Home News and Views የህወሃት አገዛዝ ስለምን ዐይነት አብዮታዊ ዲሞክራሲና ልማታዊ  መንግስት ነው የሚነግረን ?

የህወሃት አገዛዝ ስለምን ዐይነት አብዮታዊ ዲሞክራሲና ልማታዊ  መንግስት ነው የሚነግረን ? [ ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር)]

መግቢያ

እ.አ በግንቦት ወር 1997 ዓ.ም  ቅንጅትና ህብረት ምርጫውን ሲያሸንፉ የህወሃት አገዛዝ  ህዝቡን ማስፈራራት የጀመረው እነዚህ ሁለት ድርጅቶች ስልጣን ከያዙ የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲን ተግባራዊ ያደርጋሉ በማለት ነበር። አሁን ደግሞ የያዘው ፈሊጥ የህወሃት አገዛዝ ስልጣን ይዞ እስካልቆየ ድረስ የአብዮታያዊ ዲሞክራሲና በመንግስት የተደገፈ ልማት ወይም በሱና በካድሬዎቹ እንዲሁም በአፈ-ቀላጤዎቹ አጠራር ልማታዊ መንግስት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሊሆኑ አይችሉም የሚል ነው። በተለይም አሜሪካ ያሉት በአይጋ ፎረም አካባቢ የተሰባሰቡና ለድህረ-ገጹ አንዳንድ መጣጥፎችን የሚያቀርቡ የሚያናፍሱት ወሬ በአገሪቱ ውስጥ ቀውስ ሊፈጠር የቻለው አብዮታዊ ዲሞክራሲና የልማታዊ መንግስት አጀንዳዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመሆናቸው የተነሳ ነው ይሉናል።

በአጠቃላይ ሲታይ እነዚህን በመሳሰሉትና በሌሎች የኢኮኖሚክስ ፅንሰ-ሃሳቦች ላይ የተዛባ አመለካከት ስላለ በራሱ ተቃዋሚ ነኝ በሚለው መላቅጥ በሌለው እንቅስቃሴና ለድህረ-ገጾች በሚያቀርቡ አንዳንድ ምሁራን አመለካከትና ዕምነት የህወሃት አገዛዝ ለ27 ዐመታት ያህል ተግባራዊ የሚያደርገው የኢኮኖሚ ፖሊሲና ፖለቲካ የልማታዊ መንግስትና የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አገዛዝ ነው እየተባለ ነው። እንዲያውም በአንዳንድ ምሁራን ዘንድ በአብዮታዊ ዲሞክራሲና በሊበራል ዲሞክራሲ መሀከል ያለውን ልዩነት „በማብራራት“ ፣ የህወሃት አገዛዝ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ተግባራዊ በማድረግ ላይ ያለ ነው በማለት ሊያሳምኑን ይሞክራሉ። ሌሎች ደግሞ ድሮ የግራ ዝንባሌ የነበራቸው አንዳንድ ድርጅቶችና ግለሰቦች የህወሃትን አደረጃጀት ስታሊኒስታዊ ነው በማለት ህዝቡን ያስፈራራሉ።

በተለይም የአብዮት ስም ሲነሳ ብዙዎች ቢዘገንናቸውና ቢደናገጡም የሚያስገርም አይደለም። ወይም ደግሞ ወያኔ ራሱ ለማወናበድ ሲል ይህንና የልማታዊ መንግስት ፅንሰ-ሃሳብን ቢያናፍስና ሌሎችን ኒዎ-ሊበራሎች እያለ ቢጠራ ይህንን ያህልም አያስደንቀንም። የሚያናድደኝ ግን  በአንድ ወቅት ከግራም በላይ ግራ በመሆን የሶሻሊዝምን መፈክር ይዘው ሲዘምሩና ሲያራግቡ የነበሩ ዛሬ 180 ዲግሪ ተገልብጠው አብዮትንና ሶሻሊዝምን ሲያጥላሉ፣ እንዲሁም በአለፉት 27 ዓመታት በአገራችን ምድር ሲካሄድ የነበረውና ያለው የአብዮታዊ ዲሞክራሲና የልማታዊ መንግስት አጀንዳ ነው ብለው ምድረ-ህዝብን ሲያሳስቱ ስናይ የሚዋጥልን ነገር አይደለም።

ለአንድ አገር ዕድገት፣ ለህብረተሰብ መተሳሰርና በዕሴት ላይ ለተመሰረተ ባህላዊ እንቅስቃሴ ትግል ሲደረግ ከመጀመሪያውኑ ግልጽ መሆን ያለባቸው ነገሮች አሉ። እንደሚታወቀው አብዛኛዎቹን የፖለቲካና የኢኮኖሚክስ ፅንሰ-ሃሳቦች ከውጭ የቀሰምናቸውና የምናፍሳቸው ስለሆኑ አብዛኛውን ጊዜ ተግባራዊ ሲሆኑ ጥሩና ለህዝብ የሚጠቅም ውጤትን ከማምጣት ይልቅ ሀብትን አውዳሚና ኃይልን በታኝ ይሆናሉ። በአብዮቱ ወቅትና ባለፉት 27 ዐመታት የተካሄዱት እንቅስቃሴዎችና ተግባራዊ የሆኑት ፖሊሲዎች በሙሉ ረጋ ባለመልክና በሰፊው ተጠንተው ተግባራዊ እንዲሆኑ ባለመደረጋቸው የአገራችን ዕድገት ወደ ፊት ከመራመዱ ይልቅ ወደ ኋላ እንዲጓዝ ሊደረግ በቅቷል። ህብረተሰባችንም ተዘበራርቆና ህዝቡም ተምታቶበት ወዴት እንደሚያመራ ግራ ተጋብቶ እናያለን።

ስለሆነም በአገራችን ምድር ስኬታማ ውጤት እንዲመጣ ከተፈለገና፣ ሰላምና መረጋጋትም እንዲሰፍን ምኞታችን ከሆነ የግዴታ ተግባራዊ በሚሆኑ ፖሊሲዎች ብቻ ሳይሆን፣ በፅንሰ-ሃሳቦችም  ላይ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲኖረን ያስፈልጋል። ይህ ብቻ ሲሆንና፣ በተለይም ነገሮች ከቲዎሪና ከኢምፔሪካል አንፃር እየተተነተኑ ሲቀርቡ ተግባራዊ በሚሆኑበት ጊዜ የተጠበቀውን ውጤት ሊያመጡ ወይም ሊያሳዩ ይችላሉ። ከዚህ በመነሳት የአብዮታዊ ዲሞክራሲን፣ የልማታዊ መንግስትን፣ የኒዎ-ሊበራልንና፣ በአጠቃላይ ሲታይ የኢኮኖሚክስንና የዕድገትን ትርጉም አጠር አጠር ባለመልክ ለማቅረብ እሞክራለህ።

አብዮታዊ ዲሞክራሲ ማለት ምን ማለት ነው ?

