Home News and Views የአማራ ብሄረተኝነትና የገባበት ቅርቃር (ሳም ሚካኤሎቪች)

የአማራ ብሄረተኝነትና የገባበት ቅርቃር (ሳም ሚካኤሎቪች)

ህወሃት አራት ኪሎን በተቆጣጠረ ማግስት በየስፍራው አውጭጪኝ መሰል ስብሰባዎች ይካሄዱ ነበር። ጎባ ከተማ ውስጥ የተካሄደ አንድ ስብሰባ ላይ አንዱ ይነሳና በአካባቢው ለዘመናት የኖሩትን አዛውንት ‘ ነፍጠኛ’ ሲል ከስሶ በአደባባይ ከፍ ዝቅ ያደርጋቸዋል። አዛውንቱም እድል ሲሰጣቸው ” እኔ ነፍጠኛ ከሆንኩ አንተ ንፍጣም ነህ ” ሲሉ ንግግራቸውን ይጀምራሉ ( ጦቢያ መጽሄት ላይ ነው ያነበብኩት ) ። ምሳሌውን ያነሳሁት ሽግግር በመጣ ቁጥር በህዝብ መሀል የሚፈጠረውን ልዩነት ለማስታወስ ነው። በይበልጥ ግን የዜያኔውን የኦሮሞ ማህበረሰብ ስሜት እንዲያስረዳልኝና የዛሬው የአማራ ብሄረተኝነት ተመሳሳዩን እየደገመ እንደሆነ ለማሳየት ነው።

የአሁኑ የአማራ ብሄረተኝነት የ 1983 ትን የኦሮሞ ብሄረተኝነት አይነት ነው። የተጠራቀመ ብሶት ፣ ብስጭትና ያንን በተገኘው አጋጣሚ የማሳየት ዝንባሌ ይታይበታል። የኦሮሞ ተወላጆችና ልሂቃን በ1983 አማራ የተባለው ሁሉ ላይ እንዳደረጉት የዛሬዎቹ የአማራ ብሄረተኝነት መሪዎችም ትግሬ የተባለን ሁሉ ማንቁርቱን የማነቅ ስሜት ውስጥ ናቸው። ይህንን ስል የአማራ ህዝብ ላለፉት 27 አመታት የደረሰበትን ግፍና መከራ ለመቀልበስ አይታገል እያልኩ አይደለም። ነገር ግን ይህንን ኢፍትሀዊነት ለመታገል የሚወስደው መንገድ ይበልጥ ቁስሉን ወደማከክ ይወስደዋል ወይንስ ወደማከም የሚለውን ውይይት ለመጫር ነው።

የአማራ ብሄረተኝነት ቅርቃር ውስጥ እንዲገባ ካደረጉት ጉዳዮች ዋንኛው ሀሳቡ ኢላማ ያደረገው ኦነግ እና ህወሃት መራሹን ጸረ አማራ ፕሮጀክት ለማክሸፍ ‘ እሾህን በእሾህ ‘ የሚል ስትራቴጂ ይዞ መምጣቱ ላይ ነው። ችግሩ ያለው እነዚህ ሁለት ሀይሎች በሀገሪቱ ወቅታዊ ፓለቲካ እዚህ ግባ የሚባል ፋይዳ የሌላቸው መሆኑ ነው። ህወሃት እና ኦነግ ተኮር ስትራቴጂው ግን የአማራ ብሄርተኝነት እነ ዶ/ር አብይ ከሚመሩት ‘ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው’ ፓለቲካ እጅግ አርቆት ” አማራዊነት ሱስ ነው’ እሚል አነስተኛ ጎጆ ውስጥ እንዲኖር አስገድዶታል። የአማራ ብሄረተኝነት የእነ ለማ መገርሳን ኢትዮጵያ ሱሴ ፓለቲካ እንዳይቀላቀል ደግሞ በመከራ የሰበሰበው ደጋፊው ድሮ ወደለመደው የአንድነት ፓለቲካ ተመልሶ እንዳይነጉድበት ስጋት ሆኖበታል።

የአማር ብሄረተኝነት ቅርቃር ውስጥ መግባቱን ማሳያ ሌላው ጉዳይ የህሳቤው መሪዎች መረጥን ያሉት
” ደምና አጥንት ተኮር” የብሄር ፓለቲካ ነው። እነሱ ሲሉት አዲስ ካልመሰላቸው በስተቀር ይሄ ደግሞ ወያኔ ሲያቀነቅነው የነበረው የብሄር አደረጃጀት ነው።

