Home News and Views እንዲህ አደረጉ እንዲባልልን ስላልፈለግን እንጂ ከ100 እስረኛ በላይ አስፈትተናል!-ሰራዊት ፍቅሬና ሸዋፈራው ደሳለኝ

እንዲህ አደረጉ እንዲባልልን ስላልፈለግን እንጂ ከ100 እስረኛ በላይ አስፈትተናል!-ሰራዊት ፍቅሬና ሸዋፈራው ደሳለኝ

እረ ጎበዝ! የህወሃት መገልገያ የነበሩት አርቲስቶች የአሳዳሪያቸው ሙት አመት እንኳ ሳይሞላ ፍጥጥ ብለው ከደሙ ንጹህ ነን ማለታቸውን ተያይዘውታል። ምን ታስቦ ይሆን…?

ሰራዊት ፍቅሬና ሸዋፈራው ደሳለኝ በፋና ቴሌቪዥን ቀርበው “እንዲህ አደረጉ እንዲባልልን ስላልፈለግን እንጂ ከ100 ሰዎች በላይ ከእሥር አስፈትተናል።  በምርጫ 97 የታሰሩትን የቅንጅት አመራሮች እንዲፈቱ በረከት ስምኦንን የሞገትነው እኛ ነን!” ሲሉ ሥሰማ ጆሮዬን ተጠራጠርኩት???። ልቦለድ ለፊልምና ለድራማ ብቻ መስሎኝ ኢንተርቪውም ላይ ይቻላል እንዴ? ወይስ ከአህያ የዋለች ጊደር …. ተምራ ትመጣለች እንዲሉ ከህወሃት የዋሉት አርቲስትም ኩሸት ተምረው መጥተው ነው?? ይህን ያህል መዋሸት ከደፈሩ ነገ ደግሞ አርበኞች ግንቦት 7 ነበርን ቢሉ ማን ያግዳቸዋል? እድሜ ለፎቶ ሾፕ  ከዚህ ቅፍፍ እዚያ ልጥፍ ማድረግ ብቻ ነው..።(ከላይ ያለውን ምስል ልብ ይሏል)

በነገራችን ላይ ፋና ቲቪና ኤል ቲቪ ሰሞኑን የህወሃት ተላላኪ እንደነበሩ የሚታወቁ አርቲስት ተብዬ ግለሰቦችን በተከታታይ የሚያቀርቡበት ምክንያት አልገባኝም። የጥልቅ ተሃድሶው ቀጣይ ክፍል ነው? ወይስ የጎደፈ ስብእናን ና ሃጢያት አጠባ ነው?

አውቀን በድፍረት፤ በስግብግብነት ፤ የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ ብለን አጥፍተናልና ይቅር በሉን ለማለት እንዳልሆነ ከሁሉም ቃለ መጠይቅ ተረድተናል። ታዲይ ሳምሶን ማሞ፤ ሰራዊት ፍቅሬ፤ሸዋፈራው ደሳለኝን አይነት ሰዎች በተከታታይ የቀረቡት ምክንያቱ ምን ይሆን? ።ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ለግዜው ልተወውና ወደ ቃለ መጠይቁ ይዘት ልለፍ።

ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት የሰራዊትና የሸዋፈራው ድፍረት በጣም በጣም አስገርሞኛል። ጎበዝ!! ውሸት በአዋጅ ተፈቀደ እንዴ? “ከ100 እሰረኞች በላይ አስፈትተናል። የቅንጅት መሪዎች እንዲፈቱ በረከትን ሞግተናል።” ምን ይሄ ብቻ ጋዜጠኛው “ የሰባዊ መብት ጥሰት በተበራከተበት፤ ንጹሃን በሚታሰሩበትና በሚገደሉበት ወቅት እናንተ “የከፍታ ዘመን” በሚል ያቀረባችሁት ዝግጅት የህወሃትን መንግስት ለማስደሰት አይደለምን? አይነት ጥያቄ ሲያቀርብላቸው፤ እነ ቅደደው ምንም ሳያፍሩ “ ሌላው በሌላ ሊተረጉመው ይችላል፤ የኛ ሃሳብ ግን ሰላም ከሌለና እስረኞች ካልተፈቱ የከፍታ ዘመን አይሆንም የሚል ነበር” በማለት አስቂኝ መልስ ሰጥተዋል።