በመጀመሪያ አብዮት የሚለውን ፅንሰ-ሃሳብ እንመልከት። አብዛኛውን ጊዜ አብዮት የሚባለው ፅንሰ-ሃሳብ ከኢንዱስትሪ ዕድገት ጋር ሲያያዝ፣ የኢንዱስትሪ አብዮት በመባል በሁላችንም መንፈስ ውስጥ ሊቀረጽ ችሏል። ይሁንና በኢኮኖሚክስ የታሪክ ተመራማሪዎች ዕምነት የኢንዱስትሪ አብዮት ከመቅጽበት የተካሄደ ሳይሆን አንድ ሰው በፈጠረው ቴክኖሎጂ ላይ ሌላው በመቀጠልና በማዳበር ወይም በማስፋፋት በአንድ ወቅት የኢንዱስትሪ እንቅስቃሴ የታየበት እንደሆነ ይናገራሉ;፡ በተጨማሪም ተሰበጣጥረው የተለያዩ ምርቶችን ያመርቱ የነበሩ ትናንሽ እንዱስትሪዎች በአንድ አጠቃላይ የአመራረት ስልት በመደራጀት ወደ ፋብሪካነት የተለወጡበትና፣ ከዚህ በፊት የትናንሽ ኢንዱስትሪዎች ባለቤት የነበረው ራሱ ወደ ሰራተኛነት የተለወጠበትን ሁኔታ የኢንዱስትሪ አብዮት ብለው  ይጠሩታል።

ወደ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ስንመጣም የመጀመሪያው አብዮት የተካሄደው እ.አ በ1640 በእንግሊዝ አገር ሲሆን፣ ዕድገትን በሚፈልገው በአዲሱ የከበርቴ መደብና የሊበራል አስተሳሰብ ባላቸው ምሁራን በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ ሰፋፊ መሬቶችንና የመንግስትን መኪና በሚቆጣጠረውና ለውጥን በማይፈልገው በአሪስቶክራሲው መደብና በንጉሱ መሀከል ነበር። ከ20 ዓመት የርስበርስ ጦርነት በኋላ የከበርቴው መደብና ሊበራል ኃይሎች በአሸናፊነት በመውጣት ለካፒታሊዝም ዕድገት አመቺ ሁኔታን ሊፈጥሩ ችለዋል። ሁለተኛው አብዮት ደግሞ  እ.አ በ1789 ዓ.ም በፈረንሳይ አገር የተካሄደ ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም ያረጀውንና ዕድገትን የሚቀናቀነውን  በንጉስ ሊውስ 16ኛ የሚመራውን ኋላ-ቀር አገዛዝ አሽቀንጥሮ የጣለ አብዮት ነበር። አብዮቱ አሰቃቂ ቢሆንም ለአዲስ የፖለቲካ አስተሳሰብ በር የከፈተና ፈረንሳይን ወደ ህብረ-ብሄር እንድታመራ ያደረገ ነው።  በሶስተኛ ደረጃ ሰፋ ባለመልክ በኮሙኒስቶችና በሶሻል ዲሞክራቶች በመመራት በጀርመን ምድር በ1848 የተካሄደው አብዮታዊ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ ይህ አብዮታዊ እንቅስቃሴ ብዙ የአውሮፓ አገሮችን ያዳረሰ ነበር።  በወቅቱ የወዝአደሩ መደብ ቀስ በቀስ እየተደራጀና ለመብቱ መታገል እንዳለበት የተገለጸለት ነበር። ይህም ሊሆን የቻለው በጊዜው የወዝአደሩ መደብ በቀን ከአስርና ከአስራ ሁለት ሰዓት በላይ ይሰራ ስለነበረና፣ የህፃናትም ስራ የተስፋፋ ስለነበር ወዝአደሩ የግዴታ የስራ ሰዓት እንዲቀነስ ብቻ ሳይሆን ለዲሞክራሲያዊ መብቶች በመታገል የራሱን አገዛዝ ለመትከል የሚንቀሳቀስበት ዘመን ነበር። በተለይም እንደጀርመን የመሳሰሉት አገሮች በአምባገነናዊ የሞናርኪዎች አገዛዝ የተነሳ የዲሞክራሲ ነፃነቶች የታፈኑበት ዘመን ስለነበርና ከፍተኛም ብዝበዛ በመካሄዱ ይህንን ለመግታት ሲባል የግዴታ ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ ሊካሄድ ቻለ። ይሁንና ግን እንቅስቃሴው ሊከሽፍ ሲችል፣ እነቢስማርክ የማህበራዊ መሻሻል ህጎችን በማውጣት በኮሙኒስቶችና በሶሻል ዲሞክራቶች የሚመራውን እንቅሳቅሴ ሊያኮላሸው ችሏል። በቢስማርክም የማህበራዊ ፖሊሲ አማካይነት አጠቃላይ የህክምና ኢንሹራንስ፣ የጡረታ አበልና ሌሎች የማህበራዊ ፖሊሲዎች ተግባራዊ በመሆን ወዝአደሩ የዕድገት ተካፋይ ሊሆን ችሏል። በፖሊሲው መሰረትም የኢንዱስትሪና የንግድ ባለሀብቶች በእኩል ደረጃ በማውጣት የማህበራዊ መስኩን እንዲደጉሙ ተደርገዋል። ይህ ዐይነቱ የቢስማርክ የማህበራዊ ፖሊሲ እስከዛሬ ድረስ የሚሰራበት ነው።

በአራተኛ ደረጃ  እ.አ በ1917 ዓ.ም  በራሺያ ምድር የተካሄደው አብዮት ነው።  ይህ የራሺያ አብዮት እነሌኒን በሚመሩት በቦልሺቢኪ ፓርቲ  የተካሄደና ግቡንም የመታ ሲሆን፣ ከራሺያ አልፎ ዓለም አቀፋዊ ተፅዕኖም ነበረው። ለአብዮቱም ዋና ምክንያት የዛር መንግስት እስከዚያ ጊዜ ድረስ አስፈላጊውን የጥገና ለውጦች ለማካሄድ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ነው። ንጉሱና ቤተሰቦቹ በተደንላቀቀ ሁኔታ ሲኖሩ፣ ሰፊው የራሺያ ህዝብ ደግሞ በድህነትና በረሃብ ዓለም ውስጥ የሚኖር ነበር። ይህ ሁኔታና በተለይም ደግሞ ከ1914-1918 ዓ.ም የጀርመን ወራሪዎች በራሺያ ላይ በከፈቱት የመጀመሪያው ዓለም ጦርነት አገዛዙ ተዳክሞ ስለነበር እነሌኒን ይህንን ተጠቅመው በ1917 ዓ.ም የጥቅምትን አብዮት አወጁ። በዚህም የተነሳ የጦርነት ኮሙኒዝም የሚባለውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ በማወጅ በጦርነቱ ምክንያት የደቀቀውን ኢኮኖሚ እንዲያገግም ለማድረግ አስፈላጊ እርምጃዎች ተወሰዱ። በዚህም መሰረት በግል ይዞታ ስር የሚገኙ የንግድ እንቅስቃሴዎችንና ኢንዱስትሪዎችን በመንግስት ቁጥጥር ስር በማዋል፣ በተለይም የእርሻው ዘርፍ ተጨማሪ ምርት(Surplus Product) ያመርት ዘንድ አስፈላጊው እርምጃዎች ተወሰዱ። ይሁንና ይህ ፖሊሲ እንደተጠበቀው ውጤታማ ባለመሆኑ፣ እነ ሌኒን ይህንን የጦር ኢኮኖሚ በአዲስ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመተካት የገበያ ኢኮኖሚ ሊስፋፋና ሊዳብር የሚችልበትን ሁኔታ አመቻቹ። በአዲሱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሰረትም(New Economic Policy) ትናንሽ የንግድ መደብሮችና(Retail Trade)፣ ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች በግል ይዞታ ስር እንዲውሉ ሲደረግ፣ ባንኮች፣ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች፣ የውጭው ንግድ፣ የመንገድና የመገናኛ መመላለሻዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲቀሩ ተደረገ። አብዮቱ እስከፈነዳና እነዚህ ፖሊሲዎች ተግባራዊ እስከተደረጉ ድረስ አብዛኛው የራሺያ ግዛትና ህዝብ በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎች ነገሮች ከሌሎች የምዕራብ አውሮፓ አገሮች ጋር ሲወዳደር እጅግ ወደ ኋላ የቀረ ነበር። ለዚህም ነው እነ ሌኒን ይህንን ኋላ-ቀርነት በመገንዘብ በራሺያ ምድር ሁለ-ገብ የሆነ መብራት(Electrification) መግባት ወይም መስፋፋት እንዳለበትና፣ ይህም ለኢንዱስትሪ መስፋፋትና ማደግ የመጀመሪያው ቅድመ-ሁኔታ እንደሆነ ያወጁት።

