Home News and Views ከጥገና ለውጥ ወደ ሽግግራዊ ጥገና ለውጥ (ምዕመን ፈለቀ)

ከጥገና ለውጥ ወደ ሽግግራዊ ጥገና ለውጥ (ምዕመን ፈለቀ)

 

 

የዶ/ር ዓቢይ የያኔው ቃል ኪዳን። ሁላችንም ተለያይተናል። አይጠቅመንም። በመደመር፣ በጋራ አስበን በጋራ እንሥራ የሚል ነበረ። እኔም፣ እገሌም፣ ድርጅቴም፣ እናንተም ተግባብተን አገራችንን በእኩልነት እናስተዳደር። ሁሉም በሀሳቡ ተስማማ፣ ብሎም የወደፊቷ ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት ወሰነ።

መጀመሪያ ላይ፣ ዶ/ር ዓቢይ ነጻነት ቀጥሎም አንድነት እንደሚያሻን አውቆ እየተንቀሳቀሰ ነበር። እመራችኋለው ያለው በዋናነት ህግን ለማስከበር፣ የአገር ሰላምን እና ዳር ድንበርን ለማስጠበቅ ነበር። ይህ በማንኛውም ሁኔታ ላይ ያለ መንግሥት አቋምም ግዴታም ነው።

መነሻው ላይ፣ ሀሳቡ ከሀስባችን ጋር የተቀራረበ ነበር። በመጀመሪያ ለሁሉም ነጻነትን አረጋገጠ። በተከታይ የስኬት ጉዞው፣ ብዙ በጎ ሥራዎችን ሠራ፥ የቡራዩ ተፈናቃዮችን ሲያጽናና ነበር። ደሳሳ በሆነች በእማሆይ አዱኛ ጎጆ ተገኝቶ ቡና አጣጪም ነበር። በዓመቱ መግቢያ ላይ፣ ወጣቶች ወደ ሥራ የሚሰማሩበትን መላ ዘየደ። እርሱንም ተከትለው፣ የአዲስ አበባ ወጣቶች የሥራቸው መጀመሪያ በማድረግ የከተማዋን ቆሻሻ አጸዱ። በዚያ ወቅት እርሱ አገልጋይ ነበር። በእውነት፣ ለተበተነው መንጋ እረኛ ነበር። ደስታው ደስታችን፣ ችግሩ ችግራችን ነበር። ሌላው ቢቀር ሲጠፋ በጸሎት የሚለምኑለት ብዙ እናቶች ነበሩ። በኔ አስተያየት፣ ዶ/ር ዓቢይ እስከ ለገጣፎ ነዋሪዎች መፈናቀል ድረስ፣ ለውጡን በተሳካ ሁኔታ መርቷል።

ዶ/ር አብይ፣ የተቀበለውን አደራ ለመወጣት አቅም አንሶታል። ብዙ ጉዳዮች ከእርሱ ቁጥጥሩ ውጪ እየሆኑ ነው። ካለፉት አገዛዞች ውድቀት አልተማረም። ነገር ግን፣ አጉል ተስፋ ሰንቆ፣ እርሱም እንደ ቤተ ሙከራ አይጥ ያሰበውን ሊሞክርብን ቀጥሏል።

