Home News and Views ኢትዮጵያ ትቅደም ፍትሕ መጽሔት || ሊያደምጡት የሚገባ

ኢትዮጵያ ትቅደም ፍትሕ መጽሔት || ሊያደምጡት የሚገባ

1 COMMENT

 1. “አብዮቱ እንቁላሌን ከመበላት ያስጥልልኛልን?..”
  ጌድዮን በቀለ
  Gedionbe56@yahoo.com
  ኖቬምበር 8፣ 2020 አርሊንግተን ፤ቨርጅንያ
  ጊዜው ሚያዝያ 1991 አ,ም ነበር፤ በኢትዮጵያ ወገን ከ70ሽህ በላይ ወጣቶችን ቅርጥፍ አርጎ የበላው የባድሜ ጦርነት መፈንዳቱ ይፋ የሆነበት፤ የወያኔና ሻቢያ የጫጉላ ሽርሽር ያበቃበት እለት፡፡ ቦታው ባህርዳር የአማራ ክልል መናገሻ ከተማ፤
  እንደተለመደው ከጓደኞቼ ጋር ሆኘ ዘወትር እራት ከምበላበት ኤርትራዊው አቦይ ኪዳኔ ግሮሰሪ ጓዳ ባለገመዱ ሶፋ ላይ ተቀምጨ ያቦይ ኪዳኔ ልጅ ማርታ ከጎረቤታቸው ካለው ምግብ ቤት ያዘዝኩትን ራት አምጥታልኝ አጎንብሼ እየጎራረስኩ በቢራየ አወራርዳለሁ፡፡ ከስራ አምሽቼም ብወጣ እንኳ ቋሚ ደንበኛና ቤተኛ ስለሆንኩ የግሮሰሪው ባለቤት ልጅ ማርታ ምግብ ቤቱን አስከፍታ በልዩ ትእዛዝ አሰርታ ስለምታስመጣልኝ እራት አጥቸ አላውቅም፡፡
  እንደኔ ሌላው የመሸታ ቤቱ ደንበኛ በስካር አንደኛነቱ የተጨበጨበለት የክልሉ የደህንነት ቢሮ ሃላፊ የትም ውስኪውን ሲጋት አምሽቶ ያቦይን ግሮሰሪ ሳይረግጥ አያድርም፡፡ በዚህ የተነሳ ከእኔ ጋር አዘውትረን እንገናኛለን፤ ዛሬም እንደወትሮው ሁሉ ገና በሁለት ሰአት ከምሽቱ ጥንቢራው ዞሮ እየተንገዳገደ ገባና ከእኔ በስተቀኝ በኩል ካለው አግዳሚ ወንበር ላይ ወርዶ ዘጭ አለ፡፡ “ እህም… ነጋዴው አለህ እንዴ? “ አለና ተደላድሎ ሳይቀመጥ የነገር ጉሸማውን ለመጀመር አኮበኮበ፤
  “ አለሁ የት እሄዳለሁ?” አልኩት ደረቅ ፈገግታ አሳይቼ፤ “ የለም! የለም! አገር ሲወረር የት ነበርክ? ማለቴ ነው” አለኝ እየተለፋደደ፤ ትውውቃችን ከጎንደር ጨዋ ሰፈር ጀምሮ በ1960ዎቹ መጨረሻ ኢህአሠን ተቀላቅለን ጫካ እስከገበንበት ይዘልቃል፡፡ ዛሬ እሱ የባለጊዜዎቹ “ድል አድራጊ” ገዥዎች ዋና የደህንነት ሹም እኔ ደግሞ በአንደበቱና እውቀቱ አዳሪ የኮምፒዩተር ባለሙያ መምህር ሆኜ ብንገናኝም በመነቋቆር የተሞላው ጨዋታችን ግን ከነበረን የቆየ የትውውቅ ስንቅ የሚቆነጠር ነበር፡፡
