Home News and Views የሊቅ ዐቢይ አስቸጋሪው ምርጫ። የግል አስተያየት (ከኀይሌ ላሬቦ)

የሊቅ ዐቢይ አስቸጋሪው ምርጫ። የግል አስተያየት (ከኀይሌ ላሬቦ)

 

የሊቅ ዐቢይና የነለማ ቡድን ተብሎ የሚጠራውን አንጃ ደጋፊዎች፣ አብዛኞቹ ኢትዮጵያዊነትን የሚያራምዱ የአንድነት ጐራ ናቸው ብል ስሕተት አይመስለኝም። የነለማ ቡድን ግን ሁሉም የኢሕአዴግ አባላት ናቸው። የዚህ ቡድን  ደጋፊዎች ያልተገነዘቡት ነገር ቢኖር፣ ኢትዮጵያዊነትና ኢሕአዴግ በመልካም እንተርጉም ካልን ሆድና ጀርባ፣ በመጥፎ እናስመስል ከተባለ ደግሞ እባብና ርግብ መሆናቸውን ነው። ምንም ብንመኝ፣ ሁለቱ በፍጹም አብረው ሊኖሩም ሊደመሩም አይችሉም። “መደመር” የሚለው የሊቅ ዐቢይ ፈሊጥ ለነዚህ ሁለቱ በፍጹም አይሠራም። ባንድ አልጋ እንኳን ቢተኙ፣ ሕልማቸው ተጻራሪ ነው። ኢትዮጵያዊነት ዘመን ተሻጋሪና ለማንም የማይበገር፣ ሌላውን ጐረቤቱንም ሆነ አካባቢውን እያሰፋና እያቀፈ የሚሄድ፣ እንከን የለሽ ስብጥርና ጒንጒን ማንነት ነው። ኢትዮጵያም ሆነ ኢትዮጵያዊነት የሚታወቁት በተፈጥሯቸው ማንንም አስተናጋጅና ዐቃፊ በመሆናቸው ነው። የኢትዮጵያዊነት ዐቃፊነት፣ ኢትዮጵያ ከተባለው ግዙፍ ምድር መጥቆ ወሰኑንና ድንበሩን ዐልፎ፣ ለሌላውም ዓለምና ሕዝብ ተትረፍርፏል። የዓለም፣ በተለይም ጭቁንና ጥቊር፣ ሕዝብ በምዕራባውያን መብቱ ተጨፍልቆ ይኖር በነበረበት ወቅት፣ የነፃነትና የእኩልነት ትግሉን ድምፅ፣ በያለበት ሲያክላላው፣ ሲያስተጋባው፣ ሲያክለውና ሲያንረው ቈይቶ፤ የኋላ ኋላ ግቡን ለመምታት የበቃው በኢትዮጵያዊነት ዙርያ በመሰለፍና በመሰባሰብ ነው።

ኢሕአዴግ በተቃራኒ በባሕርዩ ከፋፋይ፣ በልዩነት ላይ ያተኰረ፣ በጥላቻ መሠረት ላይ የተካበ፣ የጐጠኞችና የአገር ከሓጂዎች ጥርቅማጥርቅም ነው ማለት ይቻላል። ብዙዎች የሚሳሳቱት ኢሕአዴግን እንደፖለቲካ ድርጅት እያዩ ነው። ኢሕአዴግ የተፈጠረው የኢትዮጵያን ጥፋት ከኋላ ሁነው ይሸርቡ በነበሩት በውጭ ኀይሎች ሤራና ምክር ሲሆን፣ በእጁ ጠፍጥፎት ህልውና የሰጠው ግን፣ የታላቂቷ ትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት ሕዝባዊ ሓርነት ወያኔ (ሕወአት) ነው። ሕወአት በኢትዮጵያ ጥንታዊነትና ታላቅነት አያምንም። ለሕወአት ከራሱ ዐልፎ ዓለምን ያደነቀው፣ የመላው ዓለም ጥቊርና ጭቁን ሕዝብ የሚኰራበት፣ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚጀምረው፣ የ’አማራ’ ንጉሥ ብሎ ከሚጠራው ከአፄ ምኒልክ ዳግማዊ ነው። የቀረው የሰካራሞቹ፣ የባለምትሐቶቹና የባለአስማቶቹ ደብተሮች የፈጠራ ሐተታ ነው። ከስድስት ሺ ዓመታት በላይ ያስቈጠረውን፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ የርስበርስ መወላለድ፣ በአምቻና በጋብቻ መተሳሰር፣ በባህልና በሀብት መሰበጣጠር፣ በቋንቋና በሃይማኖት መወራረስ፣ ሕወአት አጥብቆ ይክዳል። በሕወአት ትርክት መሠረት፣ ኢትዮጵያ አንድ አማራ በተባለ ጨቋኝ ብሔረሰብ ወረራ የተቋቋመች፣ መቶ ዓመት የማይሞላ ታሪክ ያላት አገር ናት። በተጨማሪ፤ ኢትዮጵያ፣ አማራው በሁሉም ዘርፍ የበላይነቱን ይዞ ይገዛት የነበረ፣ አማራ ያልሆነው ብሔረሰብ ግን፣ በግፍና በገፍ የሚማቅባት እስር ቤት ናት።የሕወአት ሕልምና ምኞት ይህችን ኢትዮጵያን  አፍርሶ፣ ጨቋኝና ተጨቋኝ በሌለበት መልኩ፣ በድርጅቱ አምሳል በአዲስ መልክ መገንባት ነው። ይኸንን ግብ ለመምታት የሕወአት ዋና ዓላማ ‘አማራን’ ማጥፋት ነው። በሠለጠነ ቋንቋ በመተርጐም ሕወአቶች ተልእኳቸውን በመሪያቸው ስም “የመለስ ራእይ” ይሉታል። የሕወኣት ከፍተኞች መሪዎቻቸው የድርጅታቸውን ዓላማ ለማሳካት እንዲያመችላቸው ሲሉ፣ የአማርኛ ተናጋሪውን ሰብኣዊነት ለመካድ በየጊዜው ተናገሩት ተብለው በየቦታው የሚጠቀሱትን ንግግሮች ከዚህ በታች አስቀምጫለሁ። ፍርዱንና ኂሱን ለአንባቢው ልተወውና ወደዋናው ጉዳይ ልለፍ።