ዶ/ር አብይ በመደመር እርሱም ሆነ እርሱ የሚዘውረው የለውጥ ኃይል እኩል (indifferent) ሚና መጫወት እንዳለባቸው ዘንግቷል። አላቻቻለም። ችግራችን፣ እርሱ ሥልጣን ላይ መኖሩ ሳይሆን በዘር ፖለቲካ እድሳት መጠመዱ ነው። ቀርፋፋ (sluggish) የሆነውን የኢህአዴግ ሥርአት ዘበናይ (civilized) ለማድረግ ጊዜያችንን በጣም እየበላ ነው። በባሕሪው (character) ሊቃና የማይችለውን፣ በድቡሽት ላይ የተገነባ ደሳሳ ጎጆን ለማደስ ደፋ ቀና ይላል። ወደ አንድነት እወስዳችኋለው እያለ፣ በብዙ አገራት የተወገዘውን እንዲሁም የውድቀታችን ዋና ምክንያት የሆነውን የዘውግ መንግሥት በተጠናከረ ሁኔታ ለማዝለቅ ተባባሪ ሆኖ በመሥራት ላይ ነው። ሙከራውን፣ ኦዴፓ እና አዴፓ በሚለው የቅጽል ሥም ገፍቶበታል። ደግሞም፣ አዳዲስ የዘር ድርጅቶች እንዲቋቋሙ መንገድ ከፍቷል። በማኅበራዊ ድኅረገጾች የሚነፋውን ከፋፋይ የዘር ፖለቲካ አቀንቃኞችን እሽሩሩ ይላል። የዘር ፖለቲካን ምንጭ ሳያደርቅ፣ የጥላቻ ንግግሮች በህግ ይወገዱ ይላል።

ዶ/ር አብይ እርሱ እያገለገለበት ያለ የብሔር ተቋም፣ አሸናፊ እና ለወደፊት ዋና የሥልጣን ባለቤት ሆኖ ይወጣ ዘንድ በተጠና ሁኔታ ያግዛል። ቀላል ምሣሌ ብናነሳ፣ የአዲስ አበባን ምክትል ከንቲባን በአዘላቂነት ለማስቀመጥ ያስገባውን ሥላች ህግ ማንሳት ይበቃል። ይህም ኦዴፓ ለወጠነው ድምጽ ብልጫ መንገድ ጠራጊ ይሆናል። “ትሪክ” ወይም “ትሪት” የሚሉት የፈረጆች ጨዋታ።

ዶ/ር አብይ ሰላም ሲደፈርስ አውቆ ያላወቀ በመምሰል ባለጉዳዮች ከተዋከቡ በኋላ በጠባቧ መስኮት ብቅ ይላል። ሌላው (የዜጋ) ድርጅት ወደ አብዛኛው ክልል ዘልቆ ለመጪው የመንግሥት ሥልጣን እራሱን እንዳያስተዋውቅ እንቅፋት ተቀምጧል። በዘውግ ዙሪያ የሚጯጯሁ ረባሽ ድርጅቶችን አውቆ ችላ እያለ የልብ ልብ ይሰጣቸዋል። የኬኛ ፖለቲከኞች እና እንደ ኤጀቶ ያሉ በጥባጮች እስካሉ ድረስ፣ ወደፊት እንኳን በሌላው ክልል፣ ስላማዊ በምትመስለው አዲስ አበባ ተዘዋውሮ ምርጫ መቀስቀስ የሚታሰብ አልሆነም።

ከአይን መራቅ (ማፈር) ጤናማነት አይደለም። ዶ/ር አቢይ መቼ ከዓይን ራቀ ስንል፣ ከለግጣፎ ተፈናቃዮች ይጀምራል። ቀጥሎም የጌዴዎን ሕዝብን መፈናቀል እንዳላወቀ አልፏል። ሲልም፣ በእስክንድር ነጋ የሚመራውን የአዲስ አበባ (የባልደራስ) የመብት ጥያቄ ተቃወመ። በወሳኝ ችግሮች ዙሪያ አለመናገር እና ማፈር ልምዱ ሆነ። ለመጀመሪያ ጊዜ ከልባችን መራቅ ጀመረ። እናም፣ ከዚህ በኋላ ያለው ሂደት በእጅጉ አሳሰበን። ምክንያቱም ባልንጀራችን ጀርባውን ሰጥቶን በማዝገም ወደቀደመው ሥርአት እየተመለሰ ነውና።

በመሠረቱ፣ ለውጡ ጥገና እንጂ ሽግግር አለመሆኑን ሁሉም ይረዳል። ምክንያቱም ተፎካካሪ የሆኑ ቡድኖች በማዕከላዊ መንግሥት አመራር አልተካተቱም። ጥገና መሆኑ ግን በራሱ ችግር አልነበረም። ቀና ሀሳብ ያለው ብቸኛ ዜጋ፣ አገርን በበጎ ሊያሸጋግር ይችላል።

