Home News and Views ክነዓምን ዘለቀ ለአበበ ገላው

ክነዓምን ዘለቀ ለአበበ ገላው

#ኢሳት ፡ – ወዳጄ አበበ ገላው፡ –

አሁንም ትልቅ ስህተት እየፈጸምክ ነው። የሁላችንም ወዳጅ፣ የትግል ጓድ፣ ኢሳትን እሳት በማድረግ ከማናችሁም በላይ ድርሻ ያለው አርቲስት ታማኝ በየነ ሁላችሁም አቁሙ ፣ እኔ ስመጣ ሁሉንም ጉዳይ እንነጋገራለን ካለ በኋላ ይህን የራስህን ትርክት በመጻፍህና ምላሽ እንድሰጥ መገደዴ በጣም ያሳዝነኛል።
በሁላችንም ድካምና በሕዝብ ድጋፍ የተገነባውን የኢሳትን ችግሮች ከሚያባብሱት አንዱ ለመሆን በመወሰንህ በጣም አዝናለሁ ። ማንኛውም ተቋም በርካታ ችግሮች፣ እንቅፋቶች ፣ ተግዳሮቶች ይገጥሙታል፣ የመሪነት ጥንካሬ የሚለካውም በየደረጃው የሚገኙ የማኔጅመንት ፣ የመዋቅር፣ የቲክኒክ፣ የገንዘብ ችግሮችን ወዘተ ከልብ ለመቀበል ወኔው ኖሮት በሚያደርገው መፍትሄ ተኮር እንቅስቃሴና እርምጃዎች ነው ሊፈቱ የሚችሉት። ይህን ግን ለማድረግ ለበርካታ ወራት ብዙ ብንነጋገርም ብዙ ስብሰባዎችንም ያደረግን ቢሆንም መደማመጥና በጋራ ተናበን መስራት ለመቻል አልተቻለም። ኢሳትንም ሆነ የኢትዮጵያን ሕዝብም ወደሚያሳዝን ደረጃ እንደሚደርስ ለማየት ባለመቻላችሁ ዛሬ የምንገኝበት ላይ ተገፍተን የደረስነው አንተንም ጨምሮ ትልቅ የአስተውሎ (Wisdom) ከፍተኛ እጥረት ያለብን ማሕበረሰብ መሆናችን እጅግ ያሳዝነኛል’’
በዛሬው ጽሁፍ ላይ ላስቀመጥካቸው ክሶች አንድ በአንድ መልስ አልሰጥም። ነገር ግን የሚከተሉትን ነጥቦች ለማንሳት እገደዳለሁ፡
1. ለቁጥር በሚያዳግት ጊዜ የኢሳትን ችግር እየተደማመጥን እንፍታ በማለት ለሁሉም ወገኖች ሳሳስብ እንደነበረው ሁሉ ለአንተም አሳስቤሃለሁ፣ ተማጽኘሃለሁም።
2. አንተ እንዳስቀመጥከው ትላልቅ የኢሳት ውሳኔዎች የአዲሱ መንገሻ ብቻ አይደሉም። ጠቅላላ ቦርዱን – ዶር፣ አዚዝ መሀመድ፣ ዶ/ር ሙሉአለም አዳም፣ አቶ ዘላለም ተሰማንም የሚመለከቱ ናቸው። እንደዚህ አይነት ሕዝብን የሚያወናብድ ድምዳሜ መስጠት አግባብ ያልሆነ፣ ከሃቁም የራቀ ነው። በተጨማሪም እኛን የአንድ ቦርድ አባል ተጎታች የሚያደርግ፣ ሃላፊነታችንን የማናውቅ አድርገህ ማቅረብህ ያሳዝነኛል። እኔ እና አንተ በተለይ ደግሞ ከኢሳትም በፊት ለረጅም አመታት የምንተዋወቅ በመሆኑ፣ እንዲዚህ አይነት ድፍረት መጻፍህም ከማዘንም አልፎ እንደሚያበሳጨኝም ላሳውቅህ እወዳለሁ። በነገራችን ላይ የኢሳትን ችግር “በማንነት” እና በ”ፓለቲካ” ላይ የተመሰረተ እንደሆነ አድርገው ሕዝብን ለማወናበድ የሞከሩት የኢሳት ባልደረቦችም ሆነ ይህን ያራገቡ አክራሪ ብሄረተኞች ሃቁን ለማውጣት የምናፍርበትም ሆነ የምንሸማቀቅበት እንደሌለ ባለፈው በጻፍኩት መሰረት እነዚህ የቦርድ አባላት በታሪክ አጋጣሚ ሆኖ የአማራ ማህበረሰብ መሰረት ያላቸው ናቸው።
3. አንተ የኢሳት ስራ አስፈጻሚ (Executive Director) በነበርክበት ወቅት በማኔጅመንት ዙሪያ በተፈጠሩ ክፍተቶች ሳቢያ ቦርዱ ውሳኔዎች ሲወስን እኔ ኤርትራ ለአንድ ወር ሄጄ በነበረበት ወቅት እንደነበር ሁሉም የኢሳት ባልደረቦች የሚያውቁት ሃቅ ነው። ከኤርትራ ከተመለስኩ በኋላ ባነሳሃው ቅሬታና ብሶት ውሳኔውን ለማስተካከል የተሄደበት ርቀት፣ እኔም ያደረኩትን ጥረት የምታውቀው ነው። የዋሽንግተን ዲሲ የኢሳት ባልደረቦች ሁሉ የሚያውቁት ጉዳይ ነው ፡፡ እንዲሁም በጽሁፍም የሚገኝ መሆኑን ትረዳለህ ብዬ እገምታለሁ።
