Home News and Views የትግራይ ህዝብ ሆይ እዉነቱ ይህ ነዉ!! (ያሬድ ደምሴ መኮንን)

የትግራይ ህዝብ ሆይ እዉነቱ ይህ ነዉ!! (ያሬድ ደምሴ መኮንን)

አጼ ኃይለስላሴ በጠበንጃ ሃይል በደርጉ ወታደሮች ከአልጋቸዉ ሲፈነገሉ “እኔን………..!!” ያለ አንድም ብሄር አልተሰማም፡፡ በህወሃት የኩሸት የታሪክ ድርሳን ዉስጥ የንጉሱ አገዛዝ እንደ አማራ አገዛዝ ተቆጥሮ ከሁለት አስር ዓመታት በላይ ሲሰበክ ቢኖርም፣ ሃቁ ግን ሌላ ነበር፡፡በንጉሳዊዉ ስርአት መንኮታኮት ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ እንዲሁም ካፋሽ አጎንባሹ ዉጭ፣ አማራን ጨምሮ ተከፋሁ ያለ ብሄር ፈጽሞ አልተሰማም፡፡

በ17 መርፌ የተጠቀመ ቁምጣ ባጠለቁ ሲንቢሮ የህወሃት ታጋዮች ጠብደሉ የደርግ ሰራዊት ሲንደባለል እንዲሁ “ሞቴን ካንተ ጋር ያድርገዉ!!!” ያለ አንድም ብሄር አልታየም፤አልተሰማም!! የተከፋና ያዘነ ኢትዮጵያዊም አልነበረም፡፡ባለስልጣናቱም ጭምር ቢሆኑ የደርግ አገዛዝ ቋቅ ስላላቸዉ በመዉደቁ የደነገጡ እንጂ ያዘኑም አልነበሩም፡፡ ህወሃት የደርግን አገዛዝ አይኗን በጨዉ አጥባ የአማራ አገዛዝ ነዉ ብላ ቱልቱላዋን ስትነፋ ብትኖርም፣ በደርግ መዉደቅ እፎይ ያለ እንጅ አንገቱን የደፋ አንድም አማራ አልነበረም፡፡ ጭቆናን፣ ኢፍትሃዊነትንና መታፈንን የሚወድ አንድም ብሄር ሆነ ህዝብ የለም፡፡ የትግራይ ህዝብ ሆይ እዉነቱን ማወቅ ከፈለክ እዉነቱ ይህ ነዉ!! ኢትዮጵያ ዉስጥ ብሄር የሚደግፈዉ ፓርቲ ተፈጥሮ አያዉቅም!!

ዛሬ ግን ኢትዮጵያ ዉስጥ አዲስ እዉነት ጥርሱን አግጦ ከፊት ለፊታችን ቆሟል፡፡ እነሆ አንድ ብሄር ብቻ የሚደግፈዉ አምባገነንና ጭራቅ መንግስት ተከስቶ ለማየት በቅተናል፡፡ የራስ የራሴ ይጣፍጥ ፈሴ እያለ የሚገኘዉ የትግራይ ህዝብ፣ ዛሬም ለአግድም አደጉ የአብራኩ ክፋይ ህወሃት እያደገደገ ይገኛል፡፡ ህወሃትን “ተዉ!!” የሚልበት አቅም አቷል!!

አሁን ከሚታየዉ ነገር ተነስተን ማለት የምንችለዉ አንድ ነገር ብቻ ነዉ፡፡ ህወሃት የትግራይን ህዝብ በመልኩ እንደምሳሌዉ ፈጥሮታል፤ ወይም የትግራይ ህዝብ ህወሃትን በመልኩ እንደምሳሌዉ ፈጥሮታል፡፡ በአይናችን የምናየዉና በጆሯችን የምንሰማዉ እዉነት፣ እዉነት አይደለም ብሎ ድርቅ ማለት ከጅልነት ዉጭ ምንም ሊባል አይችልም፡፡ኢትዮጵየዉያን አሁን ከምናየዉ እዉነት ጋር መጋፈጥ አለብን!! የትግራይን ህዝብ እንደ ሁለት ዓመት ህጻን ማባበሉ የትም አያደርስም፡፡ እዉነቱ ሊነገረዉ ይገባል፡፡ ወደድንም ጠላንም የትግራይ ህዝብ ከህወሃት ጋር ጭልጥ ያለ ፍቅር ዉስጥ ወድቋል፡፡

አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት የትግራይ ህዝብ በህወሃት ተገዶ ሠልፍ አልወጣም፡፡ይህን የሚል ታዛቢ የዋህ ወይም ጅላጅል ነዉ፡፡ አሁን ባለዉ ነባራዊ የኢትዮጵያ ፖለቲካ፣ ህወሃት የትግራይን ህዝብ የሚያስገድድበት እንጥፍጣፊ አቅምም ሆነ ድፍረት የለዉም፡፡ ሌላዉ የህብረተሰብ ክፍል የተጎናጸፈዉ አንጻራዊ ነጻነት፣ የትግራይ ህዝብም አላጣዉም፡፡ ይሄን ያገኜዉን ነጻነት ተጠቅሞ፣ አደባባይ ወጥቶ ህወሃትን “በቃህ ከዘመዶቻችን ጋር አታቆራርጠን!!” ማለት ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን የ85 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ቁስል፣ መከራና ስቃይ የትግራይ ህዝብም ስላልሆነ አላደረገዉም፡፡