ኢሕአዴግ፣ ሕወአት በራሱ ኀይል ብቻ ግቡን ለመምታት ስለሚሳነው፣ ድርጊቱን እግብር ለማዋል ታስቦ የተፈጠረ ግንባር ነው። በተሻለ አገላለጥ የሕወአት ሥራ አስፈጻሚ አካል ቢባል ይቀላል። ኢሕአዴግ በሕወአት ተሸንሽኖ በተሰጠው ክልል፣ አማርኛ ተናጋሪውን በቋንቋ መስፈርት ብቻ እየፈረጀ፣ “ነፍጠኛ”፣ “የምኒልክ ሰፋሪ”፣ “ጨቋኝ” ወይንም “የጨቋኝ መደብ” እያለ በማሳበብ፣ ልሕቅና ደቂቅ፣ ወንድና ሴት፣ ሕፃንና ሽማግሌ፣ ነፍሰጡርና አሮጊት ሳይለይ በጅምላ ልዩልዩ ስልትና መሣርያ በመጠቀም ሲገድል፣ ሲጨፈጭፍ፣ ሀብቱንና ንብረቱን ሲነጥቅ፣ ሲያፈናቅል ኑሯል። ልክ በአውሮጳ ከጀርመን ቊጥጥር ሥር የነበሩ ግዛቶች በናዚዎች የተዛባና የሐሰት ስብከት ተመርተው፣ በአይሁዶች ላይ የፈጸሙትን ግፍ፣ ኢሕአዴግም፣ በአማርኛ ተናጋሪው ሕዝብ ላይ ከዚያ የማይተናነስ ኢሰብኣዊ ጭካኔና የዘር ማጽዳት ተግባር እንደፈጸሙ መታወቅ ይገባል። ስለዚህ በሰብእናውም ሆነ በጠባዩ ኢሕአዴግ በአውሮጳ ከታየውና ዓለምን ለአሰቃቂ ከፍተኛ ዕልቂት ከዳረጉት ከመንታው ፋሽስትና ናዚ አይለይም።

 

ሕወኣት ለኢሕአዴግ አባልነት ከፈለፈላቸው ዋናውና ከፍተኛ ሚና ከተጫወቱት አንዱ ትናንትና የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት [ኦሕዴድ] በመባል፣ ዛሬ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ስም የሚጠራው ነው። ኦሕዴድ ኦሮሞኛ ተናጋሪ ብሔረሰብ ከቀረው የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ለዘመናት በመወላለድ፣ ባህልና ቋንቋ በመወራረስ፣ ድር ማጉ ኢትዮጵያዊ መሆኑንና፣ አብዛኛው አሁን ላለበት አካባቢ (አዲስ አበባን ጭምር) መጤና አዲስ ሰፋሪ መሆኑን የረሳ ይመስላል። ከደቡብ ከኬንያ ጠረፍ ተነሥቶ እስከመሃል ኢትዮጵያ ያለውን ሰፋፊ መሬት ይዞ የሚገኘው፣ ከፊቱ ያለውን እያጠፋ፣ እንደሀዲያ፣ ከምባታና ጉራጌ የመሳሰለውን ኀይለኛውን ብሔረሰብ ደግሞ አልፎት እየሄደ፣ ጸጥለጥ ብለው የገበሩለትን ብሔረሰቦች ግን ጉዲፈቻ፣ሞጋሳ [ሞገሳ]፣ ገበር የተባሉ ሥርዐቶቹን በመጠቀም፣ ባህላቸውንና ቋንቋቸውን ደፍጥጦ፣ ሰብእናቸውን ጨፍልቆ፣ በኦሮሞነት እንዳጠመቃቸውና፣ በሁለተኛ ደረጃ ዜግነት ይገዛቸው እንደነበረ ዘንግቷል ማለት ይቻላል። ኦሕዴድም (እንደሱም “የኦሮሞ ሕዝብ ወኪልና ነፃ አውጪ” ነኝ ብሎ ራሱን በራሱ የሾመው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ))፣ እወክላለሁ ያለው ሕዝብ ራሱ “የሉባ” ሰፋሪ ሁኖ እያለ፣ አማርኛ ተናጋሪውን፣ ሕግና ሥርዐት አስጠባቂውን (በዱር በገደል ለኢትዮጵያ አንድነትና ነፃነት የሞተውን ኦሮሞን ጭምር) “መጤ”፣ “ነፍጠኛ”፣ “የምኒልክ ሰፋሪ” እያለ በመብራት እየፈለገ፣ በጥይት እየረሽነ፣ ከነሕይወቱ እየቀበረ፣ ለዘመናት ከኖረበት ቤቱና አካባቢው እያፈናቀለ፣ ከፍተኛ ግፍና በደል እንደፈጸመ ይነገርለታል ብቻ ሳይሆን፣ ሁለቱም አሁንም ቢሆን በዚህ ተግባር እንደተሰማሩ ናቸው። ሊቅ ዐቢይ እንግዴህ የዚህ ግፈኛ ድርጅት ማለትም የኦዴፓ አባል ብቻ ሳይሆን ሊቀመንበሩም ነው። ግን ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትንና ፍቅርን በመስበኩ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጫፍ እስከጫፍ በየሄደበት በሆሆታና በእልልታ ተቀብሎታል።

 

