Home News and Views ትግራይ – ቀጣይዋ የሱማሌ ክልል

ትግራይ – ቀጣይዋ የሱማሌ ክልል [ነፃነት ዘለቀ]

 

በቅድሚያ ከዘመን ወደ ዘመን መሸጋገሪያ ዋዜማ ላይ ቸሩ ፈጣሪ እንኳን በሰላም አደረሰን! 2011ዓ.ም የበርካታ ሀገራዊ ስኬቶች መመዝገቢያ እንዲሆንልን በግል እመኛለሁ፡፡ ወደሚናፍቋት ሀገራቸውና ሕዝባቸው ነገ የሚገቡትን አርበኞች ግንቦት ሰባትን ጨምሮ ሌሎችም ተመላሾች ላገራቸው ያሰቡትና ያቀዱት መልካም ነገር ሁሉ ፍሬ እንዲያፈራና ሀገራችንና ሕዝባችን ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ ዐመጠኞችም አስተዋይ ልቦና ታድለው ሰው እንዲሆኑ እጸልያለሁ፡፡

ሣልረሳው – ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም፡፡ መስከረምም መጣ – ዛሬን ጨምሮ ሦስት ቀናት ብቻ ቀሩት፡፡ ኢንጂኔር ስመኘው በቀለ መላዋን አዲ አበባን ቢንከራተት ራሱን የሚገድልበት ሥፍራ አጥቶ መስቀል አደባባይ ድረስ ሄዶ በገዛ ሽጉጡ ራሱን መግደሉን ፖሊስ ነገረን፡፡ እውነት ሊሆን ይችላል፡፡ እኔ ግን ራሴው እዛው ስሄድ ራሱን ጠይቄው እውነቱን ካልተረዳሁ በስተቀር ይህን የፈጠራ ድርሰት የሚመስል ነገር በጭራሽ አላምንም፡፡ አንዳንድ “እውነቶች” ለመታመንም ላለመታመንም እንደሚያስቸግሩ አሁን ገና ተረዳሁ፤ አፄ ኃ/ሥላሤ ከፕሬዝደንት ኒክሰን ጋር በቤተ መንግሥታቸው እየተጫወቱ ሳለ ለካንስ ኒክሰን የአፄውን ነጠላ ለጊዘው ለብሰዋት ኖሮ “Nixon, go and eat another; answer my singular.” አሉት ይባላል – ነጠላቸውን አረሳስቶ ሊወስድባቸው ሲል “ኒክሰን ሂድና ሌላህን ብላ፤ ነጠላየን መልስ” ለማለት፡፡ ስመኘው ራሱን ገደለ?

ምንም ማድረግ አልችልም፡፡ የሚሰማኝንና የሚታየኝን እናገራለሁ፡፡ ወደፊት እንደሚፈጸም በምናቤ የሚታየኝ ነገር እውን ባሆይን ደስታው አይቻለኝም፡፡ ይሁንና ከነገሮች አካሄድና ከልምድ ተነስቼ ከምናገራቸው ነገሮች ውስጥ የማይናቅ ቁጥር ያላቸው በገሃዱ ዓለም ሲፈጸሙ የማስተውልበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ የተሰማኝን ባልናገር ኅሊናየ አያስቀምጠኝምና ለዛሬ ይችን ታህል ልበል፡፡

አዎ፣ ትግራይ ቀጣይዋ የሱማሌ ክልል ናት፡፡ ግን የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ትስተካከላለች፡፡ ለምን ቢባል እግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ፊቱን ወደ ኢትዮጵያ አዙሯልና፡፡ “እግዚአብሔር” ስል የቋንቋ ጉዳይ ነው፡፡ አላህም ማለቴ ነው፤ ዋቃም ማለቴ ነው፤ ጦሳም ማለቴ ነው፡፡ የአንድ ፈጣሪ ልጆች በስም አጠራር አይጣሉም፡፡

