Home News and Views ግራ አጋቢ ምክር በውጭ ጣልቃ ገቦች (ጌታቸው አስፋው -የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ)

ግራ አጋቢ ምክር በውጭ ጣልቃ ገቦች (ጌታቸው አስፋው -የብሔራዊ ኢኮኖሚ ዕቅድ ባለሙያ)

ታዳጊ አገራት በቀጥታ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ሊገቡ ስለማይችሉ በቅድሚያ በኢኮኖሚ ልማት ራሳቸውን ማሳደግ አለባቸው ብለው ያማከሩት በገበያ ኢኮኖሚ ፍልስፍና ያደጉ ምዕራባውያን ናቸው፣ ከጊዜ በኋላ ሐሳባቸውን ቀይረው የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራም ነድፈው ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ግቡ ያሉትም እነሱው ናቸው፡፡ ከቅኝ ግዛት ማብቃት ጀምሮ እስከ ግሎባላይዜሽን በነበረው ጊዜ የእያንዳንዱ አገር ኢኮኖሚ ግንኙነት የተመሠረተው በኹለትዮሽ የአገራት ንግድ ስምምነት ላይ ስለነበረ፣ ታዳጊ አገራት ራሳቸውን ችለው በኢኮኖሚ ልማት ፍልስፍና ለአገራቸው የሚበጅ የውስጥና የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ቢያድጉ ምዕራባውያንን የሚጎዳቸው ነገር ስለሌለ አልተቃወሟቸውም፡፡

በግሎባላይዜሽን ዘመን ግን በሌላ አገር ጥሬ የተፈጥሮ ሀብት ለማደግ የንግድ ትስስር መፍጠርና በሌላ አገር ርካሽ ጉልበት ለመጠቀም በውጭ አገር መዋዕለንዋይ ማፍሰስ ተፈልጎ ምዕራባውያን መንግሥታት በዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ተጽዕኖ ታዳጊ አገራት የገበያ ኢኮኖሚን እንዲከተሉ ግፊት አደረጉ፡፡ የውስጥና የውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት ፖሊሲያቸው የዓለም ዐቀፍ ንግድን እንዳያደናቅፍ ብለው ከለከሏቸው፡፡ ለአገራቸው ከማሰብ ይልቅ ለዓለም እንዲያስቡ መከሯቸው፡፡ የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራም ወይም አንዳንዴ እንደሚጠራው የዋሽንግተን መግባቢያ ስምምነት ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ለታዳጊ አገራት በሚሰጡት ብድርና እርዳታ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ለማስገባት በቅድመ ሁኔታነት እንዲያሟሉ የነደፉት ፕሮግራም ነው፡፡

ይህን ፕሮግራም ብዙ ታዳጊ አገራት አልጠቀመንም ብለው ሲተውት፣ ዓለም ዐቀፍ ተቋማቱ ያልጠቀማቸው ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ስላላደረጉት ነው ይላሉ፡፡ የፕሮግራሙ ዋና ዓላማ ብሔራዊ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት እና ከግሎባላይዜሽን ጋር አብሮ ለመራመድ ለንግድና ለውጭ ኢንቨስትመንት በርን ክፍት ማድረግ ናቸው፡፡ ፕሮግራሙ ታዳጊ አገራት መፈጸም ያለባቸውን ግዴታዎች በአጭር ጊዜና በረጅም ጊዜ ከፋፍሎ ያስቀምጣል፡፡

የአጭር ጊዜ ግዴታዎች ብሔራዊ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የሚወሰዱ እርምጃዎች ሲሆኑ በፕሮግራሙ ውስጥ የሚከተሉት ነጥቦች ይጠቀሳሉ፡ የወለድ መጣኝን በማሳደግና የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትን በመገደብ ኢኮኖሚውን አኮማታሪ ጥብቅ የጥሬ ገንዘብ ፖሊሲ መከተል፣ የመንግሥትን መዋቅር አሳንሶ በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖረውን ሚና መቀነስና የበጀት ጉድለትን ማስወገድ፣ የውጭ ምንዛሪ መጣኝን በማርከስ በውጭ ኢኮኖሚ ግንኙነት የተንቀሳቃሽ ሂሳብ ጉድለትን ማስወገድ፣ የምግብ ድጎማን ማስቀረት፣ የመንግሥት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ዋጋ መጨመር፣ የአገር ውስጥ ብድር መጠንን መቀነስ፣ የዋጋ ንረትን መቆጣጠር ናቸው፡፡

