Home News and Views የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰራተኛ መብት ተሟጋቹንና የማሕበሩን ሊቀመንበር ከስራ አባረረ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰራተኛ መብት ተሟጋቹንና የማሕበሩን ሊቀመንበር ከስራ አባረረ

የተከበራችሁ ሰራተኞች ፣ የማህበራችን አባላትና አጋሮች፤ ማህበራችን እየተጠናከረ እና ለሰራተኛው ድምፅ እየሆነ በብዙ ጫናዎች ውስጥ (በተለይም በአስተዳደሩ የሚፈፀሙ) ተባብረን እየተጓዝን እንገኛለን።
ብዙ የማህበራችን ጉዳዮች በህግ የተያዙና ጫፍላይ የደረሱ መሆናቸው እና ይህ ወረርሽኝ መከሰቱ ጥቂት የጊዜ ክፍተት ብቻ እንጂ ሌላ የሚፈጥረው ነገር እንደማይኖር እንድታውቁ እንወዳለን።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የማህበራችን ሊቀመንበር ካፒቴን የሺዋስ ፈንታሁንን አስተዳደሩ ከስራ ውጭ አድርጎ ደሞዙ ከተቋረጠ ወራትን ማስቆጠሩ ይታወቃል። ለዚህም ክስ ተመስርቶ በሒደት ላይ በሚገኝበት ሁኔታ ደግሞ March 31, 2020 በተፃፈ ደብዳቤ ካፒቴን የሺዋስ የስራ ውሉ እንደተቋረጠ የሚገልፅ ደብዳቤ ተሰጥቶታል። ይሕ የሚጠበቅ እና የተለመደ ስትራቴጂ ስለሆነ በማህበራችን እንቅስቃሴ ላይ ነዳጅ ይጨምር ይሆን እንደሆነ እንጂ እምብዛም የሚፈጥረው ተፅእኖ እንደማይኖር ሊታወቅ ይገባል።
ይህ የማህበራችን እንቅስቃሴ ከእውነት ፣ ከፍትህ እና ከህግ የበላይነት ጥማት የመነጨ እንጂ በአንድ ወይም በጥቂት ሰዎች የጀመረ እና የሚቀጥል እንዳልሆነ መታወቅ አለበት።
ይህንን ሕገወጥ ተግባር እንደማህበር እናወግዛለን ፤ ደግሞም እንታገለዋለን በተለይም በአለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን ይህንን የብዙዎችን ሕይወት የሚቀጥፍ ወረርሽኝ ያመጣውን ሁለገብ ተፅእኖ ተገን በማድረግ የተደረገ መሆኑ ደግሞ ጉዳዩን አስፀያፊ ያደርገዋል።
ውድ ሰራተኞች ካፒቴን የሽዋስም ሆነ ማህበራችን እንደነበረ እና እየጨመረ የሚቀጥል ሲሆን ይሕ በማህበራችን ላይ ከቅድመ ምስረታ ጀምሮ እየተደረገ ያለው ጥቃት ሳያወዛግበን የፍትህ ግባችንን ለመምታት መታገል እንዳለብን መልእክታችንን እናስተላልፋለን።
ሁል ግዜም ቢሆን ለውጥ እና ልዩነት እንደሚፈጥሩ የሚታመንባቸው እንቅስቃሴዎች በጊዜው ባለ ስርዓት ወይም አስተሳሰብ ጫና ወይም ጥቃት እንደሚደርስባቸው እሙን ነው። በዚህ ጥቃት እና ጫና ውስጥ አልፈው ሲወጡ ግን ለውጥ የሚፈጥሩ እንደሚሆኑ ግን ግልፅ ነው።
መሪ ተብለው የሚታሰቡ ሰዎችን ማጥቃት ያልጠበቅነው እና የማናውቀው ስትራቴጂ ባለመሆኑ በዚህ ምክንያት የሚመጣ አሉታዊ ተፅእኖ አይኖርም።
በሰራተኛ እና በአሰሪው መካከል ያለው መስተጋብር ህግን መሰረት ባደረገ ውይይት እና በድርድር መሆን ሲገባው ፤ አስተዳደሩ ይሕን ያህል ርቀት ባለው ጥላቻ ማህበራችንን የሚያጠቃበት ምክንያት እስካሁን እንቆቅልሽ ነው።
ያም ቢሆን ሁሉም የሀገር ዜጋ ስለሆነ አሰሪው ያለምክንያት አፈናቃይ ሰራተኛውም ያለምንም ምክንያት ተፈናቃይ የሚሆንበት ዘመን አብቅቶ፤ አስተዳደሩ ያለምክንያት ማህበርን መሰረት በማድረግ ብቻ ሰራተኞችን ከማጥቃት ተመልሶ መግባባት፤ መቀራረብ እና ውይይት አስፈላጊ ነው ብሎ እስከሚያምን እና ህግን እስኪያከብር ፤ ህግን የተከተለውን አካሔዳችንን የምንቀጥል ይሆናል!

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here