Home News and Views የዶ/ር ወርቅነሕ ገበየሁ ሹመት | በእሸት በቀለ

የዶ/ር ወርቅነሕ ገበየሁ ሹመት | በእሸት በቀለ

የቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተቃውሞ የነቀነቀው መንግሥታቸውን ለመታደግ ሹም ሽር ሲያደርጉ ወርቅነሕ ገበየሁ (ዶ/ር) በውጭ ጉዳይ ምኒስትርነት ዶክተር ቴድሮስ አድኃኖምን ተኩ። ይኸ የሆነው በጥቅምት 2009 ዓ.ም. ነበር። ከሁለት አመት ገደማ በኋላ ድንገት በተባበሩት መንግሥታት የኬንያ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሲሾሙ ማን እንደሚተካቸው አልታወቀም። እርሳቸው ግን በኬንያ ቢሮውን በጊዜያዊነት ሲመሩ የቆዩትን ጋናዊቷን ማይሙናህ ሞሕድ ሻሪፍን ይተካሉ።

ውጭ ጉዳይ ምኒስትሩ የተሾሙበት የኬንያ ቢሮ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ዋና መስሪያ ቤት ነው። ከዚህ ቀደም ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ በኃላፊነት አገልግለውበታል። ወርቅነሕ በዳይሬክተር ጄኔራልነት ሲያገለግሉ በኬንያ ለሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ቢሮ እንቅስቃሴዎች ሁሉ ኃላፊነት አለባቸው። የዋና ጸሀፊው ተወካይ እንደመሆናቸው በቀጠናው ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲ እና ሌሎች አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ ምክር እና ድጋፍ ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል።

“ወርቅነህ ገበየሁ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትን የማሻሻያ ሂደት በተለይም ወቅታዊውን የአፍሪካ ቀንድ ውህደት የኢትዮጵያ መሪነት በብቃት ሲያስኬዱ ቆይተዋል” ያለው የጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጽህፈት ቤት የእንኳን ደስ አለዎ መልዕክት አስተላልፏል።

ወርቅነሕ ከዚህ ቀደም የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል፣ የትራንስፖርት ምኒስትር፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው አገልግለዋል።
የ50 አመቱ ፖለቲከኛ ለአስር ገደማ አመታት የኢትዮጵያ ፌድራል ፖሊስ ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል። ዛሬም ድረስ ይኸው ሥልጣናቸው ስማቸው ሲነሳ አብሮ ይጠቀሳል። ተቺዎቻቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጽም ነበር እየተባለ ለሚወቀሰው የደኅንነት መስሪያ ቤት የቀረቡ መሆናቸውን እያስታወሱ ተከታታይ ሹመታቸው አይዋጥላቸውም። የኦሮሚያ ጸጥታ ቢሮንም በኃላፊነት መርተዋል።

ወርቅነሕ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካ ሳይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት (የመጀመሪያ ዲግሪ) እንዲሁም ዓለም አቀፍ ግንኙነት (ማስተርስ) አጥንተዋል። ክሪምናል ጀስቲስ እና የፖሊስ ሳይንስን በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ አጥንተው ዶክተር ከተባሉ አምስት አመታት ተቆጥረዋል። እዚህ ጋ ወርቅነህ ፖለቲካ በፖሊስ ስራ ላይ የሚየሳድረውን ጫና የተነተኑበት የመመረቂያ ጥናት ሊጠቀስ ይገባል። ጥናታቸው ፖለቲካ እና የፖሊስ ስራ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከመያዙ በፊት እና በኋላ ያላቸውን ግንኙነት ይዳስሳል። በጥናታቸው ገለልተኛ መሆን የሚገባው ፖሊስ ከሕዝብ ባሻገር ተጠያቂነቱ ኢትዮጵያን ለሚመራው ፓርቲ እና ለአጋሮቹ መሆኑን የሚጠቁም መረጃ ማግኘታቸውን አትተዋል። የሚከተለው ጥቅስ ምን አልባት የጥናቱን ጭብጥ ይጠቁማል።

“policing is embedded into politics which by itself is a challenge because the police are expected to be professionally independent in order touphold the rule of law while at the same time guaranteeing the safety and security of all the inhabitants of the country. … some police officers do not have a clear understanding of the police function and to who they should be accountable to. Both quantitative and qualitative findings indicate that the police are regarded as accountable to the public, but there are also indicators that police are accountable for the ruling party and its allies.”

የወርቅነሕ ሹመት በኢትዮጵያ ከነበራቸው ኃላፊነት አኳያ ትችት አላጣውም። በሒውማን ራይትስ ዎች የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጥናት ባለሙያው ፌሊክስ ሆርን ወርቅነሕ በኢትዮጵያ የፌድራል ፖሊስ እና የደኅንነት መሥሪያ ቤት የነበራቸውን ኃላፊነት አስታውሰው እንዲህ ከፍ ላለ ሥልጣን መብቃታቸውን አሳሳቢ ብለውታል።

በ1997 ምርጫ ማግስት ወርቅነሕ ገበየሁ በበላይነት ይመሩት የነበረው የፌድራል ፖሊስ ተቃዋሚዎችን መግደል እና የጅምላ እስርን ጨምሮ የከፉ ጥሰቶች መፈጸሙን ፌሊክስ ሆርን አስታውሰዋል። የጥናት ባለሙያው የተባበሩት መንግሥታት ሰዎች የሚሾሟቸው ባለሥልጣናት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈጸም ተሳትፈው እንደሁ ማጣራት ይገባቸው እንደነበር ጥቆማ ሰጥተዋል።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here