Home News and Views አገር በአማርኛ! (ስሜታዊ ጽሁፍ)-ደረጀ ደስታ (ሊያነቡት የሚገባ)

አገር በአማርኛ! (ስሜታዊ ጽሁፍ)-ደረጀ ደስታ (ሊያነቡት የሚገባ)

 

አማርኛ ጥሩ ነገር ነው። “አማራ አለ ወይስ የለም?” የሚያስብል የመከራከሪያ ቋንቋ ነው። እኛ እንቶኔዎች አማሮች እንዴት እንደጨቆኑን የምንናገረው በአማርኛ ነው። እኛ ጎንደሮች ከጎጃሞች ስለመሻላችን ጎጃሞችም ከጎንደሮች ስለመብለጣችን ወሎዬዎች ስለቁንጅናችን… የምናወራው በአማርኛ ነው። ሸዋ “ምነው ሸዋ!” የሚለው በአማርኛ ነው። ጉራጌም አማራን የሚያቄለው በአማርኛ ነው። አዲስ አበባም አማርኛ ናት። ኦሮሞው ደራሲ በአማርኛ የጻፈው ሥነጸሁፍና የተቀኘው ቅኔ ለአማራው አማርኛ ማስተማሪያ ይሆናል። የትግሬውና ኤርትሬው መለስ ዜናዊ “ራዕይ” የተገለጠው በአማርኛ ነው። መለስ ከጠመንጃቸው በላይ ኢትዮጵያን የገዙት በአማርኛቸው ጭምር መሆኑን በአማርኛ መከራከር ይቻላል። በትግርኛ ሞተው በአማርኛ ተለቀሰላቸው። ኤርትሬዎቹም ከአማርኛ ቢገነጠሉም አማርኛ ከነሱ አልተገነጠለም። ይኸው ቴዲ አፍሮ አዲስ አበባ ተቀምጦ አስመራ ላይ ይዘፍናል። አማራ ይጠላሉ የሚባሉት ስብሐት ነጋ እንኳ “አማራ ገዢ መደብ” የሚሉትን ለመዋጋት ጫካ ከመሄዳቸው በፊት ሸዋ ወርደው፣ ሰላሌና ደብረብርሃን ላይ የአማርኛ አስተማሪ ነበሩ። አስተማሪው ትግሬ፣ ተማሪው ኦሮሞ፣ ትምህርቱ አማርኛ። አይ ይቺ አገር….!

አማርኛ የሁሉም የአፍ መፍቻ ቋንቋ ቢሆን ኖሮ፣ ማይሙም ማይም፣ ሊቁም ሊቅ መሆኑ ይለይ ነበር። አማርኛ አስተካክሎ መናገር የማይችል የእንቶኔ ብሔረሰብ ተወላጅ የሆነ ፕሮፈሰር፣ አፉን በአማርኛ ካልፈታ ማይም መስሎ ይታያል። አማርኛን የሚያቀላጣጥፈውና በአማርኛ ጥበብን ሳይሆን አፉን ብቻ የፈታ ጉግማንጉግ ሁሉ እየተነሳ፣ ተኮፍሶ ሊቅ መምሰሉም ስለ አማርኛው ነው። የአማርኛ ደካማ ጎኑ ይህ ነው። የሌላው ብሔረሰብ ሰው በቋንቋው በመናገሩ ብቻ ጎሰኛ መስሎ ሲታይ፣ አማርኛ ስር የተሸሸገው ምድረ መንደርተኛ ጎሰኛና ክፍለሀገርተኛ ግን አማርኛው ደብቆለት አያስታውቅበትም። አማርኛ ብቻውን ኢትዮጵያዊነት የሆናቸው ግብዞች እንዳሉ ሁሉ ሌላው ቋንቋ ባዕድ ያደረጋቸው ኢትዮጵያውያንም የሉም ማለት አይቻልም። ይቺ ስቃይ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖሯን አማርኛ አይሸሽግም። አንድ ምሁር ከየትኛውም ዩኒቨርስቲ ዲግሪ ቢኖረው የትኛውንም ችሎታና ተሰጥኦው ቢቸረው አማርኛ ከጎደለው ምናምኒት እንደጎደለው ተደርጎ መወሰዱ ግልጽና አለመታደል ነው። አማርኛኮ በራሱ ቋንቋ ነው እንጂ እውቀት አይደለም።

