Home News and Views ለጠ/ሚ አብይ የአሜሪካ ጉብኝት አሳሳቢ ጉዳይ

ለጠ/ሚ አብይ የአሜሪካ ጉብኝት አሳሳቢ ጉዳይ [መሳይ መኮንን]

ጠ/ሚ አብይ ከሰሙኝ…..

በእርግጥ ጊዜ የለዎትም። እርስዎ ይለፋሉ። ስለሀገር ወዲህና ወዲያ ሲሉ ጊዜ እንደማይኖርዎት አውቃለሁ። ምናልባት የእርስዎን የማህበራዊ መድረክ ጉዳዮች የሚመለከተው አካል ይህ መልዕክቴን በአጋጣሚ ካገኘው ለእርስዎ ሹክ ቢያደርግልኝ ደስ ይለኛል።

ዛሬ በዋሽንግተን የኢትዮጵያ ኤምባሲ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን አቀባበል በተመለከተ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል። በጋዜጣዊ መግለጫው መድረክ ላይ ማይክ ጨብጠው የሚታዩ ሰዎችን ምንነትና ማንነት ላጤነ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ልፋትና መልካም ስም ለማጉደፍ ሆን ተብሎ የሚያሴር ሃይል አሸናፊ መሆኑን ይረዳል። እውነት ለመናገር በእነዚህ ሰዎች በሚመራ ኮሚቴ የአቀባበል ስነስርዓቱ የሚካሄድ ከሆነ አሳፋሪ ከመሆን ባለፈ እዚህ ዲያስፖራ እሳቸውን በሞቀ ሁኔታ ለማስተናገድ ለተዘጋጀው ኢትዮጵያዊ ስድብ ነው ማለት ይቻላል። በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዙሪያ ያሉ እውነተኛ ሰዎች ከወዲሁ ቢያስቡበት የተሻለ ይመስለኛል።

ቀን ከሌሊት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ ውስጥ ገብቶ በይፋ ለውጡን ”ጸረ ኢትዮጵያ” ሲል የፈረጀ የዲያስፖራ ተጋሩ ሰብሳቢ በዚህ ኮሚቴ ውስጥ ተካቶ ፊት ለፊት መታየት ከምን ስሌት አንጻር እንደተሳበ ሊገባኝ አልቻለም። ይህ ግለሰብ መቀሌ መሽጎ ዶ/ር አብይ ላይ እየዶለተ ያለው የህወሀት ቡድን ዋና አፈ ቀላጤ መሆኑ በግልጽ የሚታወቅ ነው። ባለፉት በርካታ ዓመታት ኢትዮጵያውያን ውድ መስዋዕትነት የከፈሉበትን ትግል ሲያጥላላና ሲያበሻቅጥ የሰነበተ፡ ከእናት ድርጅቱ የተቀበለውን የዘር መርዝ በዲያስፖራው መሀል በመርጨት እኩይ ዓላማ አንግቦ የሚንቀሳቀስ መሆኑ የአደባባይ ዕውነት ነው።

ይህ ግለሰብ አለቆቹ ድባቅ እየተመቱ ወደ መቀሌ ሲያፈገፍጉ እሱ የእነሱ አፍ ሆኖ ዶ/ር አብይ ላይ መጠነ ሰፊ ቅስቀሳ ሲያደርግ የከረመ አሁንም በዚያው ተግባሩ የቀጠለ ለመሆኑ የግል ፌስቡኩንና በሚመራው ድርጅት የሚያስተላልፈውን መግለጫ በመመልከት መግለጽ ይቻላል። እንደምን የዶ/ር አብይ ውድቀት ይመጣ ዘንድ ለፍቶና ተግቶ የሚሰራ ግለሰብ ዶ/ር አብይን ለመቀበል በተዘጋጀ ኮሚቴ ውስጥ ዋና ግንባር ሆኖ ይሰለፋል? በነገራችን ላይ ይህ ግለሰብ የህወሀት አገዛዝ በድሎኛል፡ ሊገለኝ ሲል አመለጥኩ ብሎ በአሜሪካን ሐገር የፖለቲካ ጥገኝነት የተሰጠው፡ ስሙን ቀይሮ የሚኖር እንደሆነ ሰምቼአለሁ። ወረቀቱን ካገኘ በኋላ ግን አሳደደኝ ላለው አገዛዝ እየሰራ ይገኛል። የአሜሪካን ኢሚግሬሽን መረጃው እንዴት እንዳልደረሰው አላውቅም።

