Home News and Views የዶ/ር አብይ አህመድ የአሜሪካ ጉብኝት ጉዳይ – (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

የዶ/ር አብይ አህመድ የአሜሪካ ጉብኝት ጉዳይ – (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

እንደአሜሪካኖች ካላንደር በ1964 ዓ.ም. ለሰላም የኖቬል ሽልማት እጩ ሆነው ከቀረቡት 43 ሰዎች መካከል ማርቲን ሉተር ኪንግ እና ቀዳማዊ ኃይለስላሴ የመጨረሻዎቹ ነበሩ። በመጨረሻ ግን ማርቲን ሉተር ኪንግ የአመቱ ኖቬል ተሸላሚ በመሆን፤ ክብርና ሞገስን ተጎናጸፈ። ሆኖም ከአራት አመታት በኋላ ማርቲን ሉተር ኪንግ በሰው እጅ ተገደለ፤ ቀዳማዊ ኃይለስላሴም ወደ አሜሪካ በመጡ ግዜ… ወደ አትላንታ አቅንተው በማርቲን ሉተር ኪንግ መቃብር ላይ የአበባ ጉንጉን አኖሩ። በመቀጠልም ወደ ሞርሃውስ ኮሌጅ በመሄድ በዚያ ለተገኙ ኢትዮጵያውያን ንግግር አደረጉ። ዛሬም በህይወት ያሉት አቶ ቸሩ ተረፈ እና አቶ ሰለሞን በቀለ ስለዚያች ቀን ሲያጫውቱን በመደመም እናደምጣቸዋለን። ከሳቸው በኋላ ስድስት መሪዎች ተፈራረቁ… አንዳቸውንም ሳናያቸው ቀርተን፤ ሰባተኛው ንጉሥ አሜሪካ ሊገቡ ቀናቶችን እየቆጠሩ ነው። መቼም አንድ የጥቁር ህዝብ መሪ አሜሪካ ድረስ መጥቶ የማርቲን ሉተር ኪንግ መቃብር ላይ የአበባ ጉንጉን ሳያደርግ መሄዱ ትክክል ባይሆንም፤ እንደው ብቻ በህይወት ኖረን፤ የታሪክ ምስክር ለመሆን መብቃታችን ደስ ያሰኘናል። በዚያኑ መጠን ይህንን እድል ለማየት ያልበቁ፤ እንዲህ አይነቱ ቀን በኢትዮጵያ እንዲመጣ የታገሉ  ብዙዎች አሉና ሁሌም ክብር ለነዚህ ሰማዕታት ይሁን። እኛም ለሰማዕታት የክብር አበባ ጉንጉን በልባችን በማኖር በእንዲህ አይነቶቹ ቀናት ሁሉ እናስባቸዋለን።

ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ አሜሪካ በሚመጡበት ወቅት መሪ መፈክር እንዲሆን የተመረጠው ቃል፤ “ግንቡን እፈራርሰን፤ ድልድይ እንገነባለን!” የሚል ነው። ለማፍረሱ ቀድመን የምንሰለፍ ብዙ አለን፤ ድልድይ የመገንባቱ ጉዳይ ግን ብዙ ያነጋግረናል። ከብዙዎቹ መካከል አንደኛው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚጠቀምበት ሰንደቅ አላማ ነው። ህዝቡ በባንዲራው ላይ የተደነቀረውን የሰይጣን አምላኪዎች የሚጠቀሙበት የተከበበ ኮከብ ክፉኛ ጠልቶታል። አሁን አሁንማ ልጆች ጭምር ት/ቤት ሲጫወቱ… “ኮከቡን ያያቹህ… አላየንም!” እያሉ ማዜም ጀምረዋል አሉ።

ባለፈው ዳላስ ላይ በተደረገው የሰሜን አሜሪካ ዝግጅት ላይ፤ አንድም ሰው ኮከብ ያለበት የኢትዮጵያ ባንዲራ በስህተት እንኳን ይዞ አላየንም። አርብ እለት “የኢትዮጵያ ቀን” ሲከበር፤ አንዱ ካገር ቤት የመጣ ሰውዬ ወደጓደኛዬ ጠጋ ብሎ፤ “እዚህ አገር ኮከብ ያለበት ባንዲራ የለም እንዴ?” ቢለው፤ “ኮከብ እኮ የሚያስፈልገው በጨለማ ግዜ ነው። አሁን ፀሃይ ስለወጣልን ኮከብ አያስፈልገንም” ብሎ በውስጠ ወይራ ቅኔ ነገረውና ባንዲራውን ማውለብለብ ቀጠለ።

