Home News and Views ኢመማ ይፈታ!!!

ኢመማ ይፈታ!!! [ከገበያው ንጉሴ ቀድሞ የኢመማ አመራር አባል]

 

ኢህአዴግን ቀድሞ የተገዳደረውና ያጋለጠው አንጋፋው የኢትዮጵያ መመህራን ማህበር መሆኑ የሚታወቅ ነው። ኢህአዴግ ስልጣን እንደያዘ ቀድመው ማህበራቸውን በነጻነት ያደራጁት መምህራን፣ ማህበራቸ‹ው ባቀረባቸው 20 ጥያቄዎች አማካይነት፣ የአካዳሚክ ነጻነት እንዲጠበቅ፣ የትምህርት ፖሊሲው፣ የፓርቲ ፖለቲካ ማሳለጫ እንዳይሆን፣ የጎሳ ፖለቲካው ከሚፈለገው በላይ ንሮ፣ የአገሪቱን አንድነት አደጋ ላይ እንዳይጥልና መሰረታዊ የሰባዊና የመደራጀት መብቶች እንዲከበሩ ጠይቀዋል።

ኢህአዴግ ግን ከቀረቡት ጥያቄዎች ይልቅ እጅግ አድርጎ ያሳሰበው አዲሱ ኢመማ በኢህአዴግ ስር አለመሆኑ ነበር። ፈጥኖም ‘እንደ ደርግ ወታደር መፍረስ ያለበት ድርጅት ነው’ በሚል እሳቤ፣ የማፍረሻ ሰነድ አዘጋጅቶ በየደረጃው  በመተግበር፣ በአመራሩና ደጋፊዎቹ ላይ ዘመተ። ኢህአዴጋዊ መምህራን ማህበር ለማቋቋም ቆርጦ በመነሳትም፣ የማህበሩን ፕሬዝዳንት ዶክተር ታየ ወልደሰማያትን ጨምሮ በርካቶችን አሰረ፣ እሰፋ ማሩን በግፍ በጠራራ ጸሀይ አስገደለ። የማህበሩ ዋና ጸሀፊና ሌሎችም ለስደት ተዳረጉ። ቀሪዎቹ የአመራር አባላት በውጭ ከነበሩት የአመራር  አባላትና ደጋፊዎች ጋር በመቀናጀት፣ ማህበሩን አሳልፎ ላለመስጠት በራሱ በወያኔ ፍርድ ቤት ለአመታት ታገሉ። በመጨርሻ ግን ኢህአዴግ በሰየመው ሰበር ችሎት  ማህበሩ ለኢህአዴግ ሹመኞች እንዲሰጥ ተደረገ።

ማህበራቸውን ለካድሬዎች አሳልፎ ላለመስጠትና መብታቸውን ለማስክበር ሲታገሉ፣ ለስር የተዳረጉ፣ የተገደሉ፣ ከስራቸው የተባረሩና የተፈናቀሉ መምህራን በርካቶች ማሆናቸው የሚታወቅ ነው። ኢህአዴግ በመምህራን ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በሞላ የአገሪቱ ዜጎች ላይ ሲፈጽም በቆየው በደልና ጭቆና፣ ህዝብ ሆ! ብሎ በመነሳቱ፣ አሁን ካለንበት የለውጥ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን። ለውጡ፣ ገና በመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ የሚገኝና ብዙ የሚቀረው ቢሆንም፣ አመራሩ በሺ የሚቆጠሩ እስረኖችን በመፍታቱና፣ ባለፉት አመታት በአገዛዙ ለተፈጸሙ ግፎችና ግድያዎች፣ እስራቶችና ቁም ስቅሎች እውቅና በመስጠት ይቅርታ በመጠየቁ፣ ሊበረታት የሚገባው ነው።

ይሁን እንጂ፣ በኢህአዴግ ተቀፍደው የታሰሩት የሰራተኛና መምህራን ማህበራት አሁንም ታፍነው የተያዙ በመሆናቸው በስልጣን ላይ ያለው የለውጥ ሀይል በዚህ በኩልም ተገቢውን እርምጃ በመውሰድ ማህበራቱን እና ባለቤቶቹን ሊያገናኝ ይገበዋል። አሁን ያለው የኢመማ አመራር በመምህራን ፍላጎትና ምርጫ የመጣ ሳይሆን፣ በኢህአዴጋዊ አደረጃጀት የተስየመ እንደሆነ ሁሉም የሚያውቀው ነው።ዓለም በሙሉ የኢህአዴግ አገዛዝ፣ በተማሪዎች፣ መምሃራንና በአጠቃላይ፣ በዜጎች ላይ የሚፈጽመውን ግፍ ሲያውግዝ፣አንድም ቀን ድምጹ ተሰምቶ የማያውቀውም ለዚህ ነው፡፡ በትምህርት ቤቶች፣ የክፍል አለቆች ሳይቀሩ የኢህአዴግ አባሎች እንዲሆኑ ሲደረግና አጠቃላይ የትምህርቱ ስራ በፓርቲ አባላትና መዋቅር ስር ወድቆ፣ የአንድ ጠባብ ፓርቲ ፖሊሲ መፈጸሚያና ማስፈጽሚያ ሲሆን፣ አባሪ ተባባሪ ከመሆን ውጭ አንድም ጊዜ ቃዉሞ አያውቅም።