ጎበዝ! እረ እንዴት ነው ነገሩ? ወዴት እየሄድን ነው? ሰው በዚህ መጠን እንዴት ሊዋሽ ይችላል? ሌላው ይቅር አብረዋቸው ለዘመናት የሰሩት አርቲስቶች እንኳ ይታዘቡናል አይሉም? ወይስ  በረከት ስምዖን ከሂትለር ፕሮፓጋንዲስት  የወረሳት “ውሸት ሲደጋገም እውነት ይሆናል” የምትለዋን መርህ  እነሱም እንዳቅሚቲ እየሞከሯት ይሆን?

ምናለበት ቢያንስ ቢያንስ የአሳዳሪያቸው የህወሃት ሙት አመት እንኳ ሞልቶ ግፉም፤ ሃዘኑም፤ ትንሽ እስኪረሳ ቢጠብቁ?

 • መለስ ዜናዊ አፍሪካን ወክሎ ኮፐን ሃገን ሊሄድ በተዘጋጀበት ዋዜማ የቤተ መንግስቱ ድግስ ደጋሽ፤ አሳላፊ፤ አፋሽ አጎንባሽ እንደነበሩ እንዴት ይረሳል ብለው ይሆን?
 • በሶማሌ ሰው እንደ ቅጠል እየረገፈ እነሱ ግን በመንግስት ጋባዥነት ጎብኝተው ሲመለሱ ሶማሌ ክልል ለሌላውም ኤክስፖርት የሚደረግ ሰላም አለ ብለው የተሳለቁት ይረሳ መስሏቸው ነው?
 • እየተነሱ በመፍረጥ በርካታ አውሮፕላኖችን የፈጀውን የህወሃት አየር ሃይል ግቢ ጎብኝተው ሲመለሱ፤ ኢትዮጵያችን በአስተማማኝ እጅ እየተጠበቀች ነው! ኢትዮጵያን የደፈረ ውዮለት በሚል ድራማ መሰል የተንዛዛ የአድናቆት ምስክርነት የሰጠው ማን ይሆን?
 • የሚመራውን ሃገር የሚጠላው ብቸኛው የአለማችን አምባገነን ወዲ ዜናዊ ሲሞት ማቅ ለብሰው ማቅ መስለው “ምነው ተለየሕን መስከረም ሳይጠባ እንቁጣጣሽ እያልን ሳናጌጥ በአበባ ” ሲሉ የሃዘን እንጉርጉሮ ያዜሙት እነማን ይሆኑ?

እረ ስንቱ ….! እነሱ ግን ይህን ሁሉ ጸሃይ የሞቀው ህዝብ ያወቀውን የአድርባይነትና የስግብግብነት ገድላቸውን ሙልጭ አድርገው ክደው፤ ዛሬ የሰባዊ መብት ተሟጋች፤ እስረኛ አስፈቺ፤ መንግስትን ስለሰላም ጎትጓችና አስጠንቃቂ ነበርን ብለው ብቅ አሉ።

ታዲያ ምን ይባላል ይሄ ጎበዝ? በእኩይ ተግባራቸው ያሳዘኑን አንሶ አሁን ደግሞ በውሸታቸው ለምን ያበሳጩናል?

ህግ ባይፈርድባቸውም ህዝብ ግን ፈርዶባቸዋል። የህዝብ ፍርድ ደግሞ ይግባኝም ሆነ አመክሮ የለውም። በርግጥ ጥፋቱን አምኖና ተጸጽቶ ይቅርታ የጠየቀና ከበረታም ጥፋቱን በሚያካክስ በጎ ተግባር ላይ የተሰማራ ሰው በሂደት የህዝብን ይቅርታ ማግኘቱ አይቀርም። ነገር ግን ባገኙት ሚዲያ ሁሉ እየቀረቡ ሺ ግዜ ባስተባበሉና በዋሹ ቁጥር ከህዝብ እየራቁ እንጂ እየቀረቡ እንደማይሄዱ በግዜ ቢረዱት መልካም ነው። እያልኩ ትንቢት በምትመስለዋ በኃይልዬ ታደሰ ዘፈን ሁለት ስንኞች ልሰናበት።

የኢትዮጵያ አምላክ ይፈርዳል ሳይውል ሳያድር
ይጥልላታል ጠላቷን ከባንዲራው ስር …..!