እዚያው ዳላስ እያለን የአብይ ስም በተጠራ ቁጥር ጩኸቱ በዝቶ ነበር። እንዲያውም የፌዴሬሽኑም ፕሬዘዳንት ስም አብይ ስለሆነ፤ ስለአብይ ስናወራ… “አብይ ትልቁ… አብይ ትንሹ” እያልን ለማውራት ተገደን ነበር። ምሽት ላይ ደግሞ ጋዜጠኞች ሰብሰብ ብለን የወቅቱን ያገራችንን ሁኔታ መጨዋወታችን አልቀረም። በዚህ መሃል አንደኛው ጋዜጠኛ… ለሌሎች ጋዜጠኞች ጥያቄ አቀረበ። “እኔ የምለው,” ብሎ ጀመረ።

 “እኔ ‘ምለው… አጼ ምኒልክ ሞቱ፣ ቀዳማዊ ሃይለስላሴም ተገደሉ፣ ደርግም ተገረሰሰ… ካልን፤ ኢህአዴግን ምን ሆነ እንበል?” ብሎ ቢጠይቅ፤ “ኢህአዴግማ ሃክ ነው የተደረገው!” በማለት ፈጣን መልስ ሰጥቶ አስቆናል።

ኢህአዴግ ህዝቡን የበደለው እና ያስለቀሰውን ያህል… ገና ምንም አልካሰውም። እኛንም ቢሆን በፍቅር እያሸነፈ ያለው የዶ/ር አብይ አህመድ አቋም እንጂ፤ ከኢህአዴግ ጋርማ ብዙ ያላወራረድነው ሂሳብ አለን። ያላወራረድነውን እንባ-ነክ ጉዳዮች በሌላ የአጀንዳ ቅርጫት ውስጥ አስቀምጠን ቁምነገራችንን እንቀጥል። እናም “ኢህአዴግ Hack ተደረገ” የሚለውን አባባል እንደቀልድ ልንወስደው እንችላለን። ቀልዱ ግን ለኢህአዴግ ሰዎች መራር ቀልድ ነው የሚሆንባቸው። ዶ/ር አብይ አህመድ የኢህአዴግ የሚያካሂደውን የአግላይነት ጨዋታ ህግ ጥሰው፤ የዘረኝነትን ሰንሰለት በጣጥሰው፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ስላከበሩና ስላስከበሩልን ወደናቸዋል። አልፎ ተርፎም ኢህአዴግን ወደ አንድነቱ ጎራ በመደመራቸው አተረፉ እንጂ፤ አልከሰሩበትም።

እንዲህም ሆኖ ግን… ‘እንደህወሃት አይነት የኢህአዴግ ድርጅት ከጎናቸው ነው’ ለማለት ድፍረቱ የለንም። በዚህ ምክንያት የጎደለውን ለመሙላት ነው ከጎናቸው ለመሆን የምንገደደው። ከተራ ተቃውሞ ጀምሮ እስከ መግደል ድረስ… የደረሰባቸውን መገፋት ስላየን ነው በመውደድ መደመርን የመረጥነው። ይህ ብቻ አይደለም… ዶ/ር አብይ አህመድ ከኢህአዴግነቱ የበለጠ ለኢትዮጵያዊነቱ የበለጠ ዋጋ በመስጠቱ፤ ‘አንድ በሚያደርገን ኢትዮጵያዊነት ላይ መነጋገር እንችላለን’ብለን ስለምናምን ነው… የመደመራችንን ውጤት ያልጠላነው። ደግሞም “የመለያየትን ግድግዳ እንናድ” ሲባል… “ለማፍረስማ ማን ይችለናል?” ብለን ለጉዞ ተሰናዳን። ችግሩ ያለው ግድግዳው ተንዶ የሚሰራውን ድልድይ ስናስብ፤ የመገንባት ልምድ ስለሌለን ይሆናል… ገደላገደሉ ካሁኑ በዝቶብናል።