4. ለአለፈው አንድ አመት ጀምሮ የኢሳት ችግሮች የተባባሰው አንተን ጨምሮ በልዩ ልዩ ወገኖች መደማመጥ አለመቻልና ፣ አንዳንዶቻችሁ፣ በእልህ በምትወስዷቸው ሃላፊነት የጎደላቸው እርምጃዎች እንዲሁም የምትጽፋቸው የምትናገራቸው ጭምር መሆኑን በተደጋጋሚ ለአንተም ሆን ይህን ላደረጉ የኢሳት ባልደረቦች በተደጋጋሚ መንገሬን የምታስታውስ ይመስለኛል። ሰለዚህም ዛሬ ለደረስንበት የኢሳት ከፍተኛ ችግር ወይንም ቀውስ አንተ የተከተልከው ሌሎች የኢሳት ባልደረቦች (የተቀነሱትንም ያልተቀነሱትንም ጨምሮ ) ያደረጋችሁት፣ ከቅርብ ወራት ጀምሮ ደግሞ በሌሎች ሚዲያዎች ጭምር አንዳችሁ ስለሌላው የምትሰነዝሯቸው አስተያየቶች ሁሉ የገጠሙንን ችግሮችና ቅራኔዎች ለመፍታት በፍጹም እንዳልረዳ “ለውጡን ደጋፊ” ለምትባሉም ሆነ “ ለውጡን የሚቃወሙ” በሚል ለተሰለፋችሁ በተዳጋጋሚ በግልም በቡድንም እየነገርናችሁ ፣ እባካችሁ እያልን ፣ የኢሳትን ቅቡልነት፣ ተአማኒነት እየሸረሸረ፣ ኢሳትን የሚደግፈውን ማሕበረሰብም እየከፋፈለ ጭምር መሆኑን ቦርዱን በመወከል ከኢሳት ባልደረቦች ጋር በተደረጉና አንተም በነበርክባቸው ስብሰባዎች ጭምር በተደጋጋሚ ነግሬያችኋለሁ፡፡ ይህን ደግሞ በተደጋጋሚ በቅርብ ቀንም በአካል በተገናኘን ጊዜ ለአንተም በግል ነግሬሃለሁ።
5. ይህ ኢሳትን የሕዝብ ለማድረግ፣ የሕዝብ ሚዲያ ለማድረግ ፣ አዲስ ቦርድ ለማስመረጥ በባለድርሻዎች በተደረገው ስምምነት መሰረት በጋዜጠኞች የተወከላችሁት አንተ፣ አቶ ሲሳይ አጌና ፣ እንዲሁም አርቲስት አክቲቪስት ታማኝ በየነ በመሆን አሁን በስራ ላይ ከሚገኘው ቦርድ ደግሞ እኔን ጨምሮ ሶስት የቦርዱ አባላት ተወክለን ፡ የጋራ ኮሚቴም ተቋቋሞ በሚደረጉ ስብሰባዎች ጊዜም ሆነ በግልም አንተ በምትናገረው አሉታዊ ቃላትም ሆነ በምታደርጋቸው ድርጊቶች ኢሳትን ለማዳን በባለድርሻዎች በጋራ በሚደረጉ ውሳኔዎች ብቻ እንዲሆን የተስማማንበትን ፌርምዎርክ ተግባራዊ ለማድረግ እየረዳ አለመሆኑን፣ ከዚህም ድርጊት እንድትታቀብ እኔ ብቻ ሳልሆን አርቲስት አክቲቪስት ታማኝ በየነ፣ አቶ ሲሳይ አጌና እንደኔው በተደጋጋሚ ነግረውሃል።
6. ከአዲሱ ጋር አንተ የገባህበት እልህ ሁኔታዎችን ፣ ችግሮችን እንዲሁም ለችግሮቹ ያስቀመጥናቸውን የመፍትሄ አቅጣጫዎች ለማየትና ምክንያታዊ ለመሆን አለመቻልህ በጣም ያሳዝነኛል።
በቅርብ ቀን ከኢሳት “በፓለቲካ አቋም” በሚል ሰበብ ለወጡትም ፣ ለሁላችሁም በተለይ እኔና ታማኝ ስናሳስባችሁ የነበረው፣ ተደማምጠን ፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባካተተ ሁኔታ የገጠሙንን ችግሮች ሁሉ እንፍታ በማለት ነበር። የገጠመንንም ከባድ የገንዘብ ችግርም ሊፈታ የሚችለው በመካከላችን መግባባትና ኢሳት ከሁላችንም በላይ መሆኑን ስንረዳ ነው በሚል ስናሳስባችሁ ከርመናል። በግልም ሆነ በኢሳት ስቱዲዮ በተደረጉ ስብስባዎች ሁሉ ስንል የነበረው ይህና ይህ ብቻ ነበር። ሁሉም እኔ ከኢሳት በላይ ነኝ የሚል አቋም ስለያዘ እዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ አንተም አሉታዊ አስተዋጽኦ ማድረግህ እንደገለጹልህና አሁንም ያሰብከው ማንንም እንደማይጠቅም በግል የሚቀርቡህ የኢሳት ባልደረቦች በላፉት ጥቂት ቀናት ጭምር እንዳናገሩህ የምታስታውስ ይመስለኛል።