ዛሬ እንዲህ ጥንቡን ሊጥል “አቤት እገሌ እንዴት ያለ አዋቂ ነው ፣የሚናገረው እንግሊዝኛ እኮ..!” ይባል ነበር ድሮ። እንግሊዝኛ ብቻውን እውቀት በመሰለበት ዘመን ስንት ሰው በእንግሊዝኛ ለመናደድ ይጣደፍ ነበር። አማርኛም ብቻውን እውቀት፣ አንዳንዴም አልፎ ተርፎ ኢትዮጵያዊነት እየመሰለ ስንቱን አጃጅሏል። አሜሪካን አገር እንግሊዝኛ መልመድ ግዴታ ባይሆን እንኳ አስፈላጊ ነገር ነው። የእንግሊዝኛው እንግሊዝኝነት ግን እንደ ቋንቋ እንጂ እንደ አሜሪካዊነት አይታሰብም። አማርኛም እንደ ቋንቋነት እንጂ እንደ ኢትዮጵያዊነት መታሰብ አልነበረበትም። በእንግሊዝኛ አፉን ያልፈታ አሜሪካዊ ብዙ ነው። ወላጆቹ ከሜክስኮ ከቻይና ወይ ኮሪያና ሶሪያ ሊሆኑ ይችላሉ። ጥልያንም ህንድም አይሁድም ቢሆኑም ያው ነው። አሜሪካዊነታቸው ላይ አይደራደሩም። እንግሊዝኛ እንደሚያስፈልጋቸው ያውቁታል። ቋንቋው አስተሳሳሪያቸው ነው። ስለዚህ ራሳቸው የልጆቻቸው አፍ መፍቻ ያደርጉታል።

ምነው ለኛም እንዲሁ በሆነ!
አማርኛ መቻል ወይም አለመቻል የነጻ አውጭ ብዛት ሲቀፈቅፍብን ከሚያድር በአንድ ስሙ ሁሉም አፉን ቢፈታበት የታሰርነበት የገመድ ይፈታ ነበር። አማራው በሌለበት ትግሬውና ኦሮሞው ተቀምጠው አማራውን የሚያሙበት ቋንቋ መሆኑ የግድ ከሆነ በአንድ ስሙ አማርኛን ከዳር እስከዳር የኢትዮጵያ ቋንቋ አድርጎ (ለነገሩ አሁንም ድርቅና ነው እንጂ አይተናነስም) የሚገላገሉትን ወዲያ መገላገል ነበር። ምንም አይሰራም ይሄ የቋንቋ ብዛት የአሳብ ጥራት አያመጣም። ሁለት አማሮች እንኳ በአንድ አማርኛ እየተነጋገሩ መግባባት አልቻሉም። ብሔራዊ ቋንቋችንም ራሱ ወይ ይዘነው አልያዝነው ወይ ጥለነው አልጣልነው ሆኖብን ይሄው እየተግባባንበት አይደለም። 70ና 80 ቋንቋን ግን ኮተት ነው። የማንነት ኮተት! ለአንዲት ድሃ አገር ይህ ሁሉ ኮተት መዘዙ ብዙ ነው። ሁሉንም ላበልጽገው ቢሉት ብዙ ነገርና ብዙ ገንዘብ ይመዘዝበታል። የበላይነትና የበታችነት ስሜት እየፈጠረ ገዛሁ ተገዛሁ ኮራሁ ተናቅሁ የሚል ንጭንጭ ያበዛል። ሳር ቅጠሉ እየተነሳ ነጻ አውጪ ይሆንበታል። ኢትዮጵያኮ ከምትሰጠው ነጻነት የምትጠየቀው ነጻነት ይበልጣል። የገንዘብ ደሃ ብቻ ሳትሆን የነጻነትም ድሃ ናት። የማትሰጠውኮ ስላልፈለገች ብቻ ሳይሆን ስለሌላት ነው። ለስንቱ ስጥታ ትችላለች። አንዱ ቋንቋዬን አንዱ ሃይማኖቴን አንዱ ጾታዬን አንዱ ክልሌን….አቤት የተነጫናጩ ብዛት! ቡድን እንደጉንዳን እሚርመሰመስባት አገር ውስጥ የቡድን መብት ሰጠው እማይጨርሱት ነስተው እማያስቀሩት አጓጉል ነቀርሳ ነው። ፍልስፍናው ቢጣፍጥ ተግባሩ ይኮምጠጣል። አማርኛ ግን ቡድን ሳይሆን ቋንቋ ነው።

