Home News and Views ግልፅ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ መንግሥት /ዶር ተወልደ ገ/እግዚአብሄር/

ግልፅ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ መንግሥት /ዶር ተወልደ ገ/እግዚአብሄር/

ስሜ ተወልደብርሃን ገብረ እግዚአብሔር ይባላል። የካቲት 12/2012 ዓ.ም. ሰማንያ ዓመት ሞልቶኛል።

በብሪታንያ ሃገር ሰሜናዊ ዌልስ ውስጥ በሚገኘው ባንጎር ዩኒቨርሲቲ ነው የእፅዋት ስነምህዳር (ፕላንት ኤኮሎጂ)ን በዶክትሬት ዲግሪ ትምህርቴን ያጠናሁት።

ከዚህ ችሎታዬ በመነሳት ነው በሃገሬ መዲና በአዲስ አበባ የፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ሥራ ኣስኪያጅ በመሆን ሃገሬን ያገለገልኩት። ጥናትና ምርምሬን በጠቀስኩት ስነ ህይወት ዙሪያ በማድረጌም ነው የደህንነተ ህይወትን እና የዘረመል ምህንድስናን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ድርድሮችን ለማድረግ የኢትጵያን ልዑካን ስመራ የነበረው።

በደህንነተ ህይወት ላይ የተካሄዱት ዓለም አቀፋዊ ድርድሮች በውጤታቸው ልውጥ ህያዋን በማህበረሰብ፣ በኢኮኖሚና በአካባቢ ላይ የሚያደርሱዋቸውን ተፅንዖዎች የፈተሹ ነበሩ። ይህ ፍተሻ የእፀዋትም ሆኑ የእንስሳት ልውጥ ህያዋን ሊያመጡ የሚችሉዋቸውን አዲስና የማይጠበቁ ኣከባቢያዊ አደጋዎችን መርምሯል። ፍተሻው በዘረመል ምህንድስና ዘሮች ወደ ሌሎች ህያዋን የሚሸጋገሩበትን ሁኔታ እንዲሁም የተፈጠሩት ልውጥ ህያዋን ሊያመጡ የሚችሉትን መዘዝ በአንክሮ ተመልክቶአል።

በዘረ መል ምህንድስና ልውጥ ህያዋንን የመፍጠር ሂደቱ በተለየ ጥብቅ ከባቢ የሚካሄድ ቢሆንና ሊያመጣ የሚችለውም ተፅዕኖ በደንብ ተጠንቶ ለየትኞቹም ህያዋን ጉዳት የማያመጣ መሆኑ ቢረጋገጥ ኖሮ ልውጥ ህያዋንን በመፍጠር ሂደት ሊኖር ስለሚችለው መዘዝ መነጋገሩ በቀረልን ነበር። ልውጥ ህያዋኑም ለሰውም ሆነ ለእንስሳት እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት ይውሉ ዘንድ ፈቃድ ይሰጣቸውም ነበር።

የካርታኼና የደህንነተ ህይወት ፕሮቶኮል ብዝሃ ህይወትን የሚጠብቅ ዓለም አቀፍ ስምምነት ነው። ዓላማውም በዘመናዊ ዘረ መል ምህንድስና የሚሰሩት ልውጥ ህያዋን ጉዳት በማያመጣ መልኩ በጥንቃቄ እንዲያዙ፣ እንዲጓጓዙና በጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረግ ነው።

ይህም በብዝሃ ህይወት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይኖር ከመከላከሉ ባሻገር የሰው ልጅ ጤናንም ያረጋግጣል። እስከ ዛሬ ድረስ ኢትዮጵያን ጨምሮ የዓለማችን 172 ሀገራት የካርታኼናን የደህንነተ ህይወት ፕሮቶኮል አፅድቀውታል።

የካርታኼና የደህንነተ ህይወት ፕሮቶኮል በልውጥ ህያዋን የሚጠቀሙ አመራረቶች በተፈጥሮ የሚበቅሉ አዝርዕትንም ሆነ የተፈጥሮን ስርዓት ይዘው የሚራቡ የቤትና የዱር እንስሳትን፥ እንዲሁም ሌሎች የእርሻ መንገዶችን እንዳይበክል ጥንቃቄ ይደረግ ዘንድ መስፈርት አስቀምጦአል።

የካርታኼናው ፕሮቶኮል በተጨማሪም በዘረመል ምህንድስና በተፈበረኩ ምርቶች እሽግ ላይ ልውጥ ህያዋን መሆናቸውን የሚያመለክት ማስታወቂያ መለጥፍ እንደሚያስፈልግ፤ ያም በተፈጥሮ በሚበቅሉና በሚራቡ ምርቶች ብቻ መጠቀምን ለሚፈልጉቱ ምርጫ ሊሰጣቸው እንደሚችል ያትታል።

ይህም መሰረታዊ የማህበራዊ መብት ነው። ማን ምን ማብቀል እንደሚፈልግ፣ ምን መብላት እንደሚፈልግ፣ ምን መልበስና ከተፈጥሮአዊ ከባቢ ጋር ምንአይነት ግንኙነት ሊኖረው እንደሚፈልግ የመምረጥ መብት ነው።

ልውጥ ህያዋን ወደ ከባቢው አንድ ጊዜ ከገቡ እና በከባቢው ውስጥ የሚኖሩትን ህይወቶች ከለወጡ በኋላ ሁሉን ነገር መልሰን በተፈጥሮ ወደ ነበረበት መመለስ ከቶውኑ አይቻለንም። በመሆኑም መሠረታዊ የመምረጥ መብትን ጨርሶ ይሰርዘዋል።

