Home News and Views ከድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች ሕብረት – ሳተናው የተሰጠ መግለጫ

ከድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች ሕብረት – ሳተናው የተሰጠ መግለጫ

ቀን 16/05/2011 ዓ.ም. ቁጥር 001/2011
ከድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች ሕብረት – ሳተናው የተሰጠ መግለጫ

እኛ በሃገር ውስጥና በመላው ዓለም የምንገኝ የድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች ከጊዜ ወደ ጊዜ ውድቀቷ እየተፋጠነ ባለችውና፤ ተመልካች ባጣችው ድሬዳዋና ነዋሪዎቿ ላይ እየደረሰ ያለው ግፍና በደል ከመሻሻል ይልቅ እየባሰ መምጣቱን በመታዘብ ፣ በየግላችን ከንፈር እየመጠጥን መኖሩ ማብቃት አለበት ብለን በማመን በጋራ ሆነን ድሬዳዋን ወደ ቀደመ ክብሩዋ እንድትመለስ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ ተሰባስበናል።

ከሁለት አመታት በፊት በግለሰቦች እንቅስቃሴ የተጀመረው ይህ ጥረት ወደተደራጀ የማህበር እንቅስቃሴ በማደግ በከተማችን እየተከሰቱ ያሉ የመልካም አስተዳደር እጦቶችን ሲያጋልጥ እንዲሁም ህዝቡ መብትና ግዴታውን አውቆ ለተፈጻሚነቱም ዘብ ሆኖ እንዲቆም ሲቀሰቅስ ቆይቷል። ይህንን እንቅስቃሴ ለማጎልበትና ህጋዊ መሰረት ያለው ለማድረግ በኢትዮጵያ ማህበራት ማደራጃ አዋጅ መሰረት ተመዝግቦ ለመንቀሳቀስ አስፈላጊ ዝግጅቶችን እያደረግን እንገኛለን። ከዚህ ጎን ለጎን ማህበራዊ መሰረቱን ለማስፋት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን በማድረግ በቅርብ ግዜ አባላትን በውጭም በሀገር ውስጥም መመዝገብ ይጀምራል።

ይህንን እና የመመስረቻ ጉባኤውን በተመለከተ በቅርቡ መረጃ የምንሰጥ መሆኑን ለአባላት እና ደጋፊዎቻችን በደስታ እንገልጻለን። ይህንን እንቅስቃሰያችንን ለማሳለጥና ተደራሽነቱንም ለማስፋት ከምንጠቀምባቸው የፌስቡክ ፔጆቻችን (ማለትም የድሬዳዋ ልጆች ህብረት- Children of Dire Dawa Union እንዲሁም ሳተናው የድሬዳዋ ልጆች ህብረት) በተጨማሪ በዩቱብ አዲስ ሳምንታዊ ስርጭት ልንጀምር ዝግጅታችንን አጠናቀናል።

ይህ በንዲህ እንዳለ ይህን አስቸኳይ ያቋም መግለጫ እንድናወጣ ያስገደደን ከቅርብ ግዜ ወዲህ እየተበራከተ የመጣው አለመረጋጋት እና የሰላም መደፍረስ ነው። በመላው ኢትዮጵያ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ የድሬዳዋ የሰላም መደፍረስ ይሻሻላል ፣ ይለወጣል ብለን ተስፋ ብናደርግም እውነታው ግን ከድጡ ወደ ማጡ ሆኖ ረብሻና አለመረጋጋት የከተማችን የዕለት ተዕለት ዜና ሆኗል። ይህም አልበቃ ብሎ ከተማችን ድሬዳዋ የምትታወቅበት ፍቅር፣ መቻቻል፣ መተሳሰብ እና የአንድነት እሴቶችን በሚጽረር መልኩ ነገሮች ወዳላስፈላጊ መንገድ እንዲያመሩ እየተደረጉ ይገኛሉ። ጸረ ሰላም ሀይሎች ከሳምንታት በፊት በኦሮሞ እና ሶማሌ ወንድሞቻችን መካከል ቅራኔ እንዳለ በማስመሰል የፈጠሩት አለመረጋጋት ክቡር የሆነውን የሰው ህይወት ቀጥፎ የብዙዎችን ንብረት ማውደሙ የፈጠረብን የውስጥ ሀዘን ገና ሳይሽር ዛሬ ደግሞ ሌላ ልብ የሚሰብር ዜና ሰማን። የጥምቀትን በዓል ለማክበር የወጣው የእግዚአብሔር-አብ ታቦት በዓሉን አሳልፎ በእለተ ቀኑ ማለትም ጥር 13 ቀን ወደ ቦታው ከተመለሰ በኋላ፤ ምዕመናኑም ታቦቱን አስገበተው ሲመለሱ የማንንም ብሄር ፤ የማንንም ዕምነት የማይወክሉ፤ እጃቸው በደም የተጨማለቀ አካላት ያሰማሯቸው ጸረ-ሰላም ሀይሎች ሕዝበ-ክርስትያኑን በድንጋይ እና በዱላ በመደብደብ አሳፋሪ የሆነ ድርጊት ፈጽመዋል። በዚህም ምክንያት የከተማው ሕዝብ እስላም ክርስቲያን ሳይል ተቆጥቶ በመውጣት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ከተማዋ ትገኛለች። እኛም ይህንን ጉዳይ በቅርበት በመከታተል አስቸኳይ ስብሰባ ካካሄድን በሗላ የሚከተለውን ባለ አምስት ነጥብ ያቋም መግለጫ አውጥተናል።

1. እነዚህ የትኛውንም ብሄርም ሆነ ሃይማኖት የማይወክሉ አጥፊዎች ባስቸኳይ በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ። እንደከዚህ ቀደሙ ተድበስብሶ የሚቀር ሳይሆን ለህግ የበላይነት ሲባል የሚወሰድባቸው እርምጃ ለህዝቡ በይፋ እንዲገለጽ።

2. ለእነዚህ ወንጀለኞች ተልዕኮና ከለላ የሚሰጡ በአስተዳደሩ ውስጥ ያሉ አመራሮች እንዲሁም ከተማውን እያስተዳደሩ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ተጣርተው ለህግ እንዲቀርቡ

3. የፌዴራል መንግስቱ ጉዳዩ ተባብሶ የከፋ ደረጃ ሳይደርስ በፊት ችላ ማለቱን ትቶ ጣልቃ እንዲገባ

4. የተለያዩ የሚዲያ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው የወገኖቻችን ድምጽ እንዲሆኑ ጥሪ እናቀርባለን

5. የከተማዋ ነዋሪም ሁሉም በየአካባቢው ተደራጅቶ ከፖሊስ ጋር በቅንጅት በመስራት ወንጀለኞችን እንዲያጋልጥ ጥሪ እናደርጋለን ሰላም፤ ፍቅርና፤ አንድነት፤ ለመላው ሃገራችን ይሁን።

ከድሬዳዋ ልጆችና ወዳጆች ሕብረት – ሳተናው
satenawdire@gmail.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here