Home News and Views ሀዘኔ ቅጥ አጣ! የጎንደር ግጭት (አብርሃም በየነ)

ሀዘኔ ቅጥ አጣ! የጎንደር ግጭት (አብርሃም በየነ)

 

ገዳዩ ወንድሜ ሟቹም አጎቴ ነው  
                    ኧረ እናንተ ሆየ ሀዘኔ ለማን ነው?      

የሰብል ግርድ፣ የጠጅ አምቡላ፣ የጠላ አተላ፣ የአርቂም ብሪንጥ እንዳለው ሁሉ የማርክሲዝም/ሌኒንዝም ግርድና አተላም ጠባብ ብሔረተኝነት ነው። የሶቪየት ህብረት፣ የየጎዝላቪያና የችኮዝላቫኪያ ኮሚኒስቶች “የዓለም ላብ አደሮች አንድ ሁኑ” ብለው እንዳልሰበኩ ከሶቬየት ህብረት መፈረካከስ በኋላ እጅግ ወርደው የሰበኩት የዘውግ ፖለቲካን ነበር። የዘውግ ፖለቲካ በነዚህ አገራት ላይ ያስከተለው ማህበራዊ ቀውስ ባንድ ወቅት ዓለምን ሲያራኩት ተስተውሏል። ቀውሱ ህይዎት አጥፍቷል። ንብረት አውድሟል። ዜጎችን ከቀያቸው አፈናቅሏል። አሰድዷልም። ብሎም ትንንሽ ምጽዋተኛ ሀገራትን በየጎዝላቪያና በችኮዝላቫኪያ ወልዷል።

በኢትዮጵያ እየታየ ያለው ክስተትም ታሪክን ለመድገም እንዲሉ ትግብርቱ 27 ዓመታትን አስቆጥሯል። ዜጎች በአርባ ጉጉ፣ በወተር፣ በበደኖ፣ በጋምቤላ፣በጌዲዮ፣ በኮንሶ፣ በቤና ሻንጉልና ዛሬ ደግሞ በጎንደር ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። የዚህ ሁሉ መፈናቀል ምክኒያትም ወያኔ የፈጠረው ዘረኝነት ነበር። ይህ ህዝብን በዘር የማፋጀት ዓላማም ግቡ በሌላው ኪሳራ ትልቋን ትግራይ ለመገንባት መሆኑ አንድና ሁለት የለውም።

የትልቂቷ ትግራይ ምሥረታና ግንባታ ዕውን መሆን የሚችለው ኮንሶ ሲጠፋ ወይም ጋምቤላ ሲከስም አይደለም። ጎንደር የሚባል ክ/ሀገር ሲጠፋ ብቻ እንጂ። ስለሆነም ከማንም በፊት የጎንደር ህልውና መክሰም ለትልቂቷ ትግራይ ምሥረታና ግንባታ ዋስትና ሰጭ መሆኑ ታምኖበት በ1968ቱ የወያኔ ማንፌስቶ ተጠንስሦ ትግብርቱ እየተከናወነ ይገኛል። የወያኔ መሪዎች ወሎን በአገውና በኦረሞ፣ ጎጃምን በአገውና በጉምዝ ጎንደርንም በቅማንት አመጽ አማራውን አጥፍተው የነርሱን የመስፋፋት ዓላማ ዕውን ለማድረግ ነበር ስትራቴጂ ነድፈው ለ27 ዓመታት የተንቀሳቀሱት።

በወሎና በጎጃም የታሰበው የርስ በርስ ፍጅት ለጊዜው የጎላ ባይሆንም በጎንደር በቅማንትና በአማራ መሃል የተፈለገው መከፋፈል ግን ጊዚያዊ ቢሆንም ሰምሮላቸዋል። ትግሬዎቹ በፈጠሩት ልዩነት ሁለቱ ወንድማማች ማህበረሰቦች “እናንተና እኛ” ተባብለው ደም ተቃብተዋል። ከዚያም አልፈው ወደ ግልጽ ጦርነት ገብተዋል።

