Home News and Views የመደመር ፖለቲካችንና የኔሽን ቢዩልዲንግ ስራችን 

የመደመር ፖለቲካችንና የኔሽን ቢዩልዲንግ ስራችን [ገለታው ዘለቀ]

ለመሆኑ ኔሽን ቢዩልዲንግ ምንድን ነው? ከሚለው እንጀምር:: ምሁራን ስለዚህ ንድፈ ኣሳብ ምን ይላሉ? የፖለቲካ ሊቆች ኔሽን ቢዩልዲንግ ማለት ብሄራዊ ማንነትን ማነጽ ነው ይላሉ። ከዚህ ብያኔ የተወሰኑ ቁልፍ ጉዳዮችን እንወስዳለን። አንደኛ ማነጽ (construction) የሚለውን እና ብሄራዊ ማንነት (national identity) የተባሉትን ወሳኝ ቃሎች። ኔሽን ምንድን ነው? ማነጽ ማለትስ ምንድን ነው? ኔሽን ማለት በአንድ የተወሰነ ሰማይና ምድር ክልል ውስጥ የሚኖር የራሱ መንግስታዊ መዋቅርና ሲስተም የዘረጋ፣ የአንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማህበርተኛ ዓለም የመዘገበውና እውቅና የሰጠው ህዝብ ማለት ነው። ኔሽን ማነጽ ማለት  በአንድ ኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ማህበር ስር ልዩነትንና አንድነትን አቻችሎ ማኖር ማለት ነው። መደመር ማለት ነው በሌላ አነጋገር። በጥንት ጊዜ ኔሽን ቢዩልዲንግ ከባህል ማንነት ጋር የተያያዘ ስለሆነ ኣንድ ብሄራዊ ባህል ለመፍጠር የሚጥር ኣካሄድ ነበረው። ይህ በዘመናዊ የብዝሃነት ንድፈ ኣሳብ የበላይነት ተሸንፏል። በመሆኑም ኣዲሱ የኔሽን ቢዩልዲንግ ስራ የተለያየ ቋንቋና ማንነት ያላቸውን ሁሉ በአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ የማህበር ድንኳን ውስጥ ኣስማምቶ ማኖር ነው። ኔሽን ቢዩልዲንግ ማለት ብሄራዊ ማንነትን የማነጽ ምህንድስና ከሆነ መሃንዲሱ ወይም አናጺውስ ማነው? ስንል ሃላፊነቱን የወሰደው መንግስት ሆኖ እናገኛለን። ታዲያ በርግጥ አንድ ስቴት ስለ ኔሽን ቢዩልዲንግ ማሰብ ከጀመረ ኣንድም በጠገጉ ውስጥ የሰፈረው ህዝብ በሆኑ ምክንያቶች ተናግቷል፣ ወይም የሚያፈርሰው ኣደጋ ከፊቱ ተጋርጧል ማለት ነው። ብሄራዊ ማንነት ኣደጋ ላይ ወድቋል ማለት ነው። አንድ አገር ይህ ችግር ሲገጥመው ስቴት ኣሳብ ይገባውና ስለኔሽን ቢዩልዲንግ ይጨነቃል ማለት ነው። ነገር ግን ለራሱ ያልተደላደለና የተናጋ መንግስት ከሆነ ስለኔሽን ቢዩልዲንግ ማሰብ ብቻ ሳይሆን ስለራሱ ህልውናም ሊያስብ ነው። በኔሽን ቢዩልዲንግ ጊዜ ይህን የምህንድስና ስራ የሚሰራው ስቴት በመሆኑ ኣቅም የሌለው ቅቡል ያልሆነ መንግስት ወይም ስቴት ኔሽን ቢዩልድ ሊያደርግ ኣይችልምና። አናጺው ራሱ ችግር አለበትና። የተዳከመ መንግስት ሲኖር፣ ለመፍረስ የደረሰ ኔሽን ሲኖር ይህን ኣገር ለማትረፍ የስቴት ቢዩልዲንግ ስራውንም የኔሽን ቢዩልዲንግ ስራውንም ጎን ለጎን መገንባት ተገቢ ይሆናል። ስቴት ቢዩልዲንግ ማለት የተቋማትና የኢንፍራስትራክቸር ግንባታ ስራ ማለት ነው። የተጠናከረ ተቋም ያለው መንግስት ለኔሽን ቢዩልዲንግ ስራ ጥሩ ኣናጢ ሊሆን ይችላል።

