Home News and Views ንብረት እያወደሙ ኢንቨስትመንት መሳብ የማይታሰብ ነው – (ክቡር ገና)

ንብረት እያወደሙ ኢንቨስትመንት መሳብ የማይታሰብ ነው – (ክቡር ገና)

ሲራራ – Sirara

ሰላም ለአንድ አገር የኢንቨስትመንት መስፋፋትም ሆነ ለዜጎች የቀን ተቀን እንቅስቃሴና ኑሮ ትልቅ ዋጋ ያለው ነገር ነው፡፡ ይህ ጉዳይ ብዙዎችን የሚያስማማ እና ጥያቄም የማይነሳበት ጉዳይ ነው፡፡ በሰላም ረገድ በአገራችን ባለፉት ወራት የተወሰኑ ለውጦች መታየት ጀምረው ነበር፡፡ ሆኖም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ኀይሎች መሀከል የሚታዩት ስር የሰደዱ የእርስ በርስ መጠራጠሮችና አለመግባባቶች መፍትሔ ባለማግኘታቸው ምክንያት አሁንም አገሪቱንና ዜጎቿን ወድ ዋጋ የሚያስከፍሉ ግጭቶችንና ክስተቶችን እየታዘብን ነው፡፡

ግጭትና አለመረጋጋት ትልቅ የኢንቨስትመንት ፈተና ነው፡፡ ከግጭት በኋላ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ብዙ ጊዜ ይፈጃል፡፡ ኢንቨስትመንት በጣም ስስ ነገር ነው፡፡ እንክብካቤ ይፈልጋል፡፡ ሰላም እና መረጋጋት መጣ በተባለ ማግስት በአንድ ጊዜ ኢንቨስትመንት ይመጣል ማለት አይቻልም፡፡ ለዚህ ነው ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስፈልገው፡፡
ከሰሞኑ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢ የተፈጠረው ዓይነት ቀውስ፣ በተለይም በኢንቨስትመንት ላይ ያተኮረ ጥፋት እና ውድመት እያንሰራራ ያለውን የኢንቨስትመንት ዘርፍ ወደኋላ እየጎተተው መሆኑን መመልከት እንችላለን፡፡ ይህ ዓይነት ሁኔታ በቀጣይ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ለሚደረገው ምርጫ ስጋት መፍጠሩ እንዳለ ሆኖ፣ እንዲህ ያለው ክስተት ለአገሪቱ ቀጣይ ህልውናም ስጋት መደቀኑ የማይቀር ነው፡፡
እንዲህ ያሉ ውድመቶች ለወደፊቱም ቢሆን እንዳይደርሱ መከላከል፤ ጉዳት የደረሰባቸው ተቋማትም ዳግም እንዲቋቋሙ ማድረግ ለነገ የማይባል ሥራ መሆን ይገባዋል፡፡ በርካታ ሆቴሎች፣ ትምህርት ቤቶች፣ የንግድ ተቋማት ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ብዙ ንብረት ወድሟል፡፡ ስለሆነም መንግሥት እነዚህን ተቋማት ዳግም ለማቋቋም ትልቅ ሥራ መሥራት ይገባዋል፡፡ እነዚህን ተቋማት መልሶ ማቋቋም የሚጠቅመው እነሱን ብቻ ሳይሆን የአካባቢውን ነዋሪም ነው፡፡ ሌላ ኢንቨስትመንቶች በመተማመን መልክ እንዲመጡ ሊያደርጋቸው የሚችለውም እንዲህ ዓይነት መንግሥታዊ ጥረት ሲኖር ነው፡፡
የወደመውን ሀብት መልሶ እንዲተካ መደገፍ ለሌላውም አልሚ ዋስትና እንደመስጠት ነው የሚቆጠረው፡፡ ለወደመው ንብረት በቂ ካሳ ሳይሰጥ፣ የተቃጠለው ተቃጠለ በሚል መንግሥት ዝምታን ከመረጠ ግን መዋዕለንዋዩን ለማፍሰስ የሚመጣው ባለሀብት ወደኋላ እንደሚያሸሽ ግልጽ ነው፡፡ ስለዚህ ዛሬ ላይ የወደሙት ንብረቶች የሚተኩበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ርብርብ መደረግ አለበት፡፡ ይህ ርብርብና መልሶ ማቋቋም ደግሞ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡ ቶሎ ነው መጀመር ያለበት፡፡