የልዩነቱ አጀማመር

   ወያኔ የትግራይ ሪፖብሊክን ምሥረታ ያወጀው በ1968 ዓ.ም ማኒፌስቶው ነበር። የዚህ ዓላማ አራማጆች ስዩም መስፍን ስብሃት ነጋና መለስ ዜናዊ ከቀሪው የማዕከላዊ ኮሚቴ ዕውቅና ውጭ ነበር ማኒፌስቶውን ነፍስ የዘሩበት። ከጀርባቸው የተጎነጎነውን ሴራ ሲሰሙ የተቃውሞ ድምጽ ያሰሙት አረጋዊ በርሀ፣ ግደይ ዘራጺዮንና ተክሉ ዋዝ ሲሆኑ ተክሉ ሃዋዝ የህይዎት ዋጋ ሲከፍል አረጋዊና ግደይ ግን በስንብት ተወግደዋል። የወያኔን የውስጥ ለውጥ ተከትሎም መለስ ዜናዊ የመሪነት ዘንጉን ጨብጦ ትልቂቱን ትግራይ ለመመሥረትና ለመገንባት ታክቲክና ስትራቴጂ ነደፈ። ቀዳማይ ዕቅዱ ጣሊያን

 

የነደፈውን የትግራይ ትግርኝ መንግሥት መመሥረት ነበር። ኤርትራንና ትግራይን አዋህዶ። በሂደት ግን ይህ ህልም ተግባራዊነቱ እየደበዘዘ ሲመጣ እቅዱ ትግራይን ገንጥሎ አገር ወደ ማድረጉ አዘነበለ።

ከግንጠላው በፊት ግን ትግራይ በቂ የአቅም ግንባታ እንዲኖራት ከአፋር፣ ከወሎና ከጎንደር ለም መሬቶችን የመንጠቅ እቅድ ተነደፈ።

በዕቅዱም መሠረት ተጋሩ ወደ አፋር ዘልቀው የድኝና (sulfur) የጨው ማእድን ቦታዎችን አፋሮቹን በማፈናቀል ማዕድኑን ተቆጣጠሩ። ከመንግሥት ባንክ በተሰጠ ድጎማም በርካታ የትግራይ ተወላጆች በዘመናዊ እርሻ ልማት በአዋሽ ሸለቆ ተሰማሩ። የህዝብ ሰፈራም አካሄዱ። ወደ ወሎም በተመሳሳይ የትግራይ ካድሬዎች የሰፈራ ሥራውን በስፋት አከናወኑ። አሁንም ተወላጆቹን እያፈናቀሉ ትግሬዎችን በቦታው አሰፈሩ።

በጎንደር በኩል የተደረገው መስፋፋት ግን ለየት ያለ ሂደት ነበረው።

ወያኔ ገና በትግል ዘመኑ ነበር ዛሬ የትግሬ “የሆነውን” የጎንደር ግዛት በጦርነት ከኢህአፓ የነጠቀው። ቀደም ብሎ ወልቃይትን በኋላም ጠለምትን። ወልቃይትን እንደ መውጫና መግቢያ በር ተጠቅመውም በሱዳን በኩል የሚፈልገውን የውጭ እርዳታ በገፍ አስገባ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ነበር ቢትወደድ አዳነ መኮንን ከኢህአፓ ከድተው ወደ ወያኔ በሚሄዱ ሰዎች የተገደሉት። የርሳቸውን አሟሟት ተከትሎም በአርማጭሆ ህዝብና በኢህአፓ መሃል ግጭት ተፈጥሮ ኢህአፓ ቦታውን ለቆ ወደ ቋራ ሄደ። የተፈጠረውን ክፍተት ተጠቅሞ ደርግ ቦታውን እንዳይቆጣጠረው ስጋት ያደረባቸው ሁለት የትግሬ ዝርያ ያላቸው የጎንደር ተወላጆች፤ የኢዲዩ ሹማምንት የነበሩት ሻለቃ በሪሁን ገረየስና አቶ ይርጋ ደስታ ወደ ሽሬ ተጉዘው ኢህአፓ የለቀቀውን አርማጭሆን ቄ አቀረቡ። ስለደህንነቱ ስጋቻ የነበረው ወያኔም ጥያቄውን ባቀረቡለት ግለሰቦች ዋስትና ተሰጥቶት ጥያቄአቸውን ተቀብሎ አርማጭሆ ገባ።