እውነት ነው!

 

1 COMMENT

 1. August 25, 2013 at 7:18 PM

  ===ፈንጂ ነው ይቅርታ ።ባንዳ ላይ ትፉና:-ይትፉና።===
  +++++++++++++አቢይ+ኢትዮጵያዊ=ሥጋዊ-ወመንፈሳዊ.
  የምን ጠጋ ጠጋ፣-
  የምን ልጥፍ ልጥፍ፤-
  የምን መተሻሸት፣-
  የምን ውትፍ ውትፍ፤-
  የምን መልመጥመጥ ነው፣-
  የምን ደፋ ቀና፤-
  የሚፈሰው ደሙ መቼ ደረቀና???…
  ይህች ትንሽ ትንሽ:-ያደረች ባቄላ
  ብዙ ትሆናለች ሕዝብ አልስማማም ብላ::
  ድንጋይ ያቀበሉ፣ስንሞት ትናንትና፤-
  እስኪ አሁን ያሳዩን ፣-
  ባንዳ ላይ ይትፉና።
  እለበለዚያ ግን እመኑን እያሉ:-
  ባንዳዎች የሆኑ ሰላምተኞች አሉ::
  እኮ ምን ተገኝቶ አጨብጫቢዎቹ፤
  በዚህ በዚያ ገብተው እዚህ ተከማቹ???…
  ይቅርታን ነፍገው ሕዝብን እንደናቁ፤-
  እንዴት ባደባባይ ለመታየት በቁ???…
  ቀረ’ኮ ይሉኝታ ቀረ’ኮ መደበቅ፤-
  በጉጅሌ ጉያ ሕዝብ ላይ መሳለቅ።
  ሕሊናቸው ትናንት የተጨማለቀ፤-
  ምን እንዳደረጉን ሕዝቡ እያወቀ:-
  ስንቱ ባንዳ ጀሌ ገድሎ የተደበቀ:-
  እንዴት ባንዲት ጀንበር:-
  የሕዝብ-ደም ተፋቀ???…
  ዛሬም ባንዳን አይተው የሚጨማለቁ፤-
  የሕዝብ እንደሆኑ፣እውነቱን እንዲያውቁ፤-
  ድንጋይ ያቀበሉ፣ስንሞት ትናንትና፤-
  እስኪ አሁን ያሳዩን ፣-
  ባንዳ ላይ ይትፉና።
  ግለሰቦች ክደው ሕዝብን ሲበድሉ፤
  አምባገነኖቹ ዕድሜ ያገኛሉ።
  እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ምንም ላልታጠቁ፤
  በጉልበት በብረት ዛሬም ለሚጠቁ፤
  በተለይ በዚህ ወቅት የሰላም እጃቸው፤
  የአጋዚ ጥይት ገድሎ ለሚፈጃቸው፤
  መድኃኒት ነው ፈንጂ ሕዝብን የበደሉ፤
  አደባባይ ውጥተው
  “በድለናል” ካሉ።
  እናም እንደማዲንጎ በሕዝብ የተረታ፤
  ይውጣና አሁኑኑ:-
  ፈንጂ ይስጥ በይቅርታ።
  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ ይህን ጥሪ ስማ፤
  በልቦናህ ጻፈው ማን እንደሚያቅማማ።
  ልጆችህ ሲደፉ በዓጋዚ ስትደማ፤
  በየስርቻው ሞልቷል ቢጠራ ‘ማይሰማ።
  እሰዬን አስተውል፣እነገብሩ አሥራትን፤
  ያን ታምራት ላይኔ ያስገነጠላትን።
  በየመድረኩ ላይ ዛሬም የሚዋሹ፤
  በዜና አንባቢነት ህሊና ያቆሸሹ።
  ሞልተዋል ድርቅ የለም ለምተናል የሚሉ፤
  ጉጅሌ ለበላው ጅለው የተጃጃሉ።
  እነዚህን ሁሉ ሐቁ እንዲፈጃቸው፤
  የእነ መሓሙድ ይቅርታ ወጥቶ ያፈንዳቸው።
  እናም ሕዝቡን ስሙት አድምጡት ላንድአፍታ፤