ይሁንና የሊቅ ዐቢይ ሥራ እስካሁን ድረስ ተከታዮቹንና ደጋፊዎቹን በቃላት ከማሞኘት ዘልሎ የሄደ መስሎ አይታየኝም። በቅርቡ በአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ስብሰባ ሥነሥርዐት ላይ ባደረገው ንግግሩ፣ የኦዴፓ መሪዎች በለገጣፎና በአዲስአበባ ዙርያ፣ ጽንፈኞቹ ናቸው የተባሉት ደግሞ ወኪልና ደጋፊ አፍ ባጣው በጌዴዎ ሕዝብ ላይ፣ እየፈጸሙ ባሉት ግፍ፣ ጭፍጨፋና ፍንቀላ እስካሁን ድረስ አንዲትም ቃል ትንፍሽ አላለም። አንዱን ጐሣ በክልሌ መኖር  አይገባህም ብሎ ማጽዳት የኢሕአደግ መሠረታዊ እምነቱ ስለሆነ፣ ሊቅ ዐቢይ ለነዚህ ጉዳዮች ደንታም ያለው አይመስልም።

ሊቅ ዐቢይ ብዙ ደጋፊዎች እንዳሉት ይገባኛል። ለእኔ ግን አያያዙ ገና ከመጀመርያው አልጣመኝም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ካንድ መሪ ኢትዮጵያ የሚለውን ቃል ለብዙ ጊዜ ስላልሰማና፣ ቃሉ በአንድ መሪ አፍ ተደጋግሞ ሲጠራ ማየቱ በጣም ስለጠማው፣ ሊቅ ዐቢይ በየጊዜው “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ” ሲል በሚያስተጋባው ጩኸቱና ማር በተቀባ ንግግሩ የብዙዎቹን ዐይን እያሳወረ የሄደ ይመስለኛል። ይሁንና በኔ አስተያየት እስካሁን ድረስ አንድም መሠረታዊ የሆነ ለውጥ አላመጣም። ኢሕአዴግና ሕገመንግሥቱ እንዳሉ ናቸው። ይልቅስ ሊቅ ዐቢይ፣ ሕወአት ኀይል በመጠቀም እግብር ላይ ለማዋል ያልቻለውን የጐሣ የክልል ሥርዐት፣ ተቃዋሚውን በማፍዘዝና በማደንዘዝ እያጠናከረው ሄዷል ብቻ ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ በጥብቅ ሥር እያስያዘውም ይገኛል። ደጋፊዎቹ የረሱት ነገር ቢኖር፣ ኢትዮጵያን ማሞገስ ከማንኛውም የአገር መሪ የሚጠበቅ መሆኑን ነው። እስረኞችንም መፍታት እንደትልቅ ነገር አድርጎ መቊጠሩ እጅግ የተሳሳተ አመለካከት እንደሆነ መታወቅ ይገባል። እስረኞቹ የፈጸሙት ምንም ዐይነት ወንጀል የለም። ይልቅስ ሰዎቹ ከመጀመርያውኑ መታሰር የማይገባቸው፣ የኢሕአዴግ የግፍና የጭካኔ ሰለባና መግለጫ ናቸው። የታሰሩትም ሊቅ ዐቢይ ራሱ አሁን የሚያሞግሳትን የኢትዮጵያን ስም ስለጠሩ፣ እየመራ ያለውን የኢሕአዴግን የጐሣ ፖለቲካ ስለተቹ ብቻ ነው። ሊቅ ዐቢይ ግን ደጋግሞ የኢትዮጵያን ስም ቢጠራም፣ አጠንክሮ እየደገፈና እያራመደ ያለው የጐሣን ፖለቲካ ነው።

ሊቅ ዐቢይ ተጨማሪ ጉዱ በየጊዜው ብልጣብልጥ/ሸዋጅ ለመሆን መሞከሩ ነው። የብዙዎቹን ብሔረሰቦች መፈናቀልና መገደል እስካሁን ድረስ በሕወአት እያሳበበ ቈይቷል። የራሱ ወገን ሲያደርግም በሕወኣት ተተናኩለው ነው እስከማለትም ደርሷል። በቅርቡ የለገጣፎን ሕዝብ ያፈናቀለችው እሱ ራሱ ሊቀ መንበር ሁኖ የሚመራው የራሱ ድርጅት ወገንና ሹም ናት። ርግጠኛ አይደለሁም እንጂ ራሱ ወይንም አቶ ለማ የሾሟት ሳትሆን አትቀርም ብዬ አምናለሁ። ሊቅ ዐቢይ ስለጉዳዩ ሲጠየቅ የሰጠው መልስ፣ ካንድ ዱርዬ/ሸዋጅ እንጂ፣ በፍጹም ከአንድ ጤናማ የአገር መሪ (ያውም ለኖቤል ሽልማት ይታጭ እየተባለ ካለ) አይጠበቅም። ይኸንን በተመለከተ፣ ከሁሉም ይበልጥ የገረመኝና ማመን ያቃተኝ ድርጊቱን አለማውገዙ ብቻ ሳይሆን፣ እንደአንድ አገር መሪ ለተፈናቀሉትም ሆነ ለአፈንቃዮቹ አንድም ነገር አለማለቱና ምንስ ዐይነት እርምጃ እየተወሰደ እንዳለ አለመናገሩ ነው። ሊቅ ዐቢይ ደጋግሞ የሚሰብክልን የመደመር ፖሊቲካ መሠረቱና ዐምዱ ፍትሕ፣ ነፃነትና እኩልነት መሆኑን የተረዳ አይመስልም። ከመንግሥት ፍቅር መጠበቅ ሞኝነት ነው። ፍትሕ፣ ነፃነትና እኩልነት ግን የመንግሥት ግዴታው ነው። እነሱ ከሌሉ መንግሥት የለምና።