ስለዚህ ወይ አማርኛን ውደዱ ወይ ሌላ ቋንቋ ውለዱ…በቃ! ምነው እነ መንግሥቱ፣ እነ መለስ፣ አምባገነን መሆናቸው ካልቀረ ይህን ውለታ የጣሉልን አምባገነኖች ቢሆኑ ጥሩ ነበር። ወዲያ ሁልሽንም ጠራርጎ ወይ አማርኛን፣ ወይም ኦሮምኛን ከሆንልንም ትግርኛን ወይም አዲስ ቋንቋን ቢሆን ፈልስፎ ጎንፋጎኛን፣ ወይ አዶርባኛን የኢትዮጵያ ቋንቋ አድርጎ፣ በቃ አዳሜ አርፈሽ አንድ ቋንቋ ተናገሪ! ካሁን በኋላ ፊትሽን ወደሚጠቅምሽ ልማት ምናምንሽ አዙሪ ነጭናጫ ሁላ!… ማለት ቢችሉ ደግ ነበር። ከስለት ሁሉ ያጠፋሁት እንዲህ ያለውን ስልጣን ስጠኝ ብዬ አለመሳሌ ነው። እውነቴንኮ ነው አሁን አንድ ቋንቋ ካላግባባን ሺ ልሳን ምን ያደርግልናል? “ኑ እንውረድ አንዱ ያንዱን ነገር እንዳይሰማ ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው…. “ በሚል እግዜር የባቢሎኖችን ቋንቋ እንደደባለቀው እኛም ነገር እየተደበላለቀብን እንዳይሆን። ማንነት ተደባልቆብናል!

አማርኛ በደቡብ ብሄራዊ ቋንቋ ነው። አማሮች ግን ከደቡብ ተባረው ወጥተዋል። በምዕራብ ደሞ ቋንቋው ሌላው ነው- ግን እዚያም ተነቅለዋል። ጓንጉል ከቤንሻንጉል እየተባረረ ሲነቀል ትዕዛዙ በአማርኛ ነው። አማርኛን ወዶ አማራውን መጥላት በአማርኛ እንዴት ተብሎ ይገለጻል? ብልጦቹ ግን አሁን ገብቷቸዋል። አማራን በአማርኛ እየተዋጉ አማራ ይመካበታል የሚሉትን መገለጫዎቹን እየወሰዱ ቀዳዳዎቻቸውን እየደፈኑበት (እየጣፉበት) ነው። አንድነታውያን የሚሏቸውን አክራሪዎች አክርረው እየከረከሩ፣ እነሱ አንድነታውያን፣ ባንዲራውያን፣ ዳር ድንበራውያን፣ አባይና ግድባውያን እየሆኑ ነው። ፣ አማርኛ ጫካ ሆነው የሚዋጉት፣ ቤተመንግሥት ሲገቡ ደግሞ የሚሞቱለት ቋንቋ መሆኑም እየታየ ይመስላል።

የአማራው ገዢ መደብ የተባለውም አማራ ቢሆን አማራውን ሲመጠውና ሲግጠው ኖረ እንጂ መደብነቱን ለአማራው አላሳየም። አማርኛም አማራውን ከሞፈር ቀንበር አልገላገለውም። ያው እንደሌላው ብሄረሰብ ሁሉ አማራውም ዱቄት ሆኖ በሌሎቹ አመድነት እንዲስቅ ለአጓጉል የፖለቲካ ብሽሽቅ ሲዳረግ ኖረ። አማራም ትግሬም ኦሮሞም የተባለች ሁላ ወደ ሥልጣን ስትመጣ ሁሏም አማርኛን ማቀላጠፍ ኢትዮጵያዊነትን በአማርኛ መዘመር ትጀምራለች።