በዚህ በዛሬው ውይይታችን ረገጥ ኣድርገን የምንነጋገረው በስቴት ቢዩልዲንግ ንድፈ ኣሳብ ዙሪያ ሳይሆን በኔሽን ቢዩልዲንግ ንድፈ ኣሳብ ላይ ነው። በዚህ መሰረት የሚከተሉትን ቁልፍ ጉዳዮች እያነሳን እንወያይ።

በመጀመሪያ ደረጃ የኔሽን ቢዩልዲንግ ኣሳብ የምናነሳው ኔሽን ሊፈርስ ስለሆነ ወይም ኣደጋ ስለተጋረጠበት ነው ብለናል። ታዲያ ኔሽንን ምን ምን እክሎች ሊያፈርሱት ወይም ሊያናጉት ይችላሉ? ብለን መጀመሪያ እንወያይ።

ኔሽን የመፍረስ ኣደጋ የሚያንዣብብበት በሚከተሉት ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች ነው። እነዚህ ዋና ዋና ምክንያቶች

 1. የኔሽን ሃርድዌር  መፍረስ ሲኖር
 2. የኔሽን ሶፍትዌር መናጋት ሲኖር ነው። 

በሃርድ ዌር ስር ሊገለጹ የሚችሉ የኔሽን መፍረስ ኣደጋዎች ምን ምን ናቸው ? ብለን እንጠይቅ። የሰው ልጅ ተሰባስቦ ደካማም ሆነ ጠንካራ  መንግስት የሚባለውን ጠገግ የሚቀልሰው በሆነ ሰማይ ስር መሬት ላይ ነው። የዚህን ዓለም ኑሮ የሚገፋበት፣ ቤት ሰርቶ የሚኖርበት፣ ከፍሬው በልቶ የሚጠግብበት፣ ኣምልኮን የሚያደርግበት፣ ሞቶ የሚቀበርበት ግዛት ይሰራል። በዚህ ግዛቱ ውስጥ ሰማይና ምድሩ፣ የተፈጥሮ ሃብቱ፣ እንስሳቱና እጽዋቱ ሁሉ የጋራው ሆኖ እንዲኖር ያስፈልጋል። ኔሽን የሚባለውና ብሄራዊ ኣንድነት የሚገለጸው በዚህ ግዛት ስር የሰፈረው ህዝብ የዚህ ግዛት ባለቤትነቱን ሲያረጋግጥ ነው። ይህ የሰው ልጅ ተሰባስቦ የሚኖርበት ግዛት ኣንድ የኔሽን ሃርድዌር ወይም ፊዚካል  ማንነት ነው። የመሬት አንድነት ማለት ነው። ብዙ የአፍሪካ ሃገራት እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ኔሽን ኣይባሉም ነበር። በቅኝ ግዛት ስር ስለነበሩ ግዛት ስላልነበራቸው። ኢትዮጵያ ግን ነጻ ሃገር እንዴውም ኩሩ ነጻ ህዝብ ተብለን የኖርነው ግዛታችን ስላልፈረሰ ነው። ኩሩ ነጻ ህዝብ ዛሬ ስለኔሽን ቢዩልዲንግ በጣም መጨነቍ ኣሳዛኝ ቢሆንም በፍጥነት ይህንን ችግር የመቅረፍ ሃላፊነት ኣለብን።

ኔሽን ግዛቱ ሲገሰስ ኔሽንነቱ ይፈርሳል። በታሪክ አጋጣሚ አይሁዳውያን ለረጅም ዘመን በዓለም ዙሪያ ተበትነው ኖረዋል። ታዲያ ቆይተው የኔሽን ቢዩልዲንግ ኣሳብ ሲመጣ መሰባሰብና የእስራኤልን መንግስት ዳግም መመስረት ነበረባቸውና እነሆ እንደገና  መንግስታቸውን መስርተው በግሩም ሁኔታ የመንግስትን ስርዓት አዋቅረው በአንድ ጠገግ ስር ይኖራሉ። እስራኤላውያን ዛሬ በዓለም ላይ ጠንካራ ከሚባሉ ሃገራት መካከል አንድ የማይከፋፈል ጠንካራ ኔሽን ገንብተው ኔሽን ሆነው ይኖራሉ። የእድገታቸውን ፍጥነት ስናይ ኣስደናቂ የኔሽን ቢዩልዲንግ ምህንድስና ጥበባቸው እንደመማለን። አይሁዳውያን ተበታትነው በሚኖሩበት ዘመን ኔሽን ሊባሉ ኣይችሉም ነበር። ኔሽን  የሚባለው ፖለቲካዊ ንድፈ ኣሳብ በቦታና በጊዜ በሰማይና በመንግስት መዋቅር የሚገለጽና የሚገዛ ነውና።