ከኤምባሲው የውስጥ ምንጭ ያገኘሁት መረጃ እንደሚያመለክተው ዶ/ር አብይ ወደ አሜሪካ ሲመጡ አቀባበሉን እንዲያስተባብር የተሰየመው ኮሚቴ አብዛኞቹ አባላት በሁለት ቢላዋ ሲበሉ የከረሙ፡ የነጻነት ታጋዮችን በስውርና በአደባባይ ሲሰልሉና ሲያሳስሩ የነበሩ፡ ከህወሀት አገዛዝ ጋር እጅና ጓንት ሆነው ከፍተኛ ገንዘብ እየተቀበሉ ህዝብ ላይ በደል ሲፈጽሙ የሚታወቁ፡ በአጭሩ በዲያስፖራው ውስጥ የመርዝ ብልቃጥ ሆነው ሲረብሹና ሲከፋፍሉ የሰነበቱ ናቸው። ዲያስፖራው በሀገሩ ጉዳይ ባይተዋር እንዲሆን የህወሀት አገዛዝ በተለያዩ ዘርፎች ያሰማራቸው ግለሰቦች ቆባቸውን ሳያወልቁ ለዶ/ር አብይ አቀባበል ባለቤት ሆነው ከፊት መስመር ተሰልፈዋል።

በኮሚቴው ውስጥ ከሀገር ቤት የሚመራውና የውጭ ጉዳይ ቃል አቀባይ የሆነው መለስ አለምም እንደሚገኝበት ሰምቼአለሁ። ይህ ሰው ቀን ቀን ቃል አቀባይ ማታ ማታ ዱላ አቀባይና ገራፊ መሆኑ ተጋልጧል። ከተሸነፈውና መቀሌ ከመሸገው የህወሀት ቡድን ጋር ስለመሰለፉ ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም። በአካል ማዕከላዊ እየሄደ በውድቅት ሌሊት ኢትዮጵያውያንን ወፌ ላላ የሚገርፍን ሰው በፍርድ ለመጠየቅ ለጊዜው ባይቻል እንኳን በእንዲህ ዓይነት መድረክ ላይ ከፊት እንዲሆን መደረጉ በእጁጉን የሚያም ነው።

አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን አሁንም ድረስ አዲሱ ለውጥ የሚተናነቀው፡ ለመዋጥና ከለውጡ ጋር ለመጓዝ ያልፈቀደ፡ ከአራት ኪሎ ቤተመንግስት ይልቅ ለመቀሌው ተሸናፊ ቡድን ልቡ ያደላ፡ የሚታወቅበት አደርባይ ባህሪው በዚህን የለውጥ ጊዜ ሊለቀው ያልቻለው ሰው ነው። ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ይህ ግለሰብ አሁንም የህወሀት የበላይነት በኤምባሲው ተጠብቆ እንዲቆይ እያደረገ ነው። ትዕዛዝ የሚቀበለው ከመቀሌ ነው። የዶ/ር አብይን የለውጥ ግስጋሴ በማንኳሰስ ”ተራ ተወዳጅነት ለማትረፍ” እያለ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በግልጽ የሚወርፍና በየኮሪደሩ የሚያንሾካሹክ እንደሆነ በቅርበት የሚያውቁት ሰዎች ይናገራሉ። ይህ ሰው የሚመራው ኮሚቴ ነው እንግዲህ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመቀበል ሽር ጉድ እያለ ያለው።

የቀድሞ ጠ/ሚር ሃይለማርያም ደሳለኝ ዘመድና የህወሀቱ ጋዜጠኞች ማህበር ተጠሪ ነኝ የሚለው አንድ ግለሰብም የዚሁ ኮሚቴ አባል ሆኖ ከፊት ለፊት ተደርድሯል። ይህ ግለሰብ እነእስክንድር የታሰሩት በወንጀላቸው እንጂ በጋዜጠኝነታቸው አይደለም ብሎ በአደባባይ የተናገረ፡ ለዚህም ከህወሀት ዳጎስ ያለ ገንዘብ ኪሱ የተሸጎጠለት፡ በስደተኝነት ስም ወደ ዋሽንግተን ዲስ መጥቶ ዲያስፖራውን እየስለለ የሚገኝ ነውረኛ ግለሰብ ነው። ቲ ጂ ቴሌቪዥን የተሰኘ ኮሜዲ ዜናዎችን የሚሰራ በዲያስፖራ ውስጥ እክ እንትፍ ተደርጎ የተጣለ፡ የተገለለ፡ የህወሀትን አገዛዝ እድሜ ለማርዘም ከራሱ እድሜ ቀንሶ የታገለ፡ ለህወሀት ክብር የሱን ውርደት ተቀብሎ የኖረ ሌላ ግለሰብም የዶ/ር አብይ አቀባበል ኮሚቴ አባል መሆኑን ለማወቅ ችዬአለሁ።

