Home News and Views የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ ይፋ ሆነ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ ይፋ ሆነ

 

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል፣ ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ ይፋ አደረገ።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቢተ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የአዋጁን ማስፈጸሚያ ደንብ አጠቃላይ ይዘት በሚመለከት ዛሬ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 93 ንኡስ አንቀፅ 4 መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማስፈጸሚያ ደንብ ማውጣት እንዳለበት ይደነግጋል።

በዚህም መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ያወጣውን ማስፈጸሚያ ደንብ አጠቃላይ ዝርዝር በሚመለከት
ወ/ሮ አዳነች አብራርተዋል።

ማስፈጸሚያ ደንቡ አራት ዋና፣ ዋና ፍሎች ያሉት ሲሆን፣ ይኸውም ክልከላን የሚያስቀምጥ፣ ግዴታዎችን የሚጥል፣ የአስፈጻሚ አካላትን ድርሻ እንዲሁም ልዩ፣ ልዩ ድንጋጌዎችን የያዘ መሆኑ ተጠቅሷል።

ክልከላን በሚመለከት ማንኛውም ሃይማኖታዊም ሆኑ ፖለቲካዊ ስብሰባዎች፣ እድር፣ ደቦ፣ እቁብ እና ሌሎችም ከአራት ሰው በላይ የሚያሳትፉ ስብሰባዎች ክልክል ናቸው።

አራት ሰዎችም ቢሆኑ አቀማመጣቸው ሁለት የአዋቂ ሰው እርምጃ አካላዊ ርቀትን የጠበቀ መሆን እንዳለበት ዐቃቤ ህጓ አብራርተዋል።

ቀብር እና ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮች ሲኖሩ ግን እየታዩ ሊፈቀዱ የሚችሉበት አሠራር መኖሩን ጠቁመዋል።

ታራሚዎች ከጠበቆቻቸው ጋር አስፈላጊው ጥንቃቄ ተደርጎ እንዲገናኙ የሚፈቀድ ቢሆንም ጥየቃ ለሚሄዱ ሰዎች ግን የማይፈቀድ መሆኑ ተገልጿል።

በፖሊስ የተያዙ እስረኞችንም ስንቅ ከማቀበል በስተቀር መገናኘት የተከለከለ መሆኑን አስረድተዋል።

በድንበር አካባቢም ከካርጎ እንዲሁም የደረቅ እና ፈሳሽ ጭነት አገልግሎቶች በስተቀር ሌሎች እንቅስቃሴዎች ዝግ ተደርገዋል።

የቤት ተከራዮች በራሳቸው ፍላጎት ካልወጡ በስተቀር ማስወጣት እና ኪራይም መጨመር በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተከልክሏል።

ሠራተኞችን መቀነስ እና የሥራ ቅጥር ውል ማቋረጥም መከልከሉን ጠቅላይ ዐቃቢተ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አብራርተዋል።

በዚህ ደንብ መሠረት ተማሪዎች እና መምህራን በኦንላይን ካልሆነ በአካል እንዲገናኙ አይፈቀድም።

ስፖርታዊ ጨዋታዎች፣ የሕፃናትም ይሁን የሌሎች መጫወቻ ስፍራዎች እንዲሁም የእጅ መጨባበጥ ሰላምታ የተከለከለ ነው።

በትራንስፖርት ዘርፍም አገር አቋራጭ አውቶቡስ ካለው ወንበር ከ50 በመቶ በላይ ተሳፋሪ መጫን የተከለከለ ነው፡፡

ምንጭ፡- ኢዜአ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here