Home News and Views የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች አለመስማማት ወደ ‘አጋር ፓርቲዎቹ’ እየተዛመተ ይሆን?

የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች አለመስማማት ወደ ‘አጋር ፓርቲዎቹ’ እየተዛመተ ይሆን?

በሶማሊ ክልል ሰሞኑን የታየው ችግር ራሱን የቻለ ነው ወይስ በኢሕአዴግ አባላት መካከል ያለው እሰጥ አገባ ያስከተለው ትኩሳት? የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች እርስበርሳቸው እየተዋቀሱ ‘አጋር’ ከሚሏቸው ፓርቲዎች ጋር ተስማምተው መቀጠል ይችላሉ? እነዚህ እና መሰል ጥያቄዎችን ለመመለስ በሶማሊ ክልል የሆነውን እንደማሳያ ላንሳ።

ኢሕአዴግ የአራት ክልሎች እና የፌዴራል መንግሥቱ ገዢ ፓርቲ ነው። የሌሎቹ አምስት ክሎች ገዢ ፓርቲዎች ኢሕአዴግ ‘አጋር’ በሚል ይጠራቸዋል። በምርጫ ቦርድ አሠራር ‘አጋር’ አደረጃጀት ስለሌለ እንደተለያዩ ፓርቲዎች ነው የሚመለከታቸው። በርግጥ የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎችም ለብቻቸው ተመዝግበዋል። ነገር ግን በጋራ በኢሕአዴግ ሥም ስለተመዘገቡ አንድነታቸው በምርጫ ቦርድ ይታወቃል፤ የጋራ መተዳደሪያ ደንባቸውም ምርጫ ቦርድ ውስጥ ተሰንዶ ተቀምጧል። ‘አጋር ድርጅቶቹ’ ጋር ኢሕአዴግ ያለው ግንኙነት ግን በምርጫ ቦርድ ያልተመዘገበ፣ ደንቡም ግልጽ ያልሆነ ነው። የሚታወቅ የጋራ የሥራ አስፈፃሚ የላቸውም። ይህ ጉዳይ ኢሕአዴግ የእነዚህን አምስት ክልላዊ መንግሥታት “ሁኑ እንዳላቸው ብቻ የሚሆኑ አሻንጉሊቶች ናቸው” ለሚለው ሕዝባዊ ጥርጣሬ ማረጋገጫ ሆኖ ከርሟል። ምክንያቱም ‘አጋር ድርጅቶቹ’ ከኢሕአዴግ ያፈነገጠ ውሳኔ አሳልፈው አያውቁም። ሰሞኑን በኢትዮጵያ ሶማሊ ክልል የተፈጠረው ችግር እና የፌዴራል መንግሥቱ ሊቆጣጠረው አለመቻል ግን የዚህ አዛዥ-ታዛዥነት ዘመን ሊያበቃ እንደሚችል አመላክቷል።

የሶማሊ ክልል የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ከፀደቀ ወዲህ ባሉት 23 ዓመታት ውስጥ አሁን በጊዜያዊነት የተቀመጡትን ክልላዊ ፕሬዚደንት ሳይጨምር፥ 10 ፕሬዚደንቶችን አፈራርቋል። ከፕሬዚደንት አብዲ ሞሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌይ) በስተቀር ቀደሚዎቹ ዘጠኝ ፕሬዚደንቶች መካከል ከ3 ዓመት በላይ ሥልጣን ላይ ለአንድ ሙሉ የምርጫ ጊዜ ያገለገለ ፕሬዚደንት በክልሉ አልነበረም። ፕሬዚደንት አብዲ ኢሌይ ግን ለ8 ዓመታት ሥልጣን ላይ በመቆየት የክልሉን ሪከርድ ሰብረዋል። የክልሉ አመራሮች ሥልጣን ላይ የማይቆዩት በፖለቲካዊ አለመረጋጋት ጦስ ነው።