ህወሃት ስልፍ የሚወጣበት እንጂ ሠልፍ የሚወጡለት ድርጅት እንዳልሆነ የትግራይ ህዝብ አሳምሮ ያዉቃል፡፡ይሁን እንጂ ዛሬም የትግራይ ዘመዶቻችን ከሰዉ በላዉ ጭራቅ ድርጅት ጎን ተሰልፈዉ በቁስላችን ላይ እንጨት እየሰደዱብን ይገኛሉ፡፡ለምን?ለምን ግን የኛ ቁስል የነሱ ቁስል ሊሆን አልቻለም? የትግራይን ህዝብ ግን ምን ነካዉ?

አንዳንድ ጸሃፍት እንደሚያስቡት የትግራይ ህዝብ የመረጃ እጥረትም የለበትም፡፡ ጨቅ መረጃ አለዉ፡፡ ሁሉንም ነገር ጠንቅቆ ይገነዘባል፡፡ የአብራኩ ክፋዮች የሰሩትን ግፍ፣ ጭካኔ፣ ወንጀል፣ ዝርፊያ አንድ ባንደ አሳምሮ ያዉቃል፡፡ ዛሬ ከሌላዉ ጊዜ በተሻለ፣ ሌላዉ ኢትዮጵያዊ የሚከታተላቸዉ ሚዲያዎች ለትግራይ ህዝብም ክፍት ሆነዉ መረጃ በማቀበል ላይ ናቸዉ፡፡ ሆኖም ግን የትግራይ ህዝብ የሚሰማዉ መስማት የሚፈልገዉን ብቻ ነዉ!! መስማት የሚፈልገዉ ደግሞ የህወሃትን የበላይነትና ቅዱስነትን ብቻ ነዉ!!

የትግራይ ወገኖቻችን ህወሃት ለኢትዮጵያ ህዝብ ባለዉለታ ነዉ ብለዉ ማሰባቸዉ ፌዝ ነዉ፡፡ ህወሃት ለኢትዮጵያ ህዝብ የሰራዉ አንድም ዉለታ የለም፡፡ ደርግን መጣሉ እንደዉለታ ሊቆጠርለት ይችል የነበረዉ፣ ህወሃት በደርግ መቃብር ላይ የተሻለ ስርአት ቢገነባ ነበር፡፡ ይህ ደግሞ አልሆነም!! የትግራይ ህዝብ ሆይ እዉነቱ ይህ ነዉ!! እየመረረህም ቢሆን ተቀበለዉ፡፡

እብሪተኛዉ ህወሃት ትናንት የደርግን ስርአት ለመገርሰስ የቻለዉ ጀግና ስለነበረ ይመስለዋል፡፡ ይሄንን ቅዠቱን የትግራይ ህዝብ አምኖ እንዲቀበለዉ አድርጎታል፡፡ በዚህም ምክንያት  የትግራይ ወጣቶች መሳሪያ ታጥቀዉ አደባባይ ሰልፍ በመዉጣት የኢትዮጵን ህዝብ ለማስፈራራት ሲሞክሩ እየታዘብን ነዉ፡፡ ህወሃት መራሹ ኢህአዴግ በደርግ ጭቆና የተንገፈገፈዉን ህዝብ ይሁንታ በማግኘቱ ነበር እስካፍንጫዉ ዘመናዊ መሳርያ የታጠቀዉን ሰራዊት ለማሸነፍ የበቃዉ፡፡ያኔ የኢትዮጵያ ህዝብ በደርግ አመራር ደስተኛ ቢሆን ኖሮ፣ ህወሃት እዚያዉ የተጸነሰችበት የደደቢት በርሃ ዉስጥ ጨንግፋ በቀረች ነበር፡፡ የትግራይ ህዝብ ሆይ እዉነቱ ይህ ነዉ!! ህወሃት ደርግን ድል ያረገችዉ ደርግ ጨቋኝ ስለነበር እንጂ የትግራይ ህዝብ ከሌላዉ ኢትዮጵያዊ የተለዬ ጀግና ሲለሆነ አይደለም፡፡

