Home News and Views የሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ወንድም አቶ ኢሳያስ ዳኘው ምርምራ ውስብስብ እንደሆነበት ፖሊስ...

የሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ወንድም አቶ ኢሳያስ ዳኘው ምርምራ ውስብስብ እንደሆነበት ፖሊስ ገለጸ

የኢትዮ ቴሌኮም ከፍተኛ የስራ ኃላፊ የነበሩት እና የሜጀር ጀነራል ክንፈ ዳኘው ወንድም አቶ ኢሳያስ ዳኘው የግዢ ስርአቱን በጣሰ መልኩ ሜቴክ ጨረታ እንዲያሸንፍ በማድረግ ወንጀል ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በጊዜ ቀጠሮ እየታየ ቢሆንም መርማሪ ፖሊሱ ምርመራው ውስብስብ እንደሆነበትና ማስረጃ ማሰባሰቡን አለማጠናቀቁን በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ተጨማሪ ቀነ ቀጠሮ እንዲሰጠው ጠየቀ።
የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛ ወንጀል ችሎት ትናንት ከመርማሪ ፖሊሱ የቀረበውን ሃሳብ አዳምጦ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ በመፍቀድም ለጥር ስድስት ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

አቶ ኢሳያስ በጠበቃቸው አማካኝነት፤ የፌዴራል ወንጀል ምርመራ ቢሮ ያቀረባቸው ምክንያቶች በተደጋጋሚ ሲቀርቡ የነበረና እስካሁን ያልተሰሩ መሆናቸውን፣ ከሜቴክና ከኢትዮ ቴሌኮም ማስረጃ እናቀርባለን ሲሉ የነበረው ከመጀመሪያው የጊዜ ቀጠሮ አንስቶ እንደነበረና እስካሁን አለመቅረቡ ተገቢ እንዳልሆነ ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡ መርማሪ ፖሊስ ምስክሮች ክፍለ ሀገር መሆናቸውን መናገራቸውን የጠቆሙት የተጠርጣሪው ጠበቃ፤ ከዚህ ውጪ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ስራ እንዳልሰሩ ጠቁመዋል፡፡ ያልሰሩበትን ምክንያት እንዲያስረዱም ጠይቀዋል፡፡

ፖሊስ እስካሁን የማጣራት ስራ ሲሰራ ከቆየ በኋላ በመስሪያ ቤቱ ኦዲት ይደረጋል መባሉ የምርመራ ስራውን ወደ ኋላ የሚመልስ መሆኑን በመጠቆምም፤ የእርሳቸው ጉዳይ ውስብስብ አይደለም፣ አንድና በቀላሉ ሊደረስበት የሚችል ሆኖ ሁለት ወራት ሙሉ በእስር ላይ መቆየታቸው ተገቢነት እንደሌለው፣ ምርመራውም ከበቂ በላይ ጊዜ መውሰዱን አመልክተዋል፡፡

ተጠርጣሪው ምስክር ያባብላሉ፣ ይጠፋሉ በሚል በዋስ ወጥተው ጉዳያቸውን እንዳይከታተሉ የቀረቡት ምክንያቶች ግምቶች ናቸው ያሉት የተጠርጣሪው ጠበቃ፤ አቶ ኢሳያስ ከ1974 ዓ.ም. አንስቶ በተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ውስጥ ማገልገላቸውን፣ በሁለት ወራት ቆይታቸውም ለፖሊስ ተባባሪ በመሆን እንጂ ማስረጃ በማጥፋት የቀረበባቸው ቅሬታ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ለፖሊስ ከዚህ በላይ ተጨማሪ ጊዜ ሊፈቅድላቸው አይገባም፣ ለዋስትና መንፈጊያ ምክንያት ስለማይሆን የዋስትና መብታቸው ይፈቀድ ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ፤ በተሰጠው የምርመራ ጊዜ በመሃል በዓል ስለነበር የነበሩት የስራ ቀናት ሶስት እንደነበሩ ጠቅሶ፤ ምስክሮች እንዲቀርቡ ማድረጉን፣ በአካል ያልተገኙትንም በስልክ እንዳገኟቸውና በበዓል ምክንያት ሊደርሱ እንዳልቻሉ ገልጸዋል፡፡ ምስክሮቹ ጠረፍ እንዳሉና መጥሪያ እንደተላከላቸው፣ ምርመራው ውስብስብ እንደሆነበትም ለችሎቱ አስረድቷል፡፡ የኦዲት ሪፖርቱ አስፈላጊ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ተጠርጣሪው ቢወጡ ማስረጃ ሊያጠፉ ምስክርም ሊያባብሉ ይችላሉ በማለት ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም የግራ ቀኙን ክርክር አዳምጦ ለሰኞ ጥር ስድስት ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here