ስለዚህ፣ ኃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ፣ የሚከተለውን እመክራለሁ

  • በዘር ፖለቲካ ኢትዮጵያ ከችግር አትላቀቅም። ሁሌም የለቅሶ ቤት ትሆናለች። ጨቅጫቃ ሚስት እና የሚያፈስ ጣራ አንድ ናቸው። የዘር ፖለቲካም እንዲሁ።
  • የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ኢህአዴግ የግድ የሚከስምበት ሥራ መሰራት አለበት። ይህም በአመጽ ሣይሆን በሰላም መሠራት አለበት። በኃላፊነት ላይ ያሉ የብሔር ውክልና ያላቸው ቱባ ባለሥልጣናትና የምክር ቤት አባላት ቀስ በቀስ እና ሚዛናዊ በሆነ መልኩ በችሎታቸው በሌላ የስራ መደብ በድጋፍ ሰጪነት የሚሰሩበት ሁኔታን ማመቻቸት ያስፈልጋል። በማእከላዊ መንግስት ጣልቃ የማይገባ ወይም ረጅም እጅ የሌለው የብሔረሰብ ምክር ቤት ማቋቋም (የኮ/ል መንግሥቱ አገዛዝን ይጠቅሷል)። በተዋረድ፣ በሲቪል ሰርቪስ፣ በፖለቲካ ትምህርት ቤት፣ በመምህራን ማኅበር፣ በሰራተኛ ማኅበር፣ በገበሬዎች ማኅበር፣ በወጣቶች ማኅበር፣ በቦርዶች በኮሚሽኖች ወዘተ ወዘተ በየደረጃው እንዲካተቱ ማድረግ።
  • በካቢኔው ውስጥ፣ ቢደመሩም በብቃት ለውጡን ማስቀጠል የማይችሉ ቁልፍ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ሥም እና በታ ሲቀያይሩ በተደጋጋሚ እናያለን። ይልቅ፣ ጠንካራ ካቤኔ መፍጠር የለውጥ ኃይሉን፣ እንዲሁም ኢህአዴግን፣ ያግዘዋል። ይህም ተፎካካሪ ከሆኑት፣ በዜግነት ፖለቲካ ላይ ከሚሰሩት ወይም ታዋቂ ግለሰቦች ሊሆን ይችላል። ጠቅላይ ሚኒስትር ከእንዲህ አይነት ባለሙያዎች ጋር መጋጠም (challenged) ያስፈልግሀል። ገብስ ገብሱን ማውራት ይበቃል።
  • ለውጡ ቀልጣፋ ጎልማሶችን ብሎም አብዛኛው የሕዝብ ቁጥር የሚይዙትን ወጣቶች እንዲያካትት ያስፈልጋል።
  • ሴቶች ባብዛኛው ውስን የመሪነት ሚና ያላቸው መሆኑን በብዙ አገራት እናያለን። የእኛ ሴቶች ባለሥልጣናት መጠናቸው የበዛ ይመስላል። አንድ ጊዜ በሴት ሰአት አልግባም ያለውን ኢትዮጵያዊ ሯጭ ባብጠለጠላችሁበት ሁኔታ ብታዩትም፣ ሀሳቤን ከመሰንዘር አልቆጠብም። ብዙ የቤት ኃላፊነት በሚወጡ በእኛ ሴቶች ቀርቶ በነጻ የሚኖሩት ያደጉ አገራት እንኳን እንዲህ በስፋት አይሞከርም። በኔ በኩል፣ ሴትን የእግር ኳስ ትጫወት ብዬ አልመክርም። ሴቶች የጦር ጄኔራል በመሆን አዋግተውል የሚለኝ ካለ ይንገረኝ። ሴቶች ከመመንተፍ የራቁ ናቸው ብል ግን አልሳሳትም።
  • በቀድሞ (ከመደመር በፊት) ወንጀላቸው የታሰሩት ከእሥር ቢፈቱ መልካም ነው። ማንም ቀድሞ ባባከነው የመንግሥት ሀብት (በፍታብሔር) እንጂ፣ በወንጀል ባይጠየቅ መልካም ይመስለኛል። ለጌታቸው አሰፋ እና ለወርቅነህ ገበየሁ የሰራ መደመር እንዴት ለያሬድ ዘሪሁን እና ለአብዲ ኢሌ አይሰራም? እርምጃችሁ ከመደመር በኋላ ወንጀል በሰሩት ላይ ያተኩር።
  • ለውጡ ባለፈው መንግሥት የተጎዱትን ሰዎች ባስቸኳይ እንዲያያቸው ያስፈልጋል። ለዚህ የሚሆኑ ትናንሽ ተቋማት አቅም በፈቀደ መገንባት አለባቸው። ሰላም ካለ የዲያስፖራው ትረስት ፈንድ እና ሌሎች አገር ወዳዶች እጃቸውን ለመዘርጋት እድል ያገኛሉ።
  • ለቁጥር አታካች የሆኑ ድርጅቶችን ከመጠፍጠፍ፣ ምን ያህሉ ሕዝብ ዘውግ ምን ያህሉ ዜግነት እንደሚፈልግ ግምታዊ ቁጥር ተወስዶ ጥቂት ፓርቲዎች መስራት ወሳኝ ነው። አመራሩና ሕዝቡ ፈጽሞ አልተገናኘም። ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ እንደሚሉት። ሕዝብ እኮ ቁመናችሁን ሳይሆን ሀሳባችሁን ነው የሚመርጠው።