  በዚህ የተነሳ ሞቅ ካላለው በፈገግታ የታጀበ ሳቅና ጨዋታ፤ ሞቅ ካለው ደግሞ በስላቅ ሳቅና ሽሙጥ እየተሸንቋቆጥንና እየተነቋቆርን እንተላለፋለን፡፡ ሁልጊዜ ስላቁ የሰላ ቢሆንም፤ በዚህ የተነሳ እኔን ለክፉ ያሰጠኛል ብዬ አስቤም ፈርቼም አላውቅም፡፡ በዚህ ምሽት ግን ደህንነቱ ወዳጄ ጥንቢራው የዞረው በመጠጡ ብቻ ሳይሆን “ ያመኑት ፈረስ.. “ እንዲሉ የፈጣሪያቸው ሻዕቢያ ክዳት እንደተጨመረበት ለማሳየት ጊዜ አላባከነም፡፡” እንግዲህ ጦርነቱ ተጀምሯል! አሁን ደግሞ ከየትኛው ጎራ ተሰልፈህ ይሆን? አለኝ ከወትሮው በተለየ የሽሙጥ ስላቁን አጠንክሮና እርግጠኛ በሆነ ስሜት፤
  “የትኛው ጦርነት? “ አልኩት የጠቀለልኩትን እየጎረስኩ ባልገባውና ባልሰማ ሰው የተረጋጋ መንፈስ፤
  “ጭራሽ! ጦርነቱን አልሰማሁም እያልከኝ ባልሆነ! “ አለኝ ከበፊቱ ተቆጥቶና ተኮሳትሮ ጉሽርጥ የመሰለውን አይኑን እያጉረጠረጠ፤
  “እውነቴን ነው ፤ ከጭምጭምታ ያለፈ አልሰማሁም፤ ጦርነት ተጀመረ እንዴ? “ አልኩት በተረጋጋና የእሱን ቁጣ ያላስተዋለ ነፈዝ በመምሰል፤
  “ ከአብዮታዊነት ጭልጥ ወዳለ ሶልዲ (ፍራንክ) አሳዳጅነት መሻገር የሚገርም መንሸራተት ነው” አለኝ፤ ሽርደዳ መሆኑ ነው ፤ ቀጠለ” ዛሬ ቁርጥ ያለ አቋምህን ማወቅ እፈልጋለሁ፤ ያለው ሁለት አማራጭ ብቻ ነው! “ የተወረረብንን ግዛት አስመልሰን ሏላዊነታችንን እናስከብራለን ፤የሚልና የለም ቀይባህር ውስጥ እንጨምራቸዋለን፤ አሰብን እንቀማቸዋለን የሚል የትምክህት ጎራ አማራጭ፤ አንተ የየትኛው ጎራ ነህ? መቸም በዚህ አያያዝህ ከትምክህተኞት ጎራ የምጸለፍ ይመስለኛል፤ አለ የምጸት ሳቅ እየሳቀ፡፡
  ”ከሁለቱም ያልሆነ ሶስተኛም ፤አራተኛም ምርጫ አለ እኮ፤ አንተ አልታየህ ይሆናል እንጅ” አልኩት እኔም በምጸት የለት እንጀራዬን እየበላሁ፡፡
  በፍጹም! ሊኖር አይችልም! ማንም ቢሆን ከነዚህ ሁለት አማራጮች አይወጣም! አለኝ፤”
  “ ሶስተኛው ወገን ቢያንስ ይጠይቃል፤ ውጊያው ለምን አስፈለገ? ከውጊያው ምን አተርፋለሁ? ይልና የሚያስገኝለትን ትርፍና ኪሳራ መዝኖ ከውጊያ በመለስ ያለ አማራጭ ላይ ሊያማትር ይችላል፤ ይሄ ቢያንስ ሶስተኛ አማራጭ ሊሆን አይችልም?” አልኩት በለበጣ የጎሪጥ እያየሁት፡፡ እስክጨርስ አልጠበቀኝም፤ ከተቀመጠበት ተፈናጥሮ ተነሳና እየተንቀጠቀጠ አምባረቀብኝ፤ “ ይሄን ያክል ትዘቅጣለህ ብየ አልጠበኩም ነበር፤ የነዋይ ፍቅርህ ከህዝባዊ ትግልና ከሃገር ፍቅር ስሜትህ ልቆ ይቦጠቡጥሃል ብዬ አልገመትኩም ነበር” አለኝ የኔ “ አገር ወዳድ ባለጊዜ”፡፡