ህወሃት በዚያ ቀወጢ የትግል ጊዜ የሰሜኑን ኢትዮጵያ ክፍል ሲቆጣጠር “እልልልል….” እያለ የተቀበለዉ፣ በህወሃት ማኒፌስቶ በጠላትነት የተፈረጀዉ የአማራ ህዝብ ነበር፡፡ የተደገሰለትን ያላወቀዉ የአማራ ህዝብ ከደርግ ጭቆና ለመላቀቅ ሲል ብቻ ህወሃትን እንደ መድህን ቆጥሮ እቅፍ ድግፍ አድርጎ ከዉስጡ ሸሽጎ ለድል አበቃዉ፡፡አማራዉን ጨምሮ አብዛኛዉ ኢትዮጵያዊ በደርግ ጭቆና በመማረሩ ብቻ፣ የሚመጣበትን ጉድ ሳያዋቅ፣ ከድል አድራጊዎቹ የህወሃት ሰራዊት ጋር አታሞ እየተመታለት አብሮ ተደለቀ፡፡ ጉድሽን ሳታውቂ አብረሽ ተደለቂ ነዉ ነገሩ፡፡እናም ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የሆነዉ ሁሉ ሆነ፡፡ብሶት የወለዳቸዉ ጉዶች በዚህ ሚሰኪን ህዝብ ላይ ሌላ የከፋ ብሶት አመጡበት፡፡

ዛሬ ግን ህወሃት ጦርነቷ የምትገጥመዉ ከደርግ ሰራዊት ጋር አይደለም፤ ከተጨቆነዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር እንጂ! የተጨቆነ ደግሞ ምንግዜም አሸናፊ ነዉ!! እናም በአደባባይ መሳርያ እያነገቡ መንጎራደዱ የትም አያደርስም!! የትግራይ ህዝብ ሆይ እዉነቱ ይህ ነዉ!!

ትግራዋይን እንደ ህዝብ ስወቅስ፣ ከትግራይ ተወላጆች መሃል የዘረኝነት ዘጎልን ሰብረዉ የወጡ አርቆ አሳቢዎች የሉም ለማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ነገሩ ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ ሆኖ ነዉ እንጂ፣ የትግራይ ምድር ኢትዮጵያን የሚታደጉ ጀግኖችን ማፍራት ታዉቅበታለች፡፡

የትግራይ ምድር ካበቀለቻቸዉ ጀግኖች መሃል፣ ለኔ የጀግኖች ሁሉ ጀግና ገብረ መድህን አርአያ ነዉ፡፡ የቀድሞዉ የህወሃት ታጋይ ገብረመድህን አርአያ፣ የግንባሩን ድርጊት ተጸይፎ ከከዳ በኋላ ባገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ የህወሃቶችን ሴራ ሲያጋልጥ ኖሯል፡፡ ዛሬም በማጋለጥ ላይ ነዉ፡፡ ህሊና ከብሄር ማንነት በላይ መሆኑን ለማወቅ ገብረመድህን በህይወት ያለ ምስክር ነዉ፡፡ የትግራይ ህዝብ ገብረመድህን እና መሰሎቹ የሚናገሩትን እዉነት ለምን እንደማይሰማ አይገባኝም፡፡ ገብረመድህን እኮ የትግራይ ህዝብ እንዲጠፋ በማሰብ አይደለም ህወሃትን ሲታገል የኖረዉ፡፡የትግራይን ህዝብ ከህወሃት ተንኮልና ክፋት ለመታደግ እንጂ፡፡ ግና ምን ያደርጋል የትግራይ ህዝብ ዛሬም የሚሰማዉ መስማት የሚፈልገዉን ብቻ ነዉ፡፡ መስማት የሚፈልገዉ ደግሞ የህወሃትን የበላይነትና ቅዱስነትን ብቻ ነዉ!!

የትግራይ ህዝብ የራስ የራሴ ይጣፍጥ ፈሴ ፣ማለቱን ትቶ እዉነቱን ሊጋፈጠዉ ግድ ይለዋል፡፡ የአብራኩ ክፋዮች ለሰሩት ወንጀል ተገቢዉን ቅጣት ማግኜት አለባቸዉ፡፡ እንደኔ እንደኔ ህወሃት የዘራዉን የትግራይ ህዝብ ማጨድ አይገባዉም!! እኛና ህወሃት አንድ ነን ብሎ፣ ልጨድ ካለ ግን ምን ማድረግ ይቻላል? መንገዱን ጨርቅ ያርግልህ ከማለት ወጭ!!

 (ይሄንን ትዝብቴን መጻፍ የጀመርኩት የዛሬ ወር ገደማ ነዉ፡፡በንዴት፣ በቁጭት ዉስጥ ሆኜ፡፡ ዛሬ የህወሃት ህመምተኞች ከታደሙበት ተዝካር መሃል ድንገት አንድ ጸበል ሲፈልቅ ያየሁ መሰለኝ፡፡ አምዶም ገ/ስላሴ የተሰኜ ፈዋሽ ጸበል!!! እናም ትግራይ ዛሬም አምዶምን የመሳሰሉ እሳት የላሱ በርካታ ወጣቶች እንዳሏት ጠረጠርኩኝ፡፡ ከትግራይ ህዝብ ጋር ለመወያየት እድሉን ያገኙ አልመሰለኝም፡፡ ይህንን ለማድረግ ከፍተኛ የገንዘብ አቅም ይጠይቃልና፡፡ የአብይ መንግስት እነዚህ ወጣቶች አጆሃ!! ብሎ ቢደግፋቸዉ ተአምር ይሰራሉ የሚል ተስፋ አለኝ፡፡)

ቸር ያሰማን

 

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here