Home News and Views ዜግነትና ጎሠኛነት | መስፍን ወልደ ማርያም

ዜግነትና ጎሠኛነት | መስፍን ወልደ ማርያም

የካቲት 2011

በማኅበራዊ ሳይንስ የኅብረተሰብ እድገት መሠረታዊ ትምህርት ነው፤ በዚህ ትምህርት ውስጥ የማናቸውም ኅብረተሰብ ታሪክ ከዝቅተኛ ደረጃ ወደከፍተኛ ደረጃ የሚሸጋገር እድገትን ያሳያል፤ በሃማኖትም ሆነ በኑሮ (ኢኮኖሚ)፣ በአስተዳደርም ሆነ በሥልጣን ከዘመን ወደዘመን እድገትን ያመለክታል፤ ይህ እድገት በፍጥነትም ሆነ በዓይነት ተመሳሳይና አንድ ዓይነት መልክ የያዘ አይደለም፤ አንዳንዱ ቆሞ የሚቀር ነው፤ አንዳንዱ ከመጀመሪያው አንሥቶ እየዳኸ የሚንቀሳቀስ ነው፤ አንዳንዱ እየበረረ አትድረሱብኝ ይላል፤ አሁን የምንነጋገርበት ርእስ፣ ዜግነትና ጎሣ፣ ይህንን የኅብረተሰብ እድገት የሚያመለክት ነው፡፡

በዝቅተኛ ደረጃ የሚንከባለሉ ሰዎች የሚኖሩበት ሥርዓት ጎሣ ነው፤ ማየት፣ መስማትና ማወቅ ለፈለገ ሰው ማስረጃው በዙሪያችን አለ፤ በሶማልያ፣ በጂቡቲ፣ በሱዳንና በየመን እያየነው ነው፤ በኢትዮጵያም እየታገለ ነው፤ በቀላሉ ልንረዳው የምንችለው ጎሣ ገና ያልተረጋጋ የቤተሰብ ስብስብ ነው፤ የሰዎች የዝምድና ዝንባሌ ያለው በቤተሰቦች ላይ ነው፤ በዚህም ምክንያት የጎሣ ሥርዓት የተረጋጋና ቅርጽ ያለው አይደለም፤ ልል ስለሆነ ለትርምስ የተጋለጠ ነው፤ በአካባቢያችን የሚገኙት ሶማልያ፣ ሱዳንና የመን ምስክሮች ናቸው፤ በኢትዮጵያ ውስጥም በኦሮምያ በማቆጥቆጥ ላይ የሚታየው ይኸው ጎሣ የምንለው ልል የቤተሰቦች ስብስብ ነው፤ በአለፉት ሀያ አምስት ዓመታት ውስጥ የልልነቱንና የዝቅተኛነቱን ልክ አይተናል፤ አንድ ብቻ ለመጥቀስ እኔ ምስክርነት ልሰጥበት የምችለው ሌንጮ ለታን ነው፤ ከግለሰብ ጋር አያይዘን አንመልከተው፤ ግለሰቡ መገለጫው ነው፡፡

በአለንበት ዘመን ዜግነት ከፍተኛውን የኅብረተሰብ የእድገት ደረጃ የሚያመለክት ይመስለኛል፤ ዜግነት የሚመሠረተው በእያንዳንዱ ግለሰብ ሉዓላዊነት ላይ ነው፤ ዜግነት የሚመሠረተው በሕዝብ ፈቃድ ላይ ነው፤ ዜግነት የሚመሠረተው በሕግ ላይ ነው፤ ዜግነት በከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለና የሠለጠነ ሕዝብ ማንነት ነው፡፡

በጎሣ ውስጥ የግለሰብ ሉዓላዊነት የሚባል የለም፤ ሉዓላዊነት ቢኖርም የጎሣው ነው፤ የጎሠኛነት የኋላቀርነቱ መሠረት የግለሰብ ሉዓላዊነት አለመኖሩ ነው፤ ጎሠኛነት ግለሰብነትን አይፈቅድም፤ ግለሰብነትን እንደጠላት አድርጎ ይቆጥረዋል፤ ያለግለሰብ ሉዓላዊነት ዴሞክራሲ የሚባል ነገር አይታሰብም፤ ከሩስያ ጀምሮ ወደምሥራቅ ያሉ አገሮች ሞክረውት ሳይሳካላቸው ቀርቶ ያፈረሱትና እያፈረሱት ያለ ማታለያ ነበር (መልከ-ጥፉን በስም ይደግፉ እንደሚባለው PEOPLE’S DEMOCRATIC REPUBLIC ሦስቱን የእንግሊዝኛ ቀላት ለመተርጎም ቀላል ነው፤ የሕዝብ፣ የሕዝብ፣ የሕዝብ! ሕዝብ ተንጠልጥሎ ቀረ! የቸገረው እርጉዝ ያገባል!)፡፡