ጎበዝ! ከድልድዩ ግንባታ በፊት እና በኋላ ያለውን ውጣ ውረድ ማሰቡ ራሱ ያደክማል። ይህን ጉዳይ አድካሚ የሚያደርገው ደግሞ በግንባታው ላይ የሚሳተፉት ኢትዮጵያውያን ገና በአንድ የሃሳብ መስመር መጓዝ አለመቻላቸው ነው፡፡ ሁሉም ሰው አንድ ሊሆን አይችልም፤ ቢያንስ ግን ለአንድ አላማ መነሳሳት ለቁምነገር ያበቃናል። አሁን ችግር ያለው ወደ አንድ አላማ የሚወስደንን አቋራጭ መንገድ እየዘጋን፤ ረዣዥም እና ውዥምዥም መንገዶችን መምረጣችን ነው። ለምሳሌ ያህል ዶ/ር አብይ አህመድ ሲመጣ፤ የተቃዋሚ ወይም የዲያስፖራ ድምጽ በመሆን የሚታወቁት “እንደታማኝ በየነ አይነት ሰዎች እንዲያስተዋውቁት ይደረግ” የሚል ሃሳብ ሲመጣ፤ አከርካሪያቸውን የተመቱ ያህል የሚያማቸው ሰዎች አሉ። ታማኝ እንዳይቀርብ የሚቃወሙ ካሉ አጭሩን መንገድ አራዘሙት ማለት ነው። ጃዋር መሃመድ መገኘቱ ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ “ጉዳት አለው” ብለው የሚያስቡ ብቻ ሳይሆን፤ የተቃዋሚዎች ስም ሲጠራ ቁርጠት የሚይዛቸው አይጠፉም። ሌላውን ትተን… ለምሳሌ ኮ/ል ጎሹ ወልዴ ተገኝተው ለአስር ደቂቃ እንዲናገሩ ቢደረግ ችግሩ ምኑ ላይ ነው?

“ዶ/ር አብይ ሲመጣ ከጋዜጠኞች ጋር ግልጽ ውይይት ያድርግ…” ሲባል ነገሩን ደጋግመው የሚያስቡበት ሰዎችም አሉ። ነገሩ ሁሉ የሚመስለው ዶ/ር አብይ አህመድ መድረክ ላይ ወጥቶ ለ45 ደቂቃ ያህል ከተናገረ በኋላ በጭብጨባ፣ በጩኸት እና በሆታ አገሩን አቅልጠን እንድንለያይ የተፈለገ ይመስላል። መቼም ወደነዋልና “ይሄም ይሁን!” ብለን ልናልፈው እንችላለን። ነገር ግን ገና ዝግጅቱ ሳይደረግ በእለቱ መውለብለብ ስለሚገባው ሰንደቅ አላማ ድልድል የሚያወጡና የሚከራከሩና ሰዎች አልጠፉም። በዚህ ሁሉ መሃል ደግሞ ቲ-ሸርት እና ሰንደቅ አላማ በመሸጥ ስለሚያገኙት ትርፍ የሚያስቡም ብዙ ናቸው።

በዚያ ላይ ገና ካሁኑ የማፈንገጥ አዝማሚያ የሚያሳየው ህወሃት ምን እንደሚያስብ ለማወቅ እንቸገራለን። ዶ/ር አብይ በሌለበት… ‘አዲስ አበባ ላይ መፈንቅለ መንግስት ያደርጋሉ’ ብለን ባናስብም፤ ሌላ የማተራመስ ስራ ላለመስራታቸው ምንም ዋስትና የለንም። እንዲያውም የህወሃት ነገር ሲነሳ አንድ ጨዋታ ትዝ አለን። ነገሩ እንዲህ ነው።

ሰውየው አንድ የድሮ ቤተ መቅደስ ከፈተና ሊገባ ሲል፤ አምላክ በራዕይ ተገልጾለት… “አንተ መልካም ሰው በህይወትህ ምን ብሰራልህ ትወዳለህ?” ይለዋል።

ሰውየውም፤ “ወደ ኢትዮጵያ በአውሮፕላን መመላለስ ሰለቸኝ። እናም ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመኪና የምመላለስበት ትልቅ ድልድይ ስራልኝ።” ይለዋል።

አምላክም፤ “ይሄ እንኳን ምህንድስናው ትንሽ ከበድ ይላል። በዚያ ላይ የምንጠቀምበትን ብረት እና ኮንክሪት በአትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ ማሳረፉ ከባድ ነው።” ይለውና ሌላ ምኞት ካለው ይጠይቀዋል።