ወዳጄ አበበ ገላው ብዙዎቻችሁ ራሳችሁን ከኢሳት በላይ አደረጋችሁ፣ ኢሳት እንደ ሜዲያ እናንተን ሕዝብ እንዲያውቃችሁ ሚና ተጫወተ፣ አንተም ሆንክ ሌሎች በጋዜጠኝነት እንዲሁም በአክቲቪስትነት በቆያችሁበት ረጅም አመታት ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ትልቅ ክብርና ዕውቅና የሰጣችሁ በኢሳት ውስጥ ባደረጋችሁት አስተዋጽኦ ነው ማለት ማጋነን አይደለም፣ ይህን ያደረግን ተቋም በዚህ መልኩ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ ማድረጋችሁ በጣም ያሳዝናኛል።

ለበርካታ ጊዜ ለብዙዎቻችሁ እንደነገርኳችሁ ፣ እኔ ብቻ ያልኩት የሚለውና አንተ ወይንም ሌላው በሚፈልገው መንገድ መሄድ አይቻልም ፣ሁሉም ባለድርሻ አካል ተደማምጦ የሚደረስበት መፍትሄ እናምጣ ስንል ፣ ለሱም እድል ሳትሰጡን የእሳት አደጋ በየሳምንቱ እየፈጠራችሁ ፣ ይህንኑ ስንከላከልና የኢሳትን የገንዘብ አቅም ለማሳደግ መደረግ ያለባቸውን ለማድረግ እንዳንችል ነበር የተደረገው። ለጊዜው ይሄው ነው። አገራችን ኢትዮጵያ በከንቱነትና በግብዝነት የተሞሉ ብዙዎች አገር በመሆኗ። ትህትና ተረግጦ በየጊዜው በምናደርጋቸው የማን አለብኝነት፣ የእልህና ፣ ሄደው ሄደው ፋይዳ የሌላቸው ልፊያና እርግጫ የሕዝብ ተስፋን ፣ የሕዝብ ልብን መስበር ትልቁ ስኬታችን መሆኑ እጅግ በጣም ያሳዝነኛል።
ከሰላምታ ጋር