ይልቅ ይህን ጅልነት ወዲያ ትቶ 80ውን ቋንቋ ወዲያ ጨፋላልቆና አቅልጦ አንድ አለት የሚወጣው ወርቅ ማውጣት ፈውስ በሆነ ነበር። የግድ አማርኛ መሆን አይገባውም። ሸኮቾም ሞርቾም ጋጎም ዳዳም ይሁን ብቻ ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርገን አንድ ቋንቋ ተጠንቶና ተመርጦ ቢወጣ ሁሉም ሰው እሱን አጥንቶ አገር አንድ ልሳን ይኖራት ነበር። ካልሆነ ግን አማርኛን እየወደዱ አማሮችን እየጠሉ ፖለቲካ ለገዢም ሆነ ተገዢ ማስቸገሩ አይቀርም። ቋንቋ ሁሉ እኮ ዝምብሎ አፍ ስለተፈታበት ወንዝ አያሻግርም። ጥበብ፣ እውቀት፣ ሳይንስ፣ ታሪክ፣ ፖለቲካና ነገረ መለኮት ካልተፈታበት አንደኛ ክፍል ላይ የተፈታው አፍ፣ ሶስተኛ ክፍል ላይ መልሶ መያዝ መለጎሙ አይቀርም። ሆኖም እያየነው ነው። ስለሆነም ሁሉም ሰው አፉን በአማርኛ ቢፈታ፣ ይሄ ሁሉም እየተነሳ የሚነጫነጭበት አማራም እረፍት ያገኝ ነበር። አማርኛውን አስረክቦ አማራ ብቻ ሆነ የቀረ ምስኪን አማራ! ደሞ እነዚህ የአማራ ገዢ መደቦች እንዳይሰሙና ይነግዱበት ዘንድ እንዳይነሱ! የወያኔው ጦስ ለትግሬው የኦነግም ለኦሮሞው እንደደረሰው የአማራውም ገዢ መደብ ለአማራው እየተረፈ ነው። ፕሮፌሰር መስፍን አማራ የለም ያሉት አለነገር አይደለም። በዚያው በነካ እፋቸው ኦሮሞም ትግሬም ጉራጌም የለም ቢሉ ጥሩ ነበር። ግን እሱ ጨዋታ እንኳ አያዋጣም ሄዶ ሄዶ ከ80ዎቹ ጋር ያጋጫል። ምንክያንቱም አንዳንዱ ህዝብም ሆነ ብሄረሰብ የቻይናን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስለሚያክል አለሁ ብሎ ሰልፍ የወጣ ቀን ህዝብ ይሁን ድርጅት መለየቱ ያስቸግራል። በዚህ የብሔርና ጎሰኝነት ምንዛሪ ጨዋታ አያያዛችን ማንነቴን ቀምቶ ኪሱ ውስጥ ደብቆብኛልና ይመልስልኝ የሚመስል አጓጉል ንትርክ እምንሰማበት ቀን ሩቅ አይመስልም። እሚገርመው ክርክሩ በአማርኛ መሆኑ ነው። ያውም አማራውን እየጨመረ!

እባክህ አማርኛ ሌሎችም አፋቸውን ይፍቱብህና አንተም አገርም ዳኑ! እንኳን የፈቱብህ ያልፈቱብህ ይተኩሱህ! ተነሳ ታጠቅ ዝመት ተዋጋ አማርኛ! ስንጽሑፍህን ምዘዘው፣ ቅኔንህ ለስሜት ዝረፈው! በሙዚቃህ አገርን አርገፈው! ጥላሁን ገሠሠ ያዚምህ፣ ሳህሌ ደጋጎ ይሞዝቅህ፣ መሀሙድ አህሙድ አቻ ገዳዎ ይበልብህ! ተው አማርኛ ሆይ አማልደኝ እባክህ! የአማርኛ ታሪክ ጸሐፊዎችን እነ ላጲሶን ጋዴቦን እነ ኢጆሌ አምቦ ሎሬት ባለቅኔዎችን እነ ጸጋዬ ገ/መድህን ቀዊሳን አፋቸውን በኦሮምኛ የፈቱትን እነ በዓሉ ግርማን ጥራቸው። ለመጀመሪያ ጊዜ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚል ቃል ፈጣሪ የሆኑት አባት ጋዜጠኞች እነ ከበደ አኒሳን አንሳቸው፣ የጦርና የጥበብ ፊታውራሪዎችን እነ አባመላ ሀ/ጊዮርጊስ ዲነግዴን እነ ባልቻ አባ ነፍሶን አንድ በአንድ ዘርዝራቸው!

