Home News and Views አጭር አስተያየት: በመስከረም አበራ ሃገራችን “ምርጫ አሁኑኑ” የሚባልባት ነች?  ላይ (ከመኮንን ተስፋዬ)

አጭር አስተያየት: በመስከረም አበራ ሃገራችን “ምርጫ አሁኑኑ” የሚባልባት ነች?  ላይ (ከመኮንን ተስፋዬ)

 

በኢትዮጵያ ያየነው ወይም እያየን ያለነው “የዘር ፓለቲካ” ከባዶ ሜዳ ላይ የተነሳ ሳይሆን በምክንያት የመጣ ነው።በራሳችን ሰዎች አልተዳደርንም፤ ቋንቋችንና ባህላችን እኩል አልተከበረም እና በኢኮኖሚው ውስጥ እኩል ድርሻ የለንም በነዚህ ላይ ማስተካከያ ይደረግ ብሎ መጠይቅ ምንም ሃሳብ ውስጡ የለውም ማለት ነባራዊ ሁኔታን መካድ ይመስለኛል። እነዚህ ብሶቶች እውነትነት አላቸው/የላቸውም ለማለት በእርጋታ መነጋገር የሚፈልግ ጉዳይ ነው? ግን ጥያቄው አለ። በቃ አለ። የሚፈሩት አሉ። የሚጠሉት አሉ። ስለጠሉት ስለሰደቡት ስለተቹት ግን አይጠፋም።

መፍትሄውስ? በዜግነት ፓለቲካ ወይስ ብሄረሰብ ላይ ያተኮር ፓለቲካ ሊፈታ ይችላል?። የኢትዮጵያ ችግር የድህነት ነው፤ የዲሞክራሲ መጉደል ነው፤ የእኩልነት መጓደል ነው፤ የሰብአዊ መብት በአግባቡ ያለመከበር ነው፤ ከዚህ በተጨማሪ እንደ ኦሮሞ ያሉ ብሄረሰቦች ባህላቸውን/ቋንቋቸውን እና ማንነታቸውን ማክበር እና ማሳደግ መፈለጋቸው ትልቅ አጀንዳ ነው። ከረጅም ጊዜ አንጻር የዜግነት ፓለቲካ የተሻለ ነው ብዬ አስባለሁ። ነገር ግን በዜግነት ላይ የተመሰረተ ፓለቲካ ቢመጣም በውስጡ የብሄር ጥያቄዎች በአሉታዊ መንገድ መመለስ ካልቻለ ውጤት አይኖረውም። በሌላ በኩል በራስ ብሄር ላይ ብቻ ማተኮር ለራሱ ለብሄረሰቡም እንኳ ዘላቂ ሰላምና እድገት አያመጣም። ማንም ተነጥሎ  ብቻውን ሊያድግ አይችልም። የሁለቱም መንገዶች አቀንቃኞች በእውነት ከልባቸው የአገራቸው ችግር እንዲፈታ ከፈለጉ አንዱ አንዱን ለማጣፋትና ለማስጠላት ከመሞከር ይልቅ ሁለቱም ጠንካራና ደካማ ጎኖች እንዳላቸው ተረድተው ለጊዜና ለህዝብ ውሳኔ መተው ይገባቸዋል። በመጨረሻ ላይ ህዝብ ራሽናል ነው። እውነተኛ እኩልነት ከሰፈነ፤ በቅንነትና ከልብ የመነጨ መከባበር ከመጣ የዘር ጉዳይ ሰከንደሪ ይሆናል፤ ሳናስበው ወደ የጋራ ጉዳዮች እንሻገረለን። ይሄ እኩልነት ግን በትእግስት፤ ሰቶ በመቀበል፤ በውይይት፤ በመደራደር የሚመጣ እንጂ በአዋጅ የሚመጣ ስላልሆነ  ጊዜ መውሰዱ አይቀርም።