የአብዲ ኢሌ ሶማሌ የአንድ ሰው ንብረት ነበረች፤ አንድ ሰው እንደፈለገው የሚያሽቃንጥባት፣ የሚዘባነንባትና የሰው ደም ሳይቀር እየገበረ ያሻውን የሚያደርግባት የግል ሀብቱ ነበረች፡፡ አብዲ ዕድሜ ለወያኔ ከኤልፓ ምሰሶ ተካይ የቀን ሠራተኝነት በማይም ጭንቅላቱ በአንዴ ተንጠላጥሎ የክልል “መሪ” የሆነ ድፍን ቅል ነበር፡፡ የሚገርመኝ ነገር – አምባገነኖች የሚመርጧቸው አገልጋዮች ማይማንና በጡንቻ የሚያስቡ ናቸው፡- አብነቶችን ባጭር ልጥቀስ – መንግሥቱ ኃ/ማርያም ሽቅርቅሩንና ለስላሳውን ፍቅረ ሥላሤ ወግደረስን ምክትሉ አደረገ -መለስ ዜናዊ ቆዳውን ኃ/ማርያም ምክትሉ አደረገ –  የቬንዞላው ሁጎ ሻቬዝ የከተማ አውቶቡስ ነጂውን ማዱሮን ምክትሉ አደረገ – የራሽው ፑቲን ቅን ታዛዡን ሜድቬዴቭን ምክትሉ አደረገ … ዝርዝሩ ይቀጥላል፡፡ (እነዶ/ር ዐቢይ ይህን ዓይነቱን የአምባገነኖች የተለመደ አሠራር እንዴት እንደሠበሩትና ለዚህ እንደበቁ ሲገርመኝ ይኖራል – by the way ለማለት ነው)፡፡ እናላችሁ  – ያ በጫት የጀዘበ አብዲ ኢሌ የሚሉት የወያኔ ቅልብ ውሻ ያን ሁሉ ግፍና በደል ይፈጽም የነበረው ትግራይ ክልል ከመሸጉ የሕወሓት ወንበዴዎች ጋር በመሻረክ እንደነበር የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ አንድ ሰው እንደዚያ ለመፈንጨት የሚተማመነው ነገር መኖር አለበት፡፡ አሁን ያ ሁኔታ ተለውጦ በሱማሌ ክልል ሰላም እየወረደ ይመስላል፡፡ ጠንቁ ሙሉ በሙሉ እስኪወገድና ቁስሉ እስኪሽር ግን ጊዜ ሊወስድ ይችላል – ያለና የሚጠበቅም ነው፡፡ ብልኅ ሴቶች – እንዲሁም ወንዶች – “የአንድ ቀን መዘዝ ካለ ዘጠኝ ወር አይመዘዝ” እንደሚሉት ባለፉት 30 እና 40 ዓመታት ውስጥ ወያኔ ያሣረፈብን የታሪክ ጠባሳ በቀጣዮቹ አምስትና አሥር ዓመታትም ጥርዥ ብርዥ እያለ ማስቸገሩ አይቀርም፡፡ እንዲያውም ከዚያም ባያልፍ፡፡

ትግራይ ውስጥ መሽገው አመቺ አጋጣሚ እየተጠባበቁ ያሉ ማፊያዎች የትግራይን ሕዝብ በመያዣነት ይዘው እየበጠበጡን ናቸው፡፡ ባለፉት ጥቂት የማይባሉ አሠርት ዓመታት ያደረሱብን ግፍና በድል አልበቃቸው ብሎ አሁንም ገና አሣራችንን ሊያበሉን ዕቅድ በመንደፍ ላይ ናቸው፡፡ ፀሐያቸው ማዘቅዘቋን መረዳት አልፈለጉም፤ አይፈልጉምም፡፡ አለበለዚያ “ከአሁን በኋላ እነሱ አራት ኪሎ ከሚገቡ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብትሾልክ ይቀላል፡፡” የክርስቶስን አነጋገር ስለኮረጅኩ ነው በጥቅስ ምልክት ያስቀመጥኩት እንጂ እውነቱ የአደባባይ እውነት ነው፡፡ ዓለም ታልፋለች እንጂ ወያኔዎች ከእንግዲህ አይሰለጥኑብንም፤ ለክፋታችንና ከፈጣሪ መንገድ ለመውጣታችን ምሥጋን ይንሳውና ከበቂ በላይ ቀጥቅጠው ገዝተውናል፡፡ ቅጣት ደግሞ አመክሮ አለው – እኛም በአመክሮ ከወያኔ ግፈኛ አገዛዝ ነፃ ወጥተናል፡፡ ወያኔ በቀደደው የጎሣ ፖለቲካ ቅኝት ተሰልፎ ወደምንጠየፈው የደምና አጥንት አፈንፋኝ ፖለቲካ የሚጨምረን ሌላ ኃይል እንዳይኖር ይልቁን መጠንቀቅ አለብን፡፡ “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” ነውና በወያኔ ሥልት ሊደንሱ የሚሹ ወርተረኞች አሰፍስፈው እየተጠባበቁ የሚገኙ ይመስላል፡፡