ወደ አበደው ዘምንም ደግሞ ከፈለግክ ምጣ። የመለስ ዜናዊን ያልተገራ አንደበት እንኳ ያጣፈጥክ አማርኛ፣ አማረ አረጋዊን እንኳ ሪፖርተር ያደረግክ አማርኛ፣ በተስፋዬ ገ/አብ እጅ እንኳ እንዴት እንድምታምር እየው! አሁን ተስፋዬ ያለ አማርኛ ምንድነው? ወጣቱ ጁሃር አማርኛን በአማርኛ ሲዋጋ መጣፈጡን ተመልከተው! እንኳን ስታፋቅር ስታጣላ ስታባላ ስታጋድል እንኳ አማርኛዬ ደስ ትላለህ። አማርኛ! አማርኛ! አማርኛ! አማርኛ! አገር ማለት አንተ ነህ። በመለስ ዜናዊም፣ በኃ/ማርያም ደሳለኝም፣ በብርሃኑ ነጋም፣ በሌንጮ ለታም በአብይ አህመድም ሆነ ለማ መገርሳ ….በሁላቸውም አንደበት ሰማንህ ከእነዚህ አንዳቸውም ቢሆኑ ከቤንሻንጉል ከተፈናቀለው አማራው ጓንጉል ጋር የሥጋ ዝምድና የላቸውም! …ዳሩ ምን ማን ሊሰማኝ።

አሁን ትግርኛ “ወያንኛ” እየሆነ፣ ቋንቋው በተሰማበት ቦታ ሁሉ ተናጋሪው ወያኔ እየመሰለ ህዝብና መንግሥት ተቀላቀለ።ይህን ቋንቋ እማልሰማበት የት አገር ልሄድ እየተባለም በከንቱ አስፎከረ። ይህ ቋንቋ ላይ የተመሰረተው የብሔርና የክልል ፖለቲካ ያመጣው ጣጣ ይመስላል። ሰውየው በሌለበት ቋንቋው እየተወከለ መወዛገቡም መከራ ሆኗል። ለየትኛውም ቋንቋ እሚሰዘነር ተቃውሞ ግን ልክ አይደለም። ምክንያቱም ችግሩ ከሰው እንጂ ከቋንቋው አይደለም። አንድ ቋንቋም ሆነው እሚናቆሩ ሺ ቋንቋም ሆነው እሚፋቀሩ አገሮች ብዙ ናቸው። ለምሳሌ አንድ ትግርኛም ሆነ አንድ አማርኛ እሚናገር ህዝብ ለጠብ በሚፈላለግባት ኢትዮጵያ ሺ ቋንቋ እሚነገርባት ድሬዳዋ ህዝቧ ተቃቅፎ ያድራል። የቋንቋ አግባቢነቱ እንደተናጋሪውም ጭምር እንጂ እንደቋንቋውም አንድነትና ልዩነት አይደለም። አህያውን ፈርቶ ዳውላውን እንዲሉ ሰውን ትቶ ቋንቋውን እንዳይሆን ሰው ቋንቋን ትቶ ከልቡ ቢያወራ ነገር በጠራ አገርም አገር በሆነች ነበር። አማርኛን ማውራት እኮ ለአማሮች ሲባል እሚወራ የውለታ ቋንቋ ሳይሆን ጉራጌውና ትግሬው ወይም ሐዲያውና ሶማሌው ለገዛ ራሳቸው ጥቅም ሲሉ እሚጠቀሙበት መሆኑም ሐቅ ነው።

ለማንኛውም ግን አንዳንድ ጊዜ ቆሽት ደብኖ ስሜት ሲወጥር አማርኛን እንደክላሽንኮቭ አቀባብሎ የቃል እሩምታ ተኩስ መልቀቅ አንጀት ያበርዳል። አቤት አማርኛ! እንደምን ደስ ይላል። እኔስ ብሆን ይቺ ኢትዮጵያ የምትባል ባልቴት አማርኛን ባትሰጠኝ ምን ይውጠኝ ነበር። “ሰው ያለውን ነው የሚሰጠው ..”..ትላለች ባማርኛ! ልክ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እንዳደረገችው!!!