በሁኔታዎች መለዋወጥ በለስ የቀናው ወያኔ ወደ ቋራ ገፍቶ በሱዳን ኃይል እገዛ ኢህአፓን መትቶ በቀላሉ ወደ መሃል አገር አቀና። አዲስ አበባንም ተቆጣጠረ። አዲስ አበባን እንደተቆጣጠረም በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም (1991 እ.ኢ.አ) መተማ ላይ የቅማንትን ህዝብ ስብስባ ጠራ። ህዝቡ ግን እኛ ሁላችንም “አማራ ነን” በማለት ደምድሞ አንድም ሰው በስብሰባው ሳይገኝ ቀረ። ተስፋ ያልቆረጠው ወኔ ቀጥሎም የአማራ ህዝብ ሰብሰባ ብሎ ጠራ። አሁንም ህዝቡ እኛ “ቅማንት ነን” ብሎ ሳይሰበሰብ ቀረ። በዚህ መልክ ሙክራው ግቡን አልመታለት ሲለው ሌላ ዘዴ ዘየደና አማራ አገር ተወልደው ያደጉ ትግሬዎችን ከሱዳን ወደ መተማ በመውሰድ በብዛት አሰፈረ።

ሰፈራው እንደተጠናቀቀም በ1987 ዓ.ም (1995 እ. ኢ.አ) አማራ የሚመስሉትን ትግሬዎች የበላይ ኃላፊ እያደረግ በየደረጃው አስቀመጠ። በዚህ መልክ የመጀመሪያው የመተማ ከንቲባ ሆኖ የተሾመው አረጋዊ የተባለ የትግራይ ተወላጅ ነበር። አረጋዊ ወደ መተማ ከመሄዱ በፊት በአርማጭሆ የቅማንት ተወላጅ የሆኑትን የአቶ ታየ መለሰን ልጅ አግብቶ በገዳሪፍ ኗሪ ነበር። እራሱንም የበላሳ ተወላጅ አድርጎ ያሰውራ ስለነበር የመተማ ህዝብ የሚያውቀው በጎንደሬነቱ እንጂ በትግሬነቱ አልነበረም።

መተማም በአረጋዊ ከንቲባነት በርካታ ትግሬዎች ከሱዳንና ከትግራይ እየመጡ የሚሰፍሩባት ከተማ ሆነች። ተጋሩም ሱቆችን ከፈቱ። ቤቶችን ገነቡ። ሌሎችንም የንግድ ስምሪቶች በስፋት ተቆጣጠሩ። ቀደም ሲል የቅማንትን ማህበረሰብ ለማሰባሰብ የተሞክሮ ዕቅዱ በቅማንትም በአማራም ሲከሽፍ የቅማንት ተወላጆችን በግል እየመረጠ የጥቅማጥቅም ተቋዳሽ በማድረግ ቅማንቱን ከአማራው ለመነጠል የህቡዕ ሥራውን ጀመረ። በዚህ ስምሪት ቀዳሚ ከነበሩት አንዱ የአረጋዊ የሚስት ወንድም የአቶ ታየ መለሰ ልጅ ነበር። ይህም ግለሰብ ዛሬ ራሱን “የቅማንት ኮሜቴ” ከሚሉት አንዱ ሆኗል።

ኮሚቴው ከወያኔ የሚለገስለትን የገንዘብ ድጎማ ተጠቅሞ በርካታ ቅማንቶችን መለመለ። ይህ ሁሉ የሚሆነው ግን በከተሜው መሃል እንጅ በገጠሩ ገበሬ መሃል አልነበረም። የገጠሩ ገበሬ በይፋ ወደ ሴራው እንዲገባ የተደረገው የ2001ዱን የህዝብ ቆጠራ ተከትሎ ነበር። ወያኔ የህዝብ ቆጠራውን በሁለት መንገድ

