Home News and Views የቤተ መንግስቱ ግርግር እና ግርግሩ የፈጠረው የአተያይ ግርግር

የቤተ መንግስቱ ግርግር እና ግርግሩ የፈጠረው የአተያይ ግርግር

|ቋጠሮ ገጽ | ትናትና በቤተ መንግስት የተፈጠረውን ግርግር ተከትሎ ሁለት ተከታታይ ጥያቄዎችን ማዕከል ያደረጉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ።
ጥያቄዎቹ፦ ግርግሩ እንዴት ከመንግስት የጸጥታና የደህንነት ኃይሎች እይታ ሊያመልጥ ቻለ? ከአሰራር ዝርክርክነት ወይስ የለውጥ አደናቃፊዎች ድብቅ ሴራ ? ይህ ጥያቄ የችግሩን መንስኤ መርምሮ ዘላቂ መፍትሄ መሻትን አልሞ የሚነሳ በመሆኑ ተገቢ ጥያቄ ነው።
ይሁንና የትኛውም አስተያየት ሰጪ ጥያቄውን ለመመለስ የሚያስችል በቂ መረጃም ሆነ ማስረጃ የለውም። በቂ መረጃ ሊኖር ያልቻለው ደግሞ መንግስት ድብቅ በመሆኑ ነው የሚሉ ወቀሳዎችም ተሰንዝረዋል። በእርግጥ የመንግስት አካላት በቂ መረጃ እንዳላቸው አልጠራጠርም። ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ለህዝብ የማይገለጹ መረጃዎች ስለሚኖሩ ሁሉንም ነገር ለህዝብ ይፋ ማድረግ ነበረባቸው/አለባቸው የሚል እምነት የለኝም።
መንግስት ድብቅ ሆነ የሚሉ ወገኖች ምን አይነት መረጃ ጠብቀው እንደነበር አልገባኝም። የኩዴታም ሆነ የአፈና ሴራ ኖሮ ቢሆን እንኳ በሰላም እስከተቋጨ ድረስ ለህዝብ ይፋ መሆን ያለበትም ሰላማዊ እልባቱ ብቻ ነው። ከሁሉ በፊት ህዝብ ሊረጋጋ ይገባዋል፡፡ በመቀጠል አስፈላጊው ምርመራ ተከናውኖ የመፍትሄ እርምጃ ከተወሰደ በኋላ ዝርዝር መረጃው ለህዝብ ይፋ ሊሆን ይችላል።  አልያ መንግስት ገና ከመነሻው ያለውን መረጃ ሁሉ ዝርግፍ አድርጎ ለህዝብ ይፋ ካላደረገ ብሎ መውቀስም እና መሞገት ትክክል አይሆንም። የቄሳርን ለቄሳር እንዲል ቃሉ የመንግስትንም ኃላፊነት ለመንግስት መተው አግባብ ይመስለኛል።
መንግስትም እንዲህ አይነት ግርግር እንዳይለመድ አፋጣኝና የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ ዘላቂ መፍትሄ መሻት ይኖርበታል። ጨው ለራስ ስትል … ነውና ይህን ደግሞ እንደሚያደርጉት ጥርጥር የለኝም።
በነገራችን ላይ፦ወታደሮቹ ወደ ቤተ መንግስት እንዲያመሩ ከገፋፋቸው ምክንያቶች አንዱ ዶ/ር አቢይ ራሳቸውን ለህዝብ ቅርብ ማድረጋቸው ይመስለኛል ።
ዶ/ር አቢይ ቤተ መንግስቱንም ሳይቀር ለህዝብ ቅርብ አድርገውታል። ወታደሮቹም ከዚሁ የቅርብነት ስሜት በመነጨ ሊያገኟቸው ቢነሳሱ ብዙም የሚያስገርም አይመስለኝም፡፤ ነገሩን ያካበደው ወታደሮች መሆናቸውና መሳሪያ መያዛቸው ነው። በመሳሪያ ወንበር ማስለቀቅ እንጂ ብር መጠየቅ ስላልተለመደ ዜናውም ጆሮ ደልቋል።  እነዚህ ሰዎች የአንድ ፋብሪካ ሰራተኞች ቢሆኑ ኖሮስ? አዎ የፋብሪካ ሰራተኞች ቢሆኑ ኖሮ ፤ ፑሻፑም እራቱም ጋ ሳይደርሱ “አቶ እግሌ የሚባለውን ሚ/ር አነጋግሩ” በምትል ሁለት መስመር መልዕክት ይሸኙ ነበር! ወታደሮቹም በፋብሪካ ሰራተኞቹ መልክ መሸኘት ቢቻል ጥሩ ነበር! ግን አልተቻለም! የተሸከሙት “ጠብ – መንጃ” ነዋ!… እንግዲህ አንዴ ሆኗል እንዳይደገም የላላውን የበር ብሎን ሁሉ በጥንቃቄና በነቂስ ማጠባበቅ ያስፈልጋል…!

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here