  ጩኸቱና ቁጣው ያስደነገጣቸው ጓደኞቼ የሰውየውን ባለጊዜነትና የስልጣን ጉልበት ስለሚያውቁ የሚገቡበት ጠፋቸው፤ ያችን ቀን ከኔ ጋር በመታየታቸው ነገ ከነገ ወዲያ በስራቸውና በህይወታቸው ላይ ሊደርስ የሚችለው መአት እያሰቡ ተሽቆጠቆጡ፡፡ ለኔ ግን ከቀድሞው የኢህአፓ ባልንጀሬ ፊት ላይ ያነበብኩት ድንፋታ ከተበለጥኩ የባዶነትና ፤ ከተከዳን ቁጭት የመነጨ የተሽናፊነት ብስጭት እንደሆነ ለመረዳት ጊዜ አልወሰደብኝም፡፡ ከዚያ በፊት በነበሩ ጊዜያቶች “የማን ወገን እንደሆንኩ” ለማወቅ ያደረገው ጥረት ሳይሳካለት መቅረቱ ተደማምሮ አቃጥሎታል፡፡ የስለላ ጥረቱ እኔን ሰውየውን ሳይሆን እኔ የማላውቀውን ማንነት ከጀርባየ ለመቆፈር መሞከሩ ያስከተለበት ኪሳራ መሆኑን እንኳ አልተገነዘበም፡፡
  “አምርረሃል እንዴ? ይሄን ያክል አገርህንና አገሬን ከእኔ አስበልጠህ እንደምታፈቅራት እየነገርከኝ ከሆነ ከመሸታ ወጭ ተገናኝተን አገሪቱ በማንኛችን ሰበብ የተነሳ እዚህ ፈተና ውስጥ እንደገባች ተነጋግረን ሂሳብ ልናወራርድ እንችላለን፤ ያኔ እጅግ ቢያንስ የመከላከል አቅሙ ቢያጥጥብኝ ያለአበሳዬ ሌሎች ባቀጣጠሉት ነበልባል ሳልጠይቅና ሳላስተውል ገብቼ የምማገድ የእሳት እራት አለመሆኔን ትረዳልኝ ይሆናል! ከማለቴ በቆመበት ሳይቀመጥ ተፈናጥሮ ወጥቶ ሄደ፡፡
  ይሁንና ጦርነቱን እኔ ብደግፍም ባልደግፍም፤ ማስቆም ግን አልተቻለኝም ነበርና በጦርነቱ የተቃጠሉና የረገፉ ወገኖቼን ልቅሶ አብሬ ከማልቀስ ግን አላመለጥኩም፡፡ እንበለ ትርፍ ደማቸው ከፈሰሰው፤ አጥንታቸው ከተከሰከሰው ከሰባ ሽህ ሙታን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ቤተሰቦች ጋር ልቤ እንደተሰበረ እስከዘንድሮ አለሁ፡፡
  “አገርህ ተወረረች “ ሲባል እየፎከረ የፈንጅ ማምከኛ ሆኖ የተማገደው ኢትዮጵያዊ በማይተካ ህይወቱ ያተረፋት አገር ከድል ማግስት ቋንቋው፤ እምነቱና ማንነቱ እየተመነዘረ ያለርህራሄ በጭካኔ የሚገድልባት፤ በቆንጮራ የተቀላው አንገቱ፤ በሳንጃ የተዘከዘከው አንጀቱ የሚቀበረበት አፈር እንዲነፈገው ሆነ፡፡ የሞተላት ኢትዮጵያ የመቆሚያ መቀበሪያውን ነፈገችው፡፡ እሳቱን የለኮሱት ነፍሰበላዎች ግን በአጥንቱና በመቃብሩ ላይ ህንጻ በህንጻ ላይ ሲገነቡ እሱ ከእነማቲዎቹ ይልሰው ይቀምሰው አጥቶ የመኖር ህልውና ተነፍጎት እንደተሳደደ ቀጥሏል፡፡
  ስለሆነም ዛሬ አብረው ገዝተውን፤ ተባብረው አዳምተውን፤ ያቋሰሉን አጋዳዮቻችን በሁለት ጎራ ተከፍለው “የማን አባት ገደል ገባ” ሲሉን አስቀድመን እንዲህ ብለን እንጠይቃለን፤
  `የጆርጅ ኦርዌሏ ዶሮ እንደጠየቀችው፤ “ ከዚህ ጦርነት ምን እናተርፋለን?” ብለን በመጠየቅ እንጀምራለን፡፡
  “ በእርግጥ አብዮቱ እንቁላሎቼን ከመበላት ያድንልኛልን? የሚታለበው ወተቴ ለጥጃየ እንደማይነፈገው ያረጋግጥልኛልን? …” እያልን እንቀጥላለን ፡፡ ከዚህ ጦርነት በኋላ በዘራቸው ፤ በቋንቋቸው፤ በእምነታቸውና በሆኑት አንዳች ምክኛት የሚታረዱ አማሮች፤ጉራጌዎች፤ ጋሞዎች፤ አገዎች፤ አፋሮች፤ ሶማሌዎች ፤ ጌዲዎዎችን ፍልሰት ይገታልን ? ብለን እንሞግታለን፡፡
  ይህ ጦርነት የሰቆቃችን ሁሉ ምንጭ የተቀዳበት መርዘኛ ብልቃጥ ላንዴና ለዘላለም ይታሸጋል? አሁን የገባንበት አበሳ ጠንሳሽ የሆነው ትህነግ በዚህ ጦርነት የሚወገድ ከሆነ እሱ የተሰራበት የሞት ሰነድ በዚህ ጦርነት ተቀዳዶ በምትኩ የህይወት ሰነድ ይተካል? ወይስ ሞታችን የገዳያችንን ሰነድ ዘላለማዊነት የማጽናት ነው?
  እንጠይቃለን! ይህ ጦርነት “ አማራ የሚባል ጭራቅ መጣብህ!” በሚል ሃሳዊ ትርክት የተዘራውን የጥላቻና ባንድ ወገን ላይ ያነጣጠረን መሰሪ የፈጠራ ዘመቻ ያስቀራልን? እያልን እየጠየቅን ፤ ለጥያቄአችንም ዋስትና የተግባር ምላሽ ማግኘት የዚህ ጦርነት ቁልፍ ተልእኮ ሊሆን ይገባል፡፡
  ከጦርነቱ መልስ በጭራሮ የዘጋነው ጎጆአችን ውስጥ የቀቀልነው ንፍሮ ተከፍቶ አለመበላቱን፤ በሰታቴ የተጣደው አጥንታችን ተግጦ መግላሊቱ ተሰብሮ በዝንብ አለመወረሩን፤ የጭራሮዋ ቤታችን ፈራርሳ መጠለያ አለማጣታችንን ካላስረገጥን ፤ እጣ ፋንታችን፤ በሞታችን አገራችንን ከማዳን ይልቅ ጨርሶ ማጣትን እንደማይስከትል ልብ እንድንል የትናንትናዎቹ ውድቀቶቻችን ትምህርት ሆነው ካላነቁን ያው ከሙታን በምን ያክል እንሻላለን??? ጥያቄ፡፡

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here