Home News and Views ዴሞክራሲ ወይስ የተረኛነት ጥያቄ? የኦሮሞ ፖለቲካ ወዴት? (፪)

ዴሞክራሲ ወይስ የተረኛነት ጥያቄ? የኦሮሞ ፖለቲካ ወዴት? (፪) [ብርሃኑ አበጋዝ (ዶ/ር)]

***
ከዘውጌ ብሔርተኞች ጋር በሐሳብ ላይ ተመሥርተን የምንገጥምበት ዘመን ነው፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ “ማነህ?” “ከወዴት ነህ?” ሳይባል፣ በዘውጋዊም ይሁን በሌላ ማንነቱ ምክንያት ምንም ዓይነት መድልዎ ሳይደረግበት በየትኛውም የአገራችን ማዕዘን በነጻነት ተዘዋውሮ የመኖርና የመሥራት መብቱ የሚከበርበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ዕውን እስኪሆን ድረስ መታገል ይጠበቅብናል፡፡ አክራሪ ዘውጌ ብሔርተኞች ለአስተዳደር እንዲመች የተከለሉ ክልሎችን የራሳቸው ብቻ በማስመሰል የእኛ አይደለም የሚሉትን የኅብረተሰብ ክፍል በልዩ ልዩ መንገድ ሲያሳድዱትና የኖረበትን ቀዬ ጥሎ እንዲሄድ ሲያደርጉት ኖረዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ ስደት/መፈናቀል ከሶሪያ በልጣ የዓለማችን ቀዳሚ አገር መሆኗ ሊያንገበግበን ይገባል፡፡

የሕወሓት መሪዎች እንወክለዋለን የሚሉት ሕዝብ በቁጥር አነስተኛ በመሆኑና ከማዕከላቸው ርቀው መምጣታቸው በፈጠረባቸው ስጋት ምክንያት ሥልጣናቸውን ሊያስቀጥሉ የሚችሉት ዘውጌ ማኅበረሰቦችን፣ በተለይም አማራንና ኦሮሞን በጠላትነት እንዲቆሙ ሲያደርጉ መሆኑን በማመን በለኮሱት እሳት በአገርና ሕዝብ ላይ መጠነ-ሰፊ በደል አድርሰዋል፡፡ የሕወሓትና ኦነግ መሪዎች በፈጠሩት የጥፋት ግንባር በአማራ ሕዝብ ላይ በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የደረሰውን ዘግናኝ ግድያና የዘር ጥራት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚያውቀው ነው፡፡ የሕወሓት አመራር አማራና ኦሮሞ አንድ ላይ አይቆሙም፣ አጥፊና ጠፊ ናቸው፤ አሳትና ውኃ ናቸው ወዘተ. የሚሉ ትርክቶችን በማድራት በእነኝህ ሕዝቦች መካከል አላስፈላጊ ጥርጣሬ፣ ጥላቻና ግጭት እንዲፈጠር ያልፈነቀሉት ድንጋይ አልነበረም፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ የአማራና ኦሮሞ ወጣቶች ያሳዩት መናበብና በኦሕዴድና ብአዴን አመራሮች መካከል የታየው መግባባት ወያኔ የቆመበትን ትርክት የደረመሰና ውድቀቱን ያፋጠነ ክስተት እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡

አሁን በሕዝባችን መስዋዕትነት የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ብዙ ለውጥ አሳይቷል፡፡ ሆኖም ያልተለወጡ መሠረታዊ ነገሮችም አሉ፡፡ እንዲያውም ከነበርንበት የመከራ ሕይወት ወደባሰ መቀመቅ ሊያስገቡን ያሰፈሰፉ አክራሪ ኀይሎችም አሉ፡፡ ኢትዮጵያ በዘውግ ማንነት ለሚያምኑትና ለተደራጁትም ሆነ ለእኛ በዜግነት ላይ የተመሠረተ ኢትዮጵያዊነትን ለምንደግፈው ወገኖች እንድትመች፣ ሁላችንም በእኩልነትና በፍትሕ ልታስተናገድ የምትችል አገር እንድትሆን ከእነኝህ አክራሪ ኀይሎች ጋር የሐሳብ ጦርነት ውስጥ መግባት ይኖርብናል፡፡ ባለፈው ጽሑፌ ለመግልጽ እንደሞከርሁት፣ ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ አንድ የፖለቲካ ቡድን ወይም አንድ ሕዝብ በበላይነት የሚፈነጭባት አገር ልትሆን የምትችልበት ምንም ዓይነት ዕድል የለም፡፡ ያለን ብቸኛ ምርጫ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ገንብተን በእኩልነትና በፍትሕ መኖር ነው፡፡ ከአፈና አገዛዝ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚደረገው ጉዞ መሰናክል የዛበት ቢሆንም ያንን አባጣ-ጎርባጥ ፈለግ ተከትለን ወደ ብርሃን ከመሄድ ውጪ ሌላ የተሻለ አማራጭ የለንም፡፡

የታሪክ ሽሚያ
***
ግፈኛው የወያኔ የበላይነት የሰፈነበት ሥርዓት የወደቀው ላለፉት 27 ዓመታት ኢትዮጵያዊያን ባደረጉት እልህ አስጨራሽ ትግልና በከፈሉት መስዋዕትነት ነው፡፡ ያን ግፈኛ አገዛዝ በመቃዎማቸው በርካታ ወገኖች የእስርና ስቃይ ሰለባ ሆነዋል፤ ተገድለዋል፤ ተሰድደዋል፡፡ ያልተነገሩ በጣም ብዙ ግፎች ተፈፅመዋል፡፡ አክራሪ የኦሮሞ ዘውጌ ብሔርተኞች ይህንን በኢትዮጵያዊያን መስዋዕትነት የተገኘ ድል ነው የእኛ ድል ነው እያሉ የቅጥፈት ታሪክ ሊጽፉ ሲባክኑ የሚታዩት፡፡
የሕወሓት መሪዎች “ተራሮችን ያንቀጠቀጠ ትውልድ” እያሉ የራሳቸውን ገድል ሲተርኩልን ኖረዋል፡፡ የደርግን አምባገነናዊ አገዛዝ ተቃውመው በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን የግፍ ሰለባ እንዳልሆኑ ሁሉ የወያኔ/ኢሕአዴግ መሪዎች ደርግን ያስወገድነው እኛ ነን የሚል ትርክት በማድራት፣ ኤልሳቤት እቁባይ የተባለችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ “ታሪክን በስፖንሰር” በሚል ግሩም ጽሑፏ እንደገለጸችው፣ በኤፈርት ስፖንሰር እየተደረጉ በርካታ “የታሪክ” እና “የጀብዱ” መጻሕፍት ተጽፈዋል፡፡ ብዙ ዘጋቢ ፊልሞችና የቴሌቪዥንና ሬዲዮ ፕሮግራሞ ተሠርተዋል፡፡ ይህ የታሪክ ሽሚያና ጀግኖች እኛ ብቻ ነን የሚለው መሠረተ-ቢስ ትርክት ሕወሓትን ምን ላይ እንደጣለው ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡

የሚያሳዝነው አሁንም ከዚህ የታሪክ ሽሚያ አለመውጣታችን ነው፡፡ አክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞች በሁሉም ኢትዮጵያዊያን መስዋዕትነት የተገኘውን ድል እኛ ያመጣነው ድል ነው እያሉ አዲስ የፈጠራ ትርክት ጀምረዋል፡፡ “የሥርዓቱን አከርካሪት የሰበረው ቄሮ ነው፤ ቄሮ የአብዮቱ መሐንዲስ ነው፤” ወዘተ. እየተባለ ነው፡፡ የኦሮሞ ወጣቶች ሻሸመኔ ላይ ከኢትዮጵያዊ ባህል ባፈነገጠ መልኩ ኢትዮጵያዊ ዜጋን ዘቅዝቀው ሲሰቅሉና ሲያቃጥሉ፣ ቡራዩና አሸዋ ሜዳ በንጹሐን ወገኖቻችን ላይ ኢሰብአዊ ድርጊት ሲፈጽሙ አትንኳቸው የተባለው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ “ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁለት መንግሥት ነው፤ የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መንግሥትና የቄሮ መንግሥት፤” እየተባለ የሚቀርበው አደገኛ ትርክት ከወዲሁ ሃይ ሊባል የሚገባው አሁንም እንደ ሕወሓት ዘመን አይነኬ የሆኑ ቡድኖች እንዳይፈጠሩና ወደቀደመው የግፍ አገዛዝ እንዳንመለስ ነው፡፡

የዚህ ዓይነት አካሄድ መቀመቅ ውስጥ እንደሚከተን ጥርጥር የለውም፡፡ ለዚህ ነው በጊዜ መስተካከልና መልክ መያዝ አለበት የምንለው፡፡ አክራሪ የኦሮሞ ዘውጌ ብሔርተኞች በሚያውቁበት ከሕወሓት የውድቀት ታሪክ ብዙ መማር ይችላሉ፡፡

ከትግራይ ገዥ መደብ ወደ ኦሮሞ ገዥ መደብ?
የሕወሓት መሪዎች ሥልጣንን ሀብት ማጋበሻ መሣሪያ አድርገው እንደተገለገሉበት ግልጽ ነው፡፡ በኢንዶውመንት ስም ባቋቋሟቸው እጅግ ግዙፍ የቢዝነስ ተቋማት ከፍተኛ ሀብት አካብተዋል፤ የአገሪቱ የግል ዘርፍ እንዲቀጭጭ አድርገዋል፡፡ ይህ ብቻ አይደለም ከሥርዓቱ ጋር ተጠጋግቶና መጠነ-ሰፊ ድጋፍ ተደርጎለት በአጭር ጊዜ የገነገነ የከበርቴ ቡድን (በአቶ ክቡር ነጋ ቃል የፓራሹት ነጋዴ) ፈጥረዋል፡፡ ሕወሓት በኢንዶውመንት ስም ያቋቋማቸው ድርጅቶችና ከሕወሓት ጋር ተጠጋግቶ ያደገው ደራሽ ከበርቴ ናቸው የትግራይ ገዥ መደብ መሠረቶች፡፡ ይህ ገዥ መደብ አሁን እንደበፊቱ እንደፈለገ የሚፋንንበት ዕድል የለውም፤ ተንኮታኩቷል ባይባልም አቅሙ በሕዝብ ትግልና መስዋዕትነት ተወስኗል፡፡

ትልቁ አደጋ የፖለቲካ ሥልጣንን የሀብት ምንጭ አድርጎ የማየቱ አስተሳሰብ አሁንም ማዕከላዊ ቦታ ይዞ የመገኘቱ ሁኔታ ነው፡፡ የሕወሓት በላይነት የነገሠበትን ሥርዓት መስዋዕትነት የጣልነው እኛ ነን፣ ስለሆነም አሁን ተራው የእኛ ነው የሚለው የአክራሪ ኦሮሞ ዘውጌ ብሔርተኞች ትርክት ይህን መሠረታዊ ዓላማ ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡ የትግራይን ገዥ መደብ በኦሮሞ ገዥ መደብ የመተካት ዓላማ ያነገቡ ኀይሎችን በመታዘብ ላይ ነን፡፡ ሁሉም ሥልጣን አይቅርብን፣ ያየነው መሬት ሁሉ የእኛ ነው የሚል አካሄድ እየተስተዋለ ነው፡፡ ይህ አደገኛ አዝማሚያ ሥር ሳይሰድ መታረም ይኖርበታል፡፡ የፖለቲካ ሥልጣንን ለአገር ሀብት መዝረፊያ ማዋል ሊቆም የሚችለው ደግሞ ገለልተኛ የሆኑ ጠንካራ አገራዊ ተቋማት ሲገነቡና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲኖር ብቻ ነው፡፡