የሊቅ ዐቢይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጨዋታው በዚህ ብቻ አላበቃም። በየጊዜው የአገሩን ችግር እንዲቀርፉ ሲል የሚያቋቁማቸው ኮሚቴዎች፣ በሥራው እንዲያግዙት ሲል የመረጣቸው አጋሮቹ ሚኒስትሮች ግልጥ አድርገው ደጋግመው የሚያመለክቱት ሊቅ ዐቢይ ያከበረውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ምን ያህል የሚያላግጥበት መሆኑን ነው ብዬ አምናለሁ። ሚኒስትሮቹን ብንመለከት፣ አጋሮቹ ሳይሆኑ ከእሺ ጌታዬ ከማለት ውጭ ሌላ ፋይዳ ያላቸው ሰዎች አይመስሉም። በየመስኩና በየአስተዳደሩ ዘርፍ ለሚታዩት ለአገሩ ችግሮች መፍትሔ እንዲያመጡ የሚመርጣቸውና የሚሾማቸው ሰዎች፣ ነፃና ገለልተኛ የሆኑ አይደሉም፤ በጉዳዩም ዕውቅና ያላቸውም ናቸው ማለት ያዳግታል። ይልቅስ ከመነሻው የችግሮቹ ጠንሳሾች፣ ፈጣሪዎችና አራማጆች ናቸው ማለቱ ይቀላል። ለይስሙላ፣ አለበለዚያም ለሽወዳና ከተጠያቂነት ለማምለጥ ካልሆነ በስተቀር፣ ማንም ጤናማና ቅንነት ያለበት ሰው፣ አገሯ ያላት የከባድ ችግሮች መፍትሔ በምንም መልክ ከነዚህ ዐይነት ሰዎች ይመጣል ብሎ እንደማያስብና እንደማይጠባበቅ ርግጠኛ ነኝ። ይኸ ዐይነቱ ፍርዴና አስተያየቴ የሊቅ ዐቢይ አማካሪዎቹን ጭምር ይመለከታል። በቅርቡ ስለአዲስ አበባ ባለቤትነት ጉዳይ ላይ ለውይይት መነሻ ሲል ስሙን ሳይገልጽ ራሱን የጠቅላይ ሚኒስቴር የሕግ አማካሪ በማለት ለሊቅ ዐቢይ የሰጠው የኢትዮጵያ ታሪክ ግንዛቤው የሹሙን ዕውቀት የሚገልጥ ከሆነ፣ ሊቅ ዐቢይ ራሱን ያጀበው በጅሎችና በጥራዘነጠቆች መሆኑን ያመለክታል። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ በነእንደዚህ ዐይነቶቹ ሰዎችና አማካሪዎች የተከበበና የሚመከር ከሆነ፣ እሱም ጠፍቶ ኢትዮጵያንም ሊያጠፋ ይችላል የሚል ጥብቅ እምነት አሳድሮብኛል[1]

በሌላው በኩል ደግሞ ሊቅ ዐቢይን ብቻ መውቀሱ ሚዛናዊነት ያጣ ፍርደገምደልነት መስሎም ይታየኛል። የአንድነት ኀይል ነን ባዮች፣ ወይንም የጐሣ ሥርዐት ይደምሰስ የሚሉ ኀይሎች ርስበርስ ከመነታረክና ቁሞ ከመመልከት በዘለለ፣ የመደራጀት ፍላጐትም ጥረትም እስካሁን ለማሳየት አልቻሉም። “ኢትዮጵያ አትጠፋም፣ ለዘላለም ትኖራለች፣ ወይንም ትኑር” ከማለት አልፎ ያሳዩት ትብብርና ተጨባጭ ተግባር የለም። የሚጠብቁት ሊቅ ዐቢይ የጐሣንና የጐጥን ሥርዐት በተአምርም በዐዋጅም ቢሆን ገርስሶ፣ የአንድነትን መና ከሰማይ አውርዶ እንዲመግባቸው ነው፣። የትግል መንገዱንም ተአምራዊ በሆነ ኀይሉ ጠራርጎ እንዲያቀናላቸው እንጂ እንደጽንፈኞቹ አጠንክረው መታገልና በየቦታው የተበታተኑትን እንደአሸን የፈላ ደጋፊያቸውን ባንድጋ ማሰለፍ ግዴታቸው እንደሆነ የተገነዘቡ አይመስሉም። እነሱ ራሳቸው ባንድ አፍ ለመናገርም ሆነ፣ የጽንፈኞቹን ድርጊት አጠንክረው ለማውገዝ ሲሞክሩ አልታዩም። ለምሳሌ ሌላው ቀርቶ በአዲስ አበባ ያለው ሕዝብ እንኳን፣ ጥቅሙና ህልውናው በጽንፈኞቹ እየተነካና እየተጐዳ እያለ፣ ከተማዋ ብዙ የተማረና የነቃ ኀይል ቢኖራትም፣ በሷ ላይ የሚደረገውን ደባና የተሸረበውን የጥፋት ምዝበራ የሚቋቋምና የሚመክት ኀይል ለማደራጀት አልቻለም። ታዲያ ጽንፈኞቹ ቢያይሉበትና ፍላጎታቸውን ለማርካት ለስለስ ቢል፣ ሊቅ ዐቢይን ብቻ መውቀሱ ፋይዳ ያለው አይመስለኝም። ይበልጥ መወቀስ ያለበት ጡንቻው እያለው ሊቅ ዐቢይ ሲደበደብ፣ ጥቅሙና ህልውናው ሲደፈር ዝም ብሎ ተመልካቹ የከተማው ነዋሪ ነው ባይ ነኝ።