አሁንም ቢሆን ይህ ፖሊሲ በተለይም በእርሻው መስክ የተጠበቀውን ውጤት ባለማምጣቱ እነስታሊን በ1928 ዓ.ም በግዴታ ላይ የተመሰረተ የህብረት እርሻ ፕርግራም(Collectivization) በማስፋፋት በተለይም የከተማውን ህዝብ ለመመገብ ጥረት አደረጉ። በዚህ ዐይነቱ የግዳጅ የህብረት ፖሊሲ አማካይነት በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ ቢሞትም፣  በተለይም ከ1930ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ ሶቭየትህብረት በኢንዱስትሪ አብዮት የመረቃ ውጤት በማስገኘትና ከተማዎችን በመገንባት አነሰም በዛም ወደፊት ልትራመድ ችላለች። የምዕራቡ ዓለም የሶቭየትህብረትን ሁለ-ገብ ዕድገት ለመቀልበስ ሲል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰላዮችን በማሰማራቱ ይህ ሁኔታ በስታሊንና በተቀሩት የቦልሺቢኪ መሪዎች መሀከል መጠራጠርንና መጠላላትን አስከተለ። በተለይም እነ ቡሃሪን የመሳሰሉ የኢኮኖሚክስ ምሁራን ለቀቅ ያለ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በመፈለጋቸውና ለዚህም በመከራክራቸው ስታሊን ይህንን ዐይነቱን አመለካከት አብዮቱን እንደመቀልበስ አድርጎ በመመልከቱ ቁጥራቸው የማይታወቁ ምሁራንን ጨረሰ።

ሶቭየትህብረት በኢኮኖሚም ሆነ በሌሎች መስኮች፣ ማለትም በባህልና በከተማዎች ግንባታ ወደፊት ልትገፋ የቻለችው የእነ ሂትለርን ጦር ድል ካደረገችና ሁለ-ገብ የአገር ግንባታ ፖሊሲ ማካሄድ ከጀመረች ወዲህ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ ስንነሳ በሶቭየትህብረትም ሆነ በተቀሩት ተቀጥያ የምስራቅ አውሮፓ አገሮች በአብዮትና በሶሻሊዝም ስም የተካሄደው የግንባታ ፖሊሲ የኢኮኖሚክስ የታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከኋላ የመያዝ(Catching-Up Strategy) የኢንዱስትሪ ተከላ እንቅስቃሴ እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ዐይነቱም ሰፋ ያለ እንቅስቃሴ ሰፊውን ህዝብ ያሳተፈ ሲሆን፣ ቀስ በቀስም ከድህነትና ከረሃብ እንዳላቀቀው የተረጋገጠ ነገር ነው። ስለሆነም በተለይም ከ1950 ዓ.ም ጀምሮ በአብዛኛዎቹ የሶሻሊስት አገሮች ሰፊው ህዝብ የመማር ዕድል ያገኘበት፣ የጤና መስክ የተስፋፋበት፣ ከተማዎች የተገነቡበትና ህዝቡም በንጹህ ቤት ውስጥ እንዲኖር የተደረገበት፣ የስራ መስክ የተረጋገጠበትና ህዝቡም ተከታታይ ገቢ እንዲያገኝ የተደረገበት ዘመን እንደነበር ይታወቃል። ይህ ዐይነቱ የሁለ-ገብ ዕድገት እንቅስቃሴ ደግሞ በጊዜው የታሪክ ግዴታ ነበር ማለት ይቻላል። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሙሉ በሙሉ የመንግስት ቁጥጥር ያለበትና በዕቅድ ይካሄድ የነበረ በመሆኑ ለፈጠራ የሚያመች አልነበረም። ከዚህም በላይ አብዛኛዎቹ የሶሻሊስት አገሮች  ልክ እንደ ምዕራብ አውሮፓ የካፒታሊስት አገሮችና አሜሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥሬ-ሀብትን የሚቀራመቱ ወይም የሚበዘብዙ ስላልነበሩ ወደ ውስጥ ለዕድገት የሚያመቻቸውን የገንዘብም ሆነ የጥሬ-ሀብት እንደልብ ማግኘት አልቻሉም። በዚህም ምክንያት የተነሳ ከሰባና ከሃምሳ ዐመት የሶሻሊስት ኢኮኖሚ ግንባታ ሙከራ በኋላ ወደፊት ሊገፉ አልቻሉም።  በአጠቃላይ ሲታይ የኢኮኖሚ ዕድገትን ታሪክ ስንመረምር በአውሮፓ ምድር ውስጥ ካፒታሊዝም ቀስ በቀስ ተግባራዊ ሊሆንና የበላይነትን ሊቀዳጅ የቻለው ሰፊውን ህዝብ በማንቀሳቀስና በስራ ላይ እንዲሰማራ በማድረግ ከብዙ ጊዜ የሙከራና የልምድ(Trial and Error) ግንባታ በኋላ እንደሆነ ጥናቶች ያረጋግጣሉ። የካፒታሊስት አገሮች በንጹህ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ አማካይነት ብቻ ነው ሊያድጉ ወይም እዚህ ደረጃ ላይ ሊደርሱ የቻሉት የሚለው የተረት ወሬ ነው። ከዚህ በመነሳት የወያኔን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ፖለቲካ እንመልከት።

የህወሃት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምንነት !

ህወሃት ስልጣን ከመያዙ በፊት እ.አ በ1974 ዓ.ም  የታሪክና የህብረተሰብ ግዴታ ሆኖ ደርግ ስልጣንን ከያዘ በኋላ የመሬት ላራሹ ታውጇል፤ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎች፣ ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር እንዲሆኑ ተደርገዋል። እንደሚታወቀው አብዮቱ ከመፈንዳቱ በፊት ከ500 000 ህዝብ በላይ በረሃብ ህይወቱን እንዳጣና፣ ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነውም ህዝባችን ደግሞ በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖር የተገደደ ነበር። አብዛኛው ህዝብ በጎጆ ቤት ውስጥ ሲኖር፣ ለብርድ፣ ለዝናብና ለአውሬ የተጋለጠ ነበር። በአፄ ኃይለስላሴ ዘመን ተግባራዊ የሆነው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ከ5% በታች የሆነውን ህዝብ የጠቀመ ሲሆን፣ ይህ ዐይነቱ የዘመናዊነት ፖሊሲ በአዲስ አበባና በአንዳንድ ከተማዎች ጎልቶ ሲታይ፣ እዚያው በዚያው ደግሞ ድህነትና በሀብት መደለብ ተፋጠው የሚታዩበት ዘመን ነበር። እንደዚሁም፣ በአዲስአበባና በተቀሩት ከተማዎች መሀከል ሰፋ ያለ ዕድገት የሚታይ ሲሆን፣ አብዛኛው ተማሪ አስራሁለተኛን ክፍል ሲጨርስ ወደ አዲስአበባ የሚመጣ እንጂ እዚያው የተወለደበት፣ ያደገበትና የተማረበት ቦታ የስራ ዕድል የሚያገኝ አልነበረም። በቂ ሁለ-ገብ የሆነ የሙያ ማሰልጠኛ መማሪያ ትምህርትቤት ባለመኖሩ፣ በተለይም ዩኒቨርሲቲ ለመግባት የማይችለው አብዛኛው ወጣት ዝም ብሎ የሚንቀዋለል ነበር። ከዚህም ባሻገር በአብዛኛዎቹ የክፍለ-ሀገራት ከተማዎችና ወረዳዎች፣ እንዲሁም የምክትል ወረዳዎች ኋላ-ቀር የሆኑ የአገዛዝ መዋቅሮች በመዘርጋታቸው፣ መስሪያቤቶቹ  ባልተማሩ ሰዎች ይተዳደሩ የነበሩ ናቸው። በየክፍለ-ሀገራቱ የሚገኙት የአስተዳደር መስሪያቤቶች በየአካባቢው የነበረውን የሰውን ኃይልና የተፈጥሮ ሀብትን ለማንቀሳቀስና ዕድገትን ለማምጣት የሚችሉ አልነበሩም። በዚህም ምክንያት አብዮቱ መፈንዳቱ የሚያስገርም አይደለም። ይሁንና ይህ አብዮት በአንድ በኩል በውስጣዊ የአደረጃጀት ድክመትና የሃሳብ አንድነት አለመኖር (Lack of Unity of Thought)፣ በሌላ ወገን ደግሞ አብዮቱን የሚቀናቀኑና ለውጥን የሚጠሉ የውስጥ ኃይሎች ከውጭ ኃይሎች ጋር በማበርና በመተባበር ርብርቦሽ በማድረጋቸው የተፈለገው ለውጥ ሊያመጣ አልቻለም። ትግሉ ዕድገትንና ለውጥን ለማምጣት የሚደረግ ከመሆን ይልቅ ስልጣንን ለመያዝ ከፍተኛ አትኩሮ ስለተሰጠው የመጨረሻ መጨረሻ ወደ ርስበርስ መተላለቅ አመራ። በብዙ ሺህ የሚቆጠር ወጣትና ምሁራዊ ኃይል ህይወቱን እንዲያጣ ተደረገ።

ይህንን ዐይነቱን በቀላሉ ለመግለጽ የሚያስቸግረውን አብዮታዊ ሂደትና የዕድገት ሙከራ ነው የውጭና የውስጥ ኃይሎች ከሶሻሊዝም ጋር በማያያዝ ዘመቻ ማካሄድ የጀመሩት። ወያኔ ወይም ህወሃት የዚህ ዐይነቱ ዘመቻ አካል አንድ የሆነና ከውስጥ ሆኖ በኢምፔሪያሊስት ኃይሎች በመደገፍ የአብዮቱን ውጤቶች ለመቀልበስ የሚታገል ፀረ-ዲሞክራሲና ፀረ-ህዝብ አካል ነበር። ህወሃት ስልጣን ሲይዝ ዋናው ተግባሩም የአብዮቱን ድሎች አይ መቀልበስ ወይም በራሱ ስር በማጠቃለል ራሱን ማደለብ ነበር።  የአብዮቱን ድሎች ለመቀልበስ ደግሞ የግዴታ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና  (IMF) በዓለም ባንክ(World Bank) የተጠናቀረ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ማካሄድ ነበር፤ ነውም። ህወሃትም ስልጣን ሲይዝ ከቀረቡለት ቅድመ-ሁኔታዎች አንዱ ይህንን የዓለም አቀፍ ኮምኒቲው በማቆላበጥ የገበያ ኢኮኖሚ ፖሊሲ እያለ የሚጠራውን ተግባራዊ ማድረግ ነበር።  በፖሊሲው መሰረትም በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩትን ኢንዱስትሪዎች፣ ትላልቅ የንግድ መደብሮች፣ ባንኮችንና የኢንሹራንስ ኩባንያዎችን ወደ ግል ሀብትነት መለወጥ ነበር። ይሁንና ግን ይህ ዐይነቱ በመንግስት ቁጥጥር ስር የነበሩትን የህዝብ ሀብቶች ወደ ግል ሀብትነት ማዘዋወር እዚያው በዚያው የተካሄደና የህወሃት ካድሬዎች ገንዘብ ከባንክ በመበደር የተቀራመቱትና የገዙት ነው። ከዚህ ውስጥ አብዛኛውን ድርሻ የሚይዘው ኢፈርት የሚባለው የእነ መለስ ዜናዊ ትልቁ ኩባንያ ነው።

ከዚህ አልፎ በዚህ ዐይነቱ የፀረ-አብዮት ፖሊሲ እርምጃዎች የአገራችን ብር ከዶላር ጋር ሲወዳደር ዝቅ እንዲል (Devaluation) ይደረጋል። የውጭው ንግድ ልቅ እንዲሆን ይደረጋል። ወደ ውስጥ ደግሞ በዋጋዎች ላይ ይደረግ የነበረው ቁጥጥር ይነሳል። በተጨማሪም ለማህበራዊ መስኮች ይመደብ የነበረው ባጀት ወደ ሌላ ይዛወራል። ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ በመባል ሲታወቅ፣ ዋና አላማውም የገበያን ኢኮኖሚ ተግባራዊ ለማድረግ የሚል ነበር። ከ1980 ዓመታት ጀምሮ ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ በብዙ የአፍሪካ አገሮች፣ በተለይም በጋናና ናይጄሪያ ተግባራዊ ቢሆንም ወደ ውስጥ ሰፋ ያለና ግልጽ የሆነ የገበያ ኢኮኖሚ እንዲገነባ አላስቻለም። በእነዚህ አገሮችና በኢትዮጵያም ጭምር በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ የኢንዱስትሪ ተከላና ሰፋ ያለ የስራ-ክፍፍል ሊካሄድና ሊዳብር አልቻለም። ከተማዎችና መንደሮችም በዕቅድ ሊሰሩና የተተከሉትም ኢንዱስትሪዎች ሰፋ ያለ የስራ መስክ ሊከፍቱና አስተማማኝ ገቢ ሊያስገቡ በፍጹም አልቻሉም። ትናንሽና ማዕከለኛ ኢንዱስትሪዎች እዚህና እዚያ በመተከል ለገበያ ኢኮኖሚ መስፋፋት መሰረት ሊጥሉ አልቻሉም። ይልቁንስ ይህ ዐይነቱ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ለአገልግሎት መስኩ መስፋፋት ነው በር የከፈተው።  ስለሆነም ኢትዮጵያና ሌሎች ይህንን የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ ያደረጉ አገሮች በሙሉ ገንዘባቸው ከዶላር ጋር ሲወዳደር ዝቅ በመደረጉ፣ በአንድ በኩል ከውስጥ ግሽበትን ሲያስፋፋ፣ በሌላ ወገን ደግሞ የንግድ ሚዛናቸው ወደታች በማሽቆልቆል በዕዳ ሊተበተቡ በቅተዋል። በዓለም የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ ግፊት ተግባራዊ የሆነው የገበያ ኢኮኖሚ እነዚህን አገሮች ስርዓት ወዳለውና በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ወደ ተመሰረተ ሁለ-ገብ የኢኮኖሚ አወቃቀር እንዲመሩ አላደረጋቸውም። በተከታታይ ተግባራዊ በሆነው ገንዘብን ዝቅ የማድረግ ፖሊሲ ምክንያት የተነሳ በተለይም የኢትዮጵያ የውጭ ንግድ $ 17 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የንግድ ሚዛን መዛባት ሲደርስበት፣ የውጭ ዕዳዋ ደግሞ ወደ $ 40 ቢሊዮን እንዲተኮስ ተደርጓል። ይህ የውጭ ብድር  ከጠቅላላው አገሪቱ በዓመት ከምታመርተው ምርት $ 69 ቢሊዮን ውስጥ 58% ውን ይይዛል ማለት ነው።  በሌላ አነጋገር፣ በተደጋጋሚ ተግባራዊ የሆነው የፀረ-አብዮታዊ ዲሞክራሲ የኢኮኖሚክ ፖሊሲ አገራችንን የባሰውኑ እያራቆታት ነው ማለት ነው። በዚያው መጠንም  የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ሲሆን፣ በደሃና በሃብታም መሀከል ያለው ልዩነት እየሰፋ እንደመጣ መገንዘብ እንችላለን። በተጨማሪም ይህ ዐይነቱ ሳይንሳዊ ይዘት የሌለው የኢኮኖሚ ፖሊሲ የአገር ሀብት እንዲወድም ያደረገና ከፍተኛ ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀልን ያመጣ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ነው አገዛዙ እስካሁን ድረስ ሲከተል የነበረው።