ጃዋር ” Oromo First ” ብሎታል ፣ መለስ ” ወርቂ ህዝቢ ” ሲል ተቀኝቶለታል ዛሬ የአብን ሰዎች ” የአማራ ትምክህት ኩራታችን ነው ” እያሉን ነው። ቀለሙ ይለያይ እንጂ ጽሁፉ ያው ነው። ችግሩ ያለው እንዲህ አይነቱን ራስን ብቻ የሚመለከት inward looking አተያይ ይዘህ የሀገር ግንባታ ውስጥ ትገባለህ የሚለው ላይ ነው።

እነ አብን እንደ ምሳሌ ያነሷትን እስራኤል እናውሳ። በዚህ ዘመን ለፓለቲከኞቻችን ምሳሌ መሆን ያለባት በጠላት ተከበብኩ የምትለው እስራኤል ናት ወይንስ ከ27 በላይ ሀገራትን ያጣመረው የአውሮፓ ህብረት ? እስራኤል ጽዮናዊነትን በሚከተል ፓሊሲ መመራቷ አተረፈች ወይንስ ሁልጊዜም በጸጥታ ስጋት ውስጥ የምትኖር ሀገር ሆነች ? ካልጠፋ ሀገር ዙሪያዋን በግንብ የምታጥረው እስራኤል የፓለቲካችን ተምሳሌት ትሁን ? ከእስራኤል የተሻለ ልንናፍቃቸው የሚገቡ የብሄር ፓለቲካን ያስቀሩና በዚህም የተሳካላቸው አፍሪካውያን ሀገሮችስ የሉም ወይ ? እንኳን በአንድ ሀገር ያለ አንድ ማህበረሰብ በዚህ የገበያ ፉክክር በበዛበት አለም ሀገራት እንኳን ራሳቸውን በቅጥር ከበው ሊኖሩ አይቻላቸውም። እንግሊዝ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ነች ። እንግሊዛውያን በደምና አጥንት ፓለቲካ ውትወታ ከአውሮፓ ህብረት ራሳቸውን ለማግለል brexit ወስነዋል። ህንዳውያና ቻይናዎቹ ሳይቀሩ አፍንጫችሁ ስር ካሉት አውሮፓውያን ጋር መገበያየት ሳትችሉ እኛ እንዴት ናፈቅናችሁ ሲሉ እያፌዙባቸው ነው።

የአማራ ብሄረተኝነት ለብሄር ፓለቲካ አዲስ ነው። አዲስ በመሆኑም ሳቢያ ርዕዮቱ ገና አልዳበረም። እንደ መትረየስ ቃላት የሚተፉ ተናጋሪዎች አሉት እንጂ ሩቅ ሀሳቢ አሰናሳዮችን ገና አላገኘም። ለዚህም ነው በዘመነ ኢትዮጵያ ሱሴ ትኩረቱን ሂሳብ ማወራረድ ላይ ከማድረግ ይልቅ የብሄሩን ጥቅሞች እያስጠበቀ ከእነ አብይ መሀመድ ጋር ግንባር ቀደም የኢትዮጵያዊነት ፕሮጀክት ውስጥ ሊገባ ያልቻለው። የብሄር ፓለቲካ ሶቅራጢሳዊ አነብናቢዎች ይፈልጋል ፣ የኦሮሞ ፓለቲካ ከለዘብተኛው ሌንጮ ባቲ ይልቅ ጃዋር መሀመድን አልያም ጸጋዬ አራርሳን ይናፍቃል። የትግራይ ፓለቲካ ከለዘብተኛው አርከበ ዑቁባይ ይልቅ ሸርዳጁን መለስ ዜናዊ ወልዷል በዚያም ሳቢያ ዋጋ ከፍሎበታል። በአንጻሩ የጥቁር አሜሪካውያን ፓለቲካ ከንግግር አሳማሪው ማርከስ ጋርቬይና ማልከም እክስ ይልቅ አቻቻዩን ማርቲን ሉተር ኪንግን መርጦ ብዙ አትርፏል። የአማራም ፓለቲካ ጥቅሙን የሚያስከብሩለትን ነገር ግን ከምሽግ ወጥተው ከሌሎች ጋር ድልድይ የሚሰሩለትን መሪዎች ወደፊት ካላመጣ ጣጣው ለራሱ መልሶ የሚተርፈው ነው የሚሆነው።

1 COMMENT

  1. ማጡን እንዢ ቅርቃሩን በምስል አላሳዩንም። ይመሳሰላሉ ማለታቸው ነው መሰለኝ። ይሆነው ሆኖ ዐማራው እንዴት እቅርቃር እንደገባ ግልጽ አድርገው አላስረዱም። ባሁኑ ጊዚ የሚያደርግው ሕልዉናውን ለማስከበር፤ ንብረቱን ለማስመለስ፤ ለተገደሉት ፍትሕ፤ ለተፈናቀሉት ቦታና ካሣ እዲሰጣቸው ወዘተ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here