የትግራይ ክልል መሪዎች በአሁኑ ወቅት ከፌዴራል መንግሥቱ አንፃር እየተጓዙ ነገረ ሥራቸው ሁሉ የአብዲ ኢሌን እየመሰለ ነው፡፡ ለማዕከላዊው መንግሥት በፍጹም አይታዘዙም፡፡ በዘረፉት የሀገር ሀብትና የጦር መሣሪያ እየተመኩ ንግግራቸውና መግለጫዎቻቸው ሳይቀሩ አንድ የአውሮፓ ኃያል አገር የሆኑ ያህል በጥጋብ ተወጥረው የሚሠሩትን አጥተዋል፡፡ ካለኢትዮጵያ ሕዝብ ፈቃድና ይሉኝታ በጉልበትና በሥልጣናቸው ወደ ትግራይ ያዘዋወሯቸውን እንደአየር ኃይልና መከላከያን የመሳሰሉ ተቋማትን ወደ ቀድሞ ቦታቸው እንዲመልሱ ቢጠየቁ አሻፈረን እንዳሉ ይነገራል፡፡ በነዚህ እርጉማን አማካይነት ትግራይ እንድትከፍለው የሚጠበቅባት ብዙ ዕዳዎችን እየከመሩባት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ትግራይ ሀገራችን የዕዳ ቀሚሷ ከልኳ እንዳያልፍና ከአሁኑ በበለጠ ሰፍቷት እንዳይንዠረገግባት ጤናማ ተጋሩ አሁን ጊዜ እያለን ይረባረቡ፡፡ “የጠሉት መውረሱ የፈሩት መድረሱ” ያለና የነበረም ነውና ለዚህች የታሪክ ምድር የኢትዮጵያ ፈርጥ ትግራይ አሁን በደኅናው ቀን እንጨነቅ፡፡ ነገር ከተበለሻሸ በኋላ ጸጸት ዋጋ የለውም፡፡

የራያንና የወልቃይትን መሬትና ሕዝብ በጉልበት ወስደው ሲያበቁ የማንነት መብቱ እንዲከበርለት የሚጠይቀውን የነዚያ አካባቢዎች ሕዝብ ድምጹ እንዳይሰማ ልክ እንደምንጊዜውም ሁሉ በኃይል አፍነው እየገደሉትና ወደ እሥር እያጋዙት ይገኛሉ፡፡ ቀድሞ ነገር በአንድ ሀገር ውስጥ የሚኖርን ሕዝብ በድንበርና በክልል እየከፋፈሉ እንዲህ ማሰቃየት አግባብ አልነበረም፡፡ ሁሉም ግዛት የሁሉም የወል ሀብት ሊሆን ሲገባው የእርሻና የማዕድን ሥፍዎችን እየመረጡ ርጥብ ርጥቡን “ይህ የኛ ነው” ደረቅ ደረቁን ደግሞ “ያ የናንተ ነው” ማለት ከቅኝ ገዢዎች አስተሳሰብ የሚመነጭና ከባዕዳን ጋር በሚኖር ግንኙነት የሚተገበር ለአንድ ሀገር ተመሳሳይ ሕዝብ ግን ዕንቆቅልሽ የሆነ ጭራሽ የማይገባ አሠራር ነው፡፡ ወልቃይት የሁሉም ኢትዮጵያውያን እስከሆነ ድረስ “የትግራይ ነው” ብሎ የተጋሩን የወደፊት ኅልውና እስከመፈታተን ሊደርስ የሚችል መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት ዕብደት ይመስለኛል፡፡ ችግሩ የሚብሰው ደግሞ ዕብደትን ለመገንዘብ አለመቻል ነው፡፡ የወያኔዎች ከንቱ ድካም ሻኛና ዳቢትን ተቆጣጥሮ በልፋጭ ቅንጥብጣቢ ሥጋ እንደመዋደቅ የሚወሰድ የሞኝ ፈሊጥ ነው፡፡ በመላዋ ኢትዮጵያ ተሰራጭቶ እንደልቡ ሀብትና ንብረት እያፈራ የሚገኝ ሕዝብ ባለቤት ከሆኑም በኋላ እነዚህ ደናቁርት ወያኔዎች ወደ ልቦናቸው ሊሰበሰቡ አልቻሉም፡፡ ምክንያቱም እልኻቸውና የቂም በቀል ጥማታቸው እየታደሰ እንጂ እየሰከነ ሊሄድ አልቻለምና፡፡ ሌላው ችግር እነሱን አምኖ የሚከተላቸውና የአምልኮት ያህል የሚሰግድላቸው የሰው ቁጥር እነሱንም እስኪያነኾልልና የልብ ልብ እየሰጠ በቀደመው ዕብሪታቸው እንዲነጉዱ ማድረጉ ነው፡፡ “ወይ መዓልቲ!”

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here