ይኸ ማለት ግን፣ ሊቅ ዐቢይ አላፊነቱን ሊወጣ ካልቻለበት ምክንያቶች እንዳንዱ ሁኖ ሊታይም ሊቀርብም አይገባውም። በአገር ውስጥም ሆነ፣ ከአገር ውጭ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንም ሳይገፋው፣ በገዛ ፈቃዱ፣ በነቂስ ወጥቶ ‘የኢትዮጵያ ኔልሶን ማንዴላ” እስከማለት የዘመረለት፣ ድጋፉን አለአንዳች ማመንታት የለገሠለት፣ ቢያንስ ለግማሽ ዘመን በአገሪቷ ታይቶ ያልታወቀ መሪ አሰኝቶታል። በኢትዮጵያውያን ዘንድ ብቻ አይደለም ሊቅ ዐቢይ አድናቆቱን ያተረፈው። በአፍሪቃና በአብዛኛውም ዓለም እንጂ። በሱ መነሣት፣ ከግማሽ ዘመን በላይ ተዋርዶና ተሽቈልቁሎ የነበረው ኢትዮጵያዊነትና ኢትዮጵያ ወደጥንታቸው ክብርና ማዕርግ ተመልሰዋል። ዓለም በሙሉ ተገርሟል። ኢትዮጵያዊ መሆን ቡራኬና ምርቃት መሆኑን ብዙዎች ተሰምቷቸዋል። ብዙዎቹም ሊቅ ዐቢይ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የአፍሪቃም ትንሣኤ መሪ ነው እስከማለት ደርሰዋል።

ሊቅ ዐቢይ ግን ይኸንን አለአንዳች ልፋት ያገኘውን ሕዝባዊ አመኔታና ክብር፣ ሞገስና ልዕልና ጠቃሚ ነገር ለመሥራት እንደመጠቀም ፈንታ አንድ ዓመት እንኳን ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በከንቱ አባከነው ማለት ይቻላል። ሁናቴውን ሳይጠብቅ በድንገት የአንድ ቢሊዮን ብር ሎተሪ ካሸነፈ፤ ኋላ ግን ምንም ሳይሠራበት በጥቂት ጊዜ ውስጥ እንዳባከነው ሰው ማምሰል ይቻላል። ዐቢይም ያደረገው ይኸንኑ ብል ስሕተት አይመስለኝም። ከተቀበለው ሕዝባዊ ደጋፍና አንጻር ስንመለከት፣ ሊቅ ዐቢይ እንኳን አገሩን ኢትዮጵያን ቀርቶ፣ በዙርያዋ ያሉትን ኤርትራንም፣ ጂቡትንም፣ ሱዳንና ሱማሌን ጭምር አጣምሮ አንድ አገር ለማድረግ ዕድል ነበረው ማለት ይቻላል። ግን እንደድንገተኛ ሎተሪ አሸናፊው፣ እሱም ዕድሉን ሳይጠቀመው እያባከነው ይገኛል ብቻ ሳይሆን በከንቱ አባክኖታልም። የዚህም ምልክት፣ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ወቀሳና ስድብ ከየአቅጣጫው አድናቂው ከነበረው ሕዝብ ሲዘንብበትና ሲጐርፍበት ማየቱ ነው።

ለታላቅ ታሪክ የታጨ ሰው ሁኖ እያለ፣ ሊቅ ዐቢይ ተኰትኩቶ ካደገበት ከኢሕአዴግ የአስተሳሰብ ቁም ሣጥን ሊወጣ አልፈለገም። የኢሕአዴግን የጐሣና የተዛባ ርእዮተ ዓለም የሙጥኝ ብሎ የያዘና ከሱም ሊላቀቅ ያዳገተው ይመስላል። ከዚህም የተነሣ፣ ከወዲያ ማዶ ያለውን ሰፊውንና የደስ ደስ ያለበትን፣ ለምለሙንና ታላቁን አድማስ ለማየት አልታደለም። እንደገባኝ፣ የጐጥና የጐሣ ርእዮተ-ዓለም ራእዩን አሳውሮታል። ወይንም ተኰትኩቶ ያደገውም ሆነ፣ ተከቦና ተወጥሮ ያለው ይኸንን ርእዮተ ዓለም በሚያቀነቅኑ ኀይሎችና ሰዎች በመሆኑ፣ ዐልፏቸውም ሆነ ጥሏቸው ለመጓዝም ሆነ፣ አንድነት፣ ነፃነትና እኩልነት ከጠማው ከሚወደው ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ሁኖ ለመገሥገሥ ፍላጎትም፣ ጥረትም አላሳየም። “መንግሥተ ሰማይን ላላየ፣ ገሃነም ድንቁ ነው” ወይንም “ዐባይን ያላየ ምንጭ ያደንቃል” የሚለው አባባል በሊቅ ዐቢይ የተፈጸመ ይመስላል። ይኸም ሁኖ ግን ሊቅ ዐቢይ አዝማሚያውን ለመቀልበስ አሁንም ዕድሉ ሰፊ ነው ብል ስሕተት አይመስለኝም። ከፊቱ ያለው ምርጫ ግን ሁለት ብቻ ነው። ሁሉንም ዐቃፊ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ወይንም ርስበርስ ከፋፋይ ኢሕአዴግና ጐጥነት። መካከለኛ መንገድ ያለ አይመስለኝም። በመኻል ቁሞ ቢቀር በሁለቱም ሳይተፋ እንደማይቀር አያጠራጥርም።

[1] የሕግ አማካሪው የአዲስ አበባን ባለቤትነት በተመለከተ ለምን ታሪክ ላይ መመሥረት እንደማያስፈልግ ምክንያቱን ሲገልጥ፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ብለን እስከዛሬ ስንጠቀምባቸው የነበረው የአንዳንድ ብሔሮችን ገድል ብቻ የሚዘክር እንጂ፣ አብዛኛውን የኢትዮጵያ ብሔር ታሪክ፣ በተለይም የኦሮሞችን ታሪክ የማይወሳ በመሆኑ ይህንን አግላይታሪካዊ መረጃለክርክር መርቻ ዋቢ” አድርጎ ለማቅረብ እንደማያምንበት ይናገራል። አንባቢው እንዲረዳ ያህል ላሳስብ የምወደው፣ ከማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ይበልጥ በሰፊ የተጻፈለት ብሔረሰብ ቢኖር የኦሮሞ ብቻ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህ በተጨማሪ እስከቅርብ ጊዜ ድረስ የሁሉም አገር (የምዕራባውያን ጭምር) ታሪክ የተጻፈው ለገዢው ክፍል በገዢው ክፍል ስለገዢው ክፍል እንጂ የተራው ሕዝብ አይደለም። የኢትዮጵያም ታሪክ ከዚህ የተለየ አይደለም።

