Home News and Views “መደመር” የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፈረስ (ምዕመን ፈለቀ)

“መደመር” የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፈረስ (ምዕመን ፈለቀ)

“መደመር” የተባለው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ፈረስ አንዴ ሶምሶማ አንዴ ሽምጥ እየጋለበ ከዋናው ፉክክር ሊያደርሰን የቆረጠ መሆኑን አሁንም እያሳየ ነው። ደግሞም ብዙኃኑ ተሳፋሪ በኖህ መርከብ መስሎት ርግቧ ይዛ የምትመጣውን ምሥራች በመጠበቅ ከመርከቧ ተጫነ። በሂደት ግን ነጂው በይሁንታ የጫናቸው ጥቂት ባዕድ ሰዎች ከመርከቧ መኖራቸው ታወቀ።

ከጥፋት ውሃ ያድነናል የተባለው መርከብ ሁሉንም እንዳግበሰበሰ፣ እንዴ ከውቂያኖስ ግድግዳ ሲላተም፣ በሌላ ጊዜ የኋሊት በመሄድ፣ ደግሞ ማዕበል ሲበረታ ከመስጠም እየደረሰ፣ ተጓዦችን ካላሰብነው ካልገመትነው አውሎ አሳደረን። መደመር ያልሞከርነው መንገድ በመሆኑ ብዙዎቻችን በፍላጎት ተቀበልነው። መደመርን ብዙዎች ጨርቄን ቅሌን፣ የናቴ መቀነት አደናቀፈኝ፣ ስንቅ ልሰንቅ ፣ ወዘተ ሳንል ገባንበት። በመደመር አድሎ ተረሳ፥ ሴትና ወንድ፣ አማኝና የማያምን፣ ሞኝና ብልህ፣ ጀግናና ፈሪ፣ የተማረና ጨዋ፣ አለቃና ምንዝር፣ ወዘተ አንድ ላይ ይጓዙ ተባለ።

መደመር መደብ አልባ ወይም ጌታና ሎሌ የማይለዩበት የገና ጨዋታ ሆነ። የተሳሳቱ አንዳንዶች እኔ ሀብታም አንተ ደሀ፣ እንዴት አብሬህ እሰለፋለሁ በማለት አጉረመረሙ። ሌሎች ደግሞ መደመርን ከሃይማኖት ጋር አገናኝተው፣ ኃጥህና ጻድቅ ሳይለዩ፣ ማን ከማን ይደመራል እያሉ በግብዝነት ፎከሩ። እንዲያው ዘንግተው እንጂ፣ መሬት፣ ጸሐይና ጨረቃ ለሁሉ በተሰሩበት ዓለም፣ የአዳም ልጅ በደረጃ እንዴት ተለይቶ ይቅረብ። መደመር መከባበር ነው። መሳ ለመሳ መሆን ነው። እናም፣ በመደመር ቀጥሎ ያለው ተጨባጭ (tangible) ሥራ ሲሠራ አየን፥ መሪአችን ዓብይ በብዙዎች ዘንድ የተዘነጋውን ቃል አስታወሰ፥ በአደባባይ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ በማለት የስልጣን ዘመኑን አሟሸ።

ገላጋያችን ዓቢይ ወደ ወህኒ የተጋዙ የህሊና እሥረኞችን አስፈታ። ሽማግሌያችን ዓብይ የተጣሉትን አስታረቀ። ዓብይ በተለያዩ አገራት የተበተኑ ዜጎች እንዲገናኙ አደረገ። ዓብይአችን ጎረቤት አገራትን በሰላም እንደአቀረበም አንዘነጋም። መሪአችን የውጪ ምንዛሪን በማረጋጋት፣ የአገር ደንህነትና ጥበቃን በተሻለ መልክ በማዋቀር፣ ለኔ ቢጤዎች የመኖሪያ ቤት ጥገና በማስጀመር እንዲሁም ጽዳት በከተማችን እንዲቀጥል በማድረግ ታታሪነቱን አሳየ። በመደመር አራት የሚሆኑ ባለሥልጣናት በሂሳብ ተግባብተው፣ ሆኖም ሌሎች ባልሥልጣናት ቢለመኑ የለበጣ እየሳቁ፣ ያሻቸውን እንዲያደርጉ፣ ይሄ ወግ ተበጀላቸው።