ሊጠቀምበት አቅዶ ተንቀሳቀሰ። በአንድ በኩል የትግሬውን ቁጥር ከፍ አድርጎ ባንፃሩ ግን በአገሪቱ የሚኖረውን የአማራ ቁጥር ለማሳነስ ሲሆን  እግረመንገዱንም አማራውንና ቅማንቱን ለማጣላት ቅማንትን የማይጨምር ቅጽ ለህዝብ ታደለ። የህዝብ ቆጠራው ቅጽ ብሔር/ብሔረሰብ በሚለው መስመር ላይ ሁለት ሳጥኖች ብቻ እንዲኖሩት ተደርጎ አንደኛው ሳጥን አማራ ሲል ሁለተኛው ሳጥን ግን ሌላ የሚል ይዘት ይዞ ለህዝብ ተሠራጨ።

በመሠረቱ በጎንደር ክ/ሀገር የሚኖሩትን ማህበረሰቦች ለማካተት አማራ፣ ቅማንት፣ አገው፣ ወይጦ፣ አዝማሪ፣ ጉምዝ፣ ቤተ እስራኤል . . . ማለት ሲገባው ቅጹ ግን “አማራና ሌላ” በማለት ሁለቱን ሳጥኖች ብቻ ለምርጫ አቀረበ። ቅጹን ተከትሎ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ቀደም ብሎ የቤት ሥራ ተሠርቶ ስለነበር ተቃውሞውም ወዲያውኑ ተነሳ። ቀደም ብሎ በተዘጋጁ የቅማንት ምሁራን። ከተዘጋጁት ምሁራንም ቀዳሚዎቹ አቶ ነጋ ጌጤና አምባሳደር ዘመነ ካሰኝ ነበሩ።

ምሁራኑ ያነሱት የማንነት ጥያቄ እየተለጠጠ ሌላ መልክ እንዲይዝ ተደረገ። በህቡዕ ይሠሩ የነበሩት እነበረክትና ወያኔዎችም ጉዳዩን አግዝፈው ወደ ክልልና ፌደራል አሸጋገሩትና የማንነት ጥያቄው በ200 ዓ.ም ለውሳኔ ህዝብ ቀረበ። ህዝበ-ውሳኔውን ተከትሎም የቅማንት ዋና ከተማ ጎንደር መሆን አለበት የሚል ቀጣይ ክርክር ተነሳ። ነገሩ እየከረረ ሄደና አማራውና ቅማንቱ “እኛና እናንተ” ወደሚል ግልጽ ልዩነት ተሸጋግሮ በላይና በታች አርማጭሆ ተወላጆች መሃል ግጭቱ ተጀመረ። የፌደራልና የክልል ሃላፊዎችም እጃቸውን እንዲያስገቡ ተደርጎ ችግሩ ገዘፈ። በመሃል ግን ስለጉዳዩ ምንም የማያውቀው አርሶ አደር የጥቃቱ ሰለባ ሆኖ ንብረቱ ወደመ። ከቀየው ተፈናቅሎ ተሰደደ። ሁኔታውም አዳዲስ ተዋናኞችን ወለደና ችግሩ ለመፍትሔ አስቸጋሪ ሆኖ ተወሳሰበ።

                               ተዋናኞች እነማን ናቸው?

    ዋናው ተዋናኝ የክልሉ መስተዳድር ነበር። ቀደም ሲል በብአዴን ውስጥ የነበሩት በረከት ሰምኦን፣ ህላዌ ዮሴፍ፣ ተክለ በርሃንና ካሳ ጥንቅሹ ውስጥ ውስጡን ሲያካሁዱት የነበረው ሴራ እነርሱ ከተወገዱ በኋልም በከፋ መልኩ ቀጥሏል። የለውጡ አካል የሆነው ቡድንም በመረጃ ያልተደገፈና ያልተጣራ ወሬ ይዞ ወገናዊ የሆነ እርምጃ መውሰዱ ነገሩን በረጠበው ላይ ሸናሽበት እንዲሉ አድርጎታል። የብአዴኑ ስህተት አልበቃ ያለ ይመስል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄም በስሜታዊነት ወገናዊ አቋም ይዞ በሳቱ ላይ ነዳጅ አርከፈከፈበት።