1 COMMENT

 1. ዶክተር ሀይሌ ላሬቦ ጽሁፎዎትን አነበብኩትኝ በእኔ እምነት እና ግምት ምንም እንከን የሚወጣለት አይመስለኝም ።የእርስዎን ጽሁፍ ለሚተቹ ወይም እኔን አድሎአዊ አመለካከት አለህ ለሚሉኝ ደግሞ የፖለቲካ ሰው ስላልሆንኩ የሚደግፉትንም ሆነ የሚቃወሙትን አስተያየትም ሆነ ምክር ለመስማት ሙሉ ፈቃደኛ ነኝ።እኔ ግን እርስዎም ሆኑ ሌሎች የፖለቲካ አዋቂዎች ወይም በሀገራችን ጉዳይ ያገባናል የ ሚሉ ሰዎች አንድን አቅጣጫ ላይ ትኩረት ሰጥተው በእዛ ላይ ርብርብ እንዲያደርጉ እፈልጋለሁ በተለይ ዶክተር አቢይ ስልጣን ላይ ከወጣ በሁዋላ እርስዎም እንዳሉት የተቃዋሚ የፖለቲካ እስረኞችን ጋዜጠኞችን የሃይማኖት መሪዎችን ከመፍታት የዘለለ በዘላቂነት የሀገሪቱን አንድነት ለማስጠበቅ እና የሀገሪትዋን ችግሮች ለመፍታት የወሰደው እርምጃ የለም።
  ልብ ብለን ያየነው እንደሆነ ዶክተር አቢይ በጣም ብልጠት የተሞላበት አካሄድ እየሄደ ነው። በእርሱ አካሄድ ደግሞ ከዚህ በፊት በሀያ ሰባት አመት የነበረው የወያኔ ስርአት ችግሮች እየተደራረቡበት ሲመጡ ለችግሮች እውነተኛ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ ውሸትን እንደ እውነት ህዝባችንን ለመጋት እየሞከረ አንዱ ሲነቃበት በሌላው የቀየረ የሀገር ማፍረሱ ስራ በመቀጠሉ ሁሉም ዘዴዎቹ ስለታወቁበት እና የህዝባችንም የነጻነት ተጋድሎ እየተጠናከረ በመምጣቱ በተለይ የቄሮው እና የአማራው ፋኖ በተለይ የእነርሱ በመሳሪያ የተደገፈ እና ፍጹም ውጤታማ ስለነበር ወያኔ መውደቁ በህዝብ ተጋድሎ እውን ሲሆን ከወያኔ ጋር የነበሩት የነ አቢይ ለማ ቲም አሸንፈናል በማለት እንደአዲስ ቡድን ወጡ
  እንግዲህ እዚህ ላይ ልብ ብለን ማየት ያለብን ዶክተር አቢይ የሀገሪትዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ በንግግሮቹ ሁሉለሀገር አንድነት ተቆርቃሪ ሰላምና ዲሞክራሲን ለማምጣት የሚተጋ መስሎ ቢናገርም ግን በተግባር እንደቀደምቶቹ አለቆቹ እነርሱ በውሸት እርሱ ደግሞ በሂደት በሚፈጠረው አጋጣሚ ለችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ሳይሰጥ ችግሮችን እያንከባለለ እና እየሸወደ ፎቶ እየተነሳ እየሳመ እያቀፈ እዚህ ደርሷል።አንዳችም አይነት ትክክለኛ መፍትሄ ሰጥቶ አያውቅም።ይህም በመሆኑ በተለይ ከአዲስ አበባ ወጣቶች እስር በሁዋላ የዶክተር አቢይ ድጋፍ እየቀዘቀዘ እና እየተጠላ መጥቶአል።
  እነዚህ ሲንከባለሉ የነበሩ ችግሮች በስልጣን ዘመኑ ምን እና ምንድን ናቸው። የሚሉትን ከማየታችን በፊት ዶክተር አቢይ ስልጣን ላይ በወጣ ጊዜ ገና ምንም ሳይሰራ ወይም በተለምዶ ፊርማው ሳይደርቅ የሀገሪትዋን የውስጥ ችግር ሳይፈታ ወደውጭ ሀገራት ያደረጋቸው ጉብኝቶች ናቸው።በተለይ የተለያየ ሽልማትና ስጦታን እኛንም ሆነ መላው አለምን ለማደናገር እና በቀላሉ ድጋፍ ለማግኘት የሄደባቸው ሀገሮች ሩዋንዳ እና ኡጋንዳን ሶማሊያ እና ጅቡቲ እንያቸው ። ከነዚህ በተለይ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳን እንመልከት እነዚህ ሁለቱ ሀገሮች ለነበረው የወያኔ መንግስት ጥልቅ ፍቅር አክብሮት እና ወዳጅነት የነበራቸው ናቸው።የእነዚህ ሁለቱ ሀገር መሪዎች በአፍሪካ የለየላቸው አምባገነኖች እናዲሞክራሲ የሚያንገሸግሻቸው ናቸው ።የኡጋንዳው መሪ ስልጣን ተክተው የመጡት እራሱን ዶክተር ፊድ ማርሻል ኢድያ አሚን በማለት በአለም አቀፍ ደረጃ በአፍሪካ ውስጥ በመሳቂያነታቸው ከሚታወቁ አምባ ገነን ደንቆሮ መሪዎችን ተክቶ ለህዝቡ የዲሞክራሲያዊ ስርአትን ስልጣን በድምጽ ብልጫ ተወዳድሮ የሚያዝባት ሀገር ትሆናለች ብሎ ህዝቡን ዋሽቶ የእድሜ ልክ ገዢ ለመሆን ቢሞትም ስልጣኑን ለልጁ ለማደላደል ከሚሞክር መሪ ነበር ሽልማት የተበረከተለት