ከሰላምታ ጋር
ነአምን ዘለቀ

ከዚህ ቀጥሎ ያለው ደግሞ በ ማርች ወር 2019 ከ አግ7 በገዛ ፈቃዴ ስለቅ ስለኔ የጻፍከውና በውቅቱ ከላይ የዘረዘርኩትን በጥቅሉ የስጠሁት መልስ እንድታየው ነው።
============================
#ወዳጄ አበበ ገላው፦
እኔን በሚመለከት ምስክርነት በይፋ ስለጻፍክ በምስጋና ልጀምር፡፡ ሆኖም የእኔ ከአርበኞች ግንቦት 7 አመራር ሃላፊነት በገዛ ፈቃዴ መልቀቅ ምክንያት በማድረግ ስለአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ እመራሮች የጻፍከው ለረጅም አመታት እብሬያቸው በዚህ ብዙ ውጣ ውረድ ባሳለፍናቸው የትግል እመታት የማውቃቸውን ከፍተኛ አመራሮች ስብእና አይገልጽም። ወፍራም መተማመን፣ መከባበር፣ ግልጽነት፣ በሃሳብ ተሟግቶ፣በጋለ ስሜት ጭምር በሀገራዊና በድርጅታዊ ጉዳዮች ላይ ተጨቃጭቆና፣ ተፋጭቶ ወደ ጋራ ዴሞክራሲያዊ ውሳኔ መሄድን፣ ስሜቶች ቢጎዱም፣ የዚህ ወይንም የዚያ ሃሳብ አሸናፊ ቢሆንም ፣ ሁላችንም ለቆምንለት ሀገራዊና ህዝባዊ አላማና ግብ በማስቀደም፣ ውጦ፣ ተዋውጦ አብሮ መራመድን ያጎለበተ ከፍተኛ እመራር ነው። መላእክት አይደለምና ስህተቶች ሊሰሩ ይችላሉ። እኔ እስከማውቀው ግን “የሴራ ፓለቲካ “ በንቅናቄው ውስጥ በበኩሌ አላውቅም። አንተም የንቅናቄውን ከፍተኛ እመራሮች እንደኔ በቅርበት ስለማታውቃቸው እንዲህ አይነት ድምዳሜ በአደባባይ መስጠት ፋይዳ ያለው ነው ብዮ አላምንም።

ሌሎች ጉዳዮች እንደሚከነክኑህ የማውቀው ስለሆነ እነዚህ ችግሮች ለመፍታት ባስቀመጥነው ያጋራ መዋቅርና አቅጣጫ መሰረት ትህትናን ተላብሰን፣ ማናችንም ከተቋም በላይ አለመሆንችንን ተረድተን፣ ሁሉም ባለድርሻዎች በጋራ ተነጋግረን፣ በጋራ መፍትሄዎች ማምጣት ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት መንገድ ነው ብዮ በድጋሚና በአደባባይ ለመምከርና ለማሳሰብ እወዳለሁ። እኔም፣ አንተም፣ ሌሎችም ባለድርሻዎች ብዙ ጊዜ የተነጋገርናቸውን ችግሮች ከአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ አመራሮችም ሆነ እኔ ከሃላፊነት መልቀቅ ጋር በማያያዝ ባናሳክረው የተሻለ ነው ብዮ እመክራለሁ።

ከአክብሮት ሰላምታ ጋር
ነአምን ዘለቀ
===============================
ጋዜጠኛ አበበ ገላው ስለ ነዓመን ዘለቀ ከግንቦት 7 መልቀቅና በአጠቃላይም ስለ ግንቦት 7 ይናገረል!!

