የቀረርቶና የፉከራ ዘመን ሳይሆን የፈጠራና የውብ ስራዎች ዘመን ነው። የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዘመን ነው።

ከላይ እንዳልኩት ከስርዓት ባሻገር ማንኛውም ህዝብ ያለበትን ሁኔታ በመገምገም የተሻለ ስራ ለመስራት መነሳት አለበት። አንድ ህብረተሰብ በኢዝም፣ ማላትም በካፒታሊዝምና በሶሻሊዝም ብቻ መገለጽ የለበትም። ወይም ደግሞ በገበያ ኢኮኖሚ መወናበድ የለበትም። ፈላስፎችና የቲዎሎጂ ሰዎች፣ የኋላ ኋላም የሳይንስ ተመራማሪዎች ምርምራቸውንና ስለሰው ልጅ አኗናር ያላቸውን ግምትና አስተሳሰብ በስርዓት በፍጹም አልገደቡም፤ ወይም ይህ ዐይነቱ ስርዓት ነው ዕድገትንና መሻሻልን ሊያመጣ ይችላል ብለው ለሃሳባቸው ገደብ የሰጡት።  ስለስራ-ክፍፍልና ስለንግድ ልውውጥ አስፈላጊነት ቢያወሱምና ቢያሳስቡም፣ ዋናው ምርምራቸው ግን ያዘነበለው የሰው ልጅ እንዴት አድርጎ ከተማዎችንና መንደሮችን ጥበባዊ በሆነ መልክ በመገንባት በስምምነት ላይ የተመሰረተ ኑሮ መኖር ይችላል በሚለው ላይ ነው። ከዚህ በመነሳት በተለይም ሄገል የሰለጠነ የሲቪል ህብረተሰብ መኖርንና የተለያዩ ኢንስቲትሽኖችን መገንባት አስፈላጊነት ያሳስባል።

ከዚህ ስንነሳ የካፒታሊዝም ዕድገት ታስቦ ብቅ ያለ አይደለም። ከብዙ ውስብስብና ትግል በኋላ በአሽናፊነት የወጣ ስርዓተ ማህበር ነው። ይሁንና ግን ይህ የመጨረሻው ስርዓት ነው ማለት አይደለም። ከመቶና ከሁለት መቶ ዐመት በኋላ ምን ዐይነት ስርዓት እንደሚመጣ ማንም ሊተነብይ በፍጹም አይችልም። ስለዚህም የገበያን ኢኮኖሚና ካፒታሊዝምን የዕድገት መጨረሻው አድርጎ መውሰድ ወይም ከዚህ አልፎ መሄድ አይቻልም ብሎ መገመት ውስንነትን ነው የሚያመለክተው። በሌላ ወገን ግን አሁን በሚካሄደው የተፈጥሮ ሀብት ውድመትና አጠቃቀም፣ እንዲሁም የማያቋርጥ የጦር መሳሪያ ምርትና ወደ ጦርነት ማምራት የሰውን ልጅ ዕድገት በብዙ መቶ ዐመታት ወደ ኋላ መጎተት ይቻላል።  የአንደኛውና የሁለተኛው ዓለም ጦርነቶች የአውሮፓን ዕድገት ለብዙ ዓመታት ወደ ኋላ ሲጎትቱ፣ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ህይወታቸው እንዲጠፋ ተደርጓል። በዚያው መጠንም እንደገና መልሶ ለመገንባት የሚያስቸግሩ የሚያማምሩ የማዕከለኛው ዘመንና የአስራሰባተኛው፣ የአስራ ስምንተኛውና የአስራዘጠነኛው ከተማዎች እንዳለ ወድመዋል። ስለሆነም የሰው ልጅ የመጨረሻው ስርዓት ላይ አልደረሰም፤ ወይም ደግሞ ወደ ኋላ ሊጓዝ አይችልም ብሎ ማሰብ ከታሪካዊ ግንዛቤ እጥረት የሚመነጭ የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው።