[በተለያዩ ጊዜአትና ቦታዎች] የደህንነተ ህይወትን በተመለከተ የተደራደሩ የኢትዮጵያ ልዑካንን መርቻለሁ። ድርድሩ ሲጀመር የአፍሪካ የተደራዳሪዎች ቡድን አባላት እኔን ዋነኛ ተደራዳሪያቸው እንድሆን መረጡኝ። ያንን ተከትሎም የአዳጊ ሀገሮች የተደራዳሪዎች ቡድን ቀዳሚ ተደራዳሪያቸው አደረጉኝ በመጨረሻም ራሱን የማያሚ ቡድን ብሎ ከሚጠራው ስብስብ በቀር ሁሉም የዓለም ተደራዳሪዎች ዋና ተደራዳሪያቸው እንድሆን ጠየቁኝ። የማያሚ ቡድን አሜሪካን፣ ካናዳን፣ አርጀንቲናን፣ ቺሊን እና ኡሩጓይን የያዘ ቡድን ነው።

ድርድሩ ኮሎምቢያ ውስጥ በምትገኘው ካርታኼና በተባለች ከተማ ውስጥ ተጠናቀቀ። እናም በደህንነተ ህይወት ላይ ስምምነት የተደረሰበት ሰነድ የካርታኼና የደህንነተ ህይወት ፕሮቶኮል ተሰኘ።

አሁን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ መንግስት በኢትዮጵያ ልውጥ ህያዋን የሆኑ አዝርዕቶች እንዲመረቱ መፍቀዱን በዜና አነበብሁ፥ ሰማሁ።

ብዙ ነገሮች ያሳስቡኛል። ከሚያሳስቡኝ ነገሮች መካከልም 130 ሄክታር የሚሸፍነው የዘረ መል ጥናት በሌሎች አጎራባች ከባቢዎች ላይ አደጋ የማይደቅን ጥብቅ እርሻ የመሆን ያለመሆኑ ጉዳይ እና እነዚህ ጉዳዮች የደህንነተ ህይወትን ዓለም አቀፍ ፕሮቶኮል ባማከለ ሁኔታ እንዴት እየተሄደባቸው ነው የሚሉት ይገኙባቸዋል። ፕሮቶኮሉ በሀገራችንም የፀደቀና ዝርዝር አሠራሮቹም በኢትዮጵያ የደህንነተ ህይወት ማዕቀፍ በአካባቢ ጉዳዮች፥ በደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ሕግ፥ ፖሊሲና መስፈርቶች የካቲት 2011 ዓ.ም. የተቀረፀለት ነው።

እነዚህ የሕግ ሂደቶች ካልተተገበሩ አሁን በሚደረገው የልውጥ ህያዋን ምርት ዙሪያ እጃቸውን ያስገቡት አካላት የካቲት 2011 ዓ.ም. የወጣውን ፕሮቶኮል እና በአዋጅ ቁጥር 655/2009 በነጋሪት ጋዜጣ ወጥቶ በቁጥር 896/2015 የተሻሻለውን ሕግ እየተላለፉ ነው።

ይህም ኢትዮጵያ ይፋዊ ባልሆነ ሁኔታ ከካርታኼናው የደህንነተ ህይወት ፕሮቶኮል ራስዋን እንዳገለለች ሊያስቆጥራት ይችላል።

እኔ እስከማውቀው እስከአሁን ድረስ ኢትዮጵያ ሕግጋቱን ጠብቃ ቆይታለች፤ አስፈላጊ ሆና ባገኘችውም ጊዜ ሕጎችዋን አሻሽላለች እንጂ በይፋ ከካርቴሄናው የደህንነተ ህይወት ፕሮቶኮል አልወጣችም።

ጡረተኛ እንደመሆኔና 80 ዓመት እንዳለፈው አንድ አረጋዊ ከኢትዮጵያ ፌደራላዊ መንግስት ጋር የቀጥታ ግንኙነት የለኝም። ስለሆነም ኢትዮጵያ የካርቴሄናውን የደህንነተ ህይወት ፕሮቶኮልን ሕጋዊ ትግበራ ገሸሽ እያደረገችው ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ጉዳይ የማጣራበት መንገድ የለኝም።

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት የካርታኼናውን የደህንነተ ህይወት ፕሮቶኮል ሕጋዊ ትግበራ ገሸሽ እያደረገው ከሆነ፤ ሀገሪቱ ዓለምአቀፍ ስምምነትን እየጣሰች መሆኑ ግልፅ ይሆናል።

ይህ እንዲሆን ሊፈቀድለት አይገባም። እናም የትውልዱ ወጣቶች በሚችሉት መንገድ ሁሉ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ዘንድ አሳስባለሁ። ይህን የምልበት ምክንያትም የካርታኼናውን የደህንነተ ህይወት ስምምነት ጨምሮ የፀደቁትን ዓለምአቀፋዊ ሕጎች በይፋ ወጥቼባቸዋለሁ ሳይሉ መጣስ በመሆኑ ነው። በሀገራችንም ሆነ በአፍሪካ አህጉር ብሎም የማያሚ ቡድን ከሚባለውና አምስት ሀገራትን ብቻ ካቀፈው ተቃዋሚ ቡድን በቀር በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የሕጋዊነት መሰረት ማናጋትም በመሆኑ ነው።

በመጨረሻም የየሀገራቸው መንግስታት የደህንነተ ህይወት ስምምነቶችን ጨምሮ ዓለምአቀፍ ሕግጋትን በዓለም ዙሪያ አክብረው መተግበራቸውን እንዲቀጥሉ ይወተውቱ ዘንድ፤ የአፍሪካን እና የቀሪውን ዓለም ወጣቶች አበክሬ አሳስባለሁ።

(ዶ/ር ተወልደብርሃን ገ/እግዚአብሔር

 

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here