By Abebe Gellaw

“የአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር አባል የነበረው ነአምን ዘለቀ ለድርጅቱ የጻፈውን የመልቀቂያ ደብዳቤ በጥሞና አነበብኩት። ነአምን ኢትዮጵያን ከህወሃቶች መንጋጋ ለማላቀቅ በተደረገው ትግል ጉልህ ሚና የተጫወተ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ መሆኑን በቅርብ የምናውቀው ሁሉ መመስከር እንችላለን።

በተለይ ብዙዎች ፖለቲካን የግልና የቡድን ጥቅም ማራመጃ፣ ሴራ መጎንጎኛ በሚያደርጉበት በዚህ ጠልፎ የመጣጣል ዘመን የራሱና የቤተሰቡን ጉዳይ ወደ ጎን ትቶ ህዝብን ለማገልገል ከልቡ የሚተጋ እንደ ነአምን አይነት ሰው በጣት የሚቆጠር ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።

ነአምን ለህሊና ያደረ ሰው ነው። ለነአምን ስንብት ዋና ምክንያት የሆነው ህይወታቸውን ለትግሉ ገብረው ግንባራቸውን ለጥይት ሰጥተው በረሃ ወርደው መከራን የተቀበሉ ታጋዮችን መልሶ ለማቋቋም በድርጅቱም ይሁን በመንግስት በቂ ትኩረት አለማግኘቱ እንቅልፍ ስለነሳው መሆኑን በጻፈው ደብዳቤው ግልጽ አድርጓል።

የቀድሞ የድርጅቱ ደጋፊ እንደነበረና አሁን ደግሞ እንደ ታዛቢ አስተያየት ለመስጠት ያህል ጉዳዩ በድርጅቱ ውስጥ ያለውን የአመራር ክፍተት የሚያሳይ አንድ እውነታ ነው። በወረታ ካምፕ እንዲገቡ የተደረጉና ከካምፕ ውጭ ሆነው ጉዳያቸውን የሚከታተሉ የድርጅቱ የቀድሞ ታጣቂዎች በድርጅቱና በአመራሩ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ማሰማት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። እነዚህ ታጋዮች ድርጅታችን ተጠቅሞ ጣለን የሚል ቅሬታ ሲያሰሙ አላየንም አልሰማንም ማለት ለማንም የማያዋጣ የህሊና ሸክም መሆኑ ብዙም አያጠያይቅም።

በተለይ ድርጅቱ እራሱን አፍርሶ ከሌሎች ጋር በጣምራ ለስልጣን የሚወዳደር የፖለቲካ ፓርቲ ከመሆኑ በፊት በግልጽ እራሱን ገምግሞ የተሻለ አሰላለፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። በተለይም የዜጋ ፖለቲካ እየሰበኩ የሴራ ፖለቲካ የሚያራምዱ አንዳንድ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አባላት ጥፋት እያደረሱና ድርጅቱ እምነት እያጣ እንዲሄድ እያደረጉት መሆኑን የምናውቅ እናውቃለን። በስብከትና ተግባር መሃል ክፍተት መኖሩ ጊዜ ጠብቆ ትልቅ ችግር መፍጠሩ አይቀሬ ነው።

ለማንኛውም የነአምን ስንብት ዋና ምክንያቶችን ድርጅቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት ይጠበቅበታል። ችሮታ ከቤት ይጀምራል ይባላል (Charity starts at home.)። አርበኝነት ያለ አርበኞቹ ከንቱ ጨዋታ ነው።”

ጋዜጠኛ አበበ ገላው

1 COMMENT

  1. ያሳዝናል እንደ እፃን ልጅ ስትነታረኩ ማየት ! ተዋርዳችሁ
    እኛንም አዋረዳችሁ። የወያኔ መሣቂያ አረጋችሁን!!!
    አሁንም ሌላ ነገር ሳትዘበራርቁ እዛው እራሳችሁ ፍቱት
    አለበለዚያ ብር ተበድሮኝ አልመለስም : ሚስቴን ጠቃቅሶ
    ነበር የምትሉ ነው የሚመስለው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here