ወደ አገራችን ስንመጣ የዛሬውና መጭው ትውልድ የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩና ታሪክን እንዲሰሩ ከፈለግን የአስተሳሰብ ለውጥ ማድረግ አለብን። ስለባንዲራና ስለሶስት ሺህ ዐመት ታሪክ እየደጋገምን ስናነሳ ያለንበትን ሁኔታ በሚገባ መገንዘበ አለብን። በምን ዐይነት ሁኔታ ውስጥ ህዝባችን እንደሚኖር ማውጣትና ማውረድ መቻል አለብን። ስለሆነም የኛ ምንነት ሁኔታችንን በመለወጥና ለመለወጥ ባለመቻል የሚወሰን ብቻ ነው። ከዚህ ውጭ ሊታሰበ አይችልም። ስለሆነም አይ ታሪክን ለመስራት መታገል ወይም ሳይሰሩ ወደ ማይቀረው ዓለም መሄድ ግዴታችን ነው ማለት ነው።

ይህንን ዐይነቱን የተቀደሰ ህልማችንን በምን ዐይነት ስርዓት ውስጥ ነው ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው ? ብለው ብዙዎች ሊጠይቁ ይችላሉ። ሰሞኑን ባወጣሁት የዶ/ር አቢይ አህመድን ጠቅላይ ሚኒስተር ሆኖ መመረጥ አስመልክቼ ያተትኩትን ሀተታ በማስመር፣ የሱ መመረጥ ብቻ ተዓምር ሊሰራ አይችልም። በሀተታዬ ላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የወያኔ አገዛዝና ጄኔራሎችና የስለላ መዋቅሩ እስካለ ድረስ ብዙም መራመድ አንችልም። እነዚህና ሌሎች የመንግስት አካሎች ውስጣዊ ይዘታቸው በከፍተኛ ደረጃ ሁለ-ገብ የሆነና የተስተካከለን ዕድገት የሚቃወሙ ናቸው። የመንግስቱና የአገዛዙ አወቃቀር የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ የሚፃረሩ ናቸው። በፍጹም ሊታደሱ ወይም ሊጠገኑ አይችሉም። ሞተሩ እንዳረጀና ለመጠግነ እንደሚያስቸግር መኪና ዐይነት የወያኔ መሪዎች ጭንቅላት ሊታደስ ወይም ሊጠገን በፍጹም አይችልም። የወያኔ አገዛዝ የሰውን ልጅ መብት እንዳለ የሚቃውምና የሚያውቅ አይደለም። ራሳቸው የወያኔ ሰዎች የማሰብ፣ የመሰማት(Feeling)፣ የማየትና ሌሎች ኦርጋኖቻቸው በሙሉ የተሰለበ ወይም የወደመ ነው የሚመስለው። ሰው መሆናቸውን የዘነጉ በመሆናቸው ለምን እንደሚኖሩ የሚያውቁ አይደሉም። በሰው ስቃይና ሀዘን የሚደሰቱ ናቸው። በድርጊታቸው እየተዝናኑ በውስኪና በኮኛክ የሚታጠቡ ናቸው። ስለሆነም ይህንን ዐይነቱን የበሰበሰ ስርዓት መሰረት አድርጎ ጥበባዊ አገር መገንባት በፍጹም አይቻልም። ጥያቄው ዶ/ር አቢይንና አንዳንድ አጋዦቹን ከዚህ ዐይነቱ የሚለበልብ እሳት እንዴት ፈልቅቆ ማውጣ ይቻላል ? የሚለውን ጥያቄ ነው መመለስ ያለብን። ስለሆነም ትግላችን የሚያቋርጥ ሳይሆን፣ ማንኛውም የሰለጠነና ጥበባዊ ስርዓትን የሚቀናቀን የመጨቆና መሳሪያ ህግ እስኪደመሰስ ድረስ መቀጠል ያለበት ነው። አገዛዙና መንግስት ሰዎች በሆኑና የሰው ልጅ ባህርይ ባላቸው መተዳደርና መመራት አለባቸው። ትግሉ ሁለመንታዊና ተከታታይነት ያለው መሆን አለበት። የበለጠ ምሁራዊና የጠለቀ እንዲሁም ሳይንሳዊ መሆን አለበት። በዚህ መልክ ብቻ ነው ወደምንፈልገው ግብ ማምራት የምንችለው። መልካም ግንዛቤ !!

 

fekadubekele@gmx.de

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here