  የሩዋንዳውም መሪ ቢሆን እርሱ ከመምጣቱ በፊት በእርስ በእርስ ጦርነት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎችዋን ያጣች ሀገርን የተረከበ ግን እርሱም ቢሆን ስልጣን ላይ ሲወጣ በህግ ሊያስጠይቀው የሚችል ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸመ ነገር ግን ሁሉንም ስልጣኖች በሀይል ተቆጣጥሮ እስከ እለተሞቱ ህዝቡን እየረገጠ ለመግዛት ከሚጥር ሌላ የአፍሪካ አውሬ እጅ ነው ሽልማትና ሙገሳ ያገኘው እና ዲሞክራት ለመምሰል እየጣረ ያለው ዶክተር አቢይ
  እነዚህ ሲንከባለሉ የቆዩ እና ተገቢ እና ትክክለኛ መፍትሄ ያልተሰጠባቸው ምን ምን ናቸው
  የመጀመሪያ የነበረው የኢንጂነር ስመኘው ጉዳይ ነው ።እኚህ ኢንጅነር በሙያቸው ባላቸው እወቀት ሀገራቸውን ለማገልገል በተሰማሩበት ሞያ የሙያ ግዴታቸውን እየተወጡ እያሉ በመሃል አዲስ አበባ በአብዮት አደባባይ በግፍ የተገደሉ እና እስካሁንም አብዛኞቻችን የእርሳቸው ግድያ እራሳቸው ፈጽመውታል የሚለው ያልተዋጠልን እና ከእርሳቸው ግድያ ጀርባ መንግስት በይፋ የሚያውቀው ገዳይ በሽፍንፍን መቅረት ይሄም ጉዳይ ጊዜ ጠብቆ ሊፈነዳ የሚችል እና ፈጽሞ የማይረሳ በግድ ህዝባችን እንዲረሳው ለማድረግ የተንከባለለ ችግር ነው
  በሁለተኛ ደረጃ በሰኔ አስራ ስድስት ግድያ የተሳተፉ ነፍሰ በላዎች የብዙ ሰው አካል እና ህይወት ቀጥፈው እኔ በበኩሌ እስከ አሁን በዚህ ጉዳይ የማውቀው ነገር የለም ከፍትህ አደባባይ ደርሶ ትክክለኛ ፍትህ ያልተሰጠበት እና በህዝብ አእምሮ እና ልብ ውስጥ ተቀብሮ ያለ መንግስትም ነገሩን ችላ በማለት አድበስብሶይ ያለ ሌላ የተንከባለለ ጉዳይ እና ከዚህ ጥቃት ጀርባ ዶክተር አቢይም ሆነ ቡድናቸው ዝምታ ሹመታቸውን ለማጠናከሪያ በቀላሉ የሀዝብ ድጋፍ ለማግኘት ሰላማዊ እና በእርሳቸው ፍቅር ያበዱ ወገኖቻቸውን ያስጨረሱበት ነው ብሎ የሚያምነበት እና ይሄም ትክክለኛ ፍርድ ባለማግኘቱ ተጨማሪ የዶክተር አቢይን ህዝባዊ ወገንተኝነትጥርጣሬ ውስጥ የከተተ እና ህዝባችንን ጥርስ ያስነከሰ የተድበሰበሰ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ተገፍቶ የተንከባለለ ችግር ነው
  በሶስተኛ ደረጃ በቡራዩ እና በስጋ ሜዳ በአንድ ብሄረሰብ ላይ ሆን ብሎ ታቅዶ ተደራጅቶ የተፈጸመ ዘግናኝ ግድያ እና ግፍ ። እኔ እዚህ ላይ በዋነኝነት ተጠያቂ መሆን የሚገባው መንግስት ነው እላለሁ ምክንያቱም በአንድ ወቅት ዶክተር አቢይ ሰራዊታችን ጠንካራ እና በቁጥርም ተቃዋሚ ነን ብለው በትጥቅ ትግል መሳሪያ ይዘው በኤርትራ ከተሞች እና ጫካዎች መሽገው ያሉት ከአንድ ክልል ሀይል በቁጥር በጣም ያነሱ እና በሰላማዊ መንገድ እንቢ ካሉ በሀይል በቀላሉ ለማሸነፍ የሚቻል መሆኑን በተጨማሪም አንዱ ባለስልጣን ደግሞ ከአፍሪካ በጥንካሬው በአምስተኛ ደረጃ የሚገኝ የመከላከያ ሀይል ያለን መሆኑን የገለጹ ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሄ ዘግናኝ ድርጊት የተፈጸመው ከማእከላዊ መንግስት አፍንጫ ስር የነበር እና ሰራዊቱ በቀላሉ ደርሶ ግጭቱን ማብረድም ሆነ ማስቆም የሚችል የነበር ሲሆን ያሁሉ ሳይደረግ ብዙ ህዝብ ተጎድቶ ከቤቱ ተፈናቅሎ አሁንም ድረስ አጥፊዎችን ወደህግ ቀርበዋል ቢባልም ግን እስከ አሁንተገቢ ፍርድ ያልተሰጠ እና ከዚህ ጥቃት ጀርባ መንግስት እና እንደ ጃዋር የመሳሰሉ ግለሰቦችን ህዝባችን በከፍተኛ ጥርጣሬ የሚያይ እና ምንም አይነት መፍትሄ ሳይገኝለት ዶክተሩ በውጭ ጉዞ በገሃድ የሚታየውን በሰው ልጆች ላይ የደረሰውን ጭካኔ ለማረሳሳት ከሀላፊነት ለመሸሽ የሚንሸራሸሩ ነገር ግን አሁንም ይሄም እየተንከባለለ ያለ ችግር ህዝብ አሸንፎ ሲወጣ ከማንም ማምለጥ የማይቻል የተዳፈነ እሳት መሆኑን