በመሆኑም ይህ የግዛት ኣንድነት ጉዳይ ዋና የኔሽን ቢዩልዲንግ ኤለመንት ነውና ግዛቱ በውስጥ በብሄር ከተሸራረፈ፣ ወይም በውጭ ወራሪ ሃይል ከተገሰሰ ያ ኔሽን ስለኔሽን ቢዩልዲንግ እንደገና ያስባል ማለት ነው። በውስጥ የተከፋፈለ ካርታ ሲፈጠርና የተፈጥሮ ሃብት ሽሚናያ ውጊያ ሲፈጠር ያን ጊዜ በዚያ ጠገግ ስር የሰፈረው ሰው ስለኔሽን ቢዩልዲንግ ኣስቦ ሃርድዌር ቤቱን ሊሰራ ካልተነሳ ያ ጠገግ ውሎ አድሮ ይፈርሳል። ይሄ እንግዲህ ሃርድዌር የሆነው የኔሽን ግንባታ ጉዳይ ነው።

ሁለተኛው ኔሽንን እንዲፈርስ የሚያደርገው ወይም ኣደጋ ላይ የሚጥለው ነገር  ደግሞ የኔሽኑ ሶፍትዌር ሲናጋ ነው። በዚህ ኣገባብ የኔሽን  ሶፍትዌር የምላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር ዝቅ ሲል ኣስረዳለሁ።

 1. ማንነት

አንድ ኔሽን ባለብዙ የቋንቋና ባህል ማንነት ወይም የአንድ ቋንቋና ባህል ማንነተ ባለቤት ሊሆን ይችላል። ብዙህ በሆነ ኔሽን ውስጥ ብሄራዊ ማንነትና የቡድን ማንነት ተከባብረው መኖር አለባቸው። በዚያ ጠገግ ስር በብሄራዊ ማንነትና በብሄር ማንነት ወይም በቡድን ማንነት መካከል መራኮት ከተነሳ ያ ቤት ሊፈርስ ነውና ስለኔሽን ቢዩልዲንግ የምናስብበት ሰዓት ተፈጠረ ማለት ነው። ሶፍትዌራችን ኣደጋ ላይ ነው ማለት ነው። ኔሽን ቢዩልዲንግ ማለት ብሄራዊ ማንነትን ማነጽ ሲሆን ይህ ማንነት በአካባቢያዊ ማንነት ማስፈራሪያ ከደረሰው፣ ካነሰና ከኮሰሰ በፍጥነት የኔሽን ቢዩልዲንግ ኣሳብ መነሳት ኣለበት።ይሄ አደገኛ ምልክት symptom ነው

 1. ነጻነት

የነጻነት እጦት ጥግ ሲመታ በጠገጉ የሰፈረው ሰው ሊበተን ይሻልና ነጻነት ማለትም የቡድንም የግለሰብም ነጻነት ካልተከበረ ኔሽን ይፈርሳል። በነጻነት እጦት በዓለማችን ብዙ መንግስታትና ህዝቦች ፈርሰዋል። አሁንም ለመፍረስ ኣዝምመው ያሉ ቤቶች ብዙ ናቸው። የፌልድ ስቴት ኢንዴክስን ብታዩ ኣንዳንድ ሃገራት በመንግስታቸው ክፋት የተነሳ ቤታቸው አዝሟል::

 1. መተማመን  (trust )

መንግስት የትረስትን ባሮ ሜትር እየመዘነ ስለኔሽን ቢዩልዲንግ ሊያስብ ይችላል። የማህበራዊ ሃብት መፍረስ ኔሽንን ያፈርሳል። በመሆኑም ቀጥታ መተማመን ማለትም በመንግስትና በህዝብ መካከል መተማመን ከወረደ፣ በግለሰቦችና በቡድኖች መካከል መተማመን ከጠፋ ኔሽን ሊበተን ይችላል። የኔሽን ቢዩልዲንግ ስራ ኣንድ ጊዜ ተጠናቆ አልቆ ለሁለተኛ ጊዜ የማንመለስበት ነገር ኣይደለም:: መተማመንን የሚያወርዱ የፖለቲካና የማህበራዊ ቀውሶች ሲፈጠሩ ኢኮኖሚያዊ እኩል ኣለመሆን ሲፈጠር ኔሽን ይፈረካከሳል። ባይፈርስም በኔጌቲቭ ሰላም እንዲኖር ያደርጋልና ይህን ጊዜ መንግስት ለኔሽን ቢዩልዲንግ ስራ ታጥቆ መውጣት ኣለበት።