በዜግነት ላይ የሚመጣ ዴሞክራሲ ወይም መንግሥተ ሕዝብ የእያንዳንዱን ግለሰብ ሉዓላዊነት በይፋ ያወጣዋል፤ በዚህም ምክንያት የግለሰቦች ችሎታ በሙሉ ነጻነትና በሙሉ ኃይሉ እየተጠናከረ ይወጣል፤ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ትርጉም የሚኖረው የግለሰብ ሉዓላዊነት በታወጀበት ብቻ ነው፤ የጎሣ ሥርዓት በዜግነት ሥርዓት ውስጥ የሚታየው እድገትና ልምላሜ ያስጎመጀዋል፤ ይመኘዋል፤ ስለዚህም በጎሣ ላይ ዴሞክራሲን ለመለጠፍ ይጥራል፤ ይህ አንዱ የጎሣ ሥርዓትን ዝቅተኛ ደረጃ የሚያስረዳ ነው፤ የግለሰብ ሉዓላዊነት በሌለበት የግለሰብን ምርጫ የሚያሳይ ዴሚክራሲ ከየት ይመጣል? የግለሰብ ነጻነት በሌለበት የግለሰብ ችሎታ ከየት ይመጣል? ግለሰብነት፣ ነጻነት፣ እድገትና ዜግነት የተያያዙ ናቸው፤ ጎሠኛነት የሦስቱም ተቃራኒ ነው፤ የአንድ ሰው ግለሰብነት የሚወጣበት መንገድ ብዙ ነው፤ ለመለዋወጥ ያለውም ችሎታ ብዙ ነው፤ በጋብቻ ብቻ አይደለም፤ በሃይማኖትም፣ በቋንቋም፣ በመኖሪያ ሰፈርም፣ በሥራም…፡፡ ዜግነት በሚንቀሳቀሰው ላይ፣ ወደፊት በሚመጣውና ባልታወቀው ላይ የተመሠረተ ነው፤ ወደፊት ለመራመድ ሁሌም ከአለፈው ጋር መታገል አለበት፡፡

ጎሣ እግዚአብሔር እንደፈጠረው የሚቆይ ነው፤ ይበታተናል እንጂ አይሰባሰብም፤ ያንሣል እንጂ አያድግም፤ይፎካከራል እንጂ አይተባበርም፤ ሚኔሶታ የአንድ ሉባ አገር አይደለም፤ አይሆንምም፤ ጎሠኛነት በማይንቀሳቀሰው፣ በአለፈውና በደረቀው ላይ የተተከለ ነው፤ ወደኋላ እንጂ ወደፊት አያይም፤ ወደኋላ ለመቅረት ሁሌም ከአዲሱና ከሚመጣው ጋር መታገል አለበት፡፡

ብሔራዊ ማንነት ትልቅ ስብስብ ነው፤ ጎሠኛ ማንነት የመንደር ስብስብ ነው፤ ብሔራዊ ማንነት የእድገት መንገድ ነው፤ ጎሠኛ ማንነት የቁልቁለት መንገድ ነው፤ ሰው የመሆን መሠረታዊው ምርጫ ይኸው ነው፡፡

አለባብሰው ቢያርሱ
ባረም ይመለሱ!

1 COMMENT

  1. In Gondar they ask people” are you Amara or are you Islam?”

    Religious leaders need to continue to preach to us on who to vote for.In Ethiopia Voting takes places in family , In Mosques., Churches , edir , neighborhood associations , Schools , sport teams and so on. That is how we know about voting since we were children. We Donot need to be preached about the voting process just because electing political leader is not “our cup of tea” ,we just need to be told who to vote for, that is why we rely on religious leaders suggestions on who to vote for.

    https://ethsat.com/2019/02/ethiopia-arson-gutted-over-dozen-churches-mosques/

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here