3 COMMENTS

 1. ሰላምታ ለደረጀ ደስታ
  አገር ባማርኛ የተሰኘ ፅሁፍህን አንብቤ እኔም አንዳች ነገር ቢሰማኝ ይሄን ጣፍኩልህ።
  በፅሁፍህ መነሻ “እነእንቶኔዎች” አማሮች እንዴት እንደጨቆኑዋቸው የሚያወሩት ባማርኛ ነው ያልከው እውነትኮ ነው። እንግዲህ እነዚህ እነእንቶኔኮ የራሳቸው አፍ የፈቱበት ቁዋንቁዋ እያላቸው ነው።
  ግን ለምን እንዲህ ሆነ? ብለህ መቸም አልጠየክም ደሬ፡ ሆኖም ግን አስበኸውም ባይሆን መልሱን መልሰኸዋል። አንተ እንዳልከው “አስተማሪው ትግሬ(ወይም አማራ) ተማሪው ኦሮሞ ትምህርቱ አማርኛ” ስለነበረ ነው። እነ እንቶኔዎች አፍ በፈቱበት በራሳቸው ቁዋንቁዋ ለምን ትግሬዎቹ ወይም አማሮቹ እንዳላስተማሩዋቸው አልገለጥክም፡ ምናልባት የነንቶኔ ቁዋንቁዋ መናኛ ነው ብለው ይሆን? “አይ ይቺ አገር” ነው ያልከው?
  ወንድሜ ደረጀ፡ እንደው የራሴአሳብ ልሞጫጭር ብዬ እንጂ አንተ ሁሉን ጨርሰኸዋል።”አይ ይቺ አገር” ባልካት ኢትዮጲያ”አማርኛ አስተካክሎ መናገር የማይችል ፕሮፌሰር(እንደኔ ዘመዶች) በቀሩት ኢትዮጲያውያን ዘንድ መሃይም መስለው ይታያሉ” እንዳልከው በመሆኑ ነው። በተጨማሪም ስታስረዳ ከነንቶኔ አንዱ”የፈለገ ዲግሪ ይኑረው አማርኛ ከጎደለው አንዳች ነገር እንደጎደለው ይቆጠራል” ብለሀል።
  ወንድሜ ደረጀ ለዚህ ነበር እንግዲህ አማሮች(አማርኛ) እንዴት እንደጨቆነን እንኳ ላለም ስናወራ ባማርኛ ብቻ የነበረው። አፍ የፈታንበት ቁዋንቁዋ ስላልነበረን ሳይሆን አንተ እንዳልከው ጎዶሎ ላለመባል ሰግተን አይመስልህም እኛ እነንቶኔዎች? በኢትዮጲያ ከተሞች የሚኖሩ ወላጆቻችን እነንቶኔ ከራሳቸው ቁዋንቁዋ ይልቅ ባማርኛ አፍ ያስፈቱን የወላጅ ነገር ሆኖባቸው ልጆቻቸው ሲያድጉ በኢትዮጲያውያን ዘንድ ገመድ አፍ ጎዶሎ እንዳይባሉባቸው ሰግተው እኮ ነው። በወላጆቻቸው ቁዋንቁዋ እንዳያወሩ ደግሞ ዘረኛ ብሔርተኛ ተብለው ይፈረጁ ነበር አንተ እንዳልከው ። ላማርኛ ተናጋሪው ግን ያ ስጋት የለበትም። አይደል ደሬ?
  ፀጋዬ ገመድህን ፊታውራሪ ሐብተ ጎርጊስ ባልቻባነብሶ አቡነ ጴጥሮስ ሳይቀሩ አማርኛን ተክነውበት ቅኔ ዘርፈው ጦር አዝምተው ድል አድርገው መለኮታዊ ቀኖና ወ ምስጢር ገልጠው አስተምረው አንዳዶቹ እናት አባት ያወጡላቸውን ስማቸዉን እንኳ ደብቀው አስደብቀዉ ወይ በክርስትና ስም አስለውጠው ኖረው ያለፉት የራሳቸው ቁዋንቁዋ ሳይኖራቸው ቀርቶ ሳይሆን አንተ እንዳልከው አንዳች ነገር የጎደላቸው ተብለው አንዳይገፉ ነበር። እንደዛ ባይሆን ኢትዮጲያ ፀጋዬ ሀብተ ጎርጊስ ባልቻ አቡነ ጴጥሮስ የሚባሉ ጀግኖች ባልነበሩዋት።