በአጭሩ ዲያስፖራው የሚጠየፋቸው፡ በስግብግብ ባህሪያቸው ሰው ሰው የማይሸቱ፡ ክብራቸውን ያዋረዱ፡ ሰዎች የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን አቀባበል በሚመራው ኮሚቴ ውስጥ ተሰግስገዋል። ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫም ሰጥተዋል። ዓይናቸውን በጨው አጥበው፡ ማይክ ጨብጠው ‘ኑ! ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንቀበል” ሲሉ ጥሪ አድርገዋል። ያሳፍራል። ያሸማቅቃል።

ዶ/ር አብይ ዲያስፖራውን ይፈልጉታል። ዲያስፖራውም በእሳቸው የለውጥ ጅምር ድጋፉን እያሳየ ነው። ሸማችና ገበያ ሊገናኙ ጊዜው ደርሷል። ለመጀመሪያ ጊዜ ዲያስፖራው ቀልቡ የወደደውን መሪ ሊቀበል የታሪክ አጋጣሚው ተፈጥሯል። ዛሬ በፓርላማ ለዲያስፖራ ኢትዮጵያውያን ያስተላለፉትን ጥሪም በደስታ የተቀበለው ኢትዮጵያዊ የትየለሌ ነው። ከእሳቸው እውነተኛና ኢትዮጵያዊ ራዕይ ጋር ለመሰለፍ ተዘጋጅቷል።

ሆኖም ሰውነታቸውን ባረከሱ፡ ከህሊናቸው ሆዳቸውን ያስቀደሙ፡ ከጸረ ኢትዮጵያ አገዛዝ ጋር እጅና ጓንት ሆነው የኖሩ፡ ኢትዮጵያውያንን ሲያሸማቅቁ የሚታወቁ ፡ ይሉኝታ የሌላቸው፡ ዶ/ር አብይ ከጀምሩት የለውጥ አብዮት ጋር ፈጽሞ መራመድ የማይችሉ፡ አደርባይና ስግብግብ ግለሰቦች በሚመሩት ኮሚቴ አማካኝነት በሚደረግ አቀባበል ዲያስፖራው እንዲሳተፍ ማድረግ አደገኛና ኪሳራው በተለይ ለለውጡ ሃዋሪያ ዶ/ር አብይ መሆኑ አይቀርም። በግሌ የማገኛቸው የዲያስፖራ አባላት በሁኔታው ፍጹም በሽቀዋል። ተናደዋል። በእነዚህ ግለሰቦች የተነሳ የአቀባበል ስነስርዓቱ እንዳይደበዝዝ ከወዲሁ ስጋታቸውን እየገለጹ ነው። በዶ/ሩ የተደሰቱት በእነዚህ ግለሰቦች ፊት መሆን ግን ተከፍተዋል።

እናም ዶ/ር አብይ የሚሰሙኝ ከሆነ ሰው ይፈልጉ። ስለሀገራቸው እድሜ ልካቸውን ሲብሰለሰሉ፡ ሲለፉና ሲተጉ የሚታወቁ፡ በጎ አሳቢዎች፡ በማህበረሰቡ ዘንድ ክብር ያላቸው ብዙ ኢትዮጵያውያን አሉና በእነሱ መሪነት እንቀበልዎ። ይህ የታሪክ አጋጣሚ የእርስዎን ከዲያስፖራው ጋር ያልዎትን ቀጣይ ግንኙነት የሚወስን ነው። በእንጋጠውና እንብላው በሚመራ ኮሚቴ እርስዎን መቀበል ለክብርዎ ጥሩም አይደለም። እርስዎን አይመጥኑም። ልጆቻቸው የሚያፍሩባቸው ሰዎች እንደምን የእርስዎን ክብር ያስጠብቃሉ? እርስዎን የመሰለ ባለራዕይ መሪ ፡ ራዕይ አልባ በሆኑ፡ ክብራቸውን ባወለቁ አንዳንዶቹ በወንጀል በሚፈለጉ ሰዎች መሪነት ብንቀበልዎ ፈጣሪም አይምረንም። አከባቢዎን ያጽዱ። የእርስዎን መንገድ ሊያቆሽሹ በአደባባይ ሳይቀር እየደነፉ ከሚገኙ የአሮጌው ስርዓት፡ የተሸነፈው ቡድን ናፋቂዎች ይርቁ ዘንድ ኢትዮጵያዊ አስተያየቴን ልሰጥዎ ፈለኩኝ።

አመሰግናለሁ

1 COMMENT

 1. ጋዜጠኛ መሳይ፥
  ጸረ ዲያስፖራ የሆነ ይህን ወስላታ “ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንቀበላለን” የሚል ኮሚቴ፣ “ጎድን” ልንለው ይገባል።

  የዛሬ 44 አመት የነበረውን የአገራችን የለውጥ ድባብ በደንብ አድርጌ አስታውሰዋለሁ። የየካቲት 66 አብዮት መሸጋገሪያ ወቅት ባብዛኛው የአሁኑን ይመስል ነበር። አንተ ያኔ አልታሰብክም። ወደ ወጣትነት የተሸጋገርኩባቸው እነዚያ ጊዜያት ለእኔ ልዩ ውበት ነበራቸው። የለውጥ ኃይል በመሆን አገሬን ወደተሻለ ሥርዓት እንደምመራ ተሰምቶኝ በልበ ሙሉነት ከእድሜ እኩያዎች ጋር ተቀላቀልኩ። ነገር ግን፣ ወጣቱ ለወገኑ በቀናነት ሲታገል፣ ታላላቆቹ ሥልጣን አስዳጃቾች ወደ ቤተ መንግሥት ሰተት ብለው ገቡ። ድካማችንን መና አስቀሩት። ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ቁጥር 1 (ደርግ) ወደ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ቁጥር 2 (ወያኔ) አሸጋገሩን። አሁን የጎለመስኩ፣ የያኔዎቹን ሥልጣን ነጣቂዎች አቻ ድሜዬ የያዝኩኝ፣ ዛሬ እንደገና ስለተከሰተው፣ ጸረ ወጣት (የለውጥ ኃይል) የሆነ የጎልማሶች ስብስብ ትንሽ ልተች።

  ዛሬ፣ በግምት ከ 105 000 000 ሕዝብ 70% የሚሆነውን የሚሸፍኑት የኢትዮጵያ ሕጻናትና ወጣቶች ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩን እቀበላለሁ እያለ የሚንተፋተፈው ኮሚቴ፣ እነዚህን ታዳጊዎች ፈጽሞ ዘንግቷል። የሽማግሌዎች ስብስብ የት ሊያደርሰን እንደሚችል ካለፈው ተሞክሮ ማየት በቂ ነው። ባይሆን ከጎናችን መርጠን አስቀምጠን እንመራቸዋለን እንጂ፣ የለውጥ ኃይልና አትራፊ የሆነውን ይህን አዲስ ትውልድ እንዴት እንተወዋለን?

  የሽማግሌዎች ስብስብ የሆነው ይህ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመቀበል የተቋቋመው ኋላ ቀር ኮሚቴ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ውብ አቀባበል ግራጫ ለማድረግ መነሳቱ በጣም የሚያሳዝን ነው። በሁሉ ስፍራ ሳይጠሯቸው አቤት የሚሉ፣ እነዚህን ሰዎች እባካችሁ አንድ በሉልን። እንዲህ አይነት ኮንሰርት መሰል መድረክ ውስጥ እንኳን ምንም ወጣት ከሌለ ምን ዓይነት ባዶ ዝግጅት እንደሚሆን አስቡት። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ የኢትዮጵያን ትንሣኤ ለመግታት እየተሠራ ያለው ሸፍጥ መጣም ያማል።

  አንተ ርቱዕ ጋዜጠኛ በመሆንህ ይህን ጉዳይ ላፍታም ቸል እንደማትል አምናለሁ። ስለዚህ፣ ከግንዛቤ እንድታስገባው አስተያየቴን ላንተ ልኬአለሁ።

  አመሰግናለሁ፦
  ሐምሌ ፳፻፲ ዓ ም

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here