የረጅም ጊዜ ግዴታዎች የመዋቅር ለውጥ ለማምጣት ከሚወሰዱ እርምጃዎች ውስጥ፣ ንግድን ነጻ ማድረግና ለአገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ከለላ አለመስጠት፣ የመንግሥት ድርጅቶችን ወደ ግል ማዞር፣ በገበያዎች ውስጥ የመንግሥት ቁጥጥርን ማስቀረት፣ አዳዲስ የገንዘብ ተቋማትን መፍጠር፣ ሙስናን መከላከልና መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ ኤክስፖርት ተኮር የውጭ ንግድ ፖሊሲን መከተል፣ የሰነድ ገበያዎችን ጨምሮ የውጭ መዋዕለንዋይን ማስተናገድ፣ የግብር ገቢን ማሳደግ ናቸው፡፡
የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራሙ በልማት ኢኮኖሚ አመለካከት ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ታዳጊ አገራትን ወደ ገበያ ኢኮኖሚ እንዲቀየሩ አድርገዋቸዋል፡፡ አንዳንድ ታዳጊ አገራት ግን በእርዳታ አሰጣጥና በሌሎች ምክንያቶች ተጽዕኖው ቢያይልባቸውም ከገበያ ኢኮኖሚው ይልቅ በልማት ኢኮኖሚ ፍልስፍናቸው ጸንተው መቆየትን መርጠዋል፡፡ የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራሙን ላለመቀበል የምርጫቸውን ትክክለኛነት ለሕዝባቸው ለማስረዳት ምሳሌ አድርገው የሚያቀርቡትም በሰፊ የመንግሥት ተሳትፎ የልማት ኢኮኖሚ ፍልስፍና የደቡብ ምሥራቅና ደቡብ እስያ አገራት በአጭር ጊዜ ውስጥ አድገው፣ የሕዝባቸውን የኑሮ ደረጃ ማሻሻላቸውን ነው፡፡ ሆኖም የሀብታቸው መጠን ዝቅተኛ በሆነበትና በፍጥነት ወደ ኢንዱስትሪ ምርት ሊገቡ ባልቻሉ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት ውስጥ፣ የልማት ኢኮኖሚና የገበያ ኢኮኖሚ ካልተደጋገፉ አንዱ የወሰደውን ሀብት ሌላው ስለሚያጣው በሀብት ሽሚያ ይጋጫሉ፡፡ ይህ ግጭትም ከተመጣጣኝ የመንግሥትና የግል ሀብት ይዞታ ድርሻ በራቀና በቀረበ ቁጥር ግጭቱ የሰፋና የጠበበ ይሆናል፡፡

ስለዚህም የእነዚህ አገሮች የመጨረሻው ዕድላቸው የኑሮ ደረጃው ዝቅተኛ በሆነ ግብር ከፋይ ሕዝባቸው ወጪ መሠረተልማት ገንብተው ምዕራባውያኑንም ምሥራቅያውያኑንም በመለመን ርካሽ ጉልበትና ድንግል መሬት ተጠቅመው መዋዕለንዋይ አፍስሰው ለውጭ የሚቀርብ የገበያ ሸቀጥ አምርተው እንዲሸጡ መጋበዝና ከሚገኘው ትርፍራፊ መጠቀም መሆኑን እያየን ነው፡፡

ደርግ በኢሕአዴግ ሲተካ የበለጸጉት አገራት እና ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ታዳጊ አገራትን ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ለማስገባት የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራም ቀርጸው የተንቀሳቀሱበት ጊዜ ስለነበር፣ ኢትዮጵያም ይህንን የመዋቅር ማሻሻያ ፕሮግራም ስትተገብርና በደርግ መንግሥት ተወርሰው የጋራ ሀብት የነበሩትን ድርጅቶች የማስተዳደር ልምድ ለሌላቸው ግለሰቦች ስትቸበችብ ከኖርች በኋላ ከኢትዮጵያውያን ዘመን አቆጣጠር 1990ዎቹ ጀምሮ ፊቷን ወደ ቻይና በማዞር የልማታዊ ኢኮኖሚ ተከታይ አገር ነኝ አለች፡፡

ሶቭየት ኅብረት በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያዎቹ ዓመታት የሶሻሊስት ኢኮኖሚን መገንባት እንደጀመረች ለመሠረተልማትና ትላልቅ ኢንዱስትሪ ግንባታ ቅድሚያ ትኩረት በመስጠት፣ መላውን አገር በኤሌክትሪክ አጥለቀለቀች፤ የባቡር ትራንስፖርት ተስፋፋ፤ የብረት ማቅለጥና ማሺነሪ ታላላቅ ኢንዱስትሪዎችም ገነባች፤ በጦር ኀይልም ከአውሮፓ የሚወዳደራት አልተገኘም፤ ከአሜሪካ የምትፎካከር ኹለተኛ ኀያል አገር ሆነች፡፡

ለዜጎቿ የፍጆታ ሸቀጦችን በማቅረብ ግን ከውጭ ሸምተው የሚኖሩት ታዳጊ አገራት ሳይቀሩ ይበልጧት ነበር፡፡ የሶቭየት ኅብረት ውድቀት ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እስከዛሬም ድረስ ምንም እንኳ የተፈጥሮ ሀብት በመታደል ከዓለም ቀዳሚ አገራት አንዷ ብትሆንም፣ በነፍስ ወከፍ ገቢ መጠን ብዙ ትናንሽ አገራት ይበልጧታል፡፡ በቅርቡ በኢኮኖሚ ቀውስ ስትናወጥ የነበረችው ግሪክ በነበራት ሃያ ስምንት ሺሕ ዶላር ነፍስ ወከፍ ገቢ የሩስያን ሰባት ሺሕ ዶላር ነፍስ ወከፍ ገቢ በአራት እጥፍ ትበልጥ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በያዘችው የልማታዊ መንግሥት አካሄድ የወደፊት እጣ ፋንታዋ ከእስያ ልማታዊ አገራት ጋር የሚመሳሰል ሳይሆን ከቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት ጋር የሚመሳሰል ሊሆን ይችላል፡፡ የገበያ ኢኮኖሚውን እና የልማት ኢኮኖሚውን ባለማመጣጠን የዜቿን የቁሳዊ ሀብት ፍላጎት፣ እንደ ተቀረው ዓለም ለመኖር መንፈሳዊ ጥማት ልታረካ ሳትችል ትቀራለች፡፡ ምናልባት ለውጭ መዋዕለንዋይ አፍሳሾች የሰዉን ጉልበትና የተፈጥሮ ሀብትን በርካሽ ዋጋ በመሸጥ የግሎባላይዜሽን ፍልስፍና መሠረት ኢትዮጵያ ከሶቭየት ኅብረት የተለየ ሁኔታ ሊገጥማት ይችል ይሆናል ይህ ግን ምናልባት ብቻ ነው፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here