ሰውየው ትንሽ አሰበና፤ “እንግዲያው ህወሃት ስለዶ/ር አብይ ምን እንደሚያስብ የማውቅበትን ፀጋ ስጠኝ።” ይለዋል።

ጥያቄው የከበደው አምላክ፤ “እኔ የምልህ… የድልድዩ ስፋት አስር ሜትር ይሁን ወይስ ሃያ?” በማለት የድልድዩን ስራ ለማከናወን እቅድ ማውጣቱን ቀጠለ። የህወሃትን ልብ ለማወቅ አስቸጋሪ ከመሆኑ የተነሳ፤ ካሜሪካ ኢትዮጵያ የሚያገናኝ ድልድይ መስራት ሊቀል እንደሚችል የሚያመለክት ምሳሌያዊ ጨዋታ ነው።

ለነገሩ ህወሃትን እንላለን እንጂ፤ በተቃዋሚ ወይም ተፎካካሪ ወገን ያለነው ሰዎች በድልድዩ ስራ ላይ ገና አልመከርንበትም። ግድግዳውን ካፈረንስን በኋላ፤ የምንሰራው ድልድይ ወደ ብሔራዊ እርቅ የሚወስደን መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። የሚሰራው ድልድይ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትህን፣ ነጻ ምርጫን፣ ነጻ ፕሬስን፣ በነጻነት መደራጀትን የሚያስገኝ ለመሆኑ ተጨባጭ ዋስትና ልናገኝ ይገባል። ወደዚያኛው ምዕራፍ የሚያደርሰን፤ ድልድይ በጠንካራ መሰረት ላይ መጣሉን ማረጋገጥ ይኖርብናል። እንደዚያ ካልሆነ በቀር “ለማፍረስ አንደኛ ነንና” ምኑንም ከዳር ሳንደርስ በራሳችን ላይ ገደል እንዳይናድብን መጠንቀቅ ብልህነት ነው።

ከላይ የዘረዝረነው አብዛኛው ጉዳይ በስነ ልቦና ራሳችንን ያዘጋጀናል በሚል ያቀረብነው ነው። ተጨባጭ ወደሆነው ቁምነገር ስናመራ ግን በመሬት ላይ ያሉት አንዳንድ እውነታዎች የሚያስፈሩ ናቸው። ለምሳሌ በዋሺንግተን ኮንቬንሽን ሴንተርሰላሳ ሺህ ሰው ያህል በነጻ እንዲታጎር ነው ውሳኔ ላይ የተደረሰው። ይህ ቀላል የሚመስል፤ ነገር ግን ከበድ ያለ ጉዳይ ነው። ልብ ብላቹህ ከሆነ ገና ቀኑ ሳይደርስ የዋሺንግተን ዲሲና አካባቢው ህዝብ ለዝግጅቱ ተነሳስቷል። እናም ዶ/ር አብይ አህመድ የሚያደርገውን ንግግር ለማዳመጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠር ህዝብ በኮንቬንሽን ሴንተር ይታደማል ተብሎ ይጠበቃል። መግቢያው ደግሞ በነጻ እንዲሆን ነው የተደረገው። ከ30 – 40 ሺህ ህዝብ በነጻ ከመግባቱ በፊት እና ከገባ በኋላ ሊፈጠር የሚችለውን የሴኩሪቲ ችግር ምን ያህል አስበንበታል?

በመጀመሪያ ደረጃ በአንዳንድ ዝግጅቶች ላይ ክፍያ የሚደረገው፤ ራሱን ያረቀ እና ምራቁን የዋጠ ሰው እንዲመጣ በማሰብ ጭምር ነው። አሜሪካ ውስጥ… እንኳንስ አዋቂው ቀርቶ ልጆች እንኳን ባቅማቸው አስር እና ሃያ ዶላር የመክፈል አቅም አላቸው። ሰው ገንዘብ ከፍሎ ሲገባ፤ ለከፈለበት ጉዳይ ዋጋ ይሰጠዋል፤ ወደአዳራሹም ውስጥ ሃላፊነት ጭምር ተሰምቶት ይገባል። ከዚያ ውጪ በነጻ ተግበስብሶ ሲገባ የMob mentality ይዞ ነው የሚደመረው። ልብ በሉ! መግቢያው በነጻ በሚሆን ግዜ ከዝግጅቱ በፊት እራስን አደራጅቶ ለመግባት እድል ይፈጥራል። አሜሪካ ውስጥ ነጻ የሆነ ነገር ባለቤት እንደሌለው ተራ ነገር ይቆጠራል። በዚህ ወቅት ተመሳሳይ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ያለምንም ተጽዕኖ እራሳቸውን አደራጅተውና አንድ ላይ ሆነው ለመግባት እድል ያገኛሉ። እንዲህ በተከፋፈለ ህብረተሰብ ውስጥ፤ ህዝብን የመከፋፈል ችሎታ ያለው ህወሃት… ይሄንን አጋጣሚ ሊጠቀምበት እንደሚችል ማሰብ ብልህነት ነው።