በመደመር ጓዶች ሁሉ ተግባብተናል ያሉ መሪ፣ አራት ብቻ መሆናቸውን ዘነጉ። ጓዴ ያሏቸው ተቀናሾች (cowards) ብዙ ተንኮል ሸረቡ። አድርባይ (opportunists) ጓዶች ጥግ ይዘው ማንሾካሸክ ተያያዙ። ተጠራጣሪዎች (cynical) እንደ ውሃ ላይ ኩበት ዋለሉ። የማይረቡትን በመቀነስ ወደፊት መሄድ ሲቻል፣ በይሁንታ በማቻቻል አብሮ መሥራት ተመረጠ። ማንም ደምረን ብሎ ሳያስገድደው፣ በድማሬው እኔም ኖሬ፣ ኃላፊነት ወስጄ በህግ እመራችኋለው ያለ መሪ፣ እራሱ እራሱ ህግን መነቅነቅ ጀመረ። አንድነት አዋጪ መሆኑን ተረድቶ ሳለ፣ መለያየትን የሚጋብዝ “ሥም” ለራሱ ወገን አስቀረ።

በዕሩቅ ያለውን የምሥራቅ አፍሪካ ድንበር አካልላለሁ ያለ፣ ዕሩቅ ተጓዥ ሳይሆን ቅርብ አዳሪ መሆኑን በግብር ስሙ “ኦዴፓ” ፈጸመ። “ኦ” እና “አ” የጪቃ እሾህ ሆነው፣ ረጅሙን ጉዞ ባጭር ሊያስቀሩ መሠረት ሲጥሉ አየን። በአንድነት ልዩነት የቆመው የኦዲፓ፣ አዴፓ የዘውግ አዙሪት፣ በልዩነት አንድነት እንዳያመጣ፣ ይበልጥ የለውጥ እርምጃ እንዲቀንስ ማለፊያ ወግ ተበጀለት። ውሎ ሲያደር መደመር በልጆች ጨዋታ ተዋጠ። እናም፣ “ጨዋታ ፈረሰ ዳቦ ተቆረሰ” ተባለ። አጓጊው መደመር ስጋት ሆነ። ምን ነው ቢሉ፣ በሬ ካራጁ ዋለ፣ አንበሣን ከጊደር አጎዳኘ፣ ነብርና ፍየል ባንድ መስክ ተሰማሩ፣ ቀበሮ ከሥጋ ቤት ገብቶ ምን ይሁነው፣ አያ ጅቦን ከወደል አህያ ጋር፣ እንዲሁም፣ ሌባን ከታማኝ፣ ድንግላዊውን ከአመንዝራ፣ ሰካራምን በአፉ መጠጥ ከማይዞረው፣ ወዘተ ማገናኘት ከባድ ፈተና ሆነ። መደመር ጉዱ ፈላ።

ዜሮ ለዜሮ በነበሩበት ወቅት የገቡትን ቃል ማፍረስ በቀላሉ ተከወነ። የማኅበሩን ህገ ደንብ የጣሱ ከመልካም ምግባር የራቁ ጓዶች፣ ባልተገመተ ሥፍራና ጊዜ የሚጥሉት አደጋ ንጹሐንን አጠፋ። በመደመር፣ ተራ ግድያ ከመፈጸም፣ እስከ መስቀል አደባባይ ፍንዳታ ብሎም ቤተ መንግሥት በአመጽ የገቡ ወታደሮች አየን። ብሎም፣ ተራውን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን መሪያችንን ሊገድል የተሰለፈ ወንጀለኛ የማይቀጣበት ሁኔታ ተከሰተ። ጉራማይሌው መደመር የአንድ ሰሞን ፌሽቲያ መሰለ። በአመጸኞች ትንኮሳ ሚሊዮኖች ሲፈናቀሉ ማየት አስጨነቀን። በውጭ አገር የመንግሥት አካል ልጅ ከቤተሰቡ ተለየ ብሎ ጮኸ፣ በኛ ዘንድ ግን ወገን ሲፈናቀል አይቶ ማለፍ ልምድ ሆነ። የእንጀራ ልጃቸው አብዲ ኢሌን ለፍርድ ያቆመ ሥርዓት፣ ዋናዎቹን እንዳላየ የሚያልፍበት ሁኔታ አይተን ታዘብን። ይልቁንም፣ ነፍሰ ገዳዮችን ትቶ፣ “ፍሪኪ” የሆኑ የአዲስ አበባ ወጣቶችን እንደ ጥጃ ማሰሩ አስገረመን።