 1. የዜጎች ስነልቡናዊ ትስስር

የጠገጉ ጠባቂ ስለኔሽን ቢዩልዲንግ ያሳስበዋል። ዜጎችን ስነልቡናቸውን የሚያራርቅ የፖለቲካና የማህበራዊ የኢኮኖሚ ከባቢዎች ካሉ እነሱን የማፍረስና ኔሽንን የመጠበቅ የማነጽ ስራ ይጠይቃል። ህዝቡን የሚያገናኘው ሶፍት ኢንፍራስትራክቸር ከፈረሰ የስነ ልቡና መራራቅ ያመጣል። የህብረት ቋንቋ መኖር የባህል መካፈል ነገር ከሌለ መቀራረብ ኣይኖርም። ሌላው ከፍተኛ ችግር ደግሞ የለሂቅ ክፍፍል ከፍ ማለት ነው። የለሂቅ ክፍፍል ሲጨምር ኔሽን ይፈርሳል።

 1. ህጎችና ኣሰራሮች የፖለቲካ ትርክቶች

ህጎችና ኣሰራሮች የፖለቲካ ትርክቶች ኔሽንን ሊያፈርሱ ይችላሉ። የስቴትና የፌደራል መንግስት ህገ-መንግስታት ከተጣረሱ፣ የፖለቲካው ትርክት ከህብረተሰቡ እሴቶች ጋር የሚጋጭ ሲሆን ህብረተሰቡ የማይፈልጋቸው ህጎች ስራ ላይ ከዋሉ፣ ህገ መንግስቱ ብሄራዊ ማንነትን ፈራሽ ካደረገው በርግጥ ያቺ ሃገር በፍጥነት ስለኔሽን ቢዩልዲንግ ልታስብ ይገባል።

 1. ባህላዊና ሃይማኖታዊ ተቋማት

የህብረተሰቡ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ተቋማት ሲነኩ በዚያ ጠገግ ስር የሰፈረውን ሰው ሊያፈርሰው ይነሳል። ስለሆነም ይህ ችግር ሲከሰት ያቺ ምድር ስለኔሽን ቢዩልዲንግ ማሰብ ኣለባት።

 1. የኔሽን መሃንዲሱ ክህሎት

ኔሽንን ያንጻል የተባለው መሃንዲስ ስቴት ሲሆን ይህ መሃንዲስ ብልሃት ከጎደለውና በሃይል ለማነጽ ከጣረ ሁል ጊዜም ሊፈርስ የደረሰን ቤት ሊሰራ ይችላል። ቡድኖች በግድ ኣሲምሌት እንዲያደርጉ በማድረግ ኔሽን ቢዩልድ ለማድረግ ዘመኑም ኣይደለምና ይህ ኣይነቱ ኣካሄድ ኔሽንን የበለጠ ያናጋልና መንግስት ይህን ጊዜ ቆም ብሎ ሊያስብ ጥበብ የተሞላበትን ኔሽን ቢዩልዲንግ ስራ ሊሰራ የሚገባው ሰዓት ላይ ይደርሳል። ለኔሽን ቢዩልዲንግ ተመራጩን ንድፈ ኣሳብ መምረጥና መተግበር ተገቢ ይሆናል።

 1. ታሪክ

ኔሽን የማነጽ ሃላፊነት ያለበት መንግስት ፖለቲካው በታሪክ ጠባሳዎች ላይ ካተኮረና ቅራኔን ካራገበ ኔሽንን እያፈረሰ ይሄዳልና ይህቺ ሃገር ቆም ብላ ማሰብ ይጠይቃታል።

 1. State building

የተጠናከረ ስቴት የማነጽ ስራ ካልተሰራ ኔሽን ሊፈርስ ይችላል። በመሆኑም ኔሽን አንጻለሁ የሚለው መሃንዲስ መንግስት ወደራሱ በማየት ተቋማቱን ማነጽ ራሱን ቀድሞ መገንባት ይጠበቅበታል ይህ ካልሆነ የሱ ጦስ ለኔሽን መፍረስ ይተርፋልና ያቺ ሃገር ቆማ የምታስብበት ሰዓት ነው።