በሌላኛው ወገን የተሰለፉት የቅማንት ኃይሎችም የወያኔን ተልዕኮ ለመፈጸም ሲሉ በወገናቸው ላይ የጅምላ ግድያ፤ አፈናና ማፈናቀል አካሄዱ። በመሃል ግን የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል እንዲሉ ራሱን አስታጥቆ ለዝርፊያ የተሠማራ አዲስ ቡድን ተፈጠረ። ይህም ቡድን የወታደር ዩኒፎርም እየለበሰ በሚወስደው ጥቃት ነገሩን የበለጠ አውሰበሰበው።

 

                                         ማጠቃለያ

ሀ.  የክልሉ መስተዳደር ቀደም ሲል በስውር እጅ የጣደውን ሲያበስል ከቆየ በኋላ ችግሩ ይፋ ከሆነ በኋላም ሁለቱንም ወገን በዕኩልነት ሚዛን ሰፍሮ ተገቢውን ዕርምጃ እንደ መውሰድ ወደ አንድ ጎን ያጋደለ እርምጃ እየወሰደ ሁኔታውን እንዲባባስ አደረገው።

ለ.  የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ወጣቶችም ለዘመናት በወያኔ ፋሽስታዊ አገዛዝ ከደረሰባቸው ግፍና መከራ ተነስተው ለወያኔ ካላቸው ጥላቻ የመነጨ ፀረ-ቅማንት እይታ አዳበሩ። ወያኔ ያደረሰባቸውን የአካል ጉዳትና ያለበሳቸውንም ቁስል እያከኩ በቅማንት በወንድሞቻቸው ላይ ሊበቀሉ ተንቀሳቀሱ። የቅማንት ኮሚቴው የሚታገዘው በወያኔ ነው ከሚል እንደምታ ተነስቶ ፋኖ በሚል መጠሪያ የታጠቀው የአማራ ወጣት በቅማንት ወንድሞቹ ላይ የጅምላ እርምጃ ወሰደ።

ሐ.  በሌላኛው ወገንም በከረረ የዘር ጥላቻ ላይ የተመሠረተው የቅማንት ወጣት ጃኖ በሚል ስም በአማራ ገበሬዎች ላይ አሰቃቂ እርምጃዎችን ይውስድ ጀመር። በመሃከል ሟች፤ ተፈናቃይና ተጠቂ በሁለቱም በኩል ምንም የማያውቀው የአማራና የቅማንት አርሶ አደር ሆነ።

መ. በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉም የወታደር መለዮ የለበሰ ዘራፊ ቡድን ሲያመቸው በቀን ሳያመቸው ግን ጨለማን ተገን አድርጎ በሚያካሂደው አፈና ዘረፋና ግድያ ሁኔታው ተወሳሰበ። ወያኔም ጎንደርን እርስ በርስ አባልቶ በማፈራረስ ነበር ትልቂቷን ትግራይ ለመገንባት በማኒፈስቶው ያጸደቀው። እናም እቅዱ ተግባር ላይ ሲውል እየታየ ነው።

ለትልቋ ትግራይ ግንባታ የመሰረት ድንጊያ ይሆኑ ዘንድም መተማ ሽንፋና ቤናሻንጉል የሰፈሩት ትግሬዎች ሱዳን ከሚገኘው የወያኔ መ/ቤት ለሚያገኙት  መሳሪያ፣ ገንዘብና ሌሎችም አቅርቦቶች ማዕከል በመሆን እልቂቱን አባብሰውታል። ሱር ኮንስትራክሽንም ቅንብሩን ሲመራ መቆየቱ ይታወሳል። በዕቅዱ መሠረት ጎንደርን ከተቆጣጠሩ በኋላ ቀጣዩ ጉዞ ወደ ምዕራብ ጎጃም፣ ወለጋና ጋምቤላ ነው።