የመልሶ ማቋቋም ሥራው እየተሠራም ግን ለዚህ ችግር ምክንያት የሆነው የፖለቲካ መናቆር እና የፖለቲካ ድህነት መቀረፍና መፍትሔ ማግኘት መቻል አለበት፡፡ እየተንከባለለ ሳይፈታ የመጣው የፖለቲካ አለመግባባት ነው ዛሬ ላይ ለደረሰው የንብረት ውድመት ምክንያት የሆነው፡፡ የፖለቲካ አለመግባባቶች በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለባቸው፡፡ ይህ ሲሆን ነው ቀጣይ ኢንቨስትመንቶች ዋስትና የሚያገኙት፡፡ ኢትዮጵያ እጅግ ፈታኝ በሆነ ድህነት ውስጥ የምትገኝ አገር ሆና ሳለ፣ ያገኘቻቸውን ኢንቨስትመንቶች የምታወድም አገር መሆን ከሆነች መቼም ከገባችበት አረንቋ አትወጣም፡፡ ይህ በደንብ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
አዲስ በወጣው የኢንቨስትመንት አዋጅ ላይ በአገሪቱ የሚገኙ ኢንቨስትመንቶች የመንግሥት ጥበቃ እንደሚኖራቸው ተደንግጓል፡፡ በእኔ እምነት ጥበቃ መደረጉ ብቻውን ለባለሀብቱ ዋስትና ይሆናል ብዬ አላስብም፡፡ ያለውን የፖለቲካ ልዩነት በሰላም እና በንግግር መፍታት መቻሉ ነው ዋስትና መሆን የሚችለው፡፡ መንግሥት ምናልባት በቀጣይ በትኩረት ይሠራበታል የሚል እምነት አለኝ፡፡ መሥራትም አለበት፡፡
ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ የደረሱ ጉዳቶች ቀለል ተደረገው ታልፈዋል፡፡ ለዚያም ነው አሁን ላይ በሚታየው መጠን የኢንቨስትመንት ጉዳት እየደረሰ ያለው፡፡ ነገሮች እንዲህ ሳይባባሱ ነው እርምጃዎች መወሰድ የነበረባቸው፡፡ “በእንቁላሌ በቀጣሽኝ” እንደሚባለው በእንቁላሉ ጊዜ እንዲህ ዓይነት ችግሮች መፍትሔ እና አስፈላጊው እርምጃ ቢወሰድባቸው ኖሮ ዛሬ ጉዳቱ በዚህ መጠን ባልጨመረ ነበር፡፡ እንደ አገር ልናፍር ይገባናል፡፡
ይህቺ አገር ኢንቨስትመንት እንድታገኝ በርካታ ማማለያዎችን ይዛ እየተሯሯጠች፣ ያሉት እንዲወድሙ ማድረጉ በቀዳዳ ጆንያ እህል ይዞ ለመሮጥ እንደመሞከር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲፈጠሩ መንግሥት ነው ሰፊውን ሚና መጫወት ያለበት፡፡ ከመንግሥት በቀር በዚህ ጊዜ ሌላ አካልን ተጠያቂ ማድረግ ትክክል ነው ብዬ አላስብም፡፡ ምናልባት የግል ባለሀብቱ የወደመውን ንብረት መልሶ ለማቋቋም በግሉ አስተዋጽዖ ሊያደርግ ይችላል፡፡
መንግሥት በመንግሥትነት ሚናው እና ኀላፊነቱ ዜጎችን ከጉዳት መታደግ መቻል አለበት፡፡ መንግሥት ያስፈለገበት ተቀዳሚ ምክንያትም ይህ ነው፡፡ የዜጎችን በሕይወት የመኖር፣ እንደልብ ተንቀሳቅሶ የመሥራትና ንብረት የማፍራት መብት መጠበቅ የመንግሥት ዋና ተግባር ነው፡፡
በባለሀብቱ ላይ እንዲህ ዓይነት መጠነ-ሰፊ ጉዳት ከደረሰ በኋላ በራስህ ተወጣው የሚባል ነገር ካለ ባለሀብቱ የከሰረውን ከስሮ ትቶ ይሄዳል እንጂ እንደ ሻለቃ ኀይሌ ገብረ ሥላሴ እኔ ራሴ መልሼ እገነባዋለሁ የሚል ባለሀብት ማግኘት በጣም ከባድ ነው፡፡