ዛሬ ግን ይኸው አመራር የለውጡ ደጋፊና አራማጅ፣ ለትምህርቱ ጥራት መውደቅም ተቆርቋሪ ህኖ ለመቅረብ እየሞከረ ነው። በመሰረቱ ከእንግዲህ፣ ይህን በርካታ መምህራንን ጨምሮ ብዙዎች የህይወት መሳዋዕትነት የከፈሉበትን ለውጥ አለመደገፍ የሚቻል አይደለም። የትምህርቱ ፖሊስና አደረጃጀቱ ፣ለዜጎች ሁለንተናዊ  ሰበዕና እንዲሁም ለአገር ዕድገት እንዲበጅ ማድረግም እንዲሁ የወቅቱ አጣዳፊ ስራ ነው። ኤመማ አባላቱን አስተባብሮ በዚህ በኩል የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ግን፣ ከኢህአሃዴግ ጥርነፋ ነጻ መውጣት አለበት። የዛሬዎቹ የኢመማ አመራሮች በካድሬ ዳኞች ‘ፍርድ’፣ እነአቶ ገሞራው ካሳና አባተ አንጎሬን የመሳሰሉት በመምህራን የተመረጡ አመራሮች ተባረው፣ የማህበሩ የቢሮ ቁልፍ የተሰጣቸው ናቸው። በመሆኑም የእነዚህ የአመራር አባላት የለውጥ ደጋፊነት የሚረጋገጠው በቅድሚያ ማህበሩን፣ ለነ አቶ ገሞራው እንኳ ባይሆን፣ለሰፊው መምህራን መልሶ ማስረከብ ሲችሉ ነው። ለዚህም መመህራን እራሳቸውን እንደገና አደራጅተው ማህበራቸውን እንዲረክቡ ጥሪ ማድረግና የኢህአዴግ መሳሪያ በመሆን ያሳደዷቸውን፣ ያባረሯቸውን መምህራን ይቅርታ መጠየቅ አለባቸው። ይህን ሳያደርጉ ያልተመረጡበትን ማህበር አመራር ይዞ ለመቆየት መሞከር ግን  የሰሩትን ስህተት አለማመን ብቻ ሳይሆን ሁለተኛ ጥፋትም ነው የሚሆነው።

በመሆኑም አሁን ያለው አመራር የመጣበት ኢህአዴጋዊ  መንገድ ኢዴሞክራሲያዊና የመምህራንንም ውክልና ያልያዘ መሆኑን በማመን፣ ከሀላፊነቱ ሊወርድና አመራሩን በማህበሩ ደንብ መሰረት መምህራን በነጻነት ለሚመርጧቸው አመራሮች ማስረክብ ይኖርበታል። አዲሱ የዶክተር አቢይ የለውጥ መንግስትም በማህበሩና የቀድሞ አመራሮቹ ላይ የደረስውን በደል በማጤን፣ አሁን ያሉት የኢመማ አመራር አባላት፣ ማህበሩን ከማንቀሳቀስ እንዲታገዱ የማድረግ ሀላፊነት አለበት። መምህራን ባስቸኳይ መሪዎቻቸውን መርጠው ማህበራቸውን እንዲረከቡና፣ ብሎም ለለውጡና ለትምህርቱ ጥራት የሚጠበቅባቸውን ያበረክቱ ዘንድም ድጋፍና ትብብር ሊደረግላቸው ይገባል።

ኢመማ ላለፉት አመታት የኢህአዴግ ጥቃት ሰለባ የሆነው፣ ድርጅቱ የሚያራምደው ፖለቲካና፣ በተለይም የትምህርቱ ፓሊሲ፣ የህዝቦችን የአንድነት ገመድ የሚበጥስና አገርንም አደጋ ላይ የሚጥል ነው በማለት በመቃወሙና በነጻነት ለመቆም በመሻቱ ነበር። በዚህ ምክኒያት ብዙዎች ከነበሩበት ቦታ ወደ ገጠር እንዲዛወሩ ተደርጓል፣ ከስራ ተባረዋል፣ ታስረዋል ተሰደዋል፣ተገድለዋልም። ለዚህም የማህበሩ ስራ ስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበረው አቶ አሰፋ ማሩ አማሟት አቢይ ምስክር ነው። እነ አቶ ገሞራው ካሳና አቶ አባተ አንጎሬ ለአመታት ተገዝግዘው ለበሽታ ተዳርገዋል። የሀዝብ ብሶትና ትግል የወለደው አዲሱ መንግስት፣ ይህን በማህበሩ አመራሮች ላይ የደረሰውን ግፍ ሊረዳውና በህይወት ላሉትም ሆነ ለሞቱት ፍትህ ኢንዲበየን ማድረግ ይጠበቅበታል። መምህራንም እንደአዲስ ተደራጅተውና ማህበራቸውን ተቆጣጥረው፣ ለማህበራቸው ነጻነትና ለዴሞክርሲ ሲሉ የተዋደቁ አመራሮቻቸውን እንደሚያስቧቸው አምናለሁ።፡

መስከረም 3 ቀን 2011 ዓም

ጸሐፊውን በ Gebeyaw2_@hotmail.com  መድረስ ይቻላል

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here