  ደረጀ፡ ለአማርኛ ቁዋንቁዋ ያለህን ፍቅር አደንቀዋለሁ። ታዲያ ትንሽ ያሳሰበኝ ነገር አለ። ለአማርኛ ያለህ ፍቅር የነንቶኔን ፹ ያህል ቁዋንቁዋ ኮተት ማለትህ ነው። በርግጥም “ላንዲት ደሀ ሀገር ይህ ሁሉ ኮተት መዘዙ ብዙ ነው።” ያልከው እውነት ነው። “አንዱ ቁዋንቁዋዬን አንዱ ሐይማኖቴን አንዱ ፆታዬን አንዱ ክልሌን” እያለ ኢትዮጲያን የነፃነት የማንነት ጥያቄ መልስ ፍልሚያ የሚካሄድባት አኬልዳማ አድርጒታል።”አቤት የተነጫናጩ ብዛት” ነው ያልከው? እኔ ግን አቤት የነፃነት ጥያቄዎችና የነፃነት ታጋዮች ብዛት ነው ያሌኩት።
  ለዚህ ሁሉ መፍትሄው ምንድነው ሲባል አንተ ያልከው”ይህን ጅልነት (የነፃነት የማንነት ጥያቄውን) ወዲያ ትቶ 80ውን የነንቶኔ ቁዋንቁዋን ጨፍልቆ አንድ የወርቅ አለት(አማርኛ) ማውጣት ነው። ወንድሜ ደረጀ በአሁኒቱ ኢትዮጲያ ይህ የሚሆን ቀርቶ የሚታሰብ አይደለም።
  “ይቺ ኢትዮጲያ አማርኛ ባትሰጠኝ ምን እሆን ነበር?” ብለህ መጠየቅህ አስተዋይነት ነው። ወንድሜ ደረጀ አማርኛ ባይኖርህ ኖሮ ማንነት ደረጀነት ኢትዮጲያዊነት ባልኖረህ ነበር። እናም ወንድሜ ደረጀ እኔም ስለባለ80 ቁዋንቁዋ ባለቤት እንቶኔዎች የምለው እነዚህ ቁዋንቁዋዎች ላንተ እንጂ ለባለቤቶቹ ኮተት አይደለም። ማንነት ነው። እናም አንድ አለት ወርቅ ለመፍጠር ይሄን ሁሉ ቁዋንቁዋ መጨፍለቅ ነውር ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው። እነንቶኔም ይህን አይነት የሰከረ የከሰረ ሀሳብ ባማርኛ እምቢኝ ብለው አብዮተኛ ከሆኑ ቆዩኮ ደሬ።
  ይልቅ አንተ እንዳልከው”እባክህ አማርኛ ሌሎችም አፋቸውን ይፍቱብህና አንተም አገርም ዳኑ”ብሎ መማፀን ይሻላል። ነገር ግን “አማርኛ ታጠቅ ተነስ ዝመት” ማለትህን አልወደድኩልህም። ይህንኑ መፈክር እንደ ጠሎት መጣፍ ሲደግም ለነበረዉ መንግሥቱ ሐይለማርያምም አልጠቀመውም።
  “አቤት አማርኛ እንዴት ደስ ይላል” ያልከውን ግን ወደድኩት። ታዲያ የነንቶኔም ቁዋንቁዋ እነርሱ ሲናገሩት እንዴት ደስ ይላል መሰለህ ደሬ ወዳጄ።