  እንደልጅ ማዲንጎ ጠይቁ ይቅርታ።
  እንደው ስንቴ ከዱን ከመካከላችን፤
  መንግሥትን ወግነው አሾፉ በሕዝባችን።
  በኪነት-በስፖርቱ በፖለቲካ-ስልጣን፤
  በምርጫ በትግል ስንቱን ጀግና አጣን።
  ይህን የሕዝብ በደል ማዲንጎ አሸንፎ፤
  አስደሰተው ሕዝቡን በይቅርታው አቅፎ።
  ሕዝቡ ትዕግስት አለው ሳይነጋ ይጠብቃል፤
  እነማን በዳዮች እንደሆኑም ያውቃል።
  እናም የበደላችሁ ያኔ ተለጥፋችሁ፤
  ዛሬውኑ ይቅርታ ጠይቁ ፈጥናችሁ።
  ባንዳውን ሳይጨምር፣ስንቱ ስው ተረታ???…
  በሆዱ በሥልጣን ለገንዘብ ተፈታ።
  ልደቱ የተባለው በቁም-ሲታይ ሞቱ፤
  መሐሙድም ርካሽ ሲሆን አየን ገልቱ።
  ያቺ አስቴር አወቀም ባለድምጻዊቷ ፤
  ኢትዮጵያን ነው የከዳች ለስንዝር ዕርስቷ።
  ንዋይ ደበበስ ቢሆን ዘምሮ ለኢትዮጵያ፤
  ወዶ ገባ ሆነ ከጉጅሌ ጉያ።
  ሰለሞን ተካልኝ ና ሲባል ብላልኝ ፤
  እንደጅብ ይጮሃል እሱስ ይጠንባልኝ።
  እነ ኃይሉ ሻወል ስንቱ ይቆጠራል፤
  ወዲያው ካያለበት እንደነጋ ይጠራል።
  እናም እንደማዲንጎ በሕዝብ የተረታ፤
  ይውጣና አሁኑኑ:-
  ፈንጂ ይስጥ በይቅርታ።
  ኃይሌስ ቢሆን ስንቴ አውቆ ተታለለ፤
  ጀግና እንዳልተባለ በወቸገል-ሥም ማለ።
  ፈንጂ ነው ዕውነታ ሐቅ ነው መናገር፤
  ጉጅሌ ኢትዮጵያን ከፋፍሏታል በዘር።
  ይኼን አትመስክሩ፤
  የኢትዮጵያ ሕዝብ አውቋል፤
  ግና ይቅርታችሁን ዓመታት ጠብቋል።
  እናም ሕዝቡን ስሙት አድምጡት ላንድአፍታ፤
  ታሪክ ሳይጠራችሁ የማታ የማታ፤
  ዛሬ ቁረጡና ቆማችሁ በዕውነታ፤
  እንደልጅ ማዲንጎ ጠይቁ ይቅርታ።
  በባንዳ ወርቅነት በዘሩ እያናፋ:-
  ኢትዮጵያዊነትን በመግደል ሊያጠፋ:-
  እንደያ ሲደነፋ የፈሪ ጉድ ይዞ:-
  ታሪክ ሲያዋርደው በኮዳው ጠምዝዞ:-
  ንገረን የት ነበርክ??…ሌሎችም ብትሆኑ:-
  ስለተቃረበ የድላችን ቀኑ::
  ኣረጋዊ በርሄ እነአቶ ግደይን፤
  ገብረ መድህን አርዓያ ሐቀኛው የእኛ ዐይን፤
  ሕዝብ በሞት ሲቆላ በዘር ሲመነጠር:-
  እንዲያ ሲፋለሙ ምን ትሰራ ነበር???…
  እናም የምን ጠጋ፣የምን ልጥፍ እቅፍ፤
  የምን “ኢዝም”ማለት፣-
  የምን ውትፍ ውትፍ።
  ያለፈው አለፈ እስኪ አሁን ጀምሩ፤
  በግልፁ አሳዩን በመትፋት አምርሩ።
  ሕዝቡን እየሰለሉ ማውራቱ ይቅርና;-
  ባደባባይ አሳዩን:-
  ባንዳላይ ትፉና::
  ድንጋይ ያቀበሉ፣ስንሞት ትናንትና፤
  እስኪ አሁን ያሳዩን ፣
  ባንዳ ላይ ይትፉና።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here