Home News and Views የኦሮሚያ እና የአዲስ አበባ የጸጥታ ኃላፊዎች ተከታትሎ መነሳት ምን ይነግረናል?

የኦሮሚያ እና የአዲስ አበባ የጸጥታ ኃላፊዎች ተከታትሎ መነሳት ምን ይነግረናል?

በጫሊ በላይነህ

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሜጀር ጄኔራል ደግፌ በዲ በድንገት ከሥልጣናቸው መነሳት ዛሬ ከተሰማ በኃላ አነጋገሪነቱ ቀጥሏል፡፡ በተለይ ከሳምንት በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ በድንገት እንዲነሱ የተደረጉት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮን ላለፉት ስድስት ወራት ሲመሩ የቆዩት ብርጋዴር ጄኔራል ከማል ገልቹ ግጥምጥሞሹ ታስቦ የተከወነ መስሏል፡፡

ሪፖርተር ጋዜጣ እንደዘገበው የፖሊስ ኮሚሽኑን ለዓመታት ሲመሩ የነበሩትን አቶ ይህደጎ ሥዩምን ተክተው በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰኔ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. የተሾሙት ሜጀር ጄኔራል ደግፌ፣ ከኃላፊነታቸው በድንገት የተነሱበት ዝርዝር ምክንያት ለጊዜው ባይታወቅም፣ ማክሰኞ ሚያዝያ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. የደረሳቸው የስንብት ደብዳቤ ግን ‹‹በጡረታ›› የሚል መሆኑን አረጋግጧል፡፡

ሆኖም ጋዜጣው ሜጀር ጄኔራል ደግፌ በጡረታ የተሰናበቱት በተቋም ደረጃ ምንም ዓይነት ችግር ገጥሟቸው ሳይሆን፣ በሕመም ምክንያት መሆኑንና ይኼንንም ከመንግሥት ጋር ውይይት አድርገው መተማመን ላይ በመድረሳቸው መሆኑን የሪፖርተር ምንጮቹ እንዳረጋገጡለት አክሏል፡፡

ተሰናባቹ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ጀነራል ከማል ገልቹ ለቢቢሲ እንደገለጹት ባለፈው ወር የደረሳቸው ደብዳቤ ከሥራ መሰናበታቸው ብቻ ከመግለጽ ያለፈ ቁምነገር አልያዘም፡፡ እናም ጀነራሉ ለምን ከኃላፊነታቸው እንደተነሱ እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ሊነሱ ስለቻሉበት ምክንያት “ግምቴ” ያሉትን አስቀምጠዋል፡፡ “በአስተዳደሩ ውስጥ የፓርቲ እና የመንግሥት ሥራ የሚሰሩበት መንገድ በእኔ ፓርቲም ሆነ በግል እምነቴ ተቀባይነት የለውም። በመንግሥት የዕለት ተዕለት ሥራ ላይ ፓርቲ ጣልቃ መግባት አለበት ብለን አናምንም” ሲሉ አንደኛውን ምክንያታቸውን አስቀምጠዋል።

አክለውም ሁለተኛውን ምክንያት ሲጠቅሱ ” መለስ ብዬ ሳስበው የፖለቲካ ተቀባይነት ለማግኘት ሲባል እኔ ወደ ስልጣን እንድመጣ የተደረገው ውሳኔ አመራሩን ጥያቄ ውስጥ የጣለው ይመስለኛል” ብለዋል፡፡

ብ/ጄኔራል ከማል ገልቹ ከ13 ዓመታት በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሰላም ጥሪ ተከትለው ከኤርትራ ባለፈው ዓመት ወደ ሃገር መግባታቸው ይታወሳል። ከዚያም ጥቅምት ወር ላይ ነበር የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደርና የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው የተሾሙት።

ከኃላፊነታቸው የተነሱት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሜጀር ጄኔራል ደግፌ በዲ ከተሾሙ ከሁለት ወራት በኋላ በተለይ ከአዲስአበባ ሕዝብ ጋር በመልካም ዜና አልተዋወቁም፡፡ መርዶ ነጋሪ ሆነው በቀረቡበት መግለጫ ብዙዎች ኮስታራ ፊታቸውን የማየት ዕድል ገጥሟቸዋል፡፡

በመስከረም ወር 2011 መጀመሪያ በአዲስአበባ ከተደረገ የተቃውሞ ሰልፍ ጋር ተያይዞ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተገደሉትን አምስት ሰዎች ጨምሮ ከመስከረም 2 እስከ መስከረም 7 ቀን 2011 በጥቅሉ 28 ሰዎች መገደላቸውን ያረዱት እሳቸው ነበሩ፡፡ በአዲስአበባ ከሰልፍ ጋር ተያይዞ የታሰሩ 1 ሺ 200 የሚሆኑ ወጣቶች ወደ ጦላይ መወሰዳቸውንም አንዳንዶቹ በባንክ ላይ የዘረፋ ሙከራ ማድረጋቸውንና በተሽከርካሪዎችና በሱቆች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን፣ አንዳንዶቹ ከሺሻ ቤት እንደተያዙ መናገራቸው ጥቂት የማይባሉ አዲስአበቤዎች ጋር ያላተማቸው ንግግር ነበር፡፡

ያም ሆነ ይህ የሁለቱ ጀነራሎች ከኃላፊነት ተነስተዋል፡፡ ምናልባት የሁለቱም ሰዎች መነሳት ጉዳይ ዶ/ር ዐብይ የሚመሩት ኦዴፓ እስካሁን በግልጽ ያሳወቀው ነገር ባይኖርም ምናልባት ከጸጥታ ሥራዎች ጋር በተገናኘ ያሳዩት የአፈጻጸም ድክመት ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል የብዙዎች ግምት ሆኗል፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here