Home News and Views ኢትዮጵያዊው ሳይንቲስት ዶ/ር እንዳወቀ ይዘንጋው አለማቀፍ ሽልማት አገኙ

ኢትዮጵያዊው ሳይንቲስት ዶ/ር እንዳወቀ ይዘንጋው አለማቀፍ ሽልማት አገኙ

ኢትዮጵያዊው የጠፈር ሳይንቲስት ዶ/ር እንዳወቀ ይዘንጋው በምድርና ጠፈር ሳይንስ ምርምር ዘርፍ ላበረከቱት ጉልህ አስተዋጽኦ የታዋቂው ጆአኒ ሲምሰን ሜዳልያ ሽልማት እንደተበረከተላቸው አሜሪካን ጂኦፊዚካል ዩኒየን ዛሬ ባወጣው ዘገባ አስታውቋል፡፡

ዶ/ር እንዳወቀ ለአለማቀፉ የጠፈር ሳይንስ ምርምር ከፍተኛ ሙያዊ አስተዋጽኦ ያበረከቱና በማስተማርና በምርምር የላቀ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ የሚገኙ ትጉህ ሳይንቲስት በመሆናቸው ማዳልያው እንደተበረከተላቸው በዋሽንግተን በተካሄደው የሽልማት ስነስርዓት ላይ ተነግሯል፡፡

ከደብረ ማርቆስ አቅራቢያ በምትገኘው አምበር የተባለች የገጠር ከተማ የተወለዱትና የልጅነት ዘመናቸውን በእረኝነት ያሳለፉት ዶ/ር እንዳወቀ፣ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥ ተግተው በመማርና ራሳቸውን በእውቀት በማነጽ በአለማቀፍ ደረጃ እውቅናን ያተረፉ ሳይንቲስት ለመሆን የበቁ የስኬት ምልክት ስለመሆናቸው ተመስክሮላቸዋል፡፡

ለአለማቀፍ ስኬት ለመብቃታቸውና ሽልማቱን ለማግኘታቸው የባለቤታቸው ወ/ሮ ምስራችና የሁለቱ ልጆቻቸው ሃና እና ዮሴፍ እንዲሁም የሌሎች ቤተሰቦቻቸውና ጓደኞቻቸው ድጋፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳደረገላቸው ዶ/ር እንዳወቀ ተናግረዋል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአፕላይድ ፊዚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያገኙትና በናዝሬት ቴክኒክ ኮሌጅና በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት ያገለገሉት ዶ/ር እንዳወቀ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ትሮምሶ በአትሞስፌሪክ ፊዚክስ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን፣ በስፔስ ፊዚክስ ፒኤችዲ ከአውስትራሊያው ላ ትሮብ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2004 ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ካሊፎርኒያን የተቀላቀሉት ዶ/ር እንዳወቀ፣ ከአምስት አመታት በኋላም ወደ ቦስተን ኮሌጅ በማቅናት በምርምርና በማስተማር ውጤታማ ስራዎችን ያከናወኑ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅትም በከፍተኛ የሳይንስ ተመራማሪነት እያገለገሉና በናሳ በሚደገፉ ግዙግ የጠፈር ሳይንስ ፕሮጀክቶችን በመምራት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

ከዚህ ቀደምም የተለያዩ ታላላቅ አለማቀፍ ሽልማቶችን ያገኙት ዶ/ር እንዳወቀ፣ በርካታ የምርምር ጽሁፎችን ለህትመት በማብቃትና በማደግ ላይ ባሉ አገራት የጠፈር ሳይንስ ትምህርትና ምርምር እንዲስፋፋ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ይታወቃሉ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here