የፍቄ_ነገር…
ስለ ፍቄ ባሰብኩ ቁጥር ልገልፀው የማልችለው ህመም ይሰማኛል:: ህልፈቱን አምኖ መቀበል ከመቸገሬ የተነሳ ቅድስት ስላሴ ቤተክርስቲያን ስገባ እንኳን ሀውልቱን ላለማየት ከራሴ ጋር የማደርገው ሙግት ይገርመኛል:: ድምፁ; ሳቁ; ጨዋታው ሁሌም በጆሮዬ ይሰማኛል:: ለመሸሽ ብሞክርም ከእውነታው ጋር ስጋፈጥ ግን ቃላት በሌለው ለቅሶ ፊቴ ይታጠባል::
“ፋኖሴ ተይ እንጂ” ብሎ ሲያፅናናኝ ይታየኛል::
ሲያቆላምጠኝ ( ፋኖስ; መብራት) እያለ ይጠራኝ ነበር::

በጣም ያውቀኛል! ስደሰት ስከፋ ሌላው ቢቀር ቦርሳዬ ውስጥ እንኳን ስንት ብር እንዳለ ያውቃል::
የሰዎችን የተሳሳተ ስእል ለማጥራት ይሟገትልኛል::
የሙያ አባት; መካሪ; ጏደኛ…..ብዙ ነው:: ይሄን ሁሉ የሚሆንላችሁን ሰው ማጣት ምን ያህል ልብ እንደሚሰብር ታውቁታላችሁ::

ግን ደግሞ ከህልፈቱ በላይ ውስጤን ያሳመመው ለህክምናው በተሰበሰበ ገንዘብ ጉዳይ የተነሳው እሰጥ አገባ ነበር:: ባከበረን በወደደን አምኖ መቀነቱን ፈቶ በረዳን ህዝብ ፊት በዛ መልክ መቅረብ እፍረት ነበር ለኔ::

ውስጤ እያረረ እንኳን አንድም ቀን በዚህ ጉዳይ ትንፍሽ ብዬ አላውቅም:: አንድም ፍቄን ማሳነስ እንዳይሆንብኝ! አንድም ቢዘገይም እንኳን የሚቀድመው የሌለ አምላክ እውነቱን ይፈርዳል ብዬ ለሱ ስለተውኩት::

ቀኑ ደርሶ ፍርድ ቤት ለቤተሰቡ መወሰኑን ወንድሙ ግርማ ተ/ማርያም ደውሎ ሲነግረኝ ተመስገን አልኩ:: አበቃ!
ከዚህ በኃላ የፍቄ ስም ያለአግባብ አይነሳም::

ሀገር ውስጥ በሶስት ሰዎች ፊርማ በስማችን የተሰበሰበውን ገንዘብ በሞዴል 85 በፍርድ ቤት በአደራ እንዲቀመጥ ፕሮሰሱን ስጀምር ከጎኔ ይቆማሉ ያልኳቸው ሁሉ ባልገባኝ ምክንያት ሲንሸራተቱ የቤተሰቡ ጠበቃ አቶ ጳውሎስ በእጅጉ እረድቶኛልና በዚህ አጋጣሚ ምስጋናዬ ይድረስህ::

ግርማም ባለቤቱ ወ/ሮ ሙሉም ለምስጋና ለምርቃት ቢደውሉም ምንም ያደረኩት ነገር ስለሌለ ምስጋናው ለረዳን ኩላሊቱን እንኳን ለመስጠት ላልሳሳው ለኢትዮጲያ ህዝብ ይሁንልኝ👏

ሁሉም ነገር እንዲህ ሊያልፍ ስንቱን ሰው ታዘብኩት! ከግምቴ አሳነስኩት! ተቀየምኩ! አለቀስኩ! በአንዳንዶች የማስመሰል ድራማ ቆሰልኩ! ( እንኳን ሰው ፊት በእግዚአብሔር ቤት እንኳን በውሸት ለመተወን ብቃት ያላቸው አሉና)
ለማይረባ የጥቅም ትስስር ህሊናቸውን የሸቀጡ ሰው መሳይ በሸንጎ!
እመኑኝ ጊዜ ይገልጣቸዋል!!!

ግን ዝም አልኩ::
ዝምታ ሞኝነት ሳይሆን የብልሆች ቋንቋ ነው!
እኛ ዝም ስንል እግዚአብሔር ይናገራልና::
አሁንም ለዘለአለም እሱ ብቻ ይናገር!

ፍቄ አንዴ ቀና ብለህ የሆነውን ሁሉ ብታይ ምንኛ በወደድኩ!
ነፍስህን ከደጋጎቹ ጎን ያኑረው🙏

1 COMMENT

 1. እየኖሩ ሞተው ሳይኖሩ የሞቱ ስንቶች አሉ ቆመው ኑረናል የሚሉ
  ጥቂቱ ለሃገር ለወገን ሲሰራ ይበልጡ ሲያላግጥ ሲሰራ ጎተራ
  ለማይኖረው ዓለም ምቾቱን ሲያመቻች አይተናል በአይናችን
  በዘመናት መሃል አልፎ|2| ብቅ ያሉ
  ብርቅዬ ስጦታ ለህዝብ ያካፈሉ
  ምንም ሳይታሰብ ጥለውን የሄድ
  ስንት አሉ በነበር እኛን ያፈዘዙ
  ሳንጠግባቸው አልፈው ትዝታ የሆኑ።
  ባንጻሩ ገምተን ይሞታሉ ብለን
  ከፈን መገነዣ ገዝተን አዘጋጅተን
  ውጪ ነፍስ ግቢ ነፈስ ሲሉ ከጎን ቆመን
  ምንም ሳይታሰብ ከሞት አፋፍ ወተው
  ይኽው እናያለን ሞትን አሸንፈው።
  ሊሞት የሚገባው ቆሞ ሲንገዳገድ
  መሞት የሌለበት ያለጊዜው ሲሄድ
  ዓለም እንደዚህ ናት ትርጉም የጠፋባት
  መቻል ነው ሃዘንን ሌላ ጥበብ የለም
  መኖርን ለመኖር አብሮ መርመስመስ ነው።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here