ከዚህ አለመረጋጋት በመነሳት የፕሬዚደንት አብዲ ኢሌይ ይህን ያክል ሥልጣን ጨብጦ መቆየት መቻል አስገራሚ ሊሆን ይችላል። ፕሬዚደንት አብዲ ኢሌይ ወደ ሥልጣነ መንበሩ ከመምጣታቸው በፊት፥ በወቅቱ በሽብርተኝነት የተፈረጀውን የኦጋዴን ብሔራዊ  ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ሠራዊትን ከኦጋዴን ጠራርጎ ለማስወጣት የተቋቋመውን ‘ልዩ ፖሊስ’ መርተዋል። ፕሬዚደንት አብዲ ኢሌይ የክልሉን ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላም ቢሆን ‘ልዩ ፖሊስ’ በክልሉ የሚንቀሳቀስ ትልቁ የታጠቀ ኃይል ሆኖ ከመቀጠሉም ባሻገር፥ ከፍተኛ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶችን በማደረስ ሥሙ ይነሳል። ከሁሉም በላይ ግን የፕሬዚደንቱን ሥልጣን ለማስጠበቅ መሣሪያ ሆኗል በመባል ደጋግሞ ይወቀሳል።

የሶማሊ ክልል ነዳጅ የተገኘበት መሆኑ የክልሉን ሀብት አስጠብቃለሁ በሚለው ኦጋዴን እና በፌዴራል መንግሥቱ መካከል ዘላቂ ውጥረት ፈጥሯል። ይህም ላለፉት ፖለቲካዊ አለመረጋጋቶች መንስዔ ነበር። በፕሬዚደንት አብዲ ኢሌይ ይመራ የነበረው የሶማሌ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ሶሕዴፓ) ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር እጅ እና ጓንት ሆኖ በመሥራት ክልሉ ውስጥ ያለውን ተቃውሞ በኃይል በመቆጣጠር ለክልሉ ጊዜያዊ መረጋጋት አስገኝቶ ነበር። ምንም እንኳን ክልሉ “የኮንትሮባንድ ንግድ መነኻሪያ ሆነ” የሚል አቤቱታ በተደጋጋሚ ቢሰማም፥ ኢትዮጵያ ከአል ሻባብ ጋር በምታደርገው ውጊያ ክልሉ ወሳኝ ጂኦግራፊያዊ ፋይዳ ነበረው። ስለዚህም የፌዴራል መንግሥቱ የክልሉን መንግሥት ጥፋቶች በዝምታ ሲያልፍ ነበር። እንዲያም ሆኖ በፌዴራሉ መንግሥት ውስጥ የነበረው ፖለቲካዊ ውክልና እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም።

አሁን በኢትዮጵያ የፖለቲካ ለውጦች መካሔድ ሲጀምሩ የፕሬዚደንት አብዲ ኢሌይ መንግሥት አዲስ ፈተና ሆኖ ብቅ ብሏል። ክልሉ የሰብአዊ መብቶች አያያዙ፣ የሙስና መነኻሪያነቱ እና ሌሎችም ጉዳዮች ለውጥ እንዲደረግበት ያላሰለሰ ጫና ፌዴራል መንግሥቱ ላይ አስከትሏል። ነገር ግን ወትሮም ያለቁጥጥር ያደገው የክልሉ ‘ልዩ ኃይል’ የፌዴራሉን ጣልቃ ገብነት በቀላሉ የማያስተናግደው ከመሆኑም ባሻገር፣ የፌዴራላዊ መዋቅር የሆነው የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብት በፌዴራሉ ጣልቃ ገብነት ተነጠቅን የሚል ቅሬታ አስከትሏል። የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ሶሕዴፓ የኢሕአዴግ አባል ድርጅት ባለመሆኑ፥ ከዚህ በፊት በፓርቲ ውስጥ ንግግር በቀላሉ ሲፈቱት የነበረውን ችግር ሶማሊ ክልል ላይ መፍታት አልተቻላቸውም።

