(መታሲቢያነቷ – ለታማኝ በየነ)
እልል አለች ኢትዮጵያ – እጆቿን ዘርግታ ወደ ሰማይ፣
ታማኝ ውድ ልጇ ዘወትር – እንዳልተለያት ስታይ፤
“ይደልዎ!” አለ ሕዝቡ – ያገር-አድን ቅኔ እንደተዘረፈ ሁሉ
በ”አቋቋም”፣ በአካሄዱ… ተማርኮ በውብ ቃሉ፤
የጥበብ ነው ተፈጥሮው – ውበት ማስተዋልን የታደለ፣
ላገር፣ ለሕዝብ በእምነት አድሮ፣ – የፍቅር ህያው ሃውልት የተከለ፤
ታማኝ ለሙያው ክህሎት – የመድረኩ ጸዳል አብሪ፣
በፈጠራው መንፈስ-አዳሽ – አገር ወዳድ ወገን አኩሪ፤
“የትዕይንተ-ጥበባት” ሞተር – የብሔራዊ ትያትር ዋልታ፣
የመድረኩ መሪ ተዋናይ – ጥበብ ለተጠማ አለኝታ፤
በ”ዘመነ-ውጥረት” ማግስት – የታዳሚው ሳቅ አፍላቂ፣
ኢትዮጵያዊው ብላቴና – ትኩስ ህይወት ተፍለቅላቂ፤
ባለቅባት፣ ባለጸጋ – ተሰጥዖ ለኪነት፣
በቀልዳ-ቀልድ እያዋዛ – አሳላፊ ክቡር እውነት፤
ከ”ፋሲሊደስ”..እስከ “ሕዝብ ለሕዝብ”… ከ”ሮሃ” እስከ “ደመራ”፣
አንጸባራቂ ኮከብ – በኪነቱ አለም ጎራ። …
የሕዝብን ድምጽ አስተጋቢ – ሃሳቡን ተንታኝ ያለፍርሃት፣
ከ”ስቴድዮም” እስከ “ዲሲ” – ከ”ሲ-ኤን-ኤን” እስከ “ኢሳት”፤
ከ”አኬልዳማ” እስከ “ፌዝ-ራሊዝም” – በመልሶ ማጥቃት ዝና፣
በመረጃ እሚያጋልጥ – የ”ኢቲቪ”ን ጉድ ገመና፤
ከአሜሪካ እስከ አውሮፓ – ከኦሺያንያ እስከ አፍሪካ፣
እንደ አበባ ጽጌረዳ – በየዕለቱ እሚፈካ።
የመጥምቁ አምሳያ – ጭው ባለው በረሃ ጯኺ፣
ከድቅድቅ ጨለማ ውስጥ አሻግሮ – መጪዋን የብርሃን ቀን ጠቋሚ።
“እኔ በቃላት አጠምቃችኋለሁ፤ በመንፈስ የሚያጠምቃችሁ ከኋላ ይመጣል፤”
እያለ ለኢትዮጵያውያን – እሚረጭ ያንድነት ፈዋሽ ጸበል።
ከባድ ሸክም ያረፈበት – የትውልዱ መሪ አውራ፣
ብሩህ ተስፋን ሰንቆ – ለጨለመበት እሚያበራ፤
የጭንቅ አጋር.. ያገር ሲሳይ – የወገኑ ባላደራ፤