  በአራተኛ ደረጃ በቅርቡ በለገጣፎ የበርካታ ኢትዮጵያውያን ቤት እነርሱ ያሉበት የድርጅት አባሎች የነበሩ በህገ ወጥ መንገድ መሬት ሲቸበችቡ እና የተለያዩ አገልግሎቶችን ህጋዊ ናችሁ ብለው ህጋዊ በሆነ ደብዳቤም ሆነ ሌሎች ማስረጃዎች እየኖሩ ያሉ ዜጎችን ቤት ንብረት በማፍረስ ወደጎዳና በመጣል የመንግስት ያለህ ሲባል እኔ አልሰማሁም ይሄ ሲደረግ በማለት በአደባባይ በህዝብ የተቀለደ እና ለእነዚህ ሁሉ ችግሮች ምንጭ የነበሩ የድርጅቱ አመራር አባሎችንወደ ህግ አቅርቦ ለተጎዳው ህዝብ መፍትሄ ከመፈልግ ይልቅወያኔ የሄደበትን መንገድ ለመጓዝ መጀመሩ ዋነኛ ያልተፈታ እና በመንከባለል ላይ ያል ችግር ከጊዜ በሁዋላ እራሳቸውን ደፍጥጦ መፍትሄ የሚገኝ መሆኑን ማመን የሚገባቸው እንደሆነ መታወቅ አለበት
  በስድስተኛ ደረጃ በተለይ አሁን ዶክተር አቢይ በዚህ ጉዳይ ትልቅ ተውኔት እየሰሩ ይገኛሉ።የጌድኦ ህዝብ ረሀብ ነውላለፍት ሶስት መንግስታት ወያኔን ጨምሮ መውደቅ ምክንያት ረሃብ ነው እነዚህ የጌድዮ ህዝቦች ሲፈናቀሉ ጥቃት ሲደርስባቸው የክልሉም ሆነ የማእከላዊው ወይም የፌዴራል መንግስቱ ያውቃል። ነገር ግን ምንም አያመጡም በሚል ህዝቡን በረሃብ እየጨረስ ህጻናት እየሞቱ አሁን ወደሶሻል ሚዲያ ችግሩ ሲወጣ እና የኢትዮጵያ ህዝብ ለወገኖቹ መረባረብ ሲጀምር አለም አቀፍ ማህበረሰቡም ለዚህ ጉዳይ አይን እና ጆሮውን ሲሰጥ ሳይወድ በግድ በሰላም ሚኒስትርዋ አማካይነት ለጉብኝት እና ጋዜጣዊ መግለጫ በቃ። እናም ዶክተር አቢይ አድበስብሶ ሊያልፈው የነበረ ጉዳይ በዚህ ችግርም በሃላፊነት መጠየቅ የሚገባቸውን አፈናቃዮችን ለማዳን እና የሀዝቡን ርብርቦሽ የራሱ በማስመሰል ጠልፎ በመውሰድ ችግሩ በደረሰበት ቦታ ላይ ፎቶ በመነሳት በማቀፍ ለማታለል እየሞከረ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው ልክ እንደ ቄሮ እና የአማራው ተጋድፍሎ በዚህም በጎን አሸንፎ ለመውጣት እና ችግሩን በማድበስበስ በራሱ ላይ ጊዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጂ እያተመደ ነው ያለበት ሁኔታ ነው ያለው።
  በመጨረሻ በሰላማዊ መንገድ ትጥቅ ፈትቶ በድርድር የገባ በሰላማዊ መንገድ በምርጫ ተወዳድሬ ስልጣን እይዛለሁ ብሎ የገባ ቡድን በፌዴራል መግስቱም ሆነ በክልሉ አቅም እና ስልጣንማለፍ የማይችል በጣም ደካማ የኦነግ ሰራዊት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ብር ዘረፈ ማለት እና ማስወራት ለማንም የማይዋጥእና ውሸት በመሆኑ ከዚህ ዝርፊያ ጀርባ በዋነኛነት ጠጠያቂ ግባ እና ዝረፍ ያለው አካል መሆኑን አሁን አቅም አለኝ ዝም በል ማለት ሌላው ትልቅ ችግር እና ከህዝብ አይን እና ጆሮ ምንም የማይሰውር እራስን የሚያስጠይቅ ያልተፈታ በይደር እነ ዶክተ ር አቢይ ሆን ብለው ለሌላ ጊዜ ገፍተው ያንከባለሉት ችግር ነው
  በመጨረሻ ዶክተ ሀይሌ ላሬቦ የመለስ ራእይ የሚለው አባባል ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማነው ከመለስ ሞት በሁዋላ ነው ።ይሄንን የተናገረችው የመለስ ሚስት አዜብ ጎላ ናት ።እኔ እንደሚመስለኝ አዜብ እንደው ንግግር ያሳመረች መስሎአት ነው እንጂ እንደው በይፋ ራእዩ ምንድነው ተብላ ብትጠየቅ የረባ መልስ አትሰጥም ።ይሄ ራእይ በኢትዮጵያ ህዝብ መክኖ ነበር ማለት ይቻላል ግን አሁን ስናየው የሞተ ስር አት በአዲስ መልክ በሌላ ብሄር ለማስቀጠል ሽር ጉድ እየተባለ ስለሆነ በወያኔ ሳይሆን በእነጅዋር ጸጋዬ አራርሳ በነዶክተር አቢይ እና ለማ ቲም ለማስቀጠል ደፋ ቀና እያሉ ይመስላል እኔ የመለስ ራእይ ማለት ሀገር ማፍረስ ህዝብ መበተን እንደ ሶሪያ የመን ማድረግ ነው

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here