 2. ወዳጄ Alkana Bushu
  ግሩም ነጥቦችን ኣንስተሃል ሆኖም ጽሁፍን ካነበብኩ በኋላ በርግጥ ደሬ እንዲህ ብሏል ብዬ መልሼ የሱንም ጽሁፍ ኣነበብክ፣ እናም ኣንዳንድ ነጥቦችን ከይዘቱ በፈነገጠ ሁኔታ out of context) የተረዳሃቸው ስለ መሰለኝ ይህን ለመጻፍ ተነሳሁ። ደረጀ ኣንዱን ቋንቋ ከሌላው እያበላለጠ ኣልመሰለኝም፣ ከዚያ ይልቅ በሃገራችን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ላይ ተመስርቶ በኣሁኑ ጊዜ ከሞላ ጎደል ኣብዛኛው ለመግባቢያነት የሚጠቀምበትን ቁንቁ ማንሳቱ ነው። ይህ ቋንቋ የቱም ሆኖ ቢሆን ኖሮ (ግዕዝ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ …)እሱ ያለውን ካለመባል ሊያስቀረው ኣይችልም ነበር፣ ከርዕስ ለውጥ በቀር። ይህን ቀጥሎ ካለው የደሬ ሃሳብ ላይ ማየት ይቻላል – ‘የግድ አማርኛ መሆን አይገባውም’ የሚለውን ኣባባል ልብ በል።
  “ይልቅ ይህን ጅልነት ወዲያ ትቶ 80ውን ቋንቋ ወዲያ ጨፋላልቆና አቅልጦ አንድ አለት የሚወጣው ወርቅ ማውጣት ፈውስ በሆነ ነበር። የግድ አማርኛ መሆን አይገባውም። ሸኮቾም ሞርቾም ጋጎም ዳዳም ይሁን ብቻ ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርገን አንድ ቋንቋ ተጠንቶና ተመርጦ ቢወጣ ሁሉም ሰው እሱን አጥንቶ አገር አንድ ልሳን ይኖራት ነበር።”
  ኣንተ ግን የወርቅ አለት ያለው አማርኛን እንደሆነ ኣድርገህ ጽፈሃል።
  መቼም የቋንቋ ብዛት እርግማን እንጂ በረከት ኣለመሆኑን ክርስቲያኑም ሆነ ሙስሊሙ በሚቀበሉት ቅዱስ ቃል የተገለጸ መሆኑን ማንም መካድ ኣይችልም። የደረጀ ኣባባልም “ቢሆን“ ነው፣ እንጂ ይሁን ኣይደለም። ይሁን ቢልም የሚቻል ነገር ኣይደለም።
  እያንዳንዱ ቋንቋ ለባለቤቱ ወርቅ ነው፣ የቱም ከየትኛው ኣይበልጥም ወይም ኣያንስም። ነገር ግን ሁሉም በገዛ ቋንቋው ኣፍ ፈትቶ እና ቋንቋውን እያሳደገ በተጨማሪ ሌላ ኣንድ በኣገር ደረጃ ስምምነት የተደረሰበት የተመረጠ የጋራ መግባቢያ የሆነ ቋንቋ ቢማር ተጠቃሚው ሁሉም ይሆን ይመስለኛል።
  ”ስለባለ80 ቁዋንቁዋ ባለቤት እንቶኔዎች የምለው እነዚህ ቁዋንቁዋዎች ላንተ እንጂ ለባለቤቶቹ ኮተት አይደለም። ማንነት ነው።“ ብለሃል፣ ቋንቋ እንዴት ማንነት ሊሆን ይችላል? እንደዛ ማሰብ መጥበብ እንደሆነ ይሰማኛል። ደግሞስ በሌላው ቋንቋ ኣፍ የፈቱ” ነገር ግን ብሔራቸው (ወላጆቻቸው) ከሌላው ዘር የሆኑት ማንነታቸው ምንድን ነው? ‘ማንነት’ ቋንቋው ምንም ይሁን ሰውነት ነው ብለን ካሰብን ትንሽ ሰፋ ይልልናል። ከዛ ይልቅ ‘የማንነት መገለጫ’ ቢባል ያስኬድ ይሆናል።
  በነገራችን ላይ ደረጀ ኮተት ሲል ኣማርኛውንም የሚጨምር መሆኑን የተረዳህ ኣይመስልም።

  እናም አንድ አለት ወርቅ ለመፍጠር ይሄን ሁሉ ቁዋንቁዋ መጨፍለቅ ነውር ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው።

 3. ጽሁፌን ሳልቋጭ በስህተት postን ነካሁ
  ”እናም አንድ አለት ወርቅ ለመፍጠር ይሄን ሁሉ ቁዋንቁዋ መጨፍለቅ ነውር ብቻ ሳይሆን ወንጀልም ነው።“ – የሚለውም ፍረጃህ ባልተባለ፣ በቢሆን ላይ የተመሰረተ ስለሆነ የሚያስኬድ ኣይመስለኝም።
  ኣሁን ኣበቃሁ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here