ከመጀመሪያ ኢትዮጵያ በርካታ የኢንቨስትመንት ማማለያዎችን እያቀረቡ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ከሚጥሩ አገሮች መሀከል የምትጠቀስ አገር ነች፡፡ አገሪቱ በርካታ ማማለያ አቅርባም ኢንቨስትመንቱ በታሰበው መጠን እየመጣ አይደለም፡፡ በዚህ ሰዓት ሁሉም አገር ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ጥረት እያደረገ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከነአሜሪካ ጋር ተወዳድራ ነው መዋዕለ ንዋይ ስባ ለማምጣት ጥረት የምታደርገው፡፡ መዋዕለንዋይ ለመሳብ ያለውን ፈተና እና ውድድር አይቶ መገመት በጣም ቀላል ነው፡፡ በዚህ መሀል በቅርቡ የታየው ዓይነት መጠነ-ሰፊ የንብረት ውድመት ሲደርስ ደግሞ ውድድሩን የማይወጡት ዳገት ያደርገዋል፡፡ ኢንቨስት ለማድረግ የሚፈልገው አካል ሌሎች አማራጮች ስለሚኖሩት ወደዚያ መሄዱ የማይቀር ነው፡፡
ስለዚህ አሁን ያለንበት ሁኔታ በጣም አስቸጋሪ እና አዳዲስ ኢንቨስትመንትን ስቦ ለማምጣት በጣም ብዙ ፈተናዎች ያሉበት ሥራ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ የትኛውም ኢንቨስተር ገንዘቡን ኢትዮጵያ ላይ ለማፍሰስ ሲመጣ መጀመሪያ የሚያየው በአገር ውስጥ ሰላም እና መረጋጋት መኖሩን ነው፡፡ ሰላም ቁልፍ ነገር ነው፡፡
ሰላም እና መረጋጋት አለመኖሩን ትተን፤ የኮቪድ-19ን ተጽዕኖ ትተን በአገሪቱ ያለው እጅግ አሰልቺና አስቸጋሪ ቢሮክራሲያዊ አሠራር የውጭ ኢንቨስትመንት እንዳይመጣ ለማድረግ በቂ ምክንያት ነው፡፡ ነገሮች ተስተካለክዋል ቢባልም መሬት ከማግኘት ጀምሮ ያለው አሠራር ግን ዛሬም በጣም ብዙ ችግሮች ያሉበት ነው፡፡ የመንግሥት የፋይናንስ አቅም ዛሬም ጥያቄ የሚነሳበት ነው፡፡ ትልልቆቹን ድርጅቶች ትተን በአነስተኛ እና መካከለኛ ደረጃ ያሉትን ተቋማት ደግፎ ከማቆየት አንጻር ሰፊ የአቅም ውስንነቶች ናቸው ያሉት፡፡
ለኢንቨስትመንት ምቹ ከባቢን ከመፍጠር አንጻር ከጎረቤት አገር ኬንያ ያነሰ ነገር ነው ያለው፡፡ አገሪቱ በኢንቨስትመንት ሳቢ እና ተመራጭ እንድትሆን ከተፈለገ በቅድሚያ የተቋማትን የተንዛዛ ቢሮክራሲ ማስተካከል፤ ለዚህም ሲባል የተማረ የሰው ኀይል ላይ ያለውን ክፍተት ለመድፈን መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በፖሊሲዎች ላይ የሚታየውን ወዲያው ወዲያው የመለዋወጥ ሁኔታ ማስቆም እና ዘላቂነት ያለው ፖሊሲን በተደራጀና በተጠና መልኩ ማዘጋጀት መቻል ይገባል፡፡ ለኢንቨስትመንት መሠረታዊ የሆኑ ጉዳዮች በማይቆራርጥ መልኩ መቋቋም ይገባቸዋል፡፡
ደግመን ደጋግመን ልናሰምርበት የሚገባን ነገር ግን ሰላም ከሌለ ሁሉም ነገር ከንቱ መሆኑን ነው፡፡ መንግሥት ሰላምና መረጋጋትን የማረጋገጥ ኀላፊነቱን በሚገባ ሊወጣ ይገባል፡፡
(ክቡር ገና)

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here