ከዚህ ስንነሳ የወያኔው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የኢኮኖሚ ፖሊሲ መሰረታዊ የሆኑ የህዝብ ፍላጎቶችን ያሟላና ሊያሟላም የሚችል አይደለም። እንደትላንትናው ዛሬም ከ27 ዓመት በኋላ አብዛኛው ህዝባችን ንፁህ ውሃ የመጠጣትና የማግኘት ዕድል የለውም። በወዳደቁ ቤቶችና ጎጆ ቤቶች ውስጥ ነው የሚኖረው። ትምህርትቤቶች የፈራረሱ ናቸው። ህክምና እንደልብ አይገኝም። አብዛኛዎቹ ከተማዎችና መንደሮች የሰው ልጅ የሚኖርባቸው አይደሉም፤ አይመስሉምም። ሁሉም ከተማዎች በዕቅድ ከረጅም ጊዜ አንፃር ተብለው የታቀዱና የተገነቡ አይደሉም። ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ የሰውን ጤንነት ያቃወሰና የሰውም ኃይል አዲስ ዕውቀት በመገብየት ህብረተሰብአዊ ሀብት እንዳይፈጠር መሰናክል የሆነ ነው። በመሰረቱ የወያኔ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አብዮታዊ የሚያሰኘው ሳይሆን ፀረ-አብዮታዊ ነው። አብዮታዊነቱ ለወያኔ የበላይ ሹማምንቶችና ለካድሬዎቹ ብቻ ነው። ያላቸውን ኃይል በመጠቀም ከፍተኛ ዘረፋ በማካሄድ ሊደልቡ የቻሉበት ሁኔታ ነው በጉልህ የሚታየው። ስለሆነም ይህ ዐይነቱ አብዮት ለእነሱ የተካሄደ እንጂ ለኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም። በመሆኑም ይህ ዐይነቱን በጎሳ የበላይነት ላይ የተመሰረተን የዚያው በዚያው የሀብት ሽግሽግና በሀብት መደለብ ነው አብዮታዊ ዲሞክራሲ እያሉ በመጥራት ትልቅ ወንጀል የሚሰሩትና የሚፈጽሙት። በዚህ መልክ ባለማወቅ ዝም ብለው የሚናፈሱ ፅንሰ-ሃሳቦች በተለይም ታዳጊውን ወጣት በማሳሳት ላይ ይገኛሉ። ከዚህ አልፈን ስንሄድ በህወሃት ዘንድ የፖሊሲ ክርክር ሲካሄድ ሰምተን አናውቅም። በመሀከላቸውም የሀብት ዘረፋንና መደለብን አስመልክቶ ክርክርና ውይይት ተካሂዶ አያውቅም። ዕድገትም በዚህ መልክ ነው የሚገለጸው ብለው ተወያይተው አያውቁም። ከዐመት ዐመት የገንዘብ ቅነሳ ፖሊሲ በማካሄድና የፕላንቴሽን ኢኮኖሚ በማስፋፋት አገሪቱን ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከተዋታል። የአገራችንን ትላልቅ የእርሻ መሬቶች አበባና ሸንኮራ አገዳ እንዲተከልባቸው በማድረግ የካፒታሊስት አገሮችን የባሰ በሀብት ክምችት እንዲደልቡ እያገዙ ነው።  በአንፃሩ ግን ሶቭየትህብረት በሌኒንም ሆነ በስታሊን ጊዜ፣ እንደዚሁም በቻይና የአብዮት ወቅት በእነ ማኦሴቱንግና በዴንግ ሲያዎፒንግ መሀከል የኢኮኖሚ ፖሊሲንም አስመልክቶ የጦፈ ክርክር ይካሄድ ነበር። አብዮትን ያካሄዱና አብዮታዊ ዲሞክራሲን ተግባራዊ ያደረጉ እነዚህ አገሮችና ሌሎች የምስራቅ አውሮፓ አገሮች የአገሮቻቸውን የእርሻ መሬቶች ወደ ፕላንቴሽን ኢኮኖሚ በፍጹም አለወጡም። ስለሆነም ወያኔን የዲሞክራሲያዊ አብዮታዊ መንግስት እያልን ከመጥራት ይልቅ በምዕራቡ ዓለም የሚደገፍ ፋሺሽታዊና ዘራፊ መንግስት እያልን ብንጠራው ለትግል የሚያመች ይሆናል። ከተጨባጩ ሁኔታ ጋር የማይስማማ ፅንሰ-ሃሳብ የምንጠቀምና የምናራግብ ከሆነ የችግሩን ምንጭ ልንረዳ አንችልም ማለት ነው። ዋናውን ችግር ካልተረዳን ደግሞ ፍቱን የሆነ መፍትሄ ማቅረብ አንችልም።  ስለሆነም ስለአንድ ህብረተሰብ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ቀውስ በምናወራበት ጊዜ መሰረታዊ ችግሩን በሚገባ መረዳት ያስፈልጋል። ይህንንም በቲዎሪ በሚገባ መተንተን አለብን፤ ምክንያቱም ካለቲዎሪ ድርጊት ወይም ተግባር ሊኖር አይችልምና።

የህወሃት የልማታዊ መንግስት ይዘት !

