Home News and Views አሜሪካ የግድቡ ውሃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት ስምምነት መፈረም አለበት አለች

አሜሪካ የግድቡ ውሃ ሙሌት ከመጀመሩ በፊት ስምምነት መፈረም አለበት አለች

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በውሃ የመሙላትና የሙከራ ሥራ ከመጀመሩ በፊት በአገራቱ መካከል ስምምነት መፈረም እንዳለበት አሜሪካ አርብ ለሊት ባወጣችው መግለጫ አመለከተች።

የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳለው ቀደም ሲል የነበረውና ግንባታው በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት እንዳይደርስ በሚለው የመርህ ስምምነት መሰረት “ግድቡን በውሃ የመሙላትና ሥራውን የመሞከር ሂደት ስምምነት ሳይደረግ መከናወን የለበትም” ብሏል።

የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስቴቨን ምኑቺን ባወጡት መግለጫ ላይ እንዳሉት ከዚህ በፊት በነበሩ ስምምነቶች መሰረት ግድቡን በውሃ የመሙላቱ ሥራ ከመጀመሩ በፊት በአገራቱ መካከል ስምምነት መፈረም አለበት።

ለዚህም በተፋሰሱ አገራት መካከል የተጀመረው ድርድር በቶሎ መጠናቀቅ እንዳለበት የሚኒስትሩ መግለጫ አመልክቶ፣ ግብጽ ስምምነቱን ለመፈረም ያሳየችውን ዝግጁነት አድንቋል።

ጨምሮም በኢትዮጵያ በኩል በጉዳዩ ላይ እየተካሄደ ያለውን ብሔራዊ ምክክር መግለጫው እንደሚረዳ በማመልከት ምክክሩ በቶሎ ተጠናቅቆ የድርድር ሂደቱን በማጠናቀቅ በተቻለ ፍጥነት ስምምነቱ እንዲፈረም ፍላጎታቸው መሆኑን የአሜሪካው ባለስልጣን በመስሪያ ቤታቸው በኩል ያወጡት መግለጫ ጠቅሷል።

ግድቡን በውሃ የመሙላት ሥራ ከመጀመሩ በፊት በዓለም አቀፍ ደረጃዎች መሰረት ሁሉም አስፈላጊ የደህንነት እርምጃዎች ተግባራዊ ከመደረጋቸው አንጻር በታችኞቹ ተፋሰስ አገራት ግብጽና ሱዳን ሕዝብ ዘንድ ያለውን ስጋት እንደሚገነዘቡ አመልክቷል።

የካቲት 19 እና 20 ዋሽንግተን ላይ በሚደረግ ስምምነት ይጠናቀቃል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ውይይት ኢትዮጵያ እያደረኩት ያለው አገራዊ ውይይትን ስላላጠናቀቅኩ መሳተፍ አልችልም ስትል ረቡዕ ዕለት በማሳወቋ ሳይካሄድ መቅረቱ ይታወሳል።

በመግለጫው ላይ የአሜሪካው የገንዝብ ሚኒስትር ቴቨን ምኑቺን ከግብጽና ከሱዳን የውጭ ጉዳይና የውሃ ሃብት ሚኒስትሮች ጋር የተናጠልና የሁለትዮሽ ውይይት ማድረጋቸውም ተመልክቷል።

ለወራት በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲካሄድ የነበረው ድርድር በቶሎ መቋጫ እንዲያገኝ እንደምትፈልግ አሜሪካ በመግለጫው አጽንኦት አስታውቃች።

አሜሪካ ሶስቱ አገራት ስምምነት እስኪፈራረሙ ድረስ ከህዳሴው ግድብ ድርድር ጋር በተያያዘ ተሳትፎዋ እንደሚቀጥልም ያረጋግጣል የገንዘብ ሚኒስቴሩ መግለጫ።

አሜሪካ በሶስቱ አገራት የህግና የቴክኒክ ቡድኖች የቀረቡ ሃሳቦችን መሰረት በማድረግ የስምምነት ሰነዱ እንዲዘጋጅ ነገሮችን ስታሳልጥ እንደነበር ፤ ዓለም ባንክ ደግሞ በስምምነቱ ሰነድ የቴክኒክ ጉዳዮች ዙሪያ ግብአት ማድረጉንም መግለጫው ያትታል።

ኢትዮጵያ ባልተሳተፈችበት የዋሽንግተኑ መድረክ ሱዳን እና ግብፅ በተናጠል ከአሜሪካና ዓለምባንክ ጋር ባደረጉት ውይይት ስምምነቱን በሚመለከት ሃሳባቸውን አንፀባርቀዋል።

አሜሪካ ባለፉት አራት ወራት የተደረጉ ተግባራት በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያሉ ሁሉንም ጉዳዮች የሚዳስስ ስምምነት እንዲደረግ የሚያስችል ውጤት አምጥተዋል ብላ እንደምታምንም በመግለጫው ተገልጿል።

በአሜሪካ ዋሽንግትን ዲሲ ለሁለት ቀናት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ላይ በሚደረገው ድርድር ላይ ኢትዮጵያ እንደማትካፈል የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር።

ሚኒስቴሩ የአሜሪካ መንግሥትና የአለም ባንክ በታዛቢነት በሚገኙበት የካቲት 19 እና 20/2012 ዓ.ም ከሱዳን እና ግብጽ ጋር ሊካሂድ በታቀደው ቀጣይ የሦስትዮሽ ድርድር ላይ ኢትዮጵያ እንደማትገኝ ያስታወቀው፣ ተደራዳሪ ቡድኑ በአገር ውስጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ውይይት ባለማጠናቀቁ መሆኑን በመግለጽ ነበር።

ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙርያ የሚያደርጉትን ድርድር የአሜሪካ መንግሥት ቀደሞ በታዛቢነት አሁን ደግሞ በአደራዳሪነት መግባቱን በመቃወም በአሜሪካ፣ ዋሽንግተን ዲሲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሰላማዊ ሰልፍ ማካሄዳቸው ይታወቃል።

ምንጭ ቢቢሲ አማርኛ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here