መሪዎቻችን ማሰርን የሚለማመዱት በከተሜው ወጣት መሆኑን እንደገና አስታወሱን። እንጠይቅህ መሪያችን፣ ልብ ካልክ፣ እኛ በግድ አደማምረን አላልን፣ አንተው እራስህ እኔው ኃላፊነቱን ወስጄ አደማምራችኋለው ብሎም አሸጋግራችኋለው ስትል፣ በጉጉት በትእግሥት ጠበቅን እንጂ። ስሌቱን አንተው አሳይተህ ስታበቃ፣ ካልፈለገቻሁ ከድምሩ ልውጣ እያልክ አስፈራራኸን። ደግሞስ አባት እንደ ልጅ እንዲህ አደረጉን፣ እዬዬ፣ የሚል ከሆነ፣ እራሱ አማራሪ መባሉስ መች ቀረ። መደመር በህግ ይመራል እያልክ፣ አንተ ግን በይሉኝታ ህግ አፈረስክ። ምክንያቱም፣ ወስላታ ጓዶችህን ፈጽሞ አልቀጣም አልክ። ሌላው ቢቀር ካንድ ከተማ ግዞት (banish) ወይም ከእንግዶች ማረፊያ (house arrest) እንዳይገቡ ችላ አልክ። መደመር ከቁም ነገር ካልተቆጠረ፣ የፈሪና የአይን አፋሮች (wimpish) መሸሸጊያ ከሆነ፣ ቶሎ የይቅርታ በርህን ዝጋ። የፈረስህም ልጓም ይጥበቅ፣ በጅምላ መደመር ያብቃ። ያም ቢሆን፣ ባልንጀራዬ አከብርሃለው። ምክንያቱም፣ እውነትን ባንተ አይቻለው። የሰበሰብከው የወገንህ ብሶት፣ ተቆጥሮ የሚያልቅ አይደለም። እልፍ ከሆነው የሕዝብህ አስተያየት፣ እኔም ድርሻዬን ላክልበት። እናም፣ እኔና አንተ በምናውቀው፣ አንድ ሰው በይቅርታ ካልቀረበ፣ ሲለወጥ ስሙን ካልቀየረ፣ ክርስትናው ምን ላይ ይጸናል።

ኬፋ ቢሉ በጴጥሮስ፣ ሳኦል ቢሉ በጳውሎስ፣ በፊተኛው ዘመን፣ አብራም ቢሆን በአብርሃም፣ ያዕቆብ ቢሉ በእስራኤል፣ ወዘተ ተቀይረው አልነበር? ደግሞም ከእኛ ዘንድ፣ እከሌ ቢሉ በወልደማርያም በገብረማርያም፣ እንዲሁም እከሊት ቢሉ በወለተማርያም በእህተማርያም፣ ወዘተ ስማቸው አልወጣም ነበር? ታዲያ፣ ያንተን “ኦዴፓ” ና “አዴፓ” ለምን በልዩነት ሥም ቀጠልከው? ስለዚህ፣ ይህን ተውላጠ ሥም በኢትዮጵያ ሥም ካልጠመቅኸው፣ መከራው እየተጫነን በመጉበጥ ጊዜውን ልንገፋ ነው። ስለ ሁዳድዋ የአፍሪካ ቀንድ ረጅም ጉዞ አመላክተህ፣ ኦዴፓ እና አዴፓ በሚል የዘውግ ሥም ዓላማህን ማጠር፣ ለአንድነት ጉዞአችን መልካም አካሄድ እንዳልሆነ ተገንዘብልን። ስለሆነም ዓብያችን፣ እስከዛሬ በታሪኳ የመረጠችውን መሪ ላላስቀመጠች አገር እድል ፈንታዋ እንዲሰምርላት፣ የለመድከውን የእምነት ቃል ምን ጊዜም ጠብቅላት። ቃልም ገብተሀል፥ ፍርድ ቤቱ፣ ምርጫ ቦርዱ እንዲሁም የፖሊስ ኃይል ነጻ ይሆናሉ ብለሀል። እናም፣ ሞኝ በመሆኔ አምንሀለው፣ ከዋልክበት በመዋል ካደርክበት አድራለሁ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here