በኢኮኖሚክስ ሊትሬቸር ውስጥ ልማታዊ መንግስት(Developmental State) በመባል የሚታወቁት ደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን፣ ሲንጋፖርና ታይዋን ናቸው። ይህ ዐይነቱ የልማታዊ መንግስት የኢኮኖሚ ፖሊሲ ዋናው ዓላማ በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ የውስጥ ገበያን ማስፋፋት ሲሆን፣ ከዚህም ባሻገር ለውጭ ከረንሲ ማግኚያ በማለት ስትራቴጂክ በሆኑ መዋዕለ-ነዋዮች ላይ መረባረብ ነበር። በተለይም የጃፓንና የደቡብ ኮሪያ አገዛዞች በመንግስት፣ በትላልቅ ኢንዱስትሪዎችና  በባንኮች መሀከል መደጋገፍ እንዲኖር በማድረግ፣ ከውስጥ የኢኮኖሚውን ዕድገት በማፋጠን ቀስ በቀስ ደግሞ በኤሌክትሮኒክስ፣ በመኪናና በብረታ ብረት ምርቶች መንጠቀው በመሄድ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነትና ከጥገኝነት በመላቀቅ ወደ ውጭ ደግሞ ሊከበሩ በቅተዋል። የመንግስትም ሚና ጥቂት ሰዎችን ማደለብ ሳይሆን ከውስጥ የተሰተካከለ ዕድገትን በማምጣት ኢኮኖሚው ብሄራዊ ባህርይ እንዲኖረው ማድረግና በጠንካራ መሰረት ላይ እንዲንቀሳቀስ ማድረግ ነው። ስለሆነም ለዚህ ዐይነቱ  በመንግስት የተደገፈ ሁለ-ገብ ዕድገት ሳይንስና ቴክኖሎጂ ቁልፍ ቦታ ሲኖራቸው፣ ይህ ዐይነቱ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ዕድገት ሁለ-ገብ በሆነ ልዩ ዕውቀት የተደገፈ ነው።

ይህ ዐይነቱ በመንግስት የተደገፈ የልማት ፖሊሲ የኒዎ-ሊበራልን የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚቃወምና፣ መንግስታቱም አንድም ጊዜ ይህንን ዐይነቱን ሀብት አውዳሚና በዕዳ ተብታቢ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በፍጹም ተግባራዊ አላደረጉም። በተጨማሪም የውጭ ንግዳቸውን በመቆጣጠር ኢንዱስትሪዎቻቸው እንዲያድጉ የዕገዳ ፖሊሲ(Protectionism) ያካሂዱ ነበር፤ አሁንም ያካሂዳሉ። በተለይም ጃፓን የእርሻ መስኳን በከፍተኛ ደረጃ ትከላከላለች። እንደዚህ ዐይነቱ በመንግስት የተደገፈ የኢኮኖሚ ፖሊሲ በ17ኛው ፣ በ19ኛውና በ20ኛው ክፍለ-ዘመን በተለያዩ የአውሮፓ አገሮችና አሜሪካንም ጭምር በሌላ መልክ ተካሂዷል። የምዕራብ አውሮፓ አገሮች በመንግስታት የተደገፈ ሁለ-ገብ የኢኮኖሚና የአገር ግንባታ ፖሊሲ ባያካሂዱ ኖሮ የኋላ ኋላ የገበያ ኢኮኖሚ የሚባለው መዳበር ባልቻለ ነበር። በታሪክ ውስጥ መንግስት ጣልቃ ሳይገባበት በግለሰብ ተሳትፎ ብቻ ያደገ የካፒታሊስት አገር ኢኮኖሚ የለም። የመንግስት ጣልቃ-ገብነት በተለይም ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ ጎልቶ የወጣበት ዘመን ሲሆን፣ እንደ ጀርመን የመሳሰሉት በጦርነቱ ከ80% በላይ ኢኮኖሚያቸውና ከተማዎቻቸው የወደሙባቸው አገሮች በመንግስት በተደገፈ ፖሊሲና በልዩ የብድር ሲስተም (Credit System) በመመካት ነው በ15 ዓመት ጊዜ ውስጥ ከተማዎችን እንደገና መገንባት የቻሉት፤ ኢንዱስትሪዎቻቸውንም በመጠጋገን ሰፊ የስራ መስክ መክፈት የቻሉት። በዚህ መሰረት ቀስ በቀስ በሁሉም አቅጣጫ የውስጥ ገበያን ሲያስፋፉ፣ በሁሉም የፌዴራል ግዛቶች ውስጥ የተስተካከለ ዕድገት ሊስፋፋና ሊዳብር ቻለ። በተለይም ትላልቅ የሳይንስና የቴክኖሎጂ የምርምር ጣቢያዎች በመንግስት የሚደጎሙ ሲሆኑ፣ ትላልቅ ኢንዱስትሪዎችም ለቴክኖሎጂ ምርምር የበኩላቸውን ገንዘብ ይመድባሉ። ስለሆነም ልማታዊ የመንግስት ፖሊሲ በተለያዩ አገሮች በተለያየ መልክ የተካሄደና የሚካሄድም ነው። በተለይም ወደ ኋላ በቀሩ እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገሮች በመንግስት የተደገፈ ሁለ-ገብ ፖሊሲ ማካሄዱ ኢኮኖሚዊና ታሪካዊ ግዴታ ነው። ይህ ካልሆነ አገራችን የማደግ ዕድሏ የመነመነ ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አገርና ህብረተሰብ የመኖር ዕድሏ እየተበላሸ ይሄዳል። ይህ በራሱ ደግሞ ማህበራዊ ውዝግብንና የእርስ በርስ ጦርነትን ያስከትላል። ስለሆነም ሰፋ ያለ ሁለ-ገብ የአገር ግንባታ ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ አማራጭ የሌለው ፖሊሲ ነው ማለት ይቻላል።

ወደ ወያኔው የልማታዊ መንግስት ፖሊሲ ስንመጣ ላይ ለማብራራት እንደሞከርኩት የተፈጥሮንና የህብረተሰብን ህግ የሚፃረር ነው። ለዘረፋ የሚያመችና ጥቂቶችን የሚያደልብ ነው። ከጥገኝነትና ከለማኝነት የሚያላቅቅ አይደለም። ያልተስተካከለ ዕድገትና ዝርክርክነት ስር እንዲሰዱ ያደረገና የሚያደርግ ነው። ሰፋ ያለ በማኑፋክቱር ላይ የተመሰረተ የስራ-ክፍፍል እንዳይዳብር ያደረገና የሚያደርግ ነው። በኢንዱስትሪዎች መሀከል በአንድ በኩል፣ በሌላ ወገን ደግሞ በኢንዱስትሪዎችና በተቀሩት የኢኮኖሚ መስኮች መሀከል መተሳሰር( Linkages or Value-added chain) እንዳይኖር ያደረገና የሚያደርግ ነው።  ስለሆነም ስራ ለሚፈልገው ሰፊው ህዝብ የስራ መስክ ሊከፍት ያልቻለና የሚችልም አይደለም። የወያኔ ልማታዊ የመንግስት ፖሊሲ እንደሰሊጥ፣ ኑግ፣ ተልባና ሌሎችም የዘይት ጥራጥሬዎች በአገር ውስጥ እየተጨመቁና እየታሸጉ ለህዝቡ እንዲዳረሱ የሚያደርግ አይደለም። በተቃራኒው ግን  እነዚህ የዘይት ቅባት እህሎች በጥሬ መልካቸው ወደውጭ በመላክ ሀብት እንዲወድም  ሊደረግ በቅቷል። በዚያው መጠንም አገዛዙ ከውጭ አገር ጤንነት የሚያቃውስ ዘይት እያመጣ በመሸጥ የውጭው ንግድ ሚዛን እንዲዛባ አድርጓል ። ይህንን ዘርፍና እጣንን፣ እንዲሁም ቡናና ሻይን የወያኔ ካድሬዎችና ኢፈርት የሚቆጣጠሩት ናቸው።