እስከዛስ?  ባለን እንጀምራልን። የምርጫ ህግ አለን፤ የሚቻለውን ያክል ፍትሃዊ አድርገን እንጠቀምበት፤ ቅንነትና እውነተኝነት ጎድሎ ነው እንጂ ያለውም ያሰራል። የምርጫ ክልሎችና ጣብያዎች አሉን፤ ህገ መንግስት፥ህግና ህግ አስፈጻሚ አለን፤ ፈጽሞ አላሰራ ስላላለ እሱኑ ይዘን ለተሻለው እንስራ። በብሄር ላይ የተደራጁ ፓርቲዎች ብዙ ናቸው፤ በዜግነት የተደራጁም እንዲሁ። ይወዳደሩ እና ምን እንዳላቸው ህዝብ ይስማ። በስሜትም ይሁን በማወቅ የፈለገውን ህዝቡ ይናገር፤ ነገም እኮ ሌላ ቀን ነው። ዛሬ ላይ እነ ዶ/ር መራራ እናሸንፋልን እንዳሉት ቢያሸንፉ እንኳ ዘላለማዊ ሆኑ ማለት አይደለም።መስከረም በብዙ ጥፋቱ ምክንያት እየጠተላ ያለው ያልሽው “የዘር ፓለቲካ” በውነት ለመጠላቱ/ላለመጠላቱ በምርጫው ላይ ምልክት እናያለን። ስለህዝቡ ወቅታዊ ስነልቦና ማንም አስቀድሞ ሊወስን አይችልም። ደግሞም እሄ አስተሳሰብ ጠፍቶ በዚህኛው እስኪተካ ምርጫ ማካሄድ የለብንም ማለት ራሱ ምርጫ ማሳጣት ነው። እነ ዶ/ር መራራ እንዳያሸንፉ ብሎ ወይም የዘር ፓለቲካ መሰረት እስኪጠፋ ብሎ ምርጫን ማራዘም ሌላ እልክ ሌላ ቁጭት በኦሮሞ ላይ ይፈጥራል። እስከዛሬ ያለው አይበቃንም?  ምናልባትም እኮ የብሄር ፓለቲካና የዜግነት ፓለቲካ  በሂደት ተራርመው የተሻለ የፓለቲካ ቅርጽ ሊያመጡ ይችላሉ። እንዲያው ሁሉም በቅንነት ሰርቶ እንኳ ኢትዮጵያን ያለ ብሄር ፓለቲካ ለማየት በጣም ረጅም አመታት ይወስዳል ብዬ አስባለሁ። ግን ይመጣል። ፍጥነቱም ኢትዮጵያ ኦሮሞንና ሌሎች ደቡባውያንንም (ሰሜነኞቹን እንዳለ ይዛ ማለቴ ነው) ባይ ዲፎልት ለመወከል/ለመምሰል በምታደርው ግስጋሴ ላይ ይመሰረታል። ለምሳሌ ኢትዮጵያ  ሲባል ኦሮምኛ ቋንቋ አብሮ (አማርኛ እንዳለ ሆኖ) የሚታሰብ፤ ኢትዮጵያ ሲባል የሲዳማ ዘመን መለወጫ ጨምበላላ  አብሮ የሚታሰብ፤ ወዘተ።  ደግሞም እኮ ዘገምተኛ ሆነ እንጂ በተለይ ከደርግ ዘመን ጀምሮ ብዙ እኩልነትን የሚያመጡ አበረታች ስራዎች ተሰርተዋል። ከአሁን በኋል አንዱ አንዱን የሚውጠበት ሳይሆን አንዱ የሌላውን ባህልና ስነልቦና ከውስጥ ከልብ የሚቀበልበት ዘመን ነው መምጣት ያለበት። አንዳንዱ ለውጥ በአዋጅና በፓሊሲ ድጋፍ ሊመጣ ይችላል፤ ብዙዎቹ ግን እንዲሁ በህዝብ ፍቃድ እና ይሁንታ የሚመጡ ናቸው። እንደ መስከረም አበራ ያሉ ጎበዝ ጸሃፊዎች ያለቸውን ችሎታና ጸጋ ለጥቂት ትችትና በብዛት ግን ለግንባታ ቢጠቀሙበት ብዙ እናተርፋለን። መስከረም እስኪ ከምትወጂው የደቡብ ባህል ውስጥ አንዱን ናሽናላይዝ ለማድረግ የሚያስችል ስራ ጀምሪ። ወይም አማርኛው እንደሚያምርብሽ ኦሮሚኛንም ሞክሪና ለሌላው ምሳሌ ሁኝ። ወይም በሌላ ኢትዮጵያውነት መልክ ተገለጪ።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here