ሌላው ቀርቶ “ፀብ ያለው በዳቦ” እንዲሉ በዚህ አይነት ተደራጅተው የገቡ ሰዎች፤ የጸባቸውን መጀመሪያ፤ ሰው ይዞት በሚገባው መፈክር ወይም በሚያውለበልበው ሰንደቅ አላማ ሊሆን ይችላል። በሰንደቅ አላማችን ላይ የሰይጣን አምላኪዎች የሚጠቀሙበትን የተከበበ ኮከብ ማየት የማንፈልገውን ያህል፤ ልሙጡን አረንጓዴ ቢጫ እና ቀይ ባንዲራ ሲያዩ የሚያማቸው ብዙ ሰዎች መኖራቸውን መዘንጋት አያስፈልግም። በሌላ በኩል የኦነግ ባንዲራ ሲውለበለብ፤ አላስፈላጊ መፈክሮች ሲስተጋቡ ይሄንን መቋቋም የማይችሉ ሰዎች ይኖሩ ይሆናል። በዚህ መሃል እንደኳስ ሜዳ አንዱ ሌላውን ቢተናኮስ እና ረብሻ ቢነሳ፤ “አሳፋሪ” ድርጊት ተብሎ ይታለፍ ይሆናል፤ በያንዳንዳችን ላይ ሊፈጥር የሚችለው ጠባሳ ግን ከበድ ያለ ነው የሚሆን።

በአጠቃላይ… መግቢያው በነጻ እንዲሆን የተወሰነው አገር ቤትም ይሁን አሜሪካ፤ ውሳኔው ትክክል አይደለም። መግቢያውን በነጻ በማድረግ ህዝብ እየተጋፋ እንዲገባ ከሆነ የተፈለገው፤ ዝግጅቱን የታሰበበት አላማ ምንም ያህል ቅንነት ያለው ቢሆንም፤ በውጤቱ ግን  ሃሳብ ሊሆን ይችላል። እናም “ልዩነትን እናፈርሳለን፤ ድልድይ እንገነባለን!” ብለን፤ ድልድዩን ጭምር እንዳናፈርሰው መጠንቀቅ ጥቅም እንጂ ጉዳት የለውም።  ይህ ማለት ግን ሰው ገንዘብ ከፍሎ ስለገባ ከላይ የተገለጹት አሉታዊ ነገሮች አይኖሩም አንልም… በብዙ መጠን ግን ሊቀንሰው እንደሚችል እናምናለን።

በሰለጠነው አለም እንደ ቲኬት ማስተር ያሉ ቲኬቱን በድረ ገጽ ላይ የሚሸጡ፤ ካስፈለገም በር ላይ ሽያጩን የሚያከናውኑ፤ የራሳቸው ሴኩሪቲ የሚያዘጋጁ፤ የተሰበሰበውንም ገንዘብ ከወጪ ቀሪ በትክክል ሰርተው በተመደበው የባንክ አካውንት ውስጥ ማስቀመጥ የሚችሉ ትላልቅ ካምፓኒዎች አሉ። እነዚህን መጠቀም ይቻላል። ገቢውንም ቢሆን… ለምሳሌ በሚቀጥለው አመት የሰሜን አሜሪካን ኳስ ጨዋታ አትላንታ መርቸዲስ ቤንዝ ስቴድየም ማድረግ ፈልገን ትንሽ የገንዘብ እጥረት ስለሚኖርብን ለፌዴሬሽናችን ቢሰጥልን አንጠላም። ይህ ካልሆነም አገር ቤት ለሚገኙ የበጎ አድራጊ ድርጅቶች ቢከፋፈል ማንም ቅር የሚለው የለም። ይህ ካልሆነም ገቢው ለተፈናቀሉ ወይም ከእስር ቤት ከወጡ በኋላ መውደቂያ አጥተው ጎዳና ላይ ለቀሩ ወገኖች ሊሰጥ ይችላል። ገንዘቡ ይምጣ እንጂ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ቀዳዳ ብዙ ነው። መገናኘታችን ካልቀረ፤ በገንዘቡ የልዩነታችንን ብቻ ሳይሆን… የድህነትን ግድግዳ ንደን… ጥቂቶችም ቢሆኑ ወደ ተሻለ ህይወት የሚሄዱበትን ተጨማሪ ድልድይ ብንሰራ ደግ ነበር።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here