ከዚህ ስንነሳ የወያኔን የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚ ፖሊሲ የልማታዊ መንግስት ፖሊሲ እያሉ መጥራት አላዋቂነት ብቻ ሳይሆን፣ ከፍተኛ ወንጀልም እንደመስራት ይቆጠራል። ከዛሬ  ጀምሮ በኢትዮጵያ ህዝብ ጎን ቆሜያለሁ፣ ለዲሞክራሲ እታገላለሁ የሚል ሁሉ የወያኔን አገር አፍራሽ ፖሊሲ ልማታዊ እያለ መጥራት አይገባውም። ከዚህ ስህተት መቆጠብ አለብን። ዝምብለን ሳናውቅ የምናራግበው መፈክር ግልጽ ለሆነ ፖሊሲ የሚያመች አይደለም። ወደፊት ሰፊውን ህዝብ የሚጠቅም በሳይንስ ላይ የተመሰረተ ሁለ-ገብ የሆነና ድህነትንና ረሃብን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ የሚያወድም ፖሊሲ ተግባራዊ እንዳይሆን የሚያግድ ነው። በዚህ ላይ መስማማት ካለ ኢኮኖሚክስ የሚለውን መሰረተ-ሃሳብ በመጠኑም ቢሆን ላብራራ። ስለኢኮኖሚክስ ምንነት ግልጽ ሲሆን ብቻ ነው ስለኢኮኖሚ ዕድገት ወይም ስለልማት ማውራት የሚቻለው።

ኢኮኖሚክስ ማለት ምን ማለት ነው ?

በአገራችን የተልምዶ አጠራር ኢኮኖሚክስ ማለት የምጣኔ ሀብት ትምህርት ማለት ነው። የታወቀው የግሪክ ፈላስፋ አርስቲቶለስ ደግሞ ኢኮኖሚክስ ማለት የቤተሰብ ማስተዳደሪያ( Household Management) እያለ ይጠራዋል። በአገራችን የተለመደው አጠራር ስለኢኮኖሚክስ የተሟላ ነገር ሊነግረን በፍጹም አይችልም። በሌላ ወገን ግን አርስቲቶለስ ኢኮኖሚክስን የቤተሰብ ማስተዳደሪያ ዘዴ ነው ብሎ ቢጠራው የሚያስገርም አይደለም። በጊዜው የግሪክ ህዝብ በተለይም በከተማዎች ውስጥ ይኖር የነበረው እንደዛሬው ሰፋ ባለመልክ የሚገለጽ የህብረተሰብ አወቃቀር አልነበረውም። አብዛኛው የኢኮኖሚ ክንዋኔ በትናንሽ መስክ የሚካሄድ ስለነበር ሰፋ ያለ የገበያ ኢኮኖሚ የዳበረበት ዘመን አልነበረም። ይሁንና አርስቲቶለስም ሆነ ፕላቶ ስለንግድ ልውውጥ፣ ስለስራ-ክፍፍልና ስለገንዘብ ምንነትና አስፈላጊነት በሰፊው አትተዋል። የእነዚህንንም ትርጉምና በአንድ አገር ውስጥም ሰለሚኖራቸው የዕድገት ሚናና ለህብረተሰብ መተሳሰር አስፈላጊ እንደሆኑ በሚገባ አብራርተዋል።

አገሮች ቀስ በቀስ ወደ ህብረ-ብሄር ሲሸጋገሩና ማዕከላዊ መንግስታት ሲቋቋሙ ይታወቅ የነበረው ኢኮኖሚክስ ሳይሆን ፖለቲካል ኢኮኖሚ በመባል ነው። ይህም ማለት ከፖለቲካ ጋር የተያያዘና የአንድን ህዝብ ዕድል መወሰኛ ዘዴ በመሆኑ ነው። ስለሆነም ስለኢኮኖሚክስ ሲወራ ስለብሄራዊ ኢኮኖሚ ማውራት እንጂ በጠያቂና በአቅራቢ መሀከል የሚገለጽ አልነበረም። በተለይም በጀርመን ምድር በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰጠው የኢኮኖሚክስ ትምህርት እንደ አሜሪካንና እንግሊዝ ኢኮኖሚክስ እየተባለ የሚጠራ ሳይሆን ብሄራዊ ኢኮኖሚ(National Economy) እየተባለ ነው። በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ-ዘመን በጀርመን ምድር ፍልስፍናና የህብረተሰብ ሳይንስ በሰፊው በመስፋፋታቸው በጊዜው የተነሱት ምሁራን ኢኮኖሚን ከማህበራዊና ከብሄራዊ ባህርይው ነጥለው አያዩትም ነበር። በእነሱም ዕምነት የኢኮኖሚ ዕድገት የማህበራዊ ጥያቄዎችንም(The Social Question) የሚያካትትና የሚፈታ መሆን አለበት። እነ አዳም ስሚዝም ቢሆኑ ስለ ስራ-ክፍፍል አስፈላጊነት፣ ስለማሺነሪና ሰለሰፊ ገበያ በማተት ኢኮኖሚ  ብሄራዊ ባህርይ እንዳለው ለየት ባለመልክ ሊገልጹ ችለዋል። በመሀከላቸው ያለው ልዩነት ግን ነፃ ንግድ በሚለውና ልቅ የገበያ ኢኮኖሚ መስፋፋት የለበትም ወይም አለበት በሚለው ላይ ነው። በ18ኛውና በ19ኛው ክፍለ-ዘመን ብቅ ያሉት የጀርመን ፈላስፎችና ሳይንቲስቶች የአንድን ህብረተሰብ ዕድገት ይመለከቱ የነበረው በተናጠል ሳይሆን ሁለንታዊ በሆነ መልክ ስለነበር እንደዚህ ዐይነት የመንግስትን ሚና አጉልቶ የሚያሳይ የኢኮኖሚ ፖሊሲና የህብረተሰብ ግንባታ አካሄድ ቅድሚያ መስጠታቸውና መሆንም እንዳለበት ማመልከታቸውና ማስተማራቸው የሚገርም አይደለም።