ቀደም ሲል ከአፋር፣ ከወሎና ከጎንደር ከተነጠቁት መሬቶች በተጨማሪ ከጎጃም የመተክል ወረዳን ወደ ትልቋ ትግራይ አካትቶ የግዛቱን የቆዳ ስፋት በመለጠጥ ኢትዮጵያን በትልቋ ትግራይ ለመተካት ሂደቱ ቀጥሏል። ለዚህም ስኬት ትግሬዎችን በመተክል ወረዳና (ቤናሻንጉል) በጋምቤላም አስፍሯል።

የህዳሴው ግድብም አሁን ካለበት ሥፍራ እንዲገነባ የተደረገው የትልቋ ትግራይን ካርታ ታሳቢ አድርጎ እንደነበር ልብ ይሏል።

                                    ምን መደረግ አለበት?  

1ኛ. የፌደራል ኃይሉ አካባቢውን እንዲ ቆጣጠር ተደርጎ ከራሱ ከአርሶ አደሩ በተውጣጡ ሽማግሌዎችና የኃይማኖት መሪዎች ገለልተኛ ኮሚቴ ተቋቁሞ በፌደራል መንግሥቱ አማካኝነት ነገሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረቱ ቢጀመር።

 

2ኛ. “የክልሉ” መስተዳድርና አብን ከቅማንት/አማራ ችግር ላይ እጃቸውን አንስተው ትኩረታቸውን በዋናው ጠላት በወያኔ ላይ አድርገው ወጣቱን በማደራጀት፣ በማሰልጠንና በማስታጠቅ ሥምሪት ላይ እንዲያተኩሩ ቢደረግ። በተለይም የክልሉ መስተዳደር ከላይ እስከታች የአስተዳዳደርና የደህንነት መዋቅሩን ወደ ማጽዳት ቢያተኩር።

3ኛ. የሁቱም ማህበረሰብ ምሁራን ወገንተኝነቱን ትተው የህዝባቸውንና የጎንደርን ህልውና በጋራ ለመታደግ ምሁራዊ ተልዕኳቸውን በቅንነት ለመወጣት ገንቢ ውይይት ቢያካሂዱና በጎንደር ላይ የያንዣበበውን የህልውና ጥያቄ ዋስትና ወዳለው የአንድነት ድባብ ቢመልሱት።

4ኛ. ከሀገር ውጭም ሆነ ሀገር ቤት ያለነው አክቲቪስት ነን የምንል ለተወሰነ ጊዜ ራሳችን ገርተን ነገሩን ከማባባስ ብንቆጠብ። በማህበራዊ ሚዲያም ሆነ በሌላ የመገናኛ ዘዴ ለሁለቱም ወገን የቤንዚን መግዣ የምንለግስ ሰዎች ዕርዳታውን ለተፈናቀሉት ወገኖቻችን ዘላቂ መቋቋሚያ እንዲሆን ብናደርገው ጎንደርን ታድገን ኢትዮያንም ከመጥፋት ልናድናት እንችላለ።

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር።

የካቲት 20011

 አብርሃም በየነ

 

 

       የመረጃ ምንጮች፤

1ኛ ታላቁ ሴራ በገብረ መድህን አርአያ

2ኛ. የ1968ቱ የወያኔ ማንፌስቶ

3ኛ. የአረጋዊ በርሀና የገበረ መድህን አርአያ ቃለ ምልልሶች

4ኛ በትምህርት ሚኒስቴር የአንደኛ ደረጃ የsocial studies መማሪያ መጽሀፍ-

  • በትግራይ ክልል ውስጥ በከፍታው ትልቁ ተራራ ራስ ዳሽን ነው ይላል።

5ኛ. በቱሪዝም ሚኒስቴር ማስታወቂያ-

* come visit Laalibela, the oldest rock hue church located in

In the region of Tigray ይላል።

6ኛ.  ከሸቴ ወልደ ህይዎት ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ።

 

 

 

 

 

 

   

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here