ለትግል እንነሳ!
***
አክራሪ ዘውጌ ብሔርተኝነት የሐሳብ ትግልን እንደጦር ይፈሩታል፡፡ ቀላሉን፣ ነገር ግን አገርና ሕዝብን የሚያወድመውን አካሄድ ነው የሚመርጡት፡፡ ሕዝብን “ተጠቃህ፣ ተዋረድህ፤” ወዘተ. ብሎ ስሜታዊ ቅስቀሳ ማድረግና ሕዝብን (በተለይ ወጣቱን) ለአመጽ ማስነሳት ይቀላቸዋል፡፡ አክራሪ ዘውጌ ብሔርተኞች አገር ሰላም ስትሆን፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሲገነባ ድጋፋቸው እንደሚወርድ ስለሚያውቁ፣ ያወቀና የነቃውን ኅብረተሰብ እንደፈለጉት ሊዘውሩት እንደማይችሉ ስለሚገነዘቡ ሁልጊዜም ከዴሞክራሲ ይሸሻሉ፡፡ ከምክንያታዊነት ይልቅ በስሜት ላይ ያተኩራሉ፡፡ ከሐቅ ይልቅ በበሬ-ወለደ ይታወቃሉ፡፡ የእኛ የሚሉት ሰው የፈለገውን ያህል ጭራቅ ቢሆን አያወግዙትም፤ እንዲያውም ከጎኑ ይቆማሉ፡፡ ትችትና ሂስ ሲቀርብባቸው በሕዝባችን ላይ ጦርነት ታወጀ፣ ይጠሉናል ወይም ይፈሩናል ወዘተ. የሚል ትርክት በማድራት አጀንዳውን ለማስቀየስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡

አክራሪ ዘውጌ ብሔርተኞች የፈለገውን ያህል ቢያለቃቅሱ ከእኛ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊትና ሁላችንም በእኩልነት የምታስተናገድ አገር እንድትሆን ከምንመኝ ኢትዮጵያዊያን የሚጠበቀው ያለ ፍርሃት ከእውነትና ከፍትሕ ጎን መቆም ነው፡፡ አክራሪ ዘውጌ ብሔርተኞች የሚናገሩትና የሚሠሩት አገርና ወገንን የሚጎዳ መስሎ ሲታየን በአደባባይ የሐሳብ ጦርነት መክፈትና ሕዝብ እውነታውን አውቆ ከፍትሕ ጎን እንዲቆም መታገል ይኖርብናል፡፡ እከሌ ምን ይለኝ ሳንል፣ ይህን ወይም ያኛውን ዘውጌ ማኅበረሰብ ትጠላለህ እንባላለን ብለን በራሳችን ላይ ማዕቀብ ሳንጥል ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ዘላቂ ሰላም ይጠቅማል የምንለውን ሐሳብ በድፍረት ማራመድ ይገባናል፡፡

ኢትዮጵያዊያን የራሳችንን ጉዳይ ለግለሰቦች ወይም ለቡድኖች አሳልፈን መስጠት አይቻለንም፡፡ የአገሬና የራሴ ጉዳይ ያገባኛል ብለን በድፍረት መሳተፍ መቻል አለብን፡፡ በግለሰቦችን ቡድኖች መልካም ፈቃድ የምንኖር መሆን የለብንም፡፡ “የምንኖርበት የፖለቲካ ሁኔታ እኛን የሚመጥን ነው ወይ?” ብለን መጠየቅ መቻል አለብን፡፡ ለመብታችን ቀናኢዎች እንሁን!

ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኖራለች!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here