የኢኮኖሚክስ ፅንሰ-ሃሳብ እየተኮላሸ የመጣው የኒዎ-ክላሲካልስ ወይም የኒዎ-ሊበራል ምሁሮች ከ19ኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ ፅንሰ-ሃሳቡን እያዛነፉ በመምጣታቸው ነው። በእነሱ ዕምነትም፣ የተመጠነ ሀብት ተግባራዊ የሚሆንበት(The Allocation of Scarce Resources)፣ የአቅራቢና የጠያቂ ጉዳይ(Supply and Demand) የፍጆታ ጉዳይ፣ አንድን ተመጥኖ የሚገኝ ሀብት አማራጭ በሆኑ ወይም በሚያዋጣ ነገር ላይ ማዋል፣ የመሳሰሉትን በማስፋፋትና የትምህርት ቤት ኢኮኖሚክስ ሊትሬቸሮችን በማጣበብ ከሳይንሳዊ ባህርይው ተነጥሎ እንዲታይ አድርገውታል። ስለሆነም ኢኮኖሚክስና ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ በማሰብ ኃይልና አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅ የሚዳብር ሳይሆን ከላይ በተገለጹት መልኮች ብቻ ነው። ከዚህም በላይ ይህ ዐይነት የኢኮኖሚክስ ፅንሰ-ሃሳብ ስለኢንስቲቱሽን አስፈላጊነትና ስለፈጠራ(Innovation)፣ እንዲሁም ስለህብረተሰባዊ አደረጃጀት በፍጹም አያወራም። ማንኛውም ኢኮኖሚያዊ ክንዋኔ በግለሰቦች መሀከል የሚካሄድ(Methodological Individualism) ሲሆን፣ ህብረተሰብአዊ ባህርይ የለውም። አንድ አገር የየግለሰቦች ድምር ውጤት እንጂ፣ እንደማህበረሰብና ህብረተሰብ የሚታይ አይደለም። እያንዳንዱ ግለሰብ በራሱ ዓለምና ለራሱ ብቻ የሚኖር ነው። ይህ ዐይነቱ የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ በተለይም ከ20ኛው ክፍለ-ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ በማቲማቲክስ እያሸበረቀ በመምጣቱ፣ አንዳንድ የኢኮኖሚክስ ምሁራንና እንደ ሚሮቭስኪ የመሳሰሉት የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪዎች ይህ ዐይነቱ አካሄድ የማቲማቲክስን ችግር ለመፍታት የሚደረግ ጥረት እንጂ የአንድን ህብረተሰብ ችግር ሊፈታ እንደማይችል አረጋግጠዋል። ሰልሆነም በኒዎ-ክላሲካል ኢኮኖሚክስ ምሁሮች ዕምነት ኢኮኖሚክስ ከሳይንስና ከቴክኖሎጂ፣ እንዲህም ከምርት ክንዋኔ ጋር የሚያያዝ ሳይሆን፣ በንጹህ መልኩ ከንግድና ከፍጆታ ጋር ብቻ የሚያያዝ ነው። በንጹህ መልኩም የአንድን ሰው በፍጆታ መርካትንና፣ በሌላ ወገን ደግሞ በምርት ክንውን ውስጥ የሚሳተፈው ባለሀብት ትርፍን ለማትረፍ የተቻለውን ሁሉ የሚያደርግ ነው።  ይህ ዐይነቱ አገላለጽ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደቫይረስ በመስፋፋቱ በተለይም በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ድህነትና መዝረክረክ የሚስፋፋበት መሳሪያ ሊሆን በቅቷል። በየአገሮቹ ውስጥ የተትረፈረፈ የተፈጥሮ ሀብት እያለ ይህንን በማውጣትና በመለወጥ ወይም በማምረት ለመጠቀም ያልተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በተለይም ዶላርና ኦይሮ የዓለም አቀፍ የንግድ ልውውጥና የሀብት ማከማቻ መሳሪያዎች(Exchange and Reserve Currency) ናቸው ተብሎ ተቀባይነት በማግኘታቸው ብዙ አገሮች ኢኮኖሚያቸውን ካለዶላርና ካለኦይሮ ማሳደግ የማይችሉ እየመሰላቸው የባሰ የዕዳ ወጥመድ ውስጥ በመግባት ህዝቦቻቸውን እያደኸዩና ኋላ-ቀርነት ስር እንዲሰድ እያደረጉ ነው። በሌላ ወገን ግን ስልጣኔዎች በሙሉ ሊስፋፏና ሊዳብሩ የቻሉት ካለዶላርና ካለኦይሮ ነው። የግብጽ፣ የግሪክ፣ የሮማውያንና የቻይና ስልጣኔዎች በሙሉ ዕውን የሆኑት በሰው የማሰብ ኃይልና ስራ ብቻ ነው። በመሆኑም በታላላቅ ፈላስፋዎችና ኢኮኖሚስቶች ምርምር መሰረት ማለትም በፊዞክራቶች፣ በመርካንትሊስት የኢኮኖሚ ምሁራን፣ በክላሲካል ኢኮኖሚስቶችና በካርል ማርክስም ጭምር የሰው ልጅ ጉልበትና የተፈጥሮ ሀብት ብቻ ናቸው ዋናው የሀብት ወይም የዕድገት ምንጮች። ገንዘብ ይህንን ሁኔታ ለማመቻቸት የሚውል መሳሪያ ብቻ ነው። ገንዘብም ራሱ የሰራ-ክፍፍልና የገበያ ዕድገት መዳበር ውጤት እንጂ በራሱ ለዕድገት ቅድመ-ሁኔታ አይደለም።

ወደ ዋናው መሰረተ-ሃስብ ስንመጣ ኢክኖሚክስ ማለት ሌላ ነገር ሳይሆን አንድን ነገር በሰው ጉልበት፣ በማሽንና በኃይል(Energy) አማካይነት መለወጥ ማለት ነው። በሌላ አነጋገር፣ ማንኛውም የጥሬ ሀብት ጠቀሜታ ላይ ከመዋሉ በፊት ካለበት ሁኔታ ወደ ሌላ ነገር መለወጥ አለበት። ለምሳሌ ብረትን ከማግኘታችን በፊት በእሳትና በማሽን አማካይነት ማቅለጥ አለብን። እንዲሁም በማሽን አማካይነት የተለያየ ቅርጽ በመስጠት የምርት መሳሪያዎችን ለመስራት እንችላለን። ሌሎች የጥሬ-ሀብትና እህሎችም በዚህ ዐይነት የክንውን ዘዴ ነው ለጠቀሜታ የሚውሉት። ሌላ ምስጢር የላቸውም። ይህም ማለት ኢኮኖሚክስ ካለሳይንሳዊ ምርምር፣ ካለቴክኖሎጂና ካለምርት ክንዋኔ ሊታሰብ በፍጹም አይችልም። ኢኮኖሚክስም ከጠቅላላው ከአንድ አገር ዕድገት ጋር የሚያያዝ ሲሆን፣ የአንድ አገር ጥንካሬና ድክመት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ ተመስርቶ በሚካሄድና፣ ሳይንሰ-አልባ በሆነ መልክ በሚገለጽ ተራ የሸቀጣ ሸቀጥ ኢኮኖሚክስ አማካይነት ነው። በሌላ አነጋገር ኢኮኖሚክስን ከፖለቲካ፣ ከማህበረሰብ፣ ከባህል፣ ከሳይንስ፣ ከቴክኖሎጂ፣ ከማኑፋክቱርና ከማሽን ነጥሎ ማየት እጅግ አደገኛ ነው። አንድ አገር በባህል ልትበለጽግ የምትችለውና ውብ ውብ ከተማዎችንና መንደሮችን መገንባት የምትችለው ኢኮኖሚክስ በሁለመንታዊ ጉኑ ከታየ ብቻ ነው። ስለሆነም የኒዎ-ክላሲካልና የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚክስ ፖሊሲዎች በሙሉ ይህንን ዐይነቱን ሁለ-ገብ የሆነ የአገር ግንባታ ዘዴ የሚጻረሩ ናቸው ። ስለዚህ ነው በአገራችን ምድር ባለፉት ስድሳ ዐመታት ድህነትና ረሃብ እየተስፋፉ የመጡት። በዚህ ዐይነቱ አካሄድ ነው ዕውነተኛ ብሄራዊ ሀብት መፍጠርና አገርን ሁለ-ገብ በሆነ መልክ መገንባት ያልተቻለው።  የአገርንም የሰውን ጉልበትና የጥሬሀብቶችን በስርዓት መጠቀም ያልተቻለው አገዛዞቻችን የተሳሳተ የኢኮኖሚክስ ፖሊሲ በመከተላቸው ነው። ከዚህ ስንነሳ አገራችንን በፀና መሰረት ላይ መገንባት ከፈለግናና ለተከታታዩም ትውልድ የሚመካበት ነገር ጥለን ለመሄድ ከፈለግን ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክና በአጠቃላይ ሲታይ ከዓለም ኮምኒቲው የኒዎ-ሊበራል የኢኮኖሚክስ ፖሊሲ መላቀቅ አለብን። መልካም ግንዛቤ !!

fekadubkele@gmx.de

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here