እባካችሁ፣ በእውቀታቸው፣ በሥራቸውና በስነምግባራቸው የተከበሩ ሰዎች የሚሏችሁን አድምጡ። በእውነት አገራችን በቀላሉ እንድትረጋጋ ከተፈለገ ከልብ መስዋትነት መከፈል ይኖርበታል። ከቤተ መንግሥት፣ ከመኳንንትነት ወይም ከቢሮክራትነት ወጥቶ ትሁት እና አገልጋይ መሆንን ይጠይቃል። ለታዳጊው ትውልድ ሲባል ይህ ሀቅ መዋጥ አለበት። ምን ይቀርባችኋል? አገርህን ሰላም ማድረግ አይሻላችሁም? የታሰራችሁበትን የህሊና ሰንሰለት መፍታት አይሻላችሁም? እውነትን የምትቀበሉት ስትወድቁ ብቻ ነው እንዴ?

ወገኖቼ የዘር ቡድን መሪዎች፣ ዘረኝነት ዓለምን ያስጨነቀ ነው። የዘር፣ የሃይማኖትና መሰል ድርጅቶች ከፋፋይ ናቸው። አእምሮን ከማጫጫት አልፈው ለኃጢያት በሽታ ይዳርጋሉ። ዘረኛ ሆኖ፣ አገርን ወይም ሕዝብን ማስተዳደር ፈጽሞ አይቻልም። የዘር ቡድኖች ከመንግሥት ሥልጣን ፈጽሞ መራቅ ይገባቸዋል። ባንድ ወቅት፣ ፕሬዝደንት ቡሽ የታሊባን ቡድንን ያንኳሰሱበት ዋና ምክንያት የእስልምና ተከታዮች በመሆናቸው ሳይሆን ከፋፋዮችና ኋላ ቀር በመሆናቸው ነበር። በንግግራቸውም፣ የስልጣኔ ጠላቶች በለዋቸው ነበር (the enemy of civilization)። የተከበርክ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የዘውግ ሥርአት የአገሪቷን ጊዜ፣ ሀብት፣ ጉልበት፣ አዕምሮ እና ነፍስ በልቶ አንተንም ተስፋ ወደ ማስቆረጥ ሳያደርስህ ቶሎ ብለህ እወቅበት። ጅብ ከሚበላህ በልተኸው ተቀደስ!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here