ኢሕአዴግ ‘ጥልቅ ተሐድሶ’ አካሔዳለሁ በሚል የፓርቲ አባላቱን ሹም ሽር ካካሔደ በኋላ የአባል ፓርቲዎቹ የውስጥ ለውስጥ ግንኙነት እንደሻከረ ደጋግሞ ይታያል። አንዳንዴ አባል ፓርቲዎቹ መካከል ያሉት ልዩነቶች የተቀናቃኝ ፓርቲዎች እያስመሰላቸው ነው። ቀድሞ “በሕወሓት የበላይነት ይመራል” እየተባለ የሚታማው ይህ ግንባር፥ የዚህ የአለቃ እና ምንዝር ግንኙነት እንዲቀየር በመሥራቱ ይመስላል አንዱ አባል ፓርቲ ሌላኛውን አባል ፓርቲ ሲያብጠለጥለው ማየት የተለመደ ሆኗል። ይህ የአባል ፓርቲዎቹ ግንኙነት መሻከር ወደ ‘አጋር’ ፓርቲዎቹም የተላለፈ ይመስላል።

ቀጣይ የኢሕአዴግ ‘አጋር’ ፓርቲዎች ሁለት አማራጮች የሚከተሉት ናቸው። ከኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች መርጠው ለአንዱ በመወገን ሌላኛው ላይ የፖለቲካ ብልጫ ማሳየት፤ አልያም ነጻነታቸውን አስከብረው በራሳቸው መወሰን። ይሁን እንጂ፣ እነዚህ የኢሕአዴግ ‘አጋር’ ፓርቲዎች የሚገዟቸው ክልሎች የሕዝብ ቁጥራቸው እንዲሁም የፖለቲካ ልኂቃኖቻቸው ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ በተናጠል ፌዴራል መንግሥቱ ውስጥ የሚኖራቸው ተፅዕኖ ደካማ ነው። ይህንን አስቀድሞ የተረዳ የሚመስለው እና በኦሕዴድና ብአዴን ትብብር ተገፍቻለሁ የሚል ቅሬታ ያለው ሕወሓት፥ ከነዚህ የኢሕአዴግ ‘አጋር’ ድርጅቶች ጋር በመተባበር የተወሰነ ተፅዕኖ ለመፍጠር ይሞክር ይሆናል። የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ሰሞኑን በፌዴራሉ እና ሶማሊ ክልላዊ መንግሥታት መካከል የነበረውን ውጥረት አስመልክቶ የወሰደው ፌዴራል መንግሥቱን ያወገዘ አቋም የዚህ አዝማሚያ ተደርጎ ተወስዷል። በዚህ አካሔድ ተመሳሳይ ችግሮች ከሌሎቹ አራት ክልሎች – አፋር፣ ጋምቤላ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ሐራሪም ሊከተል ይችላል ብሎ መጠበቅ የዋህነት አይሆንም።

በኢሕአዴግ ውስጥ በኦሕዴድ እና በብአዴን የተጀመረው አመፅ ወደ ‘አጋር’ ፓርቲዎቹ የመዝለቁ ነገር አይቀሬ ይመስላል። የኦሕዴድ እና የብአዴን አመፅ በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ የሚገባንን ክብር እና ውክልና አላገኘንም የሚል ከሆነ፥ ኢሕአዴግ ‘አጋር’ የሚላቸው ፓርቲዎች ደግሞ ጭራሹኑ የገበታው ተቋዳሽ አይደሉም ማለት ይቻላል። ኢሕአዴግ ይህንን ለመፍታት የሚችልባቸው ሁለት አማራጮች አሉት። አንዱ አማራጭ ሁሉንም ‘አጋር’ ፓርቲዎች የግንባሩ አባል እንዲሆኑ ማድረግ ሲሆን ሌላኛው አማራጭ ደግሞ ግንባሩን በማፍረስ እና ወደ ኅብረ ብሔራዊነት በመቀላቀል ሁሉንም ቀጥተኛ አባላት ማድረግ ነው። ይሁን እንጂ፣ ኢሕአዴግ በአራቱ አባል ድርጅቶቹ መካከል ሠላም ማውረድ እስኪችል ድረስ ከ‘አጋር’ ፓርቲዎቹ ጋር ኅብረት አይኖረውም። ስለዚህ የሶማሊ ክልሉ ቀውስ እና ትርምስ በሌሎችም ክልሎች የመከሰት ዕድሉ ሰፊ እና አስፈሪ ይሆናል።
በፍቃዱ ዘ ኃይሉ

አርያም ተክሌ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here