 1. የኢኮኖሚ እኩል ኣለመሆን

በጠገጉ ውስጥ የኢኮኖሚ እኩል ኣለመሆን  ከተንሰራፋ ኔሽን ቤቱ   ሊያዘም ይችላል። የብዙዎችን ቤት ያፈረሰ ይህ ነውና አንድ ሃገር በከፍተኛ የኢኮኖሚ እኩል ኣለመሆን ህይወት ከቆየ ነሽን ኣደጋ ላይ ነውና በዚህ ጊዜ ስለኔሽን ቢዩልዲንግ ይታሰባል።

ታዲያ አንድ ሃገር ስለኔሽን ቢዩልዲንግ ታጥቃ እንድትሰራ የሚያደርጉ ሁኔታዎች እነዚህ ከላይ የተገለጹት ከሆኑ በኢትዮጵያ ሁኔታ የኔሽን ቢዩልዲንግ ኣስፈላጊነት በተለይ በአሁኑ ሰዓት ምን ያህል ነው? የሚል ጥያቄ ማንሳት ኣለብን። በኢትዮጵያ ሁኔታ ከፍ ሲል ያነሳናቸው የኔሽን መፍረስ ወይም መናጋት ምልክቶች ሁሉ በሃርድዌርና በሶስፍትዌር ጎኖቻችን አካባቢ  ታይተዋል። የብሄራዊ ማንነትና የብሄር ማንነት ግጭት ውስጥ ገብተናል፣ ታሪክ ችግር ሆኖብናል፣መተማመን ወርዷል፣ የኢኮኖሚ እኩል ኣለመሆን በሰፊው ኣለ፣ የውስጥ ድንበር ፈጥረን በተፈጥሮ ሃብት ይገባኛል እንዋጋለን፣ የክልል ህገመንግስትና የፌደራል መንግስት ህግጋት እርስ በርስ ይጋጫሉ፣ የስቴት ቢዩልዲንጋችን የተጠናከረ ኣይደለም፣ መተማመን ተንኗል፣የባህልና የሃይምኖት ተቋማት ተደፍረው ቆይተናል፣ ነጻነት ኣጥተን ሰንብተናል፣የስነልቡና መያያዛችን ወርዷል። በአንድ ቃልም ነሽናችንን የሚያናጋ ወይም ሊያፈርሱ የሚችሉ ምልክቶች፣ ሲምፕተሞች ሁሉ ደምቀው ታይተዋል። ስለሆነም ኢትዮጵያ ምንም እንኳን ከወራሪ ሃይላት ራሷን የጠበቀች ኩሩ ኔሽን ነጻ ህዝብ ብትባልም በውስጥ በገጠሟት ችግሮች ምክንያት ዛሬ ከማንም በላይ ስለኔሽን ቢዩልዲንግ ስለስቴት ቢዩልዲንግ የምትነሳበት ወሳኝ ሰዓት ላይ ነን።ነገሩ ኣሳዛኝ ነው::

ታዲያ ኢትዮጵያችን ስለኔሽን ቢዩልዲንግ ኣስባ የፈረሰውን ቅጥር ለመጠገን ከወጣች የኔሽን የማነጹን ስራ በብልሃት ልታደርገው ይገባል። ብልሃት የጎደለው ያልተጠና ምህንድስና ሃገራችንን ሊጠብቅ ኣይችልም። ስለሆነም ለሃርድና ሶፍትዌር ኔሽን ቢዩልዲንግ ስራችን የሚከተሉትን ኣሳቦች ኣዋጣለሁ።

 1. ኣዲስ ቃል ኪዳን ማድረግ

ማህበረሰብ የሚቆመው በኪዳን ነው። በዚህ ቃል ኪዳን ላይ ግን እምነት ሊኖረው ወይም ሊስማማ ይገባል። በተለይ ሃርድዌር ቅጥራችንን ለማነጽ ቡድኖች ሁሉ የተቀራመቱትን መሬትና ሰማይ ለብሄራዊ ማንነት መስዋእት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።ኢትዮጵያ ውስጥ ያለን ቡድኖች አለም የማያውቀውን የኔሽን መዓት ፈጥረን ኔሽን እና ናሽናሊቲ እያልን የሃገራችንን መሬት መቀራመት ኣይጠበቅብንም። የተፈጥሮን ሃብት፣ ሰማዩን፣ በኢትዮጵያ ካርታ ውስጥ ያለውን ነን ሁሉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሊገዙት (own ሊያደርጉት ይገባል) በዚህ ኢትዮጵያውያን ቃል መግባት ሲችሉ የኔሽን ቢዩልዲንግ መሰረታችን በጸና አለት ላይ ይቆማል። ይህንን ስናደርግ ሃርድዌር የማነጽ ስራችንን ኣሳካን ማለት ነው። መሬት የብሄራዊ ማንነት መገልጫ ከሆነ ብሄራዊ ማንነትን የሚሰራውን ኣንዱን ጉዳይ ገነባን ማለት ነው።

 1. የአርበኞች ቤት ማነጽ (software)

ማንነቶች እየተናከሱ ግጭት ውስጥ ስለቆየን የሃገራችን የማንነት ኣያያዝ ሁል ጊዜም ችግር ላይ ስለቆየ ለዚህ ለብሄር ማንነት መገለጫዎች ወይም ለባህላዊ ማንነት አንድ የአርበኞች ቤት ማቋቋም ለኔሽን ቢዩልዲንግ ስራችን ወሳኝ ነው። ይህ ቤት የብሄራዊ ማንነትና የብሄር ማንነት ግጭቶችን ቀንሶ ማንነትን ጠብቆ የቡድንን ጥያቄ ይመልሳል። የአርበኞችን ቤት ካቋቋምን የሶፍትዌር ግንባታችንን ሰራን ማለት ነው። በውስጥ መሬቷ የተፈረካከሰባትን ሃገር ከጠገንን በሁዋላ የአርበኞች ቤት ከሰራን የሶፍት ወር ጥገና ሰራን ሰርተን ኔሽን ቢዩልድ አደረግን ማለት ነው።

 1. የጠፉ ባህሎችን የማስመለስና የካሳ ዘመን ኣዋጅ

አንዱ የኔሽን ቢዩልዲንግ ምህንድስናው ኤለመንት የጠፉ ባህሎችን ማስመለስ (Restore ማድረግ)ና ካሳ መሆን ኣለበት። ኢትዮጵያ ያጣቻቸውን ዋና ዋና እሴቶች ማስመለስ ይቻላል። ይህ ሂደት ቡድኖች በአሲምሌሽን ኣጣን የሚሉትን ለመካስ፣ ለብሄራዊ ፈውስና ለብሄራዊ ኣንድነት መጠናከር ይረዳል።

 1. መተማመንን በሁሉም ኣቅጣጫ መገንባት

መተማመን ሲጠፋ ቤታችን ስለሚፈርስ መንግስት ይህንን ለመስራት መትጋት ኣለበት። አንዱ የኔሽን መፍረስ ምልክት ወይም symptom የመተማመን መትነን ነው።

 1. ታሪክ ላይ የሚኖረንን መረዳት ማረቅ

የዓለምን ታሪክና የሰው ልጆችን እድገት ታሪክ ማገናዘብ የፖለቲካ ቤታችንን ከቅራኔ ማራቅና የፍቅርን የአንድነትን ድልድይ መስራት ለኔሽን ቢዩልዲንግ ወሳኝ ጉዳይ ነው።ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታ ስንጠቀም መጥፎውን ኣንመርጥም። ምክን ያቱም መጥፎውን ኣንቀጥልበትም። የምንመርጠው ደግ ደጉን ነው። ደግ ደጉን ስለምንቀጥልበት። ስለዚህ ፖለቲካ ወደፊት የሚያይ በመሆኑ ደግ ደጉን እየመረጠ ሊቀጥልበት ለፕሮፓጋንዳው ሊጠቀምበት ሲችል ነው ብሄራዊ ኣንድነት የሚገነባው::(software)

 1. የፌደራል ስርዓት ማነጽ

ለብሄራዊ ማንነት ግንባታ ዋና ጉዳይ ነው። ህጉ የክልሉን ማንነት ከብሄራዊ ማንነት በላይ ካፈረጠመው የፌደራል ስርዓቱ የተከፋፈለ ማህበረሰብን ከፈጠረ የጋራው ቤታችን ፈረሰ ማለት ነው። የስፕሪሜሲ ክለውስ ኣንቀጽ ለፌደራል ተሰጥቶ የመገንጠል ኣንቀጽን ማውጣት የኔሽን ቢዩልዲንግ ምህንድስና ዋና ተግባር ነው። ህገ-መንግስቱ ለፌደራል መንግስቱ ልእልና በማጎናጸፍ ፈንታ መገንጠልን ካካተተ ብሄራዊ ማንነት አደጋ ላይ ይወድቅብናል። መገንጠልን ተመክተው ብሄሮች የተሰበሰቡበት ቤት ቤቱን በአሸዋ ላይ እንደሰራ የሰነፍ ኣገር ቤት ያስመስልብናል። ኢትዮጵያችን የጎበዝ ኣገር ናትና ይህንን እሴት ዘወትር መጠበቅ ኣለብን። መገንጠልን መከታ ኣድርገን የማይፈርስ ኔሽን ቢዩልድ ልናደርግ ኣንችልም። ለመሆኑ መገነጣጠል ብንሻ ሰማዩን ምን ልናደርገው ነው?

በተጨማሪም የፌደራል ስርዓቱን ስናሻሽል ከዘውግ ፖለቲካ ማላቀቅና ፖለቲካውን በብሄራዊ ኣንድነት ስር ማሳደር አንድ የብሄራዊ ማንነት መገንቢያ የሶፍትዌሪ ኢንጂነሪንግ ተግባር ነውና ሃገራችን ከዘውግ ፖለቲካ መላቀቅ ኣለባት። የተደመረ ህዝብ መደመሩን ብሄራዊ ኣንድነቱን የሚገልጸው በአንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማህበርተኝነት ነው።

 1. የክልልና የፌደራል ህግጋትን ማጣጣም

ኔሽንን ኣቅፎ የሚይዘው ከፍተኛ ህግ የተጻፈም ይሁን ያልተጻፈ መገሰስ የለበትም። ይህ ህግ በክልል ከተገሰሰ ኔሽን ቢዩልድ ኣናደርግምና ህግጋትን ማጣጣም ኣንዱ የምህንድስናው ስራ ነው። ህገ-መንግስቱ አንቀጽ 32 ንኡስ አንቀጽ 2 ላይ ሰው በመረጠው ቦታ ጎጆውን ሰርቶ መኖር እንደሚችል ይገልጻል። የቤንሻንጉል ጉምዝን ክልል ህገ-መንግስት ለአብነት ብናይ አንቀጽ 2 ላይ በክልሉ ውስጥ ሌሎች ህዝቦች እንዳሉ ቢታወቅም የክልሉ ባለቤት ግን በርታ፣ ጉሙዝ፣ ሽናሻ፣ ማኦና ኮሞ ናቸው ይላል። ይጋጫል።

 1. ስነ- ልቡናዊ ትስስርና ኔትወርክ

ስነ ልቡናዊ ትስስር ለማምጣት የኪነ ጥበብ ስራዎች ሃላፊነት ኣለባቸው፣ የትምህርቱ ካሪኩለም ይህን ሊያገናዝብ ይገባል። ሌላው የሶፍት ወር ጥገና ደገሞ የሚገለጸው በቋንቋ አጠቃቀም ነው። ኔሽን ቢዩልድ እናድርግ ካልን ሶፍት ኢንፍራ ስትራክቸር ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ አንድ የዮኔን ቋንቋ መኖርና ሁሉም ቋንቋዎች ደግሞ በታችኛው የስልጣን ርከን ላይ ኦፎሺያል እንዲሆኑ በማድረግ ኔሽንን ማነጽ ይቻላል። የተደመረ ህዝብ መሆንን በዚህ ማሳየት ይቻላል። ሌላው በኔሽን ውስጥ ስነልቡናዊ ትስስር የሚያመጣው ትልቅ ነገር የለሂቅ ክፍፍል መቀነስ ነው። የአማራ ለሂቃን፣ የኦሮሞ ለሂቃን፣ የትግሬ ለሂቃን፣ የደቡብ ለሂቃን ፣እያልን የተማሩ መሪዎችን የየጎጥ አዋቂዎች ካደረግን ከፍተኛ የስነ ልቡና ልዩነት ያመጣል። ለሂቃኖችን የጉራጌ፣ የወላይታ፣ የሲዳማ እያልን ከከፋፈልን ኢትዮጵያ ለሂቅ የላትም ማለት ነው። ለሂቃን የኢትዮጵያ ለሂቅ ለመባል  መደመር ኣለባቸው።

 1. የብሄራዊ ማንነት መገለጫ ምልክቶችን ከፍ ማድረግ

እንደ ባንዲራ፣ ብሄራዊ መዝሙር፣ ህገ-መንግስት ከፍ ኣድርጎ   ማሳየትና ህዝቡ ፍቅር እንዲኖረው መስራት ኣንዱ የኔሽን ቢዩልዲንግ ስራ ነው።

 1. የኢኮኖሚ እኩልነትን ለማምጣት የሃብት ሪዲስትሪቢዩሽ ሁል ጊዜም በማያቋርጥ ሳይክል ውስጥ እንዲኖር ማድረግ ይገባል። አገሪቱ ጥሪት በያዘች ቁጥር በየአንጓው የሃብት ስርጭቱን በማስተካከል፣ እድሎችን እኩል እኩል ለማድረግ በመጣር ነው ኔሽንን የምንገነባው። ሃብት በአንድ ኣካባቢ ለረጅም ጊዜ ከቆየና ሪድስትሪቢዩሽን የትውልድን እድሜ ከፈጀ ኔሽን ይናጋልና ይህንን ማስተካከል ለኔሽን ቢዩልዲንግ ወሳኝ ነው።

በአጠቃላይ ሃገራችን ኢትዮጵያ እጅግ በጣም ስለኔሽን ቢዩልዲንግ የምታስብበት ከባቢ ውስጥ ስላለች መንግስት የምህንድስና ስራውን በፍጥነት ሊሰራ ይገባል:: የለውጡ ሃይል ራሱን እያጠናከረ በአንድ በኩል የስቴት በሌላ በኩል  የኔሽን ቢዩልዲንግ ስራውን ጎን ለጎን መስራት ኣለበት። ኢትዮጵያውያን ኩሩ ህዝብ እንደሆንን ሁሉ የውስጥ ችግራችንን ኣቃለን ጠንካራ ኔሽን እንገነባለን የሚል ተስፋ አለኝ። በአጠቃላይ የኔሽን ቢዩልዲን ስራችን የተቃና የሚሆነው በመደመር መርህ ፖለቲካችንን፣ ኢኮኖሚያችንን፣ ማህበራዊ ጉዳያችንንና ታሪካችንን ማስታረቅ ስንችል ነው።  መደመርን መርህ እያደረግን የፈረሰውን ሁሉ ስንጠግን ሄደን ሄደን ሰርተን የምናገኘው የኔሽን ግንባታ ስራችንን ነው። ለዚህ ነው የመደመር መርህ ኣብሮነትን የሚያጠናክር በመሆኑ ለኔሽን ቢዩልዲንግ ስራ ዋና ሃይል ማመንጫ አድርገን ልናየው የሚገባው። እስካሁን ካሉት ንድፈ ኣሳቦች ለኔሽን ቢዩልዲንግ ምርጥ ንድፈ ኣሳብ የሚባለው ብዝሃነት ነው። ብዝሃነትን የሚያስተናግድ ስርዓት መፍጠር ነው ኔሽንን ቢዩልድ ማድረግ ማለት። መደመር በተለይ የኔሽን ቢዩልዲንግ ስራ ዋና መርህ ነው። ኔሽን ቢዩልዲንግ ማለት በተፈጥሮው መደመር ማለት ነው። ዋናው ጉዳይ በኢኮኖሚ ስንደመር የቡድን ኢኮኖሚን ትተን በጋራ ስንሰራ፣ የዘውግ ፖለቲካ ትተን ተደምረን በአንድ ብሄራዊ ማንነት ስር ፖለቲካ ስናራምድ፣ ባህልና ቋንቋዎቻችንን የኔ ያንተም ነው ስንባባል፣ የተፈጥሮ ሃብታችንን የኔ ያንተም ነው ስንባባል ነው ተደመርን የሚባለው። ይህ ሂደት ደግሞ ኔሽን ቢዩልዲንግ ነውና መደመር የኔሽን ቢዩልዲንግ፣ የስቴት ቢዩልዲንግ መሳሪያም ፍጻሜም ነው።ስለዚህ ኢትዮጵያውያን እንራመድ እንደመርና የፈረሰውን ቤት ሰርተን እንደ ቀድሞው ሃያል ሃገር እንሁን። ስሜት ላይ የሚደርግ የኔሽን ቢዩልዲንግ ስራ ሩቅ ኣይሄድም። ለኔሽን ቢዩልዲንግ ስራ መደመርን በሁሉ አቅጣጫ በተግባር በህግ ማእቀፍ ማሳየት ኣለብን።ሁልጊዜም መደመር ይሻላል! Better together!

እግዚኣብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

አመሰግናለሁ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here