Home News and Views አማራ ከነጋሶ ጊዳዳ ምን መማር ይገባዋል?

አማራ ከነጋሶ ጊዳዳ ምን መማር ይገባዋል? [በላይነህ አባተ]

 (abatebelai@yahoo.com)

መሰልጠንን እንደ ምዕራባውያን ማሰብ፣ መልበስ፣ መዝፈን፣ መደነስ፣ መብላትና መጠጣት የሚል ሸውራራ ትርጉም ሰጥተን ተንሸዋረርንና ተወላገድን እንጅ እንደ አራት ዓይናው ጎሹ በትክክል እንድናስተውልና እንደ አቡነ ጴጥሮስ ቀጥ ብለን እንድንቆም የሚረዱን መንፈሳዊ እሴቶ ነበሩን፡፡ አይምሮን በመንፈስ ልዕልና የሚገነቡ ስልጡን ባህሎች ነበሩን፡፡

በእነዚህ ዓይምሮን በመንፈስ ልዕልና በሚገነቡ ባህሎቻችን የተማረ ሰው ይከበር ነበር፡፡ የሚከበረውም ዲግሪ ጪኖ ፒ ኤች ዲ የሚሉ ፊደሎች ከሥሙ ጫፍ እንደ ካስማ ስለከተመ ወይም ዶክተር የሚል ቃል ከሥስሙ ፊት እንደ ችካል ስለቸከለ ሳይሆን ትምህርቱን እንደ እምቧይ አፍረጥርጦ ስለሚማርና አፍረጥርጦ የተማረውን ትምህርቱንም የሚያውለው ለገንዘብ መሰብሰቢያ ወይም ለመታወቅ ሳይሆን ለህብረተሰብ አገልግሎት ስለነበር ነው፡፡ ክቡር አቶ ሀዲስ ዓለማየሁ ለዚህ ጉልህ ምሳሌ ናቸው፡፡

በስልጡን ባህላችን መሰረት እድሜው ስልሳን የተሻገረ ሰው ትልቅ ክብር ይሰጠው ነበር፡፡ ትልቅ ክብር የሚሰጠውም እድሜው ስለተቆለለ ሳይሆን በእድሜው የመንፈስ ልዕልና ዲግሪ ስለሚጭን ነበር፡፡ በእድሜ የገፋ ሰው ከፊት መቃብሩን ስለሚያይ ንስሃ ይገባና ከተንኮል፣ ከስግብግብነት፣ ከመዋሸት፣ ከመቀላመድ፣ ከማጭበርበርና ሌሎችም ከንቱ ምግባሮች ተቆጥቦ ጊዜውን እውነትን በመናገር፣ የተጣላን በማስታረቅ፣ ርትዑ ፍርድ በመስጠትና በመጸለይ ያሳልፍ ነበር፡፡ በልጅነቴ እየመከሩ ያሳደጉኝ አዛውንቶች ሁሉ በእነዚህ በጎ ምግባሮች ሲባትሉ የሚውሉ ቅዱሳን ነበሩ፡፡

በእነዚህ ቅዱሳን አዛውንቶች ቦታ ዛሬ እነ ነጋሶ ጊዳዳ ተተኩ፡፡ ነጋሶ ጊዳዳ የእድሜ ባለጠጋ ነው፡፡ ነጋሶ ጊዳዳ “የታሪክ ምሁር ነኝም” ባይ ነው፡፡ የታሪክ ምሁሩ ነጋሶ እወክላለሁ የሚለውን ሕዝብ ከትምክህተኛና ነፍጠኛ አማራ ነፃ ሊያወጣ ከእነ ሌንጮ ለታ ግንባር ተጣበቀ፤ መብቱ ነበር፡፡ ቆይቶም ያንን  ተወ ወይም ከዳና በእነ ለገሰ ዜናዊ እንደ አምባሻ ተጠፍጥፎ በተጋገረው የእነ አባ ዱላ ግንባር ተለጠፈ፤ መብቱ ነበር፡፡ ከእነ አባ ዱላ ግንባር በመለጠፉም “የሕገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን” ፕሬዘዳንት ሆነ፡፡ በፕሬዘዳንትነቱም በነፍጠኛና በትምክህተኛ ኮዶች የሚጠራውን አማራን የሚረግጠውን “ሕገ-መንግስት” ሕዝብ የመከረበት አስመስሎ አፀደቀ፣ መብቱ አልነበረም፡፡

ደደቢት በረሃ በሞሶሎኒ ብቅልነትና በነለገሰ ዜናዊ ቅልነት የተጠነሰሰውን “ሕገ-መንግስት” በጋንነት የደፈደፈው ነጋሶ ጊዳዳ በእነ ለገሰ ዜናዊ ያገሪቱ አሻንጉሊት ፕሬዘዳንት እንዲሆን ተደረገ፡፡ በአሻንጉሊትነቱ መቀጠል ሲያቅተው በለገሰ ዜናዊ ጩኸት እንደ ማሽላ ወፍ ተባረረ፡፡ በለገሰ ዜናዊ ጩኸት እንደ ወፍ መባረሩ እንደ ጀግንነት ታዬና በሕዝብ ተደነቀ፣ ተወደሰ፡፡ ኢትዮጵያ ስትነሳ አንጀቱ ስፍስፍ በሚለው አማራ ሲወደስም ከእነ ሌንጮ ግንባር ወደ እነ አባ ዱላ ግንባር እንደ ናዳ ከተንሸራተተበት ገደል ተነስቶ ወደ አንድነት ተራራ እንደ ወሰካ ወጣ፡፡ [1-2] ወደ አንድነት ተራራ በመውጣቱም አማራ እንደ ህጻን ልጅ አዝሎ “እሹሩሩ ነጌ” እያለ ዜማውን እንደ ዋሽንት አንቆረቆረው፡፡ እሹሩሩ ነጌ እየተዜመ በአማራ እንደ በኩር ልጅ የተሞላቀቀው ነጌ ጊዳዳም ያፀደቀው “ሕገ-መንግስት” ሕዝብ ያልተሳተፈበት ድሪቶ እንደነበርና ሕዝብ አፀደቀው ብሎ መናገሩም ቅጥፈት  እንደ ነበር አመነ፡፡ [3] ቅጥፈት እንደ ነበር አምኖም የኢትዮጵያን ሕዝብ ለቅጠፈቱ ይቅርታ ጠየቀ፡፡

በንስሐ የሚያምነው የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም በማይፈልገው የ”ሕገ- መንግስት” ቅርጫት ውስጥ በርበሬ የሚታጠነው አማራም ዓይኑ እንባ እንደቋጠረ ይቅር አለና ነጋሶን አቀፈው፡፡ ይህ ነጋሶን በፍቅር ያቀፈው በበርበሬ የሚታጠን ሕዝብም ከጉረሮው እየሞለቀቀ ለታክሲ ከፈለለት፣ ሻይ ቡናም አለው፡፡ ሲታመምም አውሮጳ አሳክሞ አካለ ጎደሎ ከመሆን አተረፈው፡፡

ይህ መከረኛ ሕዝብ ንስሃው እውነት መስሎት በነጋሶ ተስፋ ነበረው፡፡ ነጋሶ ግን የሕዝቡን ተስፋ አጨልሞ የግልንቢጥ ጉዞውን ጀመረው፡፡ እንደ ወሰካ ከወጣበት የአንድነት ተራራ ወደ አባ ዱላ ግንባር እንደ እንደገና እንደ ናዳ ተንሸራተተና አረፈው፡፡ [4] የግልንቢጥ ጉዞውን ለመጨረስ ከአባ ዱላ ግንባር ወደ ሌንጮ ግንባር በመንሸራተት ላይ መሆኑንም የባህር ዳርን ሕዝብ ዘለፋው አመልካች ነው፡፡

“ምሁሩ” ነጋሶ ጊዳዳ፤ እድሜ ጠጋቡ ነጋሶ ጊዳዳ በእርሱ ፕሬዘዳንትነት የፀደቀው “ሕገ-መንግስት” ሕዝብ እንደ መከረበት መስክሮ ዋሸ፡፡ ቀጥሎ ሕዝብ ያልመከረበትን ሕዝብ የመከረበት አስመስሎ በመዋሸቱ ንስሐ የገባ መስሎ ይቅርታ ጠየቀ፡፡ ሕዝቡም “ንስሐ ለገባ ይቀርታ አይነፈግም” በሚል ሕገ-መንግስቱ እንደ ቅርጫት ተደፍቶበት እርስቱን የተነጠቀው አማራ ሳይቀር ይቅር አለው፡፡ ይቅርታን አኝኮ የበላው ነጋሶ ግን ይቅር ያለውን ክቡር ሕዝብ “ሕገ-ወጥ” አለና አሁንም በክህደት በደረተው “ሕገ-መንግስት” ወነጀለው፡፡[5]

ከላይ እንደተገለጠው ወንጃዊው ነጋሶ ሕገ-መንግስቱ ሕዝብ ያልመከረበት ድሪቶ ሲል በንስሃው ወቅት ተናዞ እንደነበር ተመልክትናል፡፡ እንግዲህ ሕዝብ ያልመከረበት ድሪቶ እንዴት ሕገ-መንግስት ይባላል? ሕገ-መንግስት ካልሆነስ እንዴት ይከበራል? መከበር የሌለበትን ሕገ-መንግስት ያለማክበረን ሕዝብስ በምን ሕግና ህሊና ሊያስወነጅል ይችላል? የታሪክ “ምሁሩና” የእድሜ ጠጋቡ ነጋሶ የወንጀል ክስ በምን የሐሳብ ሰንሰለት(ሎጅክ) ሊገባን ይችላል?

ስለዚህ አማራ ደጋግሞ ከወነጀለውና የፖለቲካ አክሮባት ከተጫወተበት ነጋሶ ጊዳዳ ምን መማር ይገባዋል? ታሪክ ብል ፊታችሁን ታኮሳትሩብኝ ይሆናል፡፡ የአቋም ፅናትን ብል ኪኪ ኪኪ ኪኪኪኪ ብላችሁ ትስቁብኝ ይሆናል፡፡ ሽምግልናን ብል ሽንታችሁ እስቲያመልጣችሁ ፍርፍር ብላችሁ ትስቁ ይሆናል፡፡

አማራ ከነጋሶ የፖለቲካ አክሮባት የሚማረው “አንድነት፣ ኢትዮጵያ” እያለ እሚያታልል የፖለቲካ ቁማርተኛ እየወደዱ እንደ ጀማሪ ፍቅረኛ ባንዴ ሙክክ ማለትን ማቆምን ይሆናል፡፡

አማራ ከነጋሶ የፖለቲካ አክሮባት መማር ያለበት “ለሰው ሞት አነሰው” የሚለውን የቀበሮዋን ብሂል ይሆናል፡፡

አማራ ከነጋሶ ጊዳዳ መማር ያለበት ዛሬም እጁ አመድ አፋሽ መሆኑን ይሆናል፡፡

አማራ ከነጋሶ መማር ያለበት “አንድነት፣ ኢትዮጵያና ፍቅር” እያለ በየጊዜው የሚነሳን ጎርፍ አመጣሽ ሰባኪ መስማቱን ትቶ የራሱን የቤት ሥራ መስራት እንዳለበት ይሆናል፡፡

አማራ ከነጋሶ ተደጋጋሚ ክህደት መማር ያለበት የራሱ አይምሮና ክንድ ያላጎናፀፈውን ነፃነትና አገር ከማንም ሊያገኛት እንደማይችል እርም ማውጣት ይሆናል፡፡

አማራ ከነጋሶ የክህደት ታሪክ መማር ያለበት ነፃነቱንም ሆነ የአገሩን ህልውና ለመጠበቅ እንደ አያቶቹ በራሱ እውቀት፣ በራሱ የመንፈስ ልዕልናና በራሱ ክንድ መተማመን እንዳለበት ይሆናል፡፡
End notes

  1. Ex-Ethiopia President Negasso Gidada joins opposition, http://news.bbc.co.uk/2/hi/africa/8381120.stm (last accessed July, 2018)
  2. Negaso Gidada and Seye Abraha join UDJ, http://abbaymedia.net/negaso-gidada-and-seye-abraha-join-udj/ source reuters ((last accessed July, 2018)
  3. Yenegasso Menged’ – Ethiopia’s Former President Regrets Key Decisions He Made inOffice

https://ethiopiantimes.wordpress.com/2011/07/29/yenegasso-menged-ethiopias-former-president-regrets-key-decisions-he-made-in-office/, July 29, 2011 ((last accessed July, 2018)

  1. Negasso Gidada got his gift from OPDO. The political message? Borkena.c om. https://www.borkena.com/2018/02/21/negasso-gidada-got-his-gift-from-opdo/ ((last accessed July, 2018)
  2. የባህርዳሩ ሰልፍ ሕገመንግስቱን ሙሉ በሙሉ ይፃረራል፡/ ነጋሶ ጊዳዳ ግዮን ቁጥር 12 ሰኔ ሁለት አስር .ም ((last accessed July, 2018)

 

ሐምሌ